Category Archives: faithful

ታማኝነትህ ብዙ ነው

Webp.net-resizeimage-4-1-1080x600.jpg

ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22-23

ከእግዚአብሄር ጋር የኖሩ ሰዎች ሁሉ ስለ እግዚአብሄር ታማኝነት ይደነቃሉ፡፡

ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። ኦሪት ዘፍጥረት 32፡10

የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። መዝሙረ ዳዊት 33፡4

የእግዚአብሄር ታማኝነት ማንንም ሊያስጠልል የሚችል ታማኝነት ነው፡፡

በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። መዝሙረ ዳዊት 91፡4

የሰው አለመታመን የእግዚአብሄርን ታማኝነት አያስቀርም፡፡

የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? ወደ ሮሜ ሰዎች 3፡3

የእግዚአብሄር ታማኝነት በእኛ ታማኝነት ላይ የተደገፈ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እኛ ስንታመን የሚታመን እኛ ሳንታመን የማይታመን አምላክ አይደለም፡፡ የእኛ አለመታመን ታማኝነቱን እስከማይለውጠው ድረስ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፡፡

ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡13

ህይወታችንን ልንሰጠው የታመነ አምላክ ነው፡፡

ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 10፡39

እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡18

የጠራን እግዚአብሄር የታመነ አምላክ ነው፡፡

የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡24

በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1፡6

ከምንችለው በላይ እንድንፈተን የማይፈቅድ የታመነ ነው፡፡

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13

ከክፉ የሚጠብቀን አምላክ የታመነ ነው፡፡

ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው። 2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 3፡3

በሃጢያታቸን ብንናዘዝ ሃጢያታችንን ይቅር ሊለን የታመነና ፃዲቅ አምላክ ነው፡፡

በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡9

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ታማኝ #የታመነ #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መደገፍ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የጴጥሮስ ክህደት

pride.jpg

ብዙ ጊዜ ስለክህደት ሲነሳ ስሙ የሚነሳው ይሁዳ ነው፡፡ እንዲያውም የክህደት ሌላ ስሙ እስኪመስል ድረስ ይሁዳ ከክህደት ጋር አብሮ ይነሳል፡፡

ኢየሱስን ከካዱት ሁለት ሰዎች መካከል ይሁዳና ጴጥሮስ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጴጥሮስም ይህን ሰው አላውቀውም ብሎ ክዶዋል፡፡

ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ፦ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት፦ ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች። ዳግመኛም ሲምል፦ ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ። የማቴዎስ ወንጌል 26፡69-72

ኢየሱስ ሰውን ሊክደው እንደሚችል ያውቃል፡፡ ሰው ሊክደኝ አይችልም ማለት አደገኛ አመለካከት ነው፡፡ ሰው የሚክደን በራሱ ችግር እንጂ እኛ ስላጠፋንም አይደለም፡፡ ሃጢያት የሌለበት ኢየሱስ ተክዷል፡፡

ልካድ እችላለሁ ብሎ ልብን ማስፋት ብንካድ ጉልበት ሊሰጠን የሚችል ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሰው ሊካድ ቢችልም ሰውን ማመን ታላቅ ልብ ነው፡፡ ሰው ሊክደኝ ይችላል በሚል ፍርሃት ሰውን ማመን የሚያቆም ሰው ብቻውን ይቀራል፡፡ ሊክድ የሚችል እንዳለ የታመነ የማይክድ ሰውም ደግሞ አለ፡፡ ሊክድ በሚችለው ፍርሃት የታመነውን ሰው ማጣት ጥበብ አይደለም፡፡

ፍቅር . . . ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡7

ይሁዳ ሊክደው እንደሚችል ኢየሱስ አውቆ ነበር፡፡ ኢየሱስ እንደሚክደው አውቆ ከይሁዳ ጋር አብሮት ኖሮዋል አብሮት አገልግሏል፡፡

ኢየሱስም፦ እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው። ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና። የዮሐንስ ወንጌል 6፡70-71

ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደውም ሁሉ አስቀድሞ አውቆዋል፡፡

እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። የሉቃስ ወንጌል 22፡33-34

ይሁዳ በክህደቱ አገልግሎቱንም ህይወቱንም አጣ፡፡

በመዝሙር መጽሐፍ፦ መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም፦ ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአልና። የሐዋርያት ሥራ 1፡20

ማንም ሰው ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሰው በክህደቱ ከቀጠለ ህይወቱንና አገልግሎቱን ያጣል፡፡ ሰው ግን በክህደቱ ካዘነና ከተመለሰ እንዳልወደቀ ሆኖ እግዚአብሄር እንደገና በሃይል ይጠቀምበታል፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡10

ከይሁዳ የሚለየው ጴጥሮስ የሚመለስ ልብ ነበረው፡፡ አንዳንዴ ካልሆነ የጴጥሮስ ክህደት አይነሳም፡፡ የጴጥሮስ ክህደት ከመረሳቱ የተነሳ ጴጥሮስን የምናስታውስበት ብዙ መልካም ነገሮች አሉ፡፡ ኢየሱስ የጴጥሮስን ከውድቀቱ ባሻገር መነሳቱን አይቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ ከክህደቱ ባሻገር የጴጥሮስን ጠቃሚነቱን አይቶ ነበር፡፡

ጴጥሮስ የሚሰበር በጥፋቱ የሚያዝን ልብ ስልነበረው እግዚአብሄር ሁለተኛ እድል ሰጠው፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስ ወደፊት የማይክድበትን መንገድ ቀየሰ፡፡ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላና እንዲክድ ያደረገውንና ያሸነፈውን የፍርሃት መንፈስን የሚያሸንፍበት መንፈስ ቅዱስ ተሞላ፡፡

ጴጥሮስ በንስሃ ከተመለሰ በኋላ መንፈስ ቅዱስን በመሞላት ያሸነፈውን የፍርሃትን መንፈስ አሸነፈው፡፡

ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። የሐዋርያት ሥራ 2፡14

ጴጥሮስ ሲመለስ እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሃይል የፍቅር ራስን የመግዛት መንፈስ ሰጠው፡፡

እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡7

ማንም ሰው በክህደት ሊወድቅ ይችላል፡፡ የሚነሳውና እንደገና የእግዚአብሄር መጠቀሚያ የሚሆነው ሰው ግን በንስሃ በእግዚአብሄር ፊት የሚመለሰው ሰው ብቻ ነው፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መካድ #መታለል #ታማኝነት #ክህደት #ንስሃ #ሃዘን #መመለስ መጣል #መሰደድ #መገፋት #መውደቅ #አለመመረጥ #ተቀባይነትማጣት #ዋጋአሰጣጥ #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አምልኮ #እምነት #መከተል

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካበት 12 መፅሃፍ ቅዱሳዊ መለኪያዎች

conscious.jpgመጋቢነት  ለሰዎች ነፍስ የመትጋት የተከበረ ጥሪ ነው፡፡

ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።፡ወደ ዕብራውያን 13፡7

መጋቢነት በእግዚአብሄር የሚሰጥ ፀጋ እንጂ በሰው አነሳሽነትና ፍላጎት የሚደረግ አገልግሎት አይደለም፡፡ ማንም ሰው ማንንም ስው ለመጋቢነት ሊጠራ አይችልም፡፡ ሰውም ራሱን ለመጋቢነት ሊያሰማራ አይችልም፡፡ የመጋቢነትን ፀጋ ሰጥቶ ሰውን ለመጋቢነት የአገልግሎት ስራ ሊጠራ የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡11

ሰው በአካባቢው ያለውን ክፍተት አይቶ መጋቢ መሆን አይችልም፡፡ ሰው ስለፈለገና ስለተመኘ ብቻ መጋቢ መሆን አይችልም፡፡ ሰው የሚመገቡ ሰዎች ስላሳዘኑት ብቻ መጋቢ ሊሆን አይችልም፡፡ መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ጥሪ ነው፡፡ መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ የአገልገሎት ስጦታ ነው፡፡ መጋቢነት ፀጋ ነው፡፡

መጋቢነት ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ስጦታ ስለሆነ ብቻ ታማኝነቱ አይለካም ማለት አይደለም፡፡ ሰው በመጋቢነት ተጠርቶ ታማኝ ሊሆን ይችላል ታማኝ ላይሆን ይችላል፡፡ በመጋቢነት የተጠራ ሰው ታማኝ መሆን እግዚአብሄርም የእግዚአብሄርም ህዝብ ይጠብቅበታል፡፡  መጋቢነት በእግዚአብሄር ቃል ይመዘናል፡፡

የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካባቸው መንገዶች አሉ፡፡ እንዲሁም የመጋቢ ታማኝነት የማይለካባቸው መንገዶች አሉ፡፡

  1. መጋቢነት በሰው ብዛት አይለካም

ብዙ ሰው የሚመግብ ሰው የተሳካለት ትንሽ ሰው የሚመግብ ሰው ያልተሳካለት አይደለም፡፡ የሰው መጋቢነት የሚለካው እግዚአብሄር እንዲመግብ በሰጠው ሰዎች ላይ ባለው አገልግሎት ነው፡፡ የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ራሳቸውን የሰጡትን ሰዎች የእግዚአብሄር ቃል በታማኝነትና በትጋት በመመገቡ ነው፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው የተሰጠውን ሰዎች እንዴት በትጋት እንዳገለገላቸው በተሰጠው ሰው ብቻ ነው፡፡

እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን። እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡1-2

  1. የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን በማሳደግ አይደለም፡፡

የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የላከለትን ሰዎች ኮትኩቶ ለማሳደግ ባለው ትጋት ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ባሳደገው ሰው ቁጥር አይደለም፡፡ የመጋቢው ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን በማሳደግ አይደለም፡፡ ሰዎች ለማደግ የሚያሳድገውን የእግዚአብሄርን ቃል የሚያስተራቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም ለማደግና ለመለወጥ የሚያደርጉት እርምጃ ያሳድጋቸዋል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው በማሳደግ ሳይሆን የሚያሳድገውን የእግዚአብሄርን ቃል በትጋት እና በታማኝነት በማቅረብ ነው፡፡

እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡6-8

  1. የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠውን ሰዎች በእግዚአብሄር ቃል አውቀት ከመንፈሳዊ ከድካምና ከበሽታ ከሞት እንዲጠበቁ የሚያስችላቸውን ትምህርት ፣ ምክርና እንክብካቤ በማድረጉ ነው፡፡ የመጋቢ ሃላፊት መወጣቱ የሚመዘነው ንፁሁን የእግዚአብሄርን ቃል በተመጣጠነ ሁኔታና በሚዛናዊነት በመመገብ ራሳቸውን ከስህተት እንዲከላከሉ በማስታጠቅ ነው፡፡

ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም። ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። የሐዋርያት ሥራ 20፡20-21፣26-27

  1. የመጋቢነት ታማኝነት የሚለካው ምእመኑን በመጎብኘቱ ነው፡፡

መጋቢ የእግዚአብሄርን ህዝብ ከላይ ሆኖ ሊከታተል ይገባዋል፡፡ መጋቢ የእግዚአብሄር ህዝብ መንፈሳዊ ህይወት የበላይ ጠባቂ ነው፡፡ መጋቢ ከላይ ሆኖ መንጋውን ከተኩላ የሚጠብቅና የሚከላከል ጠባቂ ነው፡፡

በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።  የሐዋርያት ሥራ 20፡28-30

  1. የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የእግዚአብሄርን ቃል ምሳሌ በመሆን ነው፡፡

የመጋቢ ታማኝዕነት የሚለካው የሰዎችን ህይወት በመለወጥ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ቃል በአስተሳሰብ ፣ በንግግርና በአካሄድ ሞዴል ወይም ምሳሌ በመሆን ነው፡፡

ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡3

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ወደ ዕብራውያን 13፡7

  1. የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ለህዝቡ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ነው ነው፡፡

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን ከልሎ አስቸጋሪ ሁኔታን በመጋፈጡ ነው፡፡ ጠላት ህብረትን መበተን ሲፈልግ የሚመታው በስፍራው ያለን መሪ ነው፡፡ እረኛን ከመታ በጎች እንደሚበተኑ ያውቃል፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው ህዝቡን ይዞ በታማኝነት መዝለቁ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲመጣ ህዝቡን ጥሎ የሚሸሽ መጋቢ ታማኝ መጋቢ አይደለም፡፡

እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።  የዮሐንስ ወንጌል 10፡12-13

  1. መጋቢ ታማኝነት የሚለካው መጥፎ ጥቅምን ባለመመኘት ነው

የመጋነት ታማኝነት የሚለካው ያለኝ ይበቃኛል በሚል አስተሳብን ነው፡፡

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6፣8

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ሰዎችን ለጥቅማቸው እንጂ ለጥቅሙ ባለመፈለግ ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው በበጎ ፈቃድ በማገልገል ፣ በመስጠትና በመጥቀም ነው፡፡ የመጋቢ ማማኝነት የሚለካው ምእመኑን በክርስቶስ ደም እንደተገዛ ክቡር የእግዚአብሄር ህዝብ እንጂ እንደ ጥቅም ማግኛ ምንጭ ባለመመልከት ነው፡፡ መጋቢ ታማኝነቱ የሚለካው ህዝቡን እንዲያገለግል የጠራውን እግዚአብሄርን እንጂ ህዝቡን እንደ ገቢ ምንጭ ባለማየት ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅ ሲፈልግ እግዚአብሄር የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚጨምርለት በማመን ነው፡፡

ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡32-33

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ያለኝ ይበቃኛል በማለቱ ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠውን ተሰሚነት ተጠቅሞ የህዝቡን መብዛት እንጂ የራሱን መብዛት ባለመፈለግ ነው፡፡

በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3

እነሆኝ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 12፡3

  1. የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን መታገስ በመቻሉ ነው

መሪነት ወደሰው ደረጃ ወርዶ ሰውን ታግሶና ተሸክሞ ወደሌላ ደረጃ የማድረስ ጥበብ ነው፡፡ መጋቢነት ህዝቡን እግዚአብሄር ወደአየላቸው ደረጃ ለማድረስ በትግስትና በትጋት ማገልገል ነው፡፡

እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡1-2

እርሱም አለው፦ ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ። ኦሪት ዘፍጥረት 33፡13

  1. የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡ እግዚአብሄር ወዳየላቸው ቦታ መምራቱ ነው፡፡

የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ስለ ህዝቡ ከእግዚአብሄር ራእይን በመቀበል ነው፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን እግዚአብሄር ወደ አየላቸው ቦታ መውሰዱ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ወደአየላቸው ቦታ መድረስ የመጋቢውም የተመሪውን ሃላፊነት ነው፡፡ መጋቢው ስለፈለገ ብቻ ህዝቡን እግዚአብሄር ወደአየላቸው ቦታ መውሰድ አይችልም፡፡ የህዝቡ መሰጠትም ይጠይቃል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው እግዚአብሄር ለህዝቡ በልቡ ያለውን መፈለግና ህዝቡን እግዚአብሄር  ወደአየላቸው ደረጃ መምራት ነው፡፡ ህዝቡ ታማኝ ሆኖ ከተከለተለ እግዚአብሄር ወደአየለት ቦታ ይፈደርሳል፡፡

እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡28-29

  1. የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው ህዝቡን ለአገልዕግሎት ስራ በማስታጠቅና በማሰማራት ነው

መጋቢ እርሱ ብቻ ጠቃሚ ሌላው ሰው ሁሉ ተጠቃሚ ማድረግ የለበትም፡፡ እርሱ ካህን ሌሎች ህዝብ መሆን የለባቸውም፡፡ እርሱ ጠቃሚ ሌሎቹ ሁሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይገባም፡፡ መጋቢ ህዝቡን ሁሉ ሰራተኛ የሚያደርግ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡12-13

ግልገሎቼን አሰማራ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ። የዮሐንስ ወንጌል 21፡15፣17

  1. መጋቢ የበደለን በመገሰፅ የቤተክርስትያንን ቅድስና በመጠበቅ ታማኝነቱ ይታያል፡፡

መጋቢ እግዚአብሄርን ሳይሆን ሰውን ሊያስደስት የሚጥር ከሆነ ለጥሪው ታማኝ አይሆንም፡፡ መጋቢ የማስደስተውን ሰውን ስለስህተቱ መገሰፅ መማር አለበት፡፡ መጋቢ ሰውን የመገሰፅ ደስ የማያሰኝ ሃላፊነት በትጋት መወጣት አለበት፡፡ መጋቢ ለቤተክርስትያን ንፅህናና አንድነት ሰዎችን የማረምና የመቅጣት የቤተክርስትያን አባትነት ታማኝነቱን በትጋት መወጣት አለበት፡፡
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡28-29

ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡12-13

  1. መጋቢ እግዚአብሄርን በመውደድ የእግዚአብሄርን ህዝብ በመውደድና በመማር ታማኝነቱ ይለካል፡፡

መጋቢ የማይራራለትንና የማይወደውን ህዝብ ማገልገል አይችልም፡፡ መጋቢ የእግዚአብሄርን ህዝብ ሲያገለግል ብዙ ነገሮች መጣል ይገጥመዋል፡፡ የመጋቢ ታማኝነት የሚለካው የበደለውን ሰው ይቅር በማለትና ባለመጥላት ነው፡፡

በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡1-3

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ጥሪ #መገሰፅ #መምራት #ማሰማራት #መታገስ #መመገብ #መኮትኮት #ማሰማራት #መጠበቅ #ምሳሌ #ፍቅር #ምህረት #ይቅርታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

የዓመቱ ስኬት በታማኝነት ሲለካ

shutterstock_176659673 (1).jpgእግዚአብሄር ስራውን ሰርቶ ይመዝነዋል፡፡ እግዚአብሄር ምድርን ሲፈጥር ስራውን ፣ ያደረገውንና የፈጠረውን ያይና መልካም ነው ይል ነበር፡፡

እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። ዘፍጥረት 1፡31

እግዚአብሄር ስራውን ይመዝናል፡፡

አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። 1ኛ ሳሙኤል 2፡3

ስራን ስለመመዘን እግዚአብሄር ታላቁ ምሳሌያችን ነው፡፡ የእኛም ህይወትና አካሄድ በየጊዜው መመዘን አለበት፡፡ እግዚአብሄር ጊዜን በቀን ፣ በሳምንት ፣ በወርና በአመት ሲከፋፍለው ቆም ብለን ራሳችንን እንድናይ እያመቻቸልን ነው፡፡ እግዚአብሄር ቀንና ለሊትን የለየው ሰው በምሽት ዝግ እንዲልና የእግዚአብሄርን ስራ ዞር ብሎ እንዲያስብ ነው፡፡

ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። ኢዮብ 37፡7

የማይመዘን ህይወት ትክክል መሆኑ ስለማይታወቅ ለወደፊት ድፍረትን አይሰጥም፡፡ የማይመዘን ህይወት ስህተት መሆኑም  ስለማይታወቅ በጊዜ ለመመለስ አይጠቅምም፡፡ የማይመዘን ህይወት ከንቱ ህይወት ነው፡፡

ህይወታቸነ መመዘን እንዳለበት ከተረዳን በአመቱ ውስጥ በህይወታችን ስኬታማ መሆናችንን የምናውቅው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፡፡ ለመሆኑ ስኬታማነት ሊመዘን ይችላል? ስኬታማነት ከተመዘነስ የስኬታማነት መመዘኛው ምንድነው? ስኬታማ መሆናችንን በምን እናውቃለን? የሚለውን ጥያቄ በትክክል መመለስ ስኬታማ ስንሆን እንድናውቅ ስኬታማ ካልሆንን በጊዜ መንገዳችንን ቀይረን ለወደፊት ለስኬታማነት እንድንዘጋጅ ይረዳናል፡፡

በአለም  ብዙና የተለያዩ የስኬታማነት መመዘኛ ነጥቦች አሉ፡፡ የአለምን የስኬታማነት መመዘኛ ከተከተልን እንስታለን፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው አንድ የስኬተማነት መለኪያ ብቻ ነው፡፡ ይህ የስኬታማነት መለኪያ ሰው በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁን ፣ ምንም ደረጃ ይኑረው ፣ ምንም ያግኝ አያግኝ ካለአድሎ ስኬቱን በትክክል ሊለካው ይችላል፡፡

ይህ የስኬታማነት ብቸኛ መለኪያ ታማኝነት ነው፡፡

የሰው ሰኬት ባለው ሃብት መጠን አይለካም ሃብቱን ለምን ምክኒያት እንዳዋለው ታማኝነቱ እንጂ፡፡

በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19

አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው። ማርቆስ 12፡44

የሰው ስኬታማነት ባለው ተሰሚነት መጠን አይለካም ተሰሚነቱን ለምን እንደተጠቀመበት በታማኝነቱን እንጂ፡፡ የሰው ስኬት በዝናው አይለካም ዝናውን በታማኝነት ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ማዋሉ እንጂ፡፡ ሰው ዝናውም ለራሱ የግል ጥቅም በማዋሉ እግዚአብሄር ዝናውን አይሸልምም፡፡

በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡2

ሰው ስኬቱ ባለው ጥበብ አይለካም በጥበቡ ለሰዎች ጥቅም ወይም ለራሱ የግል ጥቅም ወይስ ለሰዎች ውድቀት በመስራቱ እንጂ፡፡

እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡4-5

የሰው ስኬት የሚለካው በታማኝነት መመዘኛ ብቻ ነው ፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው በአደራ ለተሰጠው ነገር ታማኝ መሆኑን አይቶ ስኬታማ መሆኑንና አለመሆኑን ሊያውቅ ይችላል፡፡

መክሊት ስለጠተሰጣቸው ሰዎች መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር አንዱንም ስለተሰጠው መክሊት ብዛትና ማነስ አልተናገረውም እንዲሁም አንዳቸውም በመክሊታቸው ብዛትም አልተለኩም፡፡ እንዲያውም የተለኩት በጥቂቱ ነው፡፡

ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡23

በህይወታችን የተሰጠን መክሊት ምንም ትንሽ ቢሆንም ታማኝነታችን ሊያመለክት ግን በቂ ነው፡፡

በዚህ አመት የህይወታችንንና የአገልግሎታችንን ስኬት የምንመዝነው እግዚአብሄር ለሰጠኝ ነገር ታማኝ ነበርኩ ወይ? የሚለውን ጥያቄ በታማኝነት በመመለስ ብቻ ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #መክሊት #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #አመት #ቀን #አዲስአመት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰው ልዩ ምልክት

o-TRUST-facebook.jpgካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መስራት አይቻልም፡፡ እግዚአብሄር እምነትን ከእኛ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር ቃሉን እንድናምን ይፈልጋል፡፡ ከደህንነት ቀጥሎ መሰረታዊው እምነት ደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልገን ሁሉ እንደሚያውቅና እንደሚጨምር ማመን ነው፡፡

ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33

ሰው ስለሚበላው ስለሚጠጣውና ስለሚለብሰው ካመነ በነፃነት ለእግዚአብሔር መኖር ይችላል፡፡ ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካመነ በሁለንተናው እግዚአብሄርን ለማገልገል ይለቀቃል፡፡

እምነት የልብ ስለሆነ አንድ ሰው ማመኑና አለማመኑን ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰውም ምልክቶች ከእግዚአብሄር ቃል መመልከት እንችላለን፡፡

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይጨነቅም፡፡

ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ጉልበቱን የእግዚአብሄርን ነገር በመፈለግ ላይ እንጂ በጭንቀት ላይ አያፈስም፡፡ የሚያምን ሰው የጭንቀትን ፍሬ ቢስነት ይረዳል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን በመፈለግ ላይ ሙሉ በሙሉ ከመጠመዱ የተነሳ ለጭንቀት የሚተርፍ ትርፍ ጊዜና ጉልበት የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ጭንቀት ጉልበቱን እንዲበላ አይደፈቅድለትም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የማያምን ሰው የእግዚአብሄርን ስራ በሚሰራበት ጊዜና ጉልበቱ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱን በትክክለኛው በእግዚአብሄር መንግስት ላይ ማፍሰስን አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው  ምንም ነገር በትክክል መስራት ሳይችል በጭንቀት ብቻ ካለፍሬ ይቀራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያስጨንቀው ነገር ጌታ እንዲሆንበት ይፈቅድለታል፡፡ ስለመሰረታዊ ግፍላጎቱ የማያምን ሰው ይጨነቃል በጭንቀትም ውድ ህይወቱን ያባክናል፡፡

ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ማቴዎስ 6፡25

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይፀልያል፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ይፀልያል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ይፀልያል በእምነትም ያመሰግናል፡፡ አማኝ የሚያስጨንቀውን ይጥላል በእግዚአብሄር ላይ መልሶም አይወስደውም፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይተማመናል ያርፋል፡፡

የማያምን ሰው በመጨነቁ ትልቅ ስራ እንደሰራ ያስባል፡፡ የማያምን ሰው መፀለይ በሚገባው ጊዜ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱንና ጊዜውን በጭንቀት ላይ ያሳልፋል፡፡ የማያምን ሰው ቢፀልይም  ጭንቀቱን መልሶ ይወስደዋል፡፡ የማያመን ሰው መጨነቁ የህይወት አንዱ ስራ ይመስለዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው ሸክሙን  በእግዚአብሄር ላይ እንዴት እንደሚጥለው አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር እንዴት እንሚያርፍ አያውቅም፡፡

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴዎስ 11፡28

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ልቡን ይሰማል፡፡

እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሞትክ አለቀልህ ጠፋህ የሚለውን የውጭውንና የአእምሮውን ድምፅ ሳይሆን የልቡን ድምፅ በዝምታ ይሰማል፡፡

በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው በአእምሮ የሚመጣውን ሃሳብ ሁሉ ያስተናግዳል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ይታወካል ሰላም የለውም፡፡

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃነስ 14፡27

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይወራረዳል፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይህን ካላገኘሁ አይሆንም የሚለው ፍላጎት የለም፡፡ የሚያምነ ሰው በምንም ነገር ውስጥ እግዚአብሄር እንደሚያስችለው ያምናል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በከፍታም በዝቅታም በምንም ነገር ውስጥ በክርስቶስ እንደሚበረታ ያውቃል፡፡

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-23

ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሰው በእግዚአብሄር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ያውቃል፡፡

እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው የሌለኝ ነገር የማያስፈልገኝ ነው ብሎ በእግዚአብሄር እረኝነትና  አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ይታመናል፡፡

እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡10-11

ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር በሰጠው ነገር ብቻ መኖር እንደሚችል ያውቃል፡፡ ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር የሰጠው ነገር ለአላማው በቂ እንደሆነ ያምናል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር እቅርቦት ላይ ምንም ትችት የለውም፡፡

ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማየታመን ሰው ገንዘቡ ተቆጥሮ እሰካልገባ አያምንም፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሚያየውን ብቻ ያምናል፡፡

ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡7-8

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከአለም ፉክክር ራሱ ያገላል፡፡

እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው በአለም ካለ ክፉ የፉክክር መንፈስ በፈቃዱ ራሱን ያገላል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው ከሌላው ጋር ተፎካክሮም ለእግዚአብሄር ኖሮም እንደማይችል ይረዳል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው የፉክክርን ክፋትና አታላይነት ይረዳል፡፡

ስለፍላጎቱ ጌታን የማያምን ግን ሰው የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ይጥራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው በሰው ፊት ሙሉ መስሎ ለመታየትና ላለመበለጥ ይዳክራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሰውን ደረጃ ለማሟላት ህይወቱን ያባክናል፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ከጭንቀት አርፎ እግዚአብሄርን ማገልገል ያቅተዋል፡፡

በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፡22

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው የተረጋጋ ህይወት አለው፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከማረፍ ውጭ ሲቅበዘበዝ አይታይም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይናወጥም፡፡ ጌታን የሚያምን ሰው ለጌታ ሙሉ ለሙሉ ለመኖር ነፃ ነው፡፡ በጌታ የሚታመን ሰው የረካ በመሆኑ ሌላውን ለማርካት ይሮጣል፡፡

የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25

ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ምሳሌ 17፡22

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ ሰላም ያለው ሰው ለሌላው ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍለጎቱ የረካ ሰው ትኩረቱ አንድ ስለሆነ ሰላሙን ሊወስድ የሚችል ምንም ሃይል አይኖርም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ያልረካ ሰው ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ለማድረግ ስለሚሞክር ሁለቱንም ማድረግ ያቅተዋል፡፡ ስለፍላጎቱ በጌታ ያልታመነ ሰው ሌሎችን ስለማገልገልና ሌሎችን ስለመጥቀም ሲሰማ ቁጣ ቁጣ ይለዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው “ምስኪን እኔ” አስተሳብ “ለእኔስ ማን አለኝ?” የሚል ምስኪንነት አስተሳሰብ አለው፡፡

ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ኢሳያስ 28፡16

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያመን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው አይጣላም አይጨቃጨቅም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው የእርሱን ነገር ከሰው ጋር አያያይዘውም፡፡

በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?ያዕቆብ 4፡1

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያመን ሰው ሰውን ለመጥቀም ሳይሆን በሰው ለመጠቀም ያስባል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያንምን ሰው ከዚህ የምጠቀመው ምንድነው ብሎ ስለግል ጥቅሙ ሁሌ ያስባል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ የማይታመን ሰው የእግዚአብሄርን አቅርቦት ስለማያይ አገልግሎትን የጥቅም ማግኛ መንገድ ያደርገዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን የፀጋ ስጦታ በጥቅም ይቸረችረዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን ነገር ሁሉ ወደግል ስሙ ያዞረዋል፡፡ ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው በግል በማይጠቀምበት ምንም ነገር ውስጥ የመሳተፍ ሃሞቱ የለውም፡፡

ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ማቴዎስ 10፡8

  1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚታመን ሰው ነውረኛ ረብን ይጠላል፡፡

ስለፍላጎቱ በአግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክቡርና ነውረኛን ጥቅምን ይለያል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው በፊቱ የመጣውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡ ስለፍላጎቱ የሚታመን ሰው ኩሩ ነው፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው ለቀቅ ብሎ ይኖራል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክብር ከእግዚአብሄር ብቻ እንደሚመጣ ይረዳል፡፡

ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7

ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9

ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው የጥቅም ደረጃ የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የማይታመን ሰው የህይወት መርህ የለውም ወደተመቸው ይገለባበጣል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው ጥቅም ይሁን እንጂ የሚንቀውና እንቢ የሚለው ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው እግዚአብሄር በክብር እንደሚባረክ አይረዳም፡፡

አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19

 

የክርስትናም የመጨረሻ ደረጃና የስኬት ጣራ ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡

 

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

40 የእምነት ጥቅሞች (ክፍል ሁለት) ዕብራውያን 11፡21-40

6656UNILAD-imageoptim-TenCommand3_029Pyxurz (1).jpg

40 የእምነት ጥቅሞች (ክፍል ሁለት) ዕብራውያን 11፡21-40

እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በስጋ አይን አይታይም፡፡ እግዚአብሄር ምን እንደሚሰራ ለማየትና ከእርሱ ጋር ለመስማማትና ለመተባበር የመንፈስ አይን ይጠይቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር በሚገባ ለመኖር በተፈጥሮአዊ አይን የማይታየውን ማየት ይጠይቃል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ለመድረስ እግዚአብሄርን ማመን ይጠይቃል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ለመድረስ እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን ለመንካት እምነት ይጠይቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ሃይል ጋር ለመገናኘት እምነት ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሄር አቅርቦት ተጠቃሚ ለመሆን እምነት ይጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ያለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነታችን ትክክል ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ልንገናኝ አንችልም፡፡

እምነት በተፈጥሮአዊ አይናችን የማናየውን ተስፋ ለማረጋገጥ ይጠቅማል፡፡ እምነት በተፈጥሮ አይናችን ስለማናየው ነገር ያስረዳል፡፡

እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዕብራውያን 11፡1

ሰው ስለተለያየ ነገር ሊመሰክር ይችላል፡፡ የእግዚአብሄር እውነተኛው ምስክርነት የሚገኘው ግን በእምነት ከመኖር ነው፡፡ እምነት የእግዚአብሄር ምስክርነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዕብራውያን 11፡2

ስለማናየው ስለወደፊቱ የበረከትን ቃል የምንለቀው በእምነት ብቻ ነው፡፡ የበረከታችን ቃል እንደሚደርስ አውቀን የምናመሰግነው በእምነት ነው፡፡

ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። ዕብራውያን 11፡21

ስለወደፊት ህይወታችንና ስለትውልዳችን የምናየው እና የምንናገረው በእምነት ነው፡፡

ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። ዕብራውያን 11፡22

ካለፍርሃት የምድራዊውን ህግ ሽረን እግዚአብሄርን የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡

ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። ዕብራውያን 11፡23

ስለ ጥሪያችን ስንል የምድራዊውን ጥቅም የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ራሳችንን ከምድራዊ ፉክክር የምናገለው በተፈጥሮ አይን የማይታየውን በማየት በእምነት ነው፡፡

ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ዕብራውያን 11፡24

እግዚአብሄር ክብደት ለሰጠው ነገር ክብደት የምንሰጠውና የናቀውን ነገር ደግሞ የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ የዘላለሙን ብድራት የምናየው በእምነት ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ያለ ማንኛውም ነገር የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሆነ የምናስተውለው በእምነት ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ ትኩረታችን ለሚፈልጉ ነገሮችን እንቢ የምንለውና ክርስቶስን ብቻ ተመልክተን ሩጫችንን በትእግስት የምንጨርሰው በእምነት ነው፡፡

ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ዕብራውያን 11፡25-26

በምድር ላይ የሚያስፈራሩትንና የሚያስጨንቁትን ነገሮች ሳንፈራ እግዚአብሄርን የምናገለግለው በእምነት ነው፡፡

የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። ዕብራውያን 11፡27

ለሩሮዋችን ሳንጨነቅ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅ የምንፈልገው በእምነት ነው፡፡

 

ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33

በመውጣት በመግባታችን ከክፉ የምንጠበቀው በእምነት ነው፡፡ በአእምሮ የማይመስለውን የእግዚአብሄርን ቃል በሞኝነት የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡

አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። ዕብራውያን 11፡28

ከከበበን ነገር የምናልፈው በእምነት ነው፡፡

በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። ዕብራውያን 11፡29

ከእኛ ሃየለ የሚበልጠውን በሰው ጉልበት የማይቻለውን አስፈሪውን የጠላትን ግዛት የምንወርሰው በእምነት እርምጃ በመውሰድ ነው፡፡

የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። ዕብራውያን 11፡30

የእግዚአብሄር ፈቃድ የምንታዘዘው በተፈጥሮአዊ አይናችን አይተን ሳይሆን ቃሉን ብቻ ሰምተን በእምነት በመታዘዝ ነው፡፡

ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። ዕብራውያን 11፡31

በምናልፍበት አስቸጋሪ ህይወት ድልን የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ የተሰጠንን የተስፋ ቃል የምናገኘው በእምነት ነው፡፡

እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ ዕብራውያን 11፡33

ከሰው ሃይልና ችሎታ በላይ የሆኑ ታእምራት በህይወታችን የሚሆኑት በእምነት ነው፡፡ የእሳት ሃይል የማይጎዳን በችሎታችን ሳይሆን በእግዚአብሄ ችሎታ ላይ በመታመን ነው፡፡ ከድካም የምንበረታው በእምነት ነው፡፡ ከእኛ እጅግ የሚበረቱትን ድል የምንረታው በእምነት ነው፡፡

የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ዕብራውያን 11፡34

ክርስትና ህይወታችንን መስዋእት እስከምናደርግ ድረስ ለጥሪያችን የምንታዘዘው በእምነት ነው፡፡

ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ዕብራውያን 11፡35

ሰው የሚጋደልለትን ነገር በደስታ የምናጣው የተሻለ ነገር እንዳለ በእምነት አይናችን አይተን ነው፡፡

የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። ዕብራውያን 10፡34

የሰዎች መሳለቂያ የምንሆነው በእምነት ነው፡፡ ክብራችንን የምንተወው በእምነት ነው፡፡ ሰው የሚያከብረውን እንዳይደርስበት ሁሉንም ነገር የሚያደርገለትን ነውር የምንንቀው በእምነት ነው፡፡

ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ ዕብራውያን 11፡36

የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት መዋረድን የማንፈራው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለመታዘዝ መሳለቂያ መሆንን የምንንቀው በእምነት ነው፡፡

. . . የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2

ማጣትን የምንንቀው በእምነት ነው፡፡ ላለማጣት ማንኛውንም ነገር የማናደርገው በእምነት ነው፡፡

በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዕብራውያን 11፡37

ማጣት እንደማያዋርደን ማግኘት እንደማያከብረን የሚያኖረን እግዚአብሄር እንደሆነ የምንረዳው በእምነት ነው፡፡

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13

የአለምን ጥቅም የምንንቀው ፣ በአለም የማንጠቀመውና በአለም ጥቅም ላይ የሙጥኝ የማንለው በእምነት ነው፡፡

ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። ዕብራውያን 11፡38

የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡31

በእምነታቸው የተመሰከረላቸው አባቶች ያመኑትን ነገር ሳያገኙ የሞቱት በእምነት ነው፡፡

እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና። ዕብራውያን 11፡39-40

40 የእምነት ጥቅሞች (ክፍል አንድ) ዕብራውያን 11፡1-20  https://www.facebook.com/notes/abiy-wakuma-dinsa/40-%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9E%E1%89%BD-%E1%8A%AD%E1%8D%8D%E1%88%8D-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%8B%95%E1%89%A5%E1%88%AB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95-111-20/10155521312419255/

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ብቸኛው መመዘኛ

Faithfulness-1.jpg 2.jpgለእግዚአብሄር ክብር እንደመፈጠራችን መጠን በህይወታችን ለእግዚአብሄር ብቻ መኖር እንፈልጋለን፡፡ የልባችን ጩኸት በእግዚአብሄር በልብና በሃሳቡ እንዳለ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አድርጎ ማለፍ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምኞት የለንም፡፡  ዳዊት በዘመኑ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግሎ አንቀላፋ ተብሎ እንደተመሰከረለት እንዲመሰከርልን እንፈልጋለን፡፡ በምድር ላይ የሚያረካን ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ብቻ ነው፡፡

ታዲያ በስኬት ማገልገላችንና አለማገልገላችን የሚለካው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አገልግለን በህይወት እንድናርፍ ያደርገናል፡፡ ከእኔ ምንድነው የሚጠበቀው? ከእኔስ ምንድነው የማይጠበቀው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ማወቅ ሃላፊነታችንን በትኩረት እንድንወጣ ያስችለናል፡፡

አንድ ቀን ጉዞዋችንን ዞር ብለን ስናየው ለእግዚአብሄር በሚገባ የተኖረ ህይወት እንድናይ እንፈልጋለን፡፡ በመጨረሻ እግዚአብሄር “መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ” እንዲለን እንጠብቃለን፡፡

ግን እግዚአብሄር ህይወታችንን የሚመዝነው በምንድነው? መመዘኛው መስፈርት ምንድነው?

እግዚአብሄር አፈፃፀማችንን የሚለካው ስለታማኝነታችን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን ስለሰጠን በእጃችን ላይ ስላለው ስጦታ እንጂ ስላልሰጠን ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን በህይወታችን ስላስቀመጠው ስለሰጠን መክሊት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀው እንዴት እግዚአብሄር ላይ በመደገፍ በታማኝነት የሰጠንን ነገር ማስተዳደራችንን ብቻ ነው፡፡

ጊዜ

የሰጠንን ጊዜ እንዴት በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል፡፡ እግዚአብሄር በቀን ስለሰጠን 24 ሰአት እንጂ ስላልሰጠን 25 ሰአት አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን 24 ሰአት ግን እንዴት ለእግዚአብሄር ክብር እንደተጠቀምንበትና እግዚአብሄር በህይወታችን ላስቀመጠው ራእይና ሃላፊነትና እንዳዋልነው ታማኝነታችን ይለካል፡፡ እግዚአብሄር ያለው አንድና ብቸኛ መመዘኛ ታማኝነት ነው፡፡

እውቀት

እግዚአብሄር የሰጠንን እውቀት ካለመሰሰት ለእግዚአብሄር መንግስት ተጠቅመንበታል? እግዚአብሄር እንዴት እውቀታችንን በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይለካል፡፡ ለተገለጠልን የፈቃዱ እውቀት ምን ያህል እየኖርን እንደሆነ ይፈትናል፡፡ ስላልተረዳነውና ስለማናውቀው የእግዚአበሄር ፈቃድ እንጠየቅም፡፡

የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48

ገንዘብ

እግዚአብሄር ለመዝራትና ለመብላት የሰጠንን ገንዘብ እንዴት እያስተዳደርን እንዳለን እንጂ ስለሌለን ስለ ቢሊዮን ብር  አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን እንዴት እንዳዋልነው ግን ይጠይቀናል፡፡

እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7፣10

ጉልበት

እግዚአብሄር የሰጠንን ማንኛውም ሃይል እንዴት እንደተጠቀምንበት ታማኝነታችንን ማየት ይፈልጋል፡፡ ያለንን ሃይልና ተሰሚነት የተጠቀምንበት ለመገንባት ይሁን ለማፍረስ ታማኝነታችንን ይለካል፡፡ ያለንን ሃይልና ጉልበት ለራሳችን ራስወዳድነት ወይም ለፍቅርና ለሌሎች ጥቅም እንዳዋልነው ማወቅ ይፈልጋል፡፡

የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 1ኛ ጴጥሮስ 4፡11

የስኬታችን አንዱና ብቸኛው መመዘኛው እግዚአብሄር የሰጠን ማንኛውም መክሊት በመልካም የማስተዳደር ታማኝነታችን ነው፡፡

ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡21

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #መክሊት #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ዓመቱ ሲመዝን

21140-pinky-promiseክርስትያን በየጊዜው ህይወቱን በእግዚአብሄር ቃል መመዘን አለበት፡፡ በየጊዜው የማይገመገምና የማይፈተሽ ህይወት ከንቱ ህይወት ነው፡፡

ሃዋሪያው የእግዚአብሄርን ስራ ለረጅም ጊዜ ከሰራ በኋላ ተመልሶ በከንቱ ሮጬ እንዳይሆን በማለት ህይወቱን ሲመዝን እናያለን፡፡

ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው። ሮሜ 14፡22

ሰዎች በትክክል ህይወታቸውን መመዘን ካልቻሉ ስህተታቸውን ማስተካከል አይችሉም፡፡ ሰዎች እንዴት ህይወታቸውን ከጊዜ ወደጊዜ መመዘን እንዳለባቸው ካላወቁ ለተሻለም ስራ አይነሱም፡፡ ሰዎች ህይወታቸውን በትክክል መመዘን ካልቻሉ ደስታቸውን ያጣሉ፡፡ ሰዎች በትክክል ህየወታቸውን ካልመዘኑ እግዚአብሄር በውስጣው ባስቀመጠው በጎነት እግዚአብሄርን ፈፅመው ማክበር አይችሉም፡፡

ህይወታችንን ግን እንዴት ነው የምንመዝነው፡፡

በክርስትና ህይወታችንን የምንመዝንበት መንገድ ታማኝነታችንን በመመዘን ብቻ ነው፡፡ ከታማኝነት ውጭ ራሳችንን ለመመዘን የምንችልበት ትክክለፃ መመዘኛ አናገፅም፡፡

ታማኝነት የህይወታችን ብቸኛው መለኪያ ነው፡፡ ሰው ታማኝነቱ የሚታየው ባለው ፣ እግዚአብሄር በሰጠውና በእጁ ባለው ነገር ነው ፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን የሰጠንን መክሊት እንዴት እንደተጠቀምንበት ነው፡፡

  • ታማኝነታችን የሚለካው ባለን እወቀት ነው፡፡

ታማኝነታችን የሚለካው በሆነ እውቀት ሳይሆን ባለን እውቀት በተሰጠን እውቀት ምን ያህል ታማኝ መሆናችን ነው፡፡

የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48

  • ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር በሰጠን ጊዜ ነው፡፡

እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ በትክክል ለእግዚአብሄር ክብር አውዬዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ቃሉን ለማንበብ በሚገባ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ጌታን ለማምለክ ተጠቅሜበታለሁ? እግዚአብሄር የሰጠኝን ጊዜ ፊቱን ለመፈለግ ተጠቅሜበታለሁ?

  • ታማኝነታችን የሚለካው በሃይል አስተዳደራችን ነው፡፡

እግዚአብሄር የሰጠንን ሃይልና ችሎታ ለክፉ ነገር ላለመጠቀም መወሰናችን ታማኞች ያደርገናል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ሃይል ግን በጥላቻና በመለያየት ላይ ካጠፋነው በታማኝነት አልተመላለስንም፡፡

  • ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር በሰጠን ገንዘብ ነው፡፡

እግዚአብሄር ለመብላት የሰጠንን መብላታችን እግዚአብሄር ለመዝራት የሰጠንን በመዝራታችን ታማኝነታችን ይለካል፡፡

  • ታማኝነታችን የሚለካው የተሰጠንን መክሊት አጠቃቀማችን ነው፡፡

ታማኝነታችን የሚለካው እግዚአብሄር የሰጠንን መንፈሳዊ ስጦታን ለቤተክርስቲያን ጥቅምና ለእግዚአብሄር ክብር እንዴት በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ነው፡፡

አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። ማቴዎስ 25፡18-19

  • ታማኝነት የሚለካው በተሰጠን ተፅእኖ ነው፡፡

ታማኝነታችን የሚለካው በተሰጠን የተሰጠንን ተሰሚነት ለእግዚአብሄ ክብር ወይም ለራሳችን ጥቅም መጠቀማችን ነው፡፡

ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡23

ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ የተባለው ባሪያ ለተሻለ ሃላፊነት ይሾማል፡፡ አስተውላችሁ እንደሆነ የጠየቃቸው ያልሰጣቸውንም ሳይሆን የሰጣቸውን አንዴት በታማኝነት እንዳስተዳደሩት ብቻ ነው፡፡ የምንመዝነው ታማኝነታችንን ብቻ ነው፡፡ ታማኝ ከነበርን ፈተናውን አልፈናልና ደስ ሊለን ይገባል፡፡

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ታማኝ #ትጉህ #መክሊት #ትውልድ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ሃሳብ #ገንዘብ #ጊዜ #ትግስት #መሪ