የቤተሰብ የአጋርነት

partnershippiece.jpgበቤተሰብ አጋርነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰዎች ውስን ከመሆናቸው የተነሳ ለተሻለ ውጤት ሌላው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተሻለ ፍሬያማነት ያለው በግንኙነት አጋርነት ነው፡፡ አጋሮቻችን በበዙ ቁጥር ፍሬያማነታችን ይበዛል፡፡ እግዚአብሄር በአጋርነት ያስቀመጠውን በረከት እንዴት መጠቀም እንደምንችል በተረዳን ቁጥር በሁሉም ነገራችን እንሰፋለን እናድጋለን፡፡

ባል በረከት ነው፡፡ ወንድ በተፈጥሮው የራሱ ሞገስ አለው፡፡ ወንድ ሚስትን ሲያገኝ በረከቱ ይበዛል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገኝ ሞገሱ ይጨምራል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገባ ብቻውን ማድረግ ከችለው በላይ ማድረግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው በአጋርነት ውስጥ የታመቀ ታላቅ ሃይል ስላለ መፅሃፍ ቅዱስ ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ የሚለው፡፡

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22.

ቤተሰብ የሚከናወነው በሚስትና በባል አጋርነት ነው፡፡ የቤተሰብ ፍሬያማነት የሚለካው ሚስት እና ባል በተናጥል ባላቸው በረከት ሳይሆን በአጋርነታቸው በሚመጣው በረከት ነው፡፡ የቤተሰብ ስኬት የሚለካው ወንድ ወይም ሴት በተናጥል ባላቸው ስኬት ስኬት ሳይሆን በአጋርነት በሚያገኙት ስኬት ብቻ ነው፡፡ የትኛውም የተናጠል ስኬት እንደአጋርነት በቤተሰብ እንደሚገኘው ስኬት ይበልጥ የበዛ አይሆንም፡፡

ወንድ ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረው ክህሎት አለው፡፡ ወንድ ቤተሰብን እንዲያገለግልበት አብሮት የተፈጠሩ ስጦታዎች አሉት፡፡ ወንድ የተጠራው ቤተሰቡን ለመጠበቅ በመከላከል ምሪትን ለመስጠት ብሎም አስቸጋሪ ነገርን ከፊት ሆኖ ለመጋፈጥ ችግሮችን ለመጠርመስ ነው፡፡ ባል የቤተሰቡ ደህንነት ለመጠበቅ ፣ ምሪትን ለመስጠትና ዋና የገቢ ምንጭ በመሆን የቤተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አገልጋይ ነው፡፡

ሴት እንዲሁ ስትወለድ የተወለደችው ለቤተሰብ ከሚጠቅም ልዩ ክህሎት ጋር ነው፡፡ ሴት በዋነኝነት ቤተሰቡ የምታገለግለው  ቤተሰቡን በማስተዳደር ለቤተሰቡ እንክብካቤ ማድረግ ነው፡፡

ወንድ በዋነኝነት የቤተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ክህሎት ከእግዚአብሄር ተችሮታል፡፡ ወንድ ከእግዚአብሄር ስለተሰጠው የመሪነት ስጦታ  ምክኒታይ የእግዚአብሄርን ፊት በመፈለግ ቤተሰቡን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ታላቅ ሸክም ተጥሎበታል፡፡

ሴት ደግሞ እግዚአብሔር በውስጥዋ ከፈጠረው ክህሎት የተነሳ ለቤተሰብዋ እንክብካቤ ለማድረግ ቤተሰቡ ያለውን ነገር በጥበብ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት በእርስዋ ላይ ወድቆዋል፡፡

በቤተሰብ ሙሉን የእግዚአብሄርን መልክ የሚያንፀባርቁት ወንድና ሴት ናቸው፡፡ የወንድና የሴት አጋርነት እግዚአብሄር በቤተሰብ ውስጥ ያስቀመጠው ሙሉ ሃይል እንዲወጣና ለብዙዎች በረከት እንዲሆን ያስችለዋል፡፡

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27

ሊተባበሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድ ከሴት ጋር ሊፎካከር በፍፁም አይችልም፡፡ አንዱ የሌላውን ጉድለት እንደሚሞላና የሌላውን ድካን እንዲሸፍን የተላከ አጋር የቤተሰብ አባል ለአንድ አላማ ሊሰሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድና ሴት ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡

የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ዘፍጥረት 9፡22-23

ወንድ ከሴት የተለየ ችሎታና ሃላፊነት አለበት፡፡ ሴትም ከወንድ የተለየ ሃላፊነትና ችሎታ ጋር ተፈጥራለች፡፡ ሁለቱም በቤተሰብ ያላቸውን ሃላፊነት ከተወጡ ቤተሰቡ እግዚአብሄር ወደዳየለት የክብር ደረጃ ይደርሳል፡፡ ሁለቱም ያላቸው ሃላፊነትና ችሎታ ክቡርና ከእግዚአብሄር የተሰጠ ነው፡፡ የሚያገለግሉበት መንገድ ይለያይ እንጂ ሁለቱም አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሚያገለግሉበት የህይወት አቅጣጫ ስልጣኑም አላቸው፡፡

እያንዳንዱ እግዚአብሄር በሰጠው የሃላፊነት ቦታ የተከበረ ነው፡፡ ባልተሰጠው ሃላፊነት አንዱ ለሌላው ይገዛል፡፡ የቤተሰቡን አጠቃላይ መሪነት በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለወንዱ ይገዛሉ፡፡ የቤተሰቡን ዝርዝር አስተዳደር በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለሴትዋ ይገዛሉ፡፡

ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ኤፌሶን 5፡21

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ሚስት #ባል #ቤተሰብ #ወንድ #ሴት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የአጋርነት ሃይል – በንግድ

handshake1.jpgየህይወት ስጦታ ሁሉ በአንድ ሰው ውስጥ የለም፡፡ በህይወት ስኬታማ ለመሆን እያንዳንዳችን ሌሎች ያስፈልጉናል፡፡ ስኬታማ ለመሆን በህይወታችን እኛ የሌለን ስጦታ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ የአንድን ሰው ህይወት የሚሰራው የሰዎች አስተዋፅኦ ነው፡፡ በህይወት ለመከናወን በአንዳንድ የህይወት ክፍላችን ከእኛ የተሻሉ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ላላው ከእኛ እንደሚሻል ካላወቅን በሰዎች የተሻለ ስጦታ መጠቀም ያቅተናል፡፡ ትኩረታችን በራሳችን ስጦታና ችሎታ ላይ ብቻ ከሆነ  የሌሎችን ስጦታ አስተዋፅኦ በህይወታችን እንገድላለን፡፡

ለእኛ ተራራ የሚሆንብንን ነገር በቀላሉ የሚሰራው ሌላ ሰው አለ፡፡ ለእኛ ጭንቅ የሚሆንብን ነገር ለሌላው እንደ ጨዋታ ነው፡፡ የስጦታችን መለያየት ልዩ ያደርገናል እንጂ እኛን ታናሽ ሌላውን ታላቅ አያደርገውም፡፡ በሌላው ስጦታና ክህሎት ለመጠቀም በተወሰነ የህይወት ክፍል ሌላው ከእኛ እንደሚሻል በትህትና መቁጠር ይጠይቃል፡፡

ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3

ለህይወት ስኬት አጋርነት ወሳኝ ነው፡፡

የንግዱን አለም ብንመለከት በአለም ላይ በንግድ ታላላቅ ጥርመሳዎች የመጡት በንግድ አጋርነት አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ነጋዴ ደንበኛን የማሳመንና ወጥቶ ምርቱን የመሸጥ ልዩ ችሎታ አለው፡፡ አንዳንዱ ነጋዴ ደግሞ ንግዱን ማስተዳደር የሚገባውንና የሚወጣውን እቃ መከታተል  እንዱሁም የተሸጡትን እቃዎች ተከታትሎ ገንዘቡን በመቀበል በመሳሰሉት የአስተዳደር ስራ የተካነ አለ፡፡ ስለዚህ በመሸጥ የተካነው ነጋዴና በማስተዳደር የተከናው ነጋዴ በአጋርነት ቢሰሩ ሁለቱ በተናጥል ከሚሰሩት የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ አንድ ንድግ በአንድ ሰው ክህሎት ላይ ብቻ ካልተደገፈና አጋሮቹ ሁሉ በጠንካራ ጎናቸውና በየክህሎታቸው ለድርጅቱ ጠንክረው ከሰሩ ድርጅቱ የማያድግበት ምክኒያት አይኖርም፡፡

ድርጅቱ ሲያድግ እምዲሁ አንዱ ለሌላው አስተዋፅኦ እውቅና ካልሰጠ እና ክብሩን ሁሉ ጨቅልሎ ኪሱ ከከተተ አጋርነቱ ሊቀጥል ብሎም በአጋርነቱን የሚገኘው ጥቅም ሊቀጥል አይችልም፡፡ የድርጅቱ ማደግና መስፋት እንጂ ክብሩን ማን ይወስደዋል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ካልሆነ በአጋርነት ድርጅት ያድጋል፡፡ በድርጅት እድገት ሲመጣ በአጋሮቹ ሁሉ ምክኒያት እንደመጣ እውቅና መስጠት ይጠይቃል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን በአጋርነት የመጣውን እድገት የእኛ ብቻ ለማድረግ ስንሞክርና በአጋርነት ሃይል የመጣውን ውጤት በእኛ ምክኒያት የመጣ ሲመስለን እንታለላለን፡፡ በአጋርነት የተለቀቀው ጥቅምን “ይህ አጋሬ ባይኖር ኖሮ ክንሩንና ጥቅሙ ሁሉ የኔ ይሆን ነበር” ብለን ካሰብን ነገር ይበላሻል፡፡ በአጋርነቱ ሁሉ ምክኒያት ጥቅሙ እንደመጣ ማስተዋል ነው፡፡ የመጣውን ውጤት ብቻ ሳይሆን በአጋርነቱ ላይ  የተደረገውን አስተዋፅኦ ብንመለከት አጋሬ ባይኖር ኖሮ ይህ ሁሉ የእኔ ይሆን ነበር ወደሚል አላግባብ ቁጭት ውስጥ አንገባም፡፡

ለተሻለ ጥቅም በአገፋርነት ለመስራት ራሳችንን ትሁት እናድርግ፡፡ በአጋርነት የመጣውን ድል የራሳችን ብቻ አናድርገው፡፡ እግዚአብሄር የሚባርከን አጋርነትን ሁሉ አይቶ ነው፡፡ በአጋርነት ያገኘነው ድል ብቻችንን ብንሆን ኖሮ የማናገኘው ድል ነው፡፡ ሚስት ስናገባ የሚለቀቅልን በረከት ሚስት ካላገባው ይጨምራል፡፡

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ንግድ #ሚስት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል

finding-a-wife.pngአንድ አሳ አጥማጅ ነበር ይባላል፡፡ ብቻውን ሲኖር በቀን አንድ አሳ ያጠምዳል ይጠብሳ ይበላል ይተኛል፡፡ ሰዎች ሚስት አግባ ብለው መከሩት፡፡ ሚስት ካገባ በኋላ በቀን ሁለት አሳ ማጥመድ ጀመረ፡፡ ልጅ ሲወልድ ሶስት አራት አምስት አሳዎች ያጠምድ ጀመረ፡፡ እንደዚህ እያለ ሰባት ልጆች በመውለዱ ከሚስቱ ጋር የሚበቃውን በድምሩ ዘጠኝ አሳ ያጠምድ ጀመረ፡፡

ሳያገባ ሲያጠምድ ከነበረው አንድ ብቻ አሳ ጋር ሲያስተያየው ዘጠኝ አሳ ብዙ ነው፡፡ እና ምን አለ ይባላል? ሚስቴና ልጆቼ ባይኖሩ ኖ ዘጠኙም የእኔ ይሆኑ ነበር አለ ይባላል፡፡ ነገር ግን በውስጡ የተቀመጠው ዘጠኙ አሳዎች የመጡት ሚስት በማግባቱና ልጆች በመውለዱ መሆኑን ዘንግቶት ነበር፡፡

የዚህ አሳ አጥማጅ ታሪክና በመጨረሻ የተናገረው ንግግር ቢያስገርመንም እንደ አሳ አጥማጁ የሚያስቡ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሄር እንደ ቤተሰብ የባረካቸው በረከት የእነርሱ ብቻ አድርገው የሚያስቡ፡፡ እራሳቸውን ብቻ የተመረቁ ሰዎች አድርገው የሚያዩና ሌላውን ግን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አሉ፡፡

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22

መፅሃፍ ሚስትን ያገኘ ከእግዚአብሄር ሞገስን ይቀበላል ይላል፡፡ ሰው ሚስት ሲያገባ በሚስቱ ስም የእግዚአብሄር አቅርቦት ይጨምራል፡፡ ሰው ሚስት ሲያገባ ካላገባው ሰው ይልቅ እንደ ቤተሰብ ሞገሱ ይበዛል፡፡ ሰው ልጅ ሲወልድ እንዲሁ ለተጨማሪ በጀት ሞገሱ ይጨምራል፡፡ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የራሱን በጀት ይዞ ነው ወደ ቤተሰቡ የሚመጣው፡፡

እግዚአብሄር መጀመሪያ ስለሚስቱ ከዚያም ስለልጆቹ ብሎ የባረከውን በረከት ሁሉ ወደ ራሱ ስም የሚያዞር ፣ ሁሉም በእርሱ ቅልጥፍና ምክኒያት እንደመጣ የሚቆጠር ሰው የተሳሳተ መረዳት ያለው ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር ቤተሰብን የሚባርከው ሁሉንም የቤተሰብ አባላት አስቦ ነው፡፡ እግዚአብሄር አቅርቦቱ የሚጨምረው በቤተሰቡ ውስጥ ባሉት አጋሮች ብዛት ልክ ነው፡፡

አንድ በቅርብ የማውቃት እህት ከመስራ ቤት ደሞዝ ሲጨመርላት ለቤት ሰራተኛዋ ደሞዝ ትጨምራለች፡፡

እግዚአብሄር ስለንግድ ድርጅቱ አባላት የባረከውን በረከት ሁሉ ለመዋጥ የሚፈልግ ሰውና እግዚአብሄር ድርጅቱን የባረከው በድርጅቱ ስለሚሰሩት ሰዎች ሁሉ ምክኒያት እንደሆነ የማያስብ ሰው የእግዚአብሄርን የበረከት መንገድ ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር የምታገለግላቸውና የሚጠቅሙህን ደንበኞች የሚልከው ስለድርጅቱ አጋር ባለቤቶችና በድርጅቱ ውስጥ ስለሚሰሩት ሰዎች ሁሉ ምክኒያት ነው፡፡ ድርጅቱ ሲያድርግ ሁሉም አብሮ እንዲያድግ እንጂ አንድ ሰው ብቻ ተለይቶ እንደተመረቀ ሁሉንም ክብር ወደራስ ማድረግ የእግዚአብሄር አሰራር አይደለም፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች ሁሉ እንደ አጋር ሰራተኛ እንጂ ባለቤቱን ሊጠቅሙ ብቻ እንደቀመጡ ያልታደሉ ሰዎች መቁጠር አግባብ አይደለም፡፡

ቤተክርስትያንም ሆነ አገልግሎት ሲያድግ የእግዚአብሄር ሞገስ የመጣው በአገልጋዪችና በተጠቃዎቹ ሁሉ ፍላጎት ምክኒያት እንደሆነ ተረድቶ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ካልሆነ በረከቱ መሰረት አይኖረውም፡፡ አገልግሎቱን እንደ አጋርነት ካላየው አንድ ሰው ብቻውን እንደ ተመረቀ ሌሎች ለእርሱ እንዲሰሩ እንደተፈጠሩ መቁጠር ሞኝነት ነው፡፡ ሁላችንም አብረን እንድናድግ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ስለ ህብረትና አጋርነት የመጣውን የእድገትን ክብር ለብቻ ጠቅልሎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ሚስት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ዘጠኙ የህብረት ጥቅሞች

fellowship.jpgየእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ፈፅመን እግዚአብሄርን በሚገባ እንድናከብረው እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ዋና ዋና በረከቶች አንዱ የቅዱሳን ህብረት ነው፡፡ የወንድሞች መሰብሰብና ህብረት የእግዚአብሄርን ስራ ከምንሰራበት ቁልፍ መንገዶች አንዱ ነው፡፡

እግዚአብሄር ራሱን አባት አድርጎ መስጠት ብቻ ሳይሆን እህቶችና ወንድሞች ስለሚያስፈልጉን አውቆ የቅዱሳንን ህብረት ሰጥቶናል፡፡

በመጀመሪያይቱ ቤተክርስትያን ለህብረትና ለመሰብሰብ እጅግ ልዩ ትኩረት ከመስጠታቸው የተነሳ የቤተክርስትያን ጥንካሬና በህብረት ያገኙትን ውጤት እንመለከተናል፡፡

በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። ሐዋርያት 2፡46-47

በኢየሱስ ስም ህብረት ባደረግን መጠን ውጤታማነታችን እየጨመረ ስለሚሄድ ታላቁን ወንጌልን የመስበክ ተልእኮዋችንን በሚገባ መወጣት እንችላለን፡፡

በቅዱሳን ህብረት ብቻ ስለምናገኛቸው በሌላ በምንም መንገድ ግን ስለማናገኛቸው ታላላቅ ጥቅሞች እንመልከት፡፡

 1. የአንድነት አምልኮን ክብር የምንለማመደው ከቅዱሳን ጋር ተሰብስበን ነው፡፡

በአንድነት ሆነን እግዚአብሄርን ማምለክ እጅግ ወሳኝና የክርስትና ህይወታችን የሚያለመለም ራሳችንን እንድንረሳና በእግዚአብሄር መንፈስ እንድንረሰርስና እንድንዋጥ የሚያስችለን ልዩ ልምምድ ነው፡፡ በአምልኮ የሚመሩንን ሰዎች የሰጠን ለህብረት እንጂ በግላችን አይደለም፡፡

ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙር 96፡6-7

 1. የፀጋ ስታዎች ተጠቃሚ የምንሆነው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

በምንሰበሰብበት ጊዜ እግዚአብሄር በሌላው ወንድማችን በኩል የሚገልፀው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ህብረቱን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ይመጣል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተሰጠው ሌላውን ለማነፅ ፣ ለማፅናናትና ለመጥቀም ነው፡፡

እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡26

ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡3

 1. የአገልግሎት ስጦታዎች የተሰጡት ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡

እግዚአብሄር ስጦታዎችን ሐዋርያትን ፣ ነቢያትን ፥ ወንጌልን ሰባኪዎችን ፥ እረኞችንና አስተማሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ እድገታችንና ክርስቶስን ለመምሰል ብሎም ለአገልግሎት ለመታጠቅ እግዚአብሄር ለቤተክርስትያን የሰጣቸውን የአገልግሎት ስጦታዎች የምንጠቀመው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡11-13

 1. ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ነው፡፡

እግዚአብሄር ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎች የሰጠው ለቤተክርስተያን ህብረት ነው፡፡ የሚያስተምሩን የሚመክሩንና የሚገስፁን በህብረት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡

እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ቆላስይስ 1፡28

ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ዕብራዊያን 13፡17

 1. የመንፈሳዊ ህይወት ደህንነታችን የሚለካው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖራችንን የምናወቅው በህብረት ስንሆን ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወደ መንግስተ ሰማያት እየሄድን እንደሆነ የምናውቀው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡ ለወንጌል እንደሚገባ የማይኖረውን የምናቀናው በህብረት ሲገኝ ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወንድማችንን እንዳላሳዘንን የምናውቀው ከወንድማችን ጋር አብረን በመኖር፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል እየኖርን መሆናችንን እርግጠኛ የምንሆነው ብቻችንን በመኖር አይደለም፡፡ ትክክል መሆናችንን የምናውቀው የምንጠየቅለት ህብረት ሲኖር ነው፡፡ ስለ እውነተኝነታችንም ሰዎች የሚመሰክሩት በህብረት ስንገኝ ነው፡፡

ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-18

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ዕብራዊያን 13፡7

 1. ፍቅርን በተግባር የምንማረውና የምንረዳው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡

ፍቅር ለሌላው መልካም ማሰብ መናገርና ማድረግ ነው፡፡ ለብቻ ኖሮ ፍቅር አለኝ ማለት አይቻልም፡፡ የሚበድልና የሚታገሱት ባለበት ነው ፍቅርን የምንለማመደው፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ባለበት ህብረት ነው ፍቅርን ፣ ይቅር ማለትን እና ምህረትን የምንለማመደው የምናሳድገው፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው ሌላውን መቀበልና መውደድን የምንማረው፡፡

ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ኤፌሶን 3፡18-19

 1. በቅዱሳን ህብረት ስንገኝ ነው የጠፋውን የምንፈልገው፡፡

በቅዱሳን ህብረት ስንሆን ነው የጠፋውን የምናውቀው፡፡ በቅዱሳን ህብረት ስንገናኝ ነው የደከመውን ሸክም ለመሸከም መተያየት የምንችለው፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ 6፡1-2

 1. ከወንድማችን ፀጋ የምንካፈለው በመገናኘት ነው፡፡

እግዚአብሄር ባሳደገን ፀጋ ሌሎችን የምንመግበው ስንገናኝ ስናወራ ስንጫወት በቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄን ቃል ስንጫወት ነው በቃል ፀጋን የምንለዋወጠው፡፡ እግዚአብሄር ባሳደገኝ የህይወት ክፍል በምናገረው የፀጋ ቃል ነው ሌላውን የፀጋ ሃይል የማካፍለው፡፡ በህብረት ነው ሌላውን የምረዳውና ካለበትና ከተያዘበት የሚወጣበትን ፀጋ የማካፍለው፡፡

ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

 1. ስንተያይ ነው አንዳችን አንዳችንን የምንሞርደው፡፡

በህብረት ነው ለፍቅርና ለመልካም ስራ የምንበረታታው፡፡ በህብረት ውስጥ ነው አንዳችን እንዳችንን የምንስለው፡፡ ስንገናኝ ነው አንዳችን የአንዳችንን የፍቅርና የመልካም ስራ ፍም የምናራግበው የምናነሳሳውና የምናቀጣጥለው፡፡

ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡24-25

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?

couple-holding-hands-anchor-tattoos-600x375.jpgከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡35-39

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 1ኛ ዮሐንስ 4፡10

ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው፤ ዕብራውያን 6፡17-19

የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ኤፌሶን 3፡16-19

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡35-39

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #የክርስቶስፍቅር #ስር #መሰረት #ትእዛዝ #መስጠት #ሃሳብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን

3dd2ec58bd3d62ca64f1dc59c8688fca.jpgያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡9-10

በአብ ቀኝ በክርስቶስ መቀመጣችን ሁሉንም የህይወት ጥያቄያችንን ይመልሳል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ባለን የክብር ብዛት ውርደትን እንታገሳለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ባለን ስፍራ ሰዎች የሚጋደሉለትን የምድርን ነገር ሃብት ፣ ዝና እና ስልጣን እንንቃለን፡፡

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ቆላስይስ 3፡1-2

 1. ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፡፡

በምድር ላይ ታዋቂ ላንሆን አንችላለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ግን ታዋቂዎች ነን፡፡ እግዚአብሄር ልኮናል ፣ እግዚአብሄር ያውቀናል ፣ እግዚአብሄር ተደስቶብናል፡፡ ሰው እንደሚያይ የማያየው እግዚአብሄር ያውቀናል፡፡ ሰው የናቀውን የሚያከብር እግዚአብሄር ዋጋ ሰጥቶናል፡፡ ጉዳዬ ልንለው የሚገባው የእግዚአብሄርን እይታ ብቻ ነው፡፡ በሰው ዘንድ ለመታወቅ ጉልበታችን አንጨርስም፡፡ ለጠራን ለመሮጥ እንጂ ለታዋቂነት ለመፍጨርጨር ትርፍ ጊዜ የለንም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን እንድንፈፅመው የጠራንን ጥሪ በዝምታ እንፈፅማለን፡፡  ሰው እንደ እግዚአብሄር አያውቀንም የሰው ማክበርን ማዋረድም አያስደንቀንም፡፡ በሰው ዘንድ ያልታወቅን ስንባል የታወቅን ነን፡፡ ሰውንም ለማስደሰት በምድር ላይ የለንም፡፡

ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ዮሃንስ 12፡43

ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ገላትያ 1፡10

 1. የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፡፡

የምንሰራው ምድራዊ እና ስጋዊ ነገር አይደለም፡፡ የምንኖረው ፣ የምንወጣውና የምንገባው በራሳችን ጉልበት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር እርዳታ በሃይል ከእኛ ጋር አለ፡፡ እንድንኖርለትና እንድናገለግለው የጠራን በሃይል ከእኛ ጋር ይሰራል፡፡ ምንም በጎ ነገር ቢገኝብን ከእርሱ ነው፡፡ በራሳችን ስንደክም እንኳን የእርሱ ሃይል ተሸክሞ ያሻግረናል፡፡ ስንደክም የእግዚአብሄ ፀጋ ይበዛልናል፡፡ ስንዋረድ እግዚአብሄር ያከብረናል፡፡ ስንደክም ያን ጊዜ ሃይለኛ ነን፡፡ የውጭ ሰውነታችን ሲጠፋ የውስጡ ሰውነታችን እለት እለት ይታደሳል፡፡ የምንሞት ስንመስል ህያዋን እየሆንን ነው፡፡

ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16

በተዋረድን ቁጥር እየጠለቅን ስር እየሰደድንና መሰረታችን እየሰፋ ነው፡፡ እምነታችን ሲፈተን ወርቅ በእሳት እንደሚፈተንና ይበልጥ እንደሚጠራ እምነታችን እየጠራና እየከበረ ነው፡፡

በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡6-7

 1. የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፡፡

ሰዎች የተለያየ ነገር ቢያደርጉን አያስቆሙንም፡፡ ምናችንንም ቢወስዱብን ራእያችችንን ፣ እምነታችንንና አገልግሎታችንን ሊወስዱብን አይችሉም፡፡ ሰዎች ሊያጠፉን ቢፈልጉ የእግዚአብሄር እጅ ከእኛ ጋር ስላል በከንቱ ይደክማሉ፡፡ በእግዚአብሄር ምህረት ስለምንኖር የሰዎችም ይሁን የሰይጣን ቁጣ በህይወታችን ላይ የሚያመጣው ልዩነት የለም፡፡

አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። ሐዋርያት 5፡38-39

ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 9፡36-37

 1. ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፡፡

በአለም በሚሆነው ነገር እናዝናለን፡፡ ሰዎች ለአለማዊነት ህይወታቸውን ሲሰጡና ለአለም ነገር ሲሮጡ ስናይ ፃድቅ ነፍሳችን ትጨነቃለች፡፡ በጌታ ግን ደስ ይለናል፡፡ በነገሮች ልናዝን እንችላለን በጌታ ግን ሁልጊዜ ደስ ይለናል፡፡ ሰላማችንና ደስታችን አለም እንደሚሰጠው በሁኔታውች የሚለዋወጥ አይደለም፡፡ በመከራ ብናልፍም በጌታ ግን ደስ ይለናል፡፡ በአለም ያለውን መከራ የምንፈጋፈጠው በደስታ ነው፡፡ በአለም ያለው የሚያሳዝን ነገር ሁሉ ተሰብስቦ በልባችን ያለውን ደስታ ሊያጠፋው አቅም የለውም፡፡ በልባችን ያለው ደስታ ከአለም ሃዘን ሁሉ ይበልጣል፡፡

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4

 1. ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፡፡

ራእያችን ሰዎችን ማገልገል እንጂ ለራሳችን መጠቀም አይደለም፡፡ ራእያችን ሰዎችን ማንሳት እንጂ ራሳችን መነሳት አይደለም፡፡ ራእያችን ሰዎችን ማገልገል እንጂ በሰዎች መገልገል አይደለም፡፡ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት እጅግ ከመባረካችን የተነሳ ለምንበላውና ለምንጠጣው አንጨነቅም፡፡ የሚያሳስበን የሰዎች መባረክ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቀኝ ከመቀመጣችን የተነሳ የዘወትር ሸክማችን ሰዎችን ባለጠጋ ማድረግ ነው፡፡

የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28

የሚያረካን ሰዎች ሲለወጡ ማየት ነው፡፡ የምንረካው ሰዎች ካሉበት ነገር ሲወጡ ነው፡፡ የምንረካው ሰዎች ከከበባቸው ነገር አልፈው ሲሻገሩ ነው፡፡ የገንዘብ ሃብት ባይኖረንም የሰው ሃብታሞች ነን፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ባይኖረንም በገንዘባችን ያፈራናቸው በሰማይ የሚቀበሉን ሰዎች አሉ፡፡

እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9

የሰው መንፈሳዊነት እና ስኬት ባገኘው ገንዘብ የሚሰራው ስራ እንጂ ባጠራቀመው በምድራዊ ሃብቱ አይለካም፡፡ በምድር ቤተመንግስት ላናስገነባ አንችላለን በህይወታችን ዘመን ሁሉ የእግዚአብሄርን ቤተክርስትያን በገንዘባችን እንደግፋለን፡፡ የብዙ ገንዘብ ባለቤቶች ባንሆንም ባለን ገንዘብ የመልካም ነገር ባለጠጎች ነን፡፡

ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡18-19

የስራችን የምስክር ደብዳቤ በብእርና ቀለም የተፃፈ ሳይሆን በእኛ አማካኝነት የእግዚአብሄር ቃል በልባቸው የተፃፈ ሰዎች ናቸው፡፡

እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ 3፡1-2

 1. አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው፡፡

በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ተባርከናል፡፡ ያለን ትልቁ ሃብት የእግዚአብሄር አቅርቦት ነው፡፡ ያለን ትልቁ ሃብት በእኛ ስም የተከፈተልን መንፈሳዊ ሂሳብ ወይም አካውንት ነው፡፡ እጃችን ባዶ ቢሆንም ከባለጠጋው አባታችን በእምነት እንዴት እንደምንቀብል የምናውቅ የእምነት ባለጠጎች ነን፡፡ ኪሳችን ባዶ ቢሆንም የሚያስፈልገንን ነገር በሚያስፈልገን ጊዜ የማያሳጣን እግዚአብሄር እረኛችን ነው፡፡ የሚታይ ሃብት ባይኖረንም የሚያስፈልገንን ሁሉ የምናገኝበት የማይታይ ሃብት አለን፡፡ ምድራዊ ሃብት ባይኖረንም እግዚአብሄርን የምናስደስትበትና ፈቃዱን በምድር ላይ የምንፈፅምበር እምነት አለን፡፡

በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ፊልጵስዩስ 4፡17

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6

ክርስቶስን የሰጠን እግዚአብሄር አብሮ ሁሉንም ሰጥቶናል፡፡ የሚጎድለን እንዳይኖር አድርጎ በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ባርኮናል፡፡

ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡21-23

ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡9-10

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ያልታወቁ #የታወቅን #የምንሞት #ሕያዋን #የተቀጣን #አንገደልም  #ኀዘንተኞች #ደስ #ድሆች #ባለጠጎች #የሌለን  #ሁሉየእኛነው #ጭንቀት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

እንደተቀመጠ መመላለስ

sitting walking.jpgክርስቶስ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ ከመክፈሉ የተነሳ በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጥ ችለናል፡፡ ክርስትናን በሙላት ለመኖር ከክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ግዴታ ነበር፡፡

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

ክርስትና ተግባራዊ ኑሮ ነው፡፡ ካልተቀመጥንና ከተቀመጥነበት የክብርና የስልጣን ስፍራ አስተሳሰብ ካልተነሳን ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ አንችልም፡፡ ተመላለሱ የሚለውን የጌታን ትእዛዝ መፈፀም የምንችለው ስለመቀመጣችን መረዳት ሲኖረን ነው፡፡ ስለመቀመጣችን ጌታን እንደ አዳኝ ከመቀበል ውጭ ምንም ያደረግነው የለም፡፡ ግን መቀመጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከእግዚአብሄር ቃል ካልተረዳን ግን የመቀመጥን ጥቅም ተጠቃሚዎች መሆን አንችልም፡፡

በክርስቶስ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ አይችልም፡፡ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ሰው ደግሞ እንደተቀመጠ ሰው ይመላለሳል፡፡ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ወይም የማያውቅ ሰው በህይወቱ ይታያል፡፡

ሰው በክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ እንዳልተቀመጠ መኖር ይችላል፡፡ መቀመጡን ያላወቀ ሰው የሚመላለሰው እንዳልተቀመጠ ሰው ነው፡፡

ያልተቀመጠ ሰው የሚመላለስባቸውምን መንገዶች እንመልከት፡-

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው አያርፍም፡፡

 

እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ነገሮችን የሚያደርገው በእረፍት አይደለም፡፡ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው ህይወቱ በግፊት የተሞላ ነው፡፡ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው መፀለይ ጭንቅ ነው ፣ የእግዚአብሄርን ቃል ማንበብና ማጥናት ተራራ ነው ፣ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው ከወንድሞች ጋር ህብረት ማድረግ ከባድ ስራ ነው ፣ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ላልተረዳ ሰው ለሌላው የኢየሱስን አዳኝነት መመስከር መከራ ነው፡፡

 

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ይጨነቃል፡፡

 

በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን የልጅነት ስፍራ እና የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባልነቱን ክብር ያልተረዳ ሰው ስለሚባላውና ስለሚጠጣው ሲጨነቅ ህይወቱን ያባክናል፡፡ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ ያልተረዳ ሰው የህይወት ግቡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን መፈለግ ሳይሆን እንደምራቂ የሚጨመረውን አህዛብ የሚፈልጉትን ነገር በመከተል ነው፡፡

 

ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡33-34

 

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው አይቆምም ይናወጣል፡፡

 

በአብ ቀኝ እንደተቀመጥን መረዳታችን የሚታየው በአስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ ነገሮች እንደፈልግናቸውና እንዳሰብናቸው ባልሄዱ ጊዜ ከሩጫችን የምናቆምና እጃችንን የምንሰጥ ከሆነ በአብ ቀኝ መቀመጣችንን አልተረዳንም፡፡ ክርስቶስን በመቀበላችን እንዲያው በነፃ የእኛን ምንም ጥረት ሳይጨምር የተሰጠንም ቢሆንም እንኳን በአብ ቀኝ መቀመጣችንን መረዳት ግን በህይወታችን ልዩነትን ያመጣል፡፡

 

ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡58

 

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በነገሮች ይፈራል፡፡

 

በክርስቶስ በአብ ቀኝ ወደ ተቀመጠ ሰው ፍርሃት በፍፁም ሊመጣ አይችልም ብንል እውነት አይሆንም፡፡ ነገር ግን በክርስቶስ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የሚያውቅ ሰው ፍርሃትን እንደማያስተናግድ እናውቃለን፡፡ እንደተቀመጠ ያወቀ ሰው ፍርሃት አያቆመውም፡፡ እንደተቀመጠ ያወቀ ሰው ፍርሃቱ እያለ ስሜቱን ሳይከተል የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀም ይቀጥላል፡፡

 

እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡7

 

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ይኖረዋል፡፡

 

በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው ስለማንነቱ እርግጠኛ ባለመሆኑ የምስኪንነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው የበታችነት ስሜት ያጠቃዋል፡፡ ያንን የበታችነት ስሜት ለመቋቋም ደግሞ በበላይነት ስሜት ሊያካክሰው ይሞክራል፡፡ የበታችነት ስሜት ያለበት ሰው ያንን ለማካካስ ሰዎችን በመቆጣጠር የበላይነት ስሜቱን ሊያሳይ ይጥራል፡፡ ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ያለበት ሰው ውድድሩ ሳይጀመር እጁን ይሰጣል፡፡ አልችልም አላልፍም አልወጣም በሚል አስተሳሰን ተሞልቶዋል፡፡ በአብ ቀኝ እንተቀመጠ ያልተረዳ ሰው የእርሱ መጨረሻ በሰዎች እጅ እንደሆነ ይመስለዋል፡፡

 

ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡12

 

 1. እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው የተሸነፈ ኑሮ ይኖራል፡፡

 

በእግዚአብሄር ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በሰይጣን ምህረት እንደሚኖር ይሰማዋል፡፡ ሰይጣን አስኮናኝ ኑር ብሎ ካልደፈቀደለት ዋጋ እንደሌለው ይሰማዋል፡፡ የእርሱ መጨረሻ በሰይጣን መጠንከርና አለመጠንከር በአለም መጠንከርና አለመጠንከር እንደሚደገፍ ይሰማዋል፡፡ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በሰይጣን ፊት ተሸናፊ ነው፡፡ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያውቅ ሰው በአለምና በምኞትዋ ፊት የተሸነፈ ነው፡፡

 

ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡57

 

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡37

 

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

 

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የመቀመጥ እውነተኛ ትርጉም

throne 5.jpgበሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያደረገውን ነገር ሁሉ ያደረገው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ የተገረፈው ስለደዌው አይደለም ስለእዐኛ ደዌ እንጂ፡፡ ኢየሱስ የሞተው ስለሃጢያቱ አይደለም ስለእኛ ሃጢያት እንጂ፡፡ ኢየሱስ የተቀበረው በሃጢያቱ ስለሞተ አይደለም በሃጢያታችን ስለሞትን እንጂ፡፡ ኢየሱስ የተነሳው ስለሃጢያቱ ስለሞተ አይደለም፡፡ ስለሃጢያታችን ስለሞትን በእኛ ምትክ እንጂ፡፡ ኢየሲስ በአብ ቀፅ የተቀመጠው በአብ ቀኝ ስላልነበረ አይደለም፡፡ እኛ በአብ ቀኝ እንድንቀመጥ እንጂ፡፡

ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ስለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ስለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በአብ ቀኝ የተቀመጠው እኛን ወክሎ ነው፡፡

በክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጠናል ማለት ምን ማለት ነው፡፡ በአብ ቀኝ የመቀመጣችን ትርጉሙ ምንድነው

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ አንደተቀበለን ያሳያል፡፡

በክርስቶስ የመስቀል ስራ ምክኒያት እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎናል፡፡ኢየሱስ የሃጢያታችን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ በመክፈሉ እግዚአብሄር እኛን ለመቀበል ደስ ብሎታል፡፡ እኛን ለመቀበል ኢየሱስ በሰራው የመስቀል ስራ እግዚአብሔር ረክቷል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ ስለከፈለ እግዚአብሄር ከዚህ በላይ የሚጠብቀው ምንም መስዋእት የለም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ፈፅሞ ከከፈለው የሃጢያት ዋጋ የተነሳ ኢየሱስን እንደ አዳኝ የተቀበልን እኛን እንዳለን ተቀብሎናል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ሮሜ 5፡10

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን በጨለማው አለም ላይ ያለንን ስልጣናችንን ያሳያል፡፡

ከክርስቶስ ጋር በአብ መቀመጣችን የእግዚአብሄርን ስራ በምድር ላይ አንዳንፈፅም የሚያግደን ምንም የጠላት ሃይል አስከማይኖር ድረስ በጠላት ሃይል ሁሉ ላይ ስልጣን እንደተሰጠን ያሳያል፡፡

እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡22

ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። ኤፌሶን 1፡18-23

እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም።ሉቃስ 10፡19

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ክብር ያሳያል፡፡

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ስለሃጢያታችን ሊሞት ብቻ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ወደምድረ የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር ናሙና ሊያሳየን ነው፡፡ ኢየሱስ እንደሰው በምድር የተመላለሰው የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር ምሳሌ ሊሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ ነው ኢየሱስ እኔ ያደረግኩትን ከዚህም በላይ ታደርጋላችሁ ያለው፡፡

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ወደ እግዚአብሄር መነግስት መፍለሳችንን ያሳያል፡፡

ኢየሱስ በሞቱ የሰይጣንን ሃይል ድል በመንሳቱ እግዚአብሄር ከጨለማው ስልጣን አድኖናል፡፡ ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት አፍልሶናል፡፡ አሁን ያለነው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ነው፡፡ ዜግነታችን ሰማያዊ ነው፡፡

እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን የእግዚአብሄርን ወራሽነታችንን ያሳያል፡፡

በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን የእግዚአብሄር ወራሽ መሆናችንን ያሳያል፡፡ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡ ስለወደፊታችን ምንም አወዛጋቢ ነገር የለውም፡፡ እኛ የእርሱ መሆናችንና የእግዚአብሄር ወራሾች መሆናችንን ለማሳየት መንፈሱን ቀብድ ሰጥቶናል፡፡

በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። ኤፌሶን 1፡13-14

እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። ኤፌሶን 1፡11

ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ሮሜ 8፡17

 1. በክርስቶስ በአብ ቀኝ መቀመጣችን ከእግዚአብሄር ጋር ማረፋችንን ያሳያል፡፡

የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር አብረን የምንሰራ ነን፡፡ እርሱ የሚሰራውን ነው የምንሰራው፡፡ እርሱ የጀመረውን ነው የምንጨርሰው፡፡ በእርሱ ሃይል ነው የምንሰራው፡፡ እርሱ ነው ከእኛ ውስጥ የሚሰራው፡፡ በእርሱ መንፈስ ነው የምንሰራው፡፡ የምንሰራውን ሁሉ የምንሰራው በእረፍት ነው፡፡ እድላችንን እየሞከርን አይደለም፡፡ የምንጋደለው ገድል ውጤቱ የታወቀ ነው፡፡ አስቀድመን አሸናፊዎች ተደርገናል፡፡ አስቀድመን መጨረሻችን ታውቆዋል፡፡ አስቀድመን ተወስነናል

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሮሜ 8፡37

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

መመላለስ ከመቀመጥ ይጀምራል

sit.jpgለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ በሰው ጉልበት የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ልጅ መመላለስ የእግዚአብሄር ሃይልና አሰራርን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ነው ከመመላለስ በፊት መቀመጥ ይቀድማል የሚባለው፡፡

በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ በተቀመጥንበት ሃይልና ምሪት ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መኖር እንችላለን፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ባለንበት ስልጣን የምድር ህይወታችንን ሃላፊነት በስኬት እንወጣለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ በናለን ልዩ ስፍራ በምደር ላይ ነገሮችን ተቋቁመን እናልፋለን፡፡

በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ኤፌሶን 1፡3

በእግዚአብሄር ዘንድ ያለን ስፍራ በምድር ስፍራ እንዳንፈልግ ይረዳናል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለብ ስልጣን በሰይጣን ፊት እንዳንዋረድ ያስችለናል፡፡ በእግዚአብሄር ልብ ያለን ስፍራ ስንረዳ ከእግዚአብሄር ውጭ በምድር ምንም ነገር በልባች የመጀመሪያውን ስፍራ እንዳይዝ ያደርገናል፡ በእግዚአብሄ ዘንድ ያለን ከፍታ ስንረዳ በምድር ያለ ምንም ዝቅታ አያስደነግጠንም፡፡ በእግዚአብሄር እንደነገስን ስንረዳ ከጌታ ውጭ ምንም ነገር ንጉስ እንዳይሆንብን ያደርጋል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለን ከፍታ በምድር ራሳችንን እንድናዋርድ ያስታጥቀና፡፡ በሰማያዊ ያለን ስፍራ ለምድር ስፍራ እንዳንፎካከር ያግዘናል፡፡ በእግዚአብሄር ያለንን ክብር ስንረዳ የምድሩን ክብር እንድንቀው ያስችለናል፡፡

ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-4

ለእርሱ ለመኖራችን የሚያስፈልገውን ነገር ሳያዘጋጅ እግዚአብሄር አልጠራንም፡፡  ለእርሱ ለመኖርና ለእርሱ በሚገባ ለመመላለስ እግዚአብሄር የጠራን ለክርስትና ህይወት ሁሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰጥቶን ነው፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

በሰማያዊ ስፍራ ሳያስቀምጠን በፊት እንደ ልጅ ለእርሱ እንድንመላለስ አልጠየቀንም፡፡

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

በክርስቶስ ያለንን ስፍራ ፣ ስልጣንና ክብር ካላወቅን ለጥሪያችን እንደሚገባ መኖር አንችልም፡፡ በክርስቶስ ያለንን አቅርቦት ካለተረዳን በአቅርቦቱ በድል መመላለስ አንችልም፡፡

ለምሳሌ መኪና የተሰራው ለመነዳት ነው፡፡ መኪና ለመገፋት አልተሰራም፡፡ መኪና የሚነዳውም ሰው ይሁን የሚገፋውም ሰው ሁለቱም መኪናውን አንድ ቦታ ቢያደርሱትም መኪና መንዳትና መግፋት ግን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ስልጣን በተረዳን ቁጥር ክርስትና እንደ መኪና መንዳት እንጂ እንደ መኪና መግፋት አይሆንብንም፡፡

እግዚአብሄር በክርስቶስ ባዘጋጀው ጥቅምና መብት ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን እግዚአብሄርን በማወቅ ማደግ አለብን፡፡ እግዚአብሄር በልቡ እንዳለው ለመመላለስ በቃሉ አማካኝነት ክርስቶስን ማጥናትና መማር አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሙላት ሊኖርብንና በክርስቶስ እውቀት ማደግ ይገባናል፡፡

በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡3

እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን እንዴት ከእግዚአብሄር ጋር በሰላም እንደምንኖር እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰላማችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄርን በተረዳነው መጠን የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን በሙላት መፍሰስ ይጀምራል፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰውን እንዴት እንደምንይዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ነገሮችን እንዴት እንደምንዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ የሰጠንን ቦታ ስንረዳ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በሙላት ፈፅመን እናልፋለን፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ከመመላለስ በፊት ማረፍ ይቀድማል

Photo to convey idea of restingለሰው የሚያስፈልገውን ማንኛውም ነገር ሁሉ በአምስት ቀን ውስጥ ከሰራ በኋላ ሰውን እግዚአብሔር የፈጠረው በስድስተኛ ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን ከሰው ጋር አረፈ፡፡ ሰው በስድስተኛ ቀን የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር በሰባተኛው ቀን እንዲያርፍ ነው፡፡

ሰው የተሰራው ለእረፍት ነው፡፡ ሰው ምንም ነገር ቢሰራ እንኳን የተሰራው በእረፍት እንዲሰራ ነው፡፡ እረፍት ማለት አለመስራት ማለት አይደለም፡፡ እረፍት ማለት አለመባዘን ፣ አለመባከን ፣ አለመጨነቅ ፣ አለመታሰር ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ነው እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ ከከፈልልን በኋላ እረፉ የሚለን፡፡

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ማቴዎስ 11፡28-29

ከመስራት በፊት ማረፍ ይቀድማል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው አርፈን በራሱ ምሪትና ሃይል ብቻ እንድንሰራ  ነው፡፡ በራሳችን ሃይልና ጉልበትን እንድንፍጨረጨር አይፈልግም፡፡

ስለዚህ ነው በመንፈሴ እንጂ በሃይልና በብርታት አይደለም የሚለው፡፡

መልሶም፦ ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ዘካርያስ 4፡6

ሰው የሚያርፈው ተጨማሪ ገንዘብ ሲኖረው አይደለም፡፡ ሰው የሚያርፈው ሰው የሚያርፈው እግዚአብሄርን ሲያውቅ ነው፡፡ ሰው የሚርፈው እግዚአብሄርን ሲያይ ነው፡፡ ሰው የሚያርፈው በእግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። መዝሙር 46፡10

ሰው የሚያርፈው በራሱ ከመሮጥ ሲመለስ ነው፡፡ ሰው የማያርፈው በራሱ ከመፍጨር ሲያርፍ ነው፡፡ ሰው የሚያርፈው በፀጥታ እግዚአብሄርን ሲመለከት ነው፡፡ ሰው ሃያል የሚሆነው በእግዚአብሄር ሲያርፍ ነው፡፡ ሰው የሚበረታው በእግዚአብሄር ሲታመን ነው፡፡

የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፣ በፀጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፡፡ ኢሳያስ 30፡15

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: