Category Archives: giving

ግብዣ ባደረግህ ጊዜ

Buffet_Setup_1.jpgየጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው፦ ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና። ሉቃስ 14፡12-14

የእግዚአብሔር መንግስት አሰራርና የአለም አሰራር እጅግ ይለያያሉ፡፡ የእግዚአብሔር መንግስትና የአለም አሰራር እጅግ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡

በአለም ያለው ግብዣ ወይም በአጠቃላይ ስጦታ አሰጣጥ መልካም ላደረገልህ ሰው ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡

በአለም ግብዣ የምትጋብዘው ሰው ወደፊት ይጠቅመኛል የምትለውን ነው፡፡ እንዲያውም እጅግ ይጠቅመኛል የምትለውንም ሰው ነው መርጠህ የምትጋብዘው፡፡ በአለም ያለው ግብዣ አላማው መጠቀም ነው፡፡

በአለም ያለው ግብዣ አላማው መጠቀም በመሆኑ ምንም ሰማያዊ ሽልማትን አያስገኝም፡፡ ሰው በምድር ለመጠቀም ብሎ ያደረገው ነገር ሁሉ በምድር ይጠቀምበታል እንጂ በሰማይ አይጠቀምበትም፡፡ ሰው በምድር ለመቀበል የሚያደርገው ማንኛውም መስጠት በሰው ልጆች ተመልሶ ይሰጠዋል እንጂ ከእግዚአብሔር የሚሰጠው ምንም ነገር የለም፡፡

ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። ማቴዎስ 6፡1-2

ሰው ከሰው ለመጠቀም ብሎ የሚያደርገው መጥቀም ምድራዊ ሂሳቡን ይሞላል እንጂ ሰማያዊ ሂሳቡን አይሞላም፡፡

በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ፊልጵስዩስ 4፡17

በክርስትና ከእግዚአብሔር ከፍ ያለ ዋጋ የሚያሰጥህ መስጠት ተመልሶ ሊሰጥህ ለማይችል ሰው መስጠት ነው፡፡ የመስጠት ክብሩ እና ብፅእናው መልሰው ሊሰጡህ ለማይችሉ ሰዎች መስጠት ነው፡፡

የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ማድረግ #መስጠት #ምጽዋት #መባረክ #ማካፈል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ሳምራዊ #ሌዋዊ #ካህን #ባልጀራህን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #ወንጌል

ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበብ

giving 7.jpg

ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሄር እንዴት እንደሚሰጡ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደሚቀበሉ አያውቁም፡፡ የእግዚአብሄርን የመስጠት መንገድ ስለማይረዱ ከእግዚአብሄር ጋር ይተላለፋሉ፡፡ ወይም ከእግዚአብሄር የመቀበለን መንገድ ስለማይረዱ የእግዚአብሄርን መስጠት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለሚጠብቁ እግዚአብሄር ቢሰጣቸው እንኳን ከእግዚአብሄር ስለተቀበሉት እውቅናንና ምስጋናን ለእግዚአብሄር አይሰጡም፡፡ ከእግዚአብሄር የመቀበል ጥበቡ ስለሌላቸው ለእግዚአብሄር አብዝቶ ለመስጠት የሚገባቸውን ያህል አይነሳሱም፡፡

ለእግዚአብሄር ገንዘብን ስንሰጠው ገንዘብን ጨምሮ ብዙ የሚሰጠን ነገሮች አሉ፡፡ ለእግዚአብሄር አብልጥን ለመስጠት ከእግዚአብሄር የመቀበልን ጥበብ መማር ያስፈልጋል፡፡ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን ፣ እውቀታችንን ፣ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ስንሰጠው ዘርፈ ብዙ በሆነ መንገድ እግዚአብሄር ይከፍለናል፡፡

ከእግዚአብሄር የማንፈልገው ነገር ስለሌለና እግዚአብሄር በሁሉም የህይወታችን እቅጣጫና በሁሉም ነገራችን ስለሚያፈልገን ከእግዚአብሄር እንዴት እንደምንቀበል ማወቅ አለብን፡፡

ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6

የእግዚአብሄር የአከፋፈል መንገዶች

  1. እግዚአብሄር በሃሳብ ይባርከናል

አንድ ስራ ከሃሳብ ይጀምራል፡፡ አንድ ነገር መስራት እንድንችል እግዚአብሄር ሃሳብን ይሰጠናል፡፡ አንድን ነገር ወደፍፃሜ እንድናመጣ እግዚአብሄር በማስፈፀሚያው ሃሳብ ይባርከናል፡፡ እግዚአብሄር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር በራእይ ይባርከናል፡፡ ገንዘብ ኖሮን ነገሮችን መረዳትና መፈፀም ካልቻልን ምን ይጠቅመናል?

በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ምሳሌ 17፡16

ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡5

  1. እግዚአብሄር በመነሳሳት ይባርከናል

እግዚአብሄር በመፈለግ ይባርካል፡፡ እግዚአብሄር ልባችንን ያነሳሳል፡፡ ምንም ሃሳቡ በሌለን ጊዜ ከመቀፅበት ልባችን አንድን ነገር ለማድረግ ይነሳሳል፡፡ አንድ ነገር ጊዜው ሲሆን እግዚአብሄር ከመቀፅበት ልባችንን ያቀጣጥለዋል፡፡ ይህንን የትኛውም ገንዘብ ሊገዛው የማይችል የእግዚአብሄር የመስጫና የመባረኪያ መንገድ ነው፡፡

ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ፊልጵስዩስ 2፡13

  1. እግዚአብሄር በድፍረት ይባርከናል

ሌላው ለእግዚአብሔር ሰጥተን እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበት መንገድ ድፍረት ነው፡፡ ከእኛ የተሻለ የሚታይ ነገር ኖሯቸው ያልደፈሩትን ነገር ለመፈፀም እንድንደፍር ድፍረትን በመስጠት ጌታ ይባረከናል፡፡ እኛም እንኳን አስኪገርመን ድረስ እንድንደፍር እምነትን ይሰጠናል፡፡ ምንም ያህል ገንዘብ ሊገዛው የማይችል እግዚአብሄር ለእኛ የሚሰጥበትና የሚባርክበት መንገድ ነው፡፡

እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ገላትያ 3፡25

ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

  1. የልቦናችንን አይኖች በማብራት ይከፍለናል

ለእግዚአብሄር ስንሰጥ ከእግዚአብሄር የምንቀበልበት ሌላው መንገድ የአይን መከፈት ነው፡፡ እግዚአብሄር አይናችንን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር እይታን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄርን የልቦናችንን አይኖች ያጠራል፡፡ እግዚአብሄር ዋጋ መስጠት ላለብን ነገር ብቻ ዋጋ እንድንሰጥ ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄር አጥርተን በማየት ይባርከናል፡፡

የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ኤፌሶን 1፡17

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #መቀበል #ጥበብ #ማስተዋል #እይታ #ሃሳብ #መነሳሳት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የመስጠት አለምአቀፋዊ ጥያቄና መልሱ

giving 111.jpgስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38

ሰው መስጠት ማካፈል ይፈልጋል፡፡ ማንም ሰው መስጠትና ማካፈል ትክክል አንደሆነ ያውቃል፡፡ መስጠትና ማካለፈል መልካም ነገር እንደሆነ የማይረዳ ሰው የለም፡፡ ሁሉም ሰው ስለመስጠት አስፈለካጊነት ያውቃል፡፡

ሰው ግን እንዳይሰጥ የሚያደርገው ምንድነው? ሰው ታዲያ እንዳይሰጥ የሚያስፈራራው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ ይህን የሰውን ሁሉ አለም አቀፋዊ ጥያቄ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ይህ ሰው እንዳይሰጥ የሚያደርገው ጥያቄ የሰው ሁሉ ሃቀኛ ጥያቄ ነው፡፡ ሰው ለመስጠትና ለማካፈል ይህ እውነተኛ ጥያቄ በትክክል ሊመለስለት ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ጥያቄ ለሰው በሚገባ ሳይመለስለት ሰውን ስጥ ማለት አግባብ አይደለም፡፡

ግን ሰው እንዳይሰጥ የሚያግደው ይህ ጥያቄ ምንድነው፡፡ ሰው ሊሰጥ ካለ በኋላ እንኳን እጁን እንዲመልሰው የሚያደርገው ጥያቄ ምን አይነት ጥያቄ ነው?

ይህን ጥያቄ ማንም ቢጠይቀው ማንም ሊኮንነው የማይገባው ሃቀኛ ጥያቄ ነው፡፡ ሰጥቼ እኔስ ባጣ የሚለው ጥያቄ በትክክል ሊመለስለት የሚገባው እውነተኛ ጥያቄ ነው፡፡ ከሰጠሁ በኋላ እኔስ ቢጎድልብኝ የሚለው ጥያቄ አለም አቀፋዊ መለስ የሚገባው አለምአቀፋዊ ጥያቄ ነው፡፡

ስለዚህ ነው ኢየሱስ ስጡ ብሎ ከተናገረ በኋላ ሰጥቼ ቢጎድልብኝስ የሚለውን የሰውን ጥያቄ መልሰ ሲሰጥ ይሰጣችሁማል ያለው፡፡

ስትሰጡ ይሰጣችኋል፡፡ እንዲያውም አለ መስጠት ማቀበል ብቻ አይደለም፡፡ መስጠት ማስተላለፍ ብቻ አይደለም፡፡ መስጠት መዝራት ነው መስጠት ማበርከት ነው፡፡ ስትሰጡ የሰጣችሁት ብቻ ሳይሆን በመልካም መስፈሪያ ተባዝቶ ይሰጣችኋል፡፡

እንዲያውም መስጠት የሰጣችኋት ብቻ ተልክቶ ተመልሶ የምትሰጣችሁ አይደለም፡፡ ተመልሶ የሚሰጣችሁ የሰጣችሁት ብቻ ሳይሆን የተነቀነቀ የተጨቆነ መስፈሪያ ይሰጣችኋል፡፡

ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ገንዘብን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ይበልጥ የተባረከበት ዋና ዋና ምክኒያቶች

o-GIVING-MONEY-facebook.jpgገንዘብን መስጠት ጥልቅ የሆነ መነሻ ሃሳብ አለው፡፡ ገንዘብን መስጠት ምክኒያት አለው፡፡ ገንዘቡን የሚሰጥ ሰው ገንዘቡን ለመስጠት በቂ ምክኒያት አለው፡፡ ገንዘብን መስጠት ከጀርባው ጥልቅ ምክኒያቶች አሉት፡፡

መስጠት ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ሰው ገንዘቡን ሲሰጥ በተዘዋዋሪ የሚናገረው ነገር አለው፡፡ ገንዘብን የመስጠት ትርጉምን እንመልከት፡፡

ገንዘብን መስጠት አምልኮ ነው፡፡

ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄርን ማምለክ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያመልከ ሰው ገንዘብን አያመልክም፡፡ እግዚአብሄርን የሚወድ ሰው ገንዘብን ይጠላል እግዚአብሄርን የሚጠጋ ሰው ገንዘብን ይንቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር መልካም ግንኙነት ያለው ሰው ከገንዘብ ጋር መጥፎ ግንኙነት አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሄር የሚገዛ ሰው ለገንዘብ እንደማይገዛ በድርጊቱ እያወጀ ነው፡፡

ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24

ገንዘብን መስጠት ምስጋና ነው፡፡

ገንዘብን ስንሰጥ እግዚአብሄር ነው የሰጠኝ እያልን ነው፡፡ ገንዘብን ስንሰጥ ለእግዚአብሄር አቅርቦት እውቅና እየሰጠን ነው፡፡ ገንዘብን ስንሰጥ አመሰግናለሁ እያልን ነው፡፡

እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7

ገንዘብን መስጠት እምነት ነው፡፡

ገንዘብ መተማመኛ ነው፡፡ ከገንዘብ በላይ መተማመኛ የሌለው ሰው ገንዘብን መስጠት አይችልም፡፡ ከገንዘብ በላይ የሚተማመንበት ያለው ሰው ግን ገንዘብን ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ስጋትን ይቀንሳል፡፡ ከገንዘብ በላይ ስጋቱን የሚቀንስለትን አምላኩን የሚያውቅ ብቻ ነው ገንዘብን የሚለቀው፡፡ ገንዘብን መስጠት የማይታየውን ማየት ይጠይቃል፡፡

ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20

ገንዘብን መስጠት ፍቅር ነው፡፡

ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ሌላው ከእኔ ይሻላል ብሎ የሚያስብ ሰው ነው፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ሌላውን የሚያከብርና ለሌላው ዋጋ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ ገንዘብን የሚሰጥ ሰው ለሌላው መልካም የሚያስብ ሰው ነው፡፡

ገንዘብን መስጠት ርህራሄ ነው፡፡

ገንዘብን መስጠት ለሌላው እንደምናስብ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት ለሌላው ርህራሄ እንዳለን ያሳያል፡፡ ገንዘብን መስጠት ለራሳችን ብቻ እንዳማናስብ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት በምድር ላይ ያለነው ሌላውን ለማገልገን እንደሆነ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄር የሰጠን የምንበላውን ብቻ እንዳልሆነና የምንዘራውንም እንደሰጠን እውቅና የምንሰጥበት መንገድ ነው፡፡

የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ሮሜ 12፡8

ገንዘብን መስጠት በእግዚአብሄር መደገፍ ነው፡፡

በገንዘብ የሚደገፍ ሰው ገንዘብን አይሰጥም፡፡ ገንዘብ የህይወት ጥያቄውን ሁሉ የሚፈታለት የሚመስለው ሰው ገንዘብን አይሰጥም፡፡ ገንዘብ ግን ውስን እንደሆነ ገንዘብ ሊገዛ የማይችላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉና እግዚአብሄርን ከገንዘብ ውጭ ስለብዙ ነገሮች እንደምንፈልገው የተረዳ ሰው ገንዘቡን ለመስጠት አይቸግረውም፡፡ የሰው ልጅ ቁልፍ በገንዘብ ውስጥ ሳይሆን በጌታ እጅ እንዳለ ያወቀ በጌታ በመመካት ገንዘበኑን ይሰጣል፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24

ገንዘብን መስጠት መኖሪያዬ ገንዘብ አይደለም ማለት ነው፡፡

ገንዘብን መስጠት መኖሪያዬ ገንዘብ አይይደለም የሚል መልክት አለው፡፡ ገንዘብን መኖሪያቸው የሆነ ሰዎችና ከገንዘብ ኑሮ ያለፈ ነገር የማይታያቸው ሰዎች ገንዘብን አይሰጡም፡፡ ገንዘብ እንደማያኖረውና የእርሱ መኖሪያ እግዚአብሄር እንደሆነ የሚያውቀ ሰው ገንዘቡን ይሰጣል፡፡

መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ዘዳግም 33፡27

ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። ዘዳግም 8፡3

ገንዘብን መስጠት ፀሎት ነው፡፡

ገንዘብን መስጠት እግዚአብሄርን በገንዘብ የምገዛቸውን ነገሮች አንተ አሟላ ማለት ነው፡፡ ገንዘብን መስጠት ስጡ ይሰጣችሁዋል የሚለውን እግዚአብሄርን መለመኛው መንገድ ነው፡፡ መስጠት እግዚአብሄርን ለተጨማሪ ገንዘብ መለመኛው መንገድ ነው፡፡ ገንዘቡን ሰጥቶ የሚጎድልበት ሰው ስለሌለ መስጠት በተዘዋዋሪ አይጉደልብኝ የሚል ልመና ነው፡፡

ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ማካፈል #መባረክ #ስጡ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #መዝራት #ከልቡ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ድሃ #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

አስተማሪ መሳጭ ታሪክ

starfish-in-hand-1024x683.jpgአንድ አረጋዊ በባሕር ዳርቻ መንገድ ላይ እየሄደ እያለ አንድ ወጣት አጎንብሶ የሆነ ነገር በማንሳት ወደ ውቆያኖስ ውስጥ ሲጥል ከሩቅ ያየዋል፡፡

እየተጠጋ ሲሄድ እያነሳ ወደውሃ ውስጥ የሚመልሰው ኮከበ ባህር /ስታር ፊሽ/ መሆኑን ተገነዘበ፡፡

ይበልጥ ተጠግቶት ደህና አደርክ ብሎ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “ምን እያደረግክ ነው?” ሲል ጠየቀው፡፡

ወጣቱ አዛውንቱን ለአፍታ ተመልክቶ “ኮከበ ባሕር ወደውቅያኖስ እየወረወርኩ ነው ይለዋል”፡፡

አዛውንቱ ፈገግ ብሎ ወጣቱን እንዲህ ሲል ጠየቀው “ለምንድነው ኮከበ ባሕሩን ወደውቅያኖስ ውስጥ የምትመልሰው ?”

ወጣቱም “ፀሐይ እየወጣ ነው ማእበሉ እየሰከነ ነውና መልሼ ውሃው ውስጥ ካልከተትኳቸው ይሞታሉ” አለው፡፡

አረጋዊውም ወጣቱን “በባሕሩ ዳርቻ ብዙ ምእራፍ ርቀት ላይ ብዙ ኮከበ ባህሮች አሉ፡፡ ያንተ እነዚህን ጥቂት ኮከበ ባህሮች ወደ ውሃው ውስጥ መመለስ ምን ልዩነት ሊያመጣ ይችላል?” ሲል ጠየቀው

ወጣቱ ጎንበስ ብሎ አንዱን ኮከበ ባህር ወደውቂያኖሱ እየወረወረ “ለዚህ ለአንዱ ኮከበ ባሕር ልዩነት አመጣለሁ” አለው፡፡

አሁንም በምድራችን ያለውን የድህነት ችግር ለመፍታት ከሞከርን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ በሁሉ ሰው ህይወት ልዩነት ማምጣት ላንችንል እንችላለን፡፡ መርዳት ለምንችለው ለአንዱ ግን ልዩነት እናመጣለን፡፡ የአንዱን ኑሮ ግን መለወጥ እንችላለን፡፡

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ድሃ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የባለጠጋው ችግሩ

poor vs rich 622.jpg

ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። ሉቃስ 16፡19-23

ይህንን ፅሁፍ ስናነብ የባለጠግነች ችግሩ ምንድነው ልንል እንችላለን፡፡ ባለጠግነቱ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ይህም ሰው ምንም የተገለፀ ችግር አናይበትም፡፡ የደሃውን ገንዘብ አልቀማም፡፡ ታክስ አላጭበረበረም፡፡ ጉቦ ተቀብሎ ማግኘት ያለበትን አልከለከለም ፣ አለማግኘት ያለበትን አልሰጠም፡፡ ባለጠጋው ሰው ድርጊቱ ያደረገው ስህተት የለም፡፡

ባለጠግነት ተሰርቶ ተጠራቅሞ በትክክለኛው መንገድ ይምጣ እንጂ ምንም ችግር የለበትም፡፡ እውነተኛ ባለጠግነት የእግዚአብሄር ስጦታ ስለሆነ ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ አሁንም ታዲያ የባለጠጋው ሰው ችግሩ ምንድነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡

ሰው ለድሃ ምፅዋት በመስጠቱ ወደመንግስተ ሰማያት ይገባል ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ አያስተምርም፡፡ ምክኒያቱም የሃጢያተኛ ሰው ምንም አይነት መልካም ምግባር እግዚአብሄርን ሊያስደስተው አይችልም፡፡ ሃጢያተኛ የሚያደርገው የተሻለው መልካም ነገር በእግዚአብሄር ፊት እንደመርገም ጨርቅ ነው፡፡

ሰው ወደ መንግስተማያት የሚገባው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሃጢያ ዋጋ እንደተከፈለለት በእምነት ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው የሚድነው በኢየሱስ ስራ ላይ ሲደገፍ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ያረካው ስራ የኢየሱስ የመስቀል ስራ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታ የሚቀበለውን ሰው እግዚአብሄር ይቀበለዋል፡፡

ስለዚህ ሃብታሙ ወደ መንግስተ ሰማይ ያልገባው መልካም ስራ ስላልሰራ አይደለም፡፡ ሰው በኢየሱስ የመስቀል ስራ በማመን እንጂ በመልካም ምግባር ወደ መንግስት ሰማያት አይገባምና፡፡ ሰው ንስሃ ገብቶእግዚአብሄር ለመዳኛ ያዘጋጀውንም ልጁን ኢየሱስን መቀበል አለበት፡፡

የሃብታሙ ሰው ችግር ምን እንደነበር ማወቅ በእኛም ህይወት ከስህተቱ እንድንማር ይረዳናል፡፡

የሃብታሙ ሰው ችግር የሰብአዊነት ስሜት ማጣት ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር የፍትህ ችግር ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር ሰውን እንደሰውነቱ ያለማክበር ችግር ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር ሌላውን ሰው እንደሰው አለመቁጠር ችግር ነው፡፡

እርሱ ሃብታም ነው ሁሉ ሞልቶለታል፡፡ ይህ ደሃ ደግሞ ተቸግሮዋል፡፡ ተጨንቋል ታሟል፡፡ በሃገራችን ኢትዮጲያ ሰሞኑን የደረሰው አደጋ ይህንን የድህነት ጩኸት ያስታውሰናል፡፡ ልባችን አዝኖዋል፡፡ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን የድህነትን ችግሮች ስንመለከት ከእኔ ምን ይጠበቃል ማለት ብልህነት ነው፡፡ ለዚህ የድህነት ችግር መፈታት የምናደርገውን አስተዋፅኦን ማሰብ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው፡፡ እኔስ በልቼ ተርፎኝ እየኖርኩ ለድሃው መነሳት የማደረግው ምን ነገር አለ ብሎ መጠየቅ ሰባዊነት ነው፡፡ ከልጆቼ ጎን ለጎን አንድ አሳዳጊ ያጣ ህፃንን መርዳትና ማሳደግ እችላሁ ማለት ይገባናል፡፡ አቅማቸው ለማይፈቅድ ልጆች የትምህርት ቤት ዩኒፎርምና የትምርት መርጃ መግዛት እችላለሁ ማለት ይገባናል፡፡

ይህ ባለጠጋ ሰው ድሃውን ተቸግሮ ያየዋል፡፡ ቢያየውም አልደነገጠም ምንም ሊያደርግለት አልፈለገም፡፡ እንደሰው አልተመለከተውም፡፡ እንደሌላው የእግዚአብሄር ፍጥረት አላየውም፡፡ እርሱም ምግብ እንደሚገባው አላሰበም፡፡ ራሱን ብቻ የተመረቀ ኮከብ እድርጎ ነበር የሚያየው፡፡ ደሃው ደግሞ እንደረተረገመ የተሻለ ኑሮ እንደማይገባው ነገር የሚያየው፡፡ ሃብታሙ ሰው ትሁት አልነበረም፡፡ ሃብታሙ ሰው ለሌላው ግድ የሚለው አልነበረም፡፡ ሃብታሙ ሰው ለሌላው የሚያዝንን የሚራራ ልብ አልነበረውም፡፡ ይህ ባለጠጋ ከዚህ ደሃ ጋር ራሱን አላስተባበረም፡፡ ይህ ባለጠጋ ከዚህ ደሃ ጋር ሊሆን አልፈለገም፡፡

የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ 12፡16

ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። (መደበኛው ትርጉም)

ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው። ያዕቆብ 1፡27

ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤ መዝሙር 82፡3

እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? ኢሳያስ 58፡7

ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤ እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤ ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥ ኢዮብ 31፡16-19

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #ድሃ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: