Category Archives: Fellowship

ቢስማሙ + በስሜ በሚሰበሰቡበት = በመካከላቸው እሆናለሁ

IMG_3804 1.jpgደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19-20

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው መጮኻችን አይደለም፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው መለመናችንና ማልቀሳችን አይደለም፡፡

ኢየሱስ በህዝቡ መካከልና መገኘት አብሮ መስራት ይፈልጋል፡፡ እኛ በመካላችን እንዲገኝና እንዲሰራ ከምንፈልገው በላይ ኢየሱስ በመካካላችን ተገኝቶ አብሮ በሃይል መስራት ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን የሚገኘው እርሱ እንዲገኝ የሚያደርገውን ነገሮችን ስናደርግ ነው፡፡

ኢየሱስ በመካላችን እንዲገኝ የሚያድርገውን ሁለት ነገሮች እንመልካት፡፡

 1. በአንድ ልብ መሆን

 

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19

በአንድ ሃሳብ መሆን ኢየሱስ በማካከላችን እንዲገኝ ያደርገዋል፡፡ አንዱ አንድ ሌላው ሌላ አላማ ካለው ኢየሱስ የተደበላለቀን ነገር ሊሰራ አይገኝም፡፡

በሃዋሪያት ላይ የእግዚአብሄር መንፈስ ከመውረዱ በፊት በአንድ ሃሳብ ይፀልዩ ነበር፡፡

በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። የሐዋርያት ሥራ 2፡1-2

ሃዋሪያው ስለዚህ ነው ደስታዬን ፈፅሙልኝ በአንድ ሃሳብ ተስማሙ እያለ የሚናገረው፡፡

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡1-2

 1. የመሰብሰብ አላማ

 

ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡20

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ መሰብሰባችን አላማ ያስፈልገዋል፡፡ እንደው ለመሰብሰብ የሆነ መሰብሰብ ኢየሱስ እንዲገኝ አያደርገውም፡፡ ኢየሱስ እንዲገኝ የሚያደርገው መሰብሰብ በስሙ የሚደረግ መሰብሰብ ብቻ ነው፡፡

በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ደግሞ ስብሰባው ሲጀመር በኢየሱስ ስም ፕሮግራማንን እንጀምራለን ማለት አይደለም፡፡ በስሙ መሰብሰብ በኢየሱስ ስም ብሎ ከመናገር ያልፋል፡፡

በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ኢየሱስን ወክሎ መሰብሰብ ማለት ነው፡፡ የኢየሱስ አላማ የእግዚአብሄርንም መንግስት ማስፋፋት እንደሆነ ሁሉ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅምና መስፋት እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ቤተክርስትያን በምድር ላይ ያለችበትን አላማ ለማስፈፀም እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት እኛ የኢየሱስ ተከታዮች ደቀመዛሙርት በምድር ላይ ያለንን የእግዚአብሄርን መንግስት እና ፅድቁን የመፈለግ አላማ ለማስፈፀም እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ በመካከል እንዲገኝ የሚያደርገውን የልብ አንድነትና የእግዚአብሄር መንግስት አላማ ከተሟላ ኢየሱስ እራሱ ይገኛል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #መገኘት #ህልውና #ቃል #ህልዎት #አንድነት #በስሜ #በኢየሱስስም #ፅድቅ #የጌታመንፈስ #አብሮነት #ክብር #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ምስክርነት #አማርኛ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነፃነት #ሞገስ #እርፍት #እርካታ #አርነት #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #ፌስቡክ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው

Publication15.jpg

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። ማቴዎስ 16፡18-20

የእግዚአብሄርን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን የተቀበሉ ሁሉ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ተወካዮች ናቸው፡፡ ኢየሱስን የተቀበሉ ሁሉ ኢየሱስ በምድር ላይ መስራት የጀመረውን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ሊፈፅሙ በምድር ላይ የተሾሙ የእግዚአብሄር ተወካዮች ናቸው፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

እግዚአብሄር በሰማይ እንዳለ ሁሉ ቅዱሳን በምድር ላይ ላይ ናቸው፡፡ በክርስቶስ ያመኑ የእግዚአብሄር ልጆች በሰማይ ያለው የእግዚአብሄር አምባሳደሮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር የሚያስፈፅሙ የኢየሱስ ተወካዮች ናቸው፡፡

አማኞች ሲሰበሰቡ ለአንድ አላማ መስበሰብ አለባቸው፡፡ አላማ የሌለው መሰባሰብ ከግብ አያደርስም፡፡ ለመሰብሰብ ብቻ የሆነ መሰብሰብ ውጤት አያመጣም፡፡ መሰብሰባችን አንድ የጋራ አላማን ይጠይቃል፡፡

እያንዳንዳችን በየራሳችን የግል አላማ ሳይሆን በአንድ አላማ መሰብሰብ ይኖርብናል፡፡ የመሰብሰባችን አላማ የኢየሱስ ስም መሆን አለበት፡፡ ስንሰበሰብ በኢየሱስ ስም ልንሰበሰብ ይገባል፡፡ የሚያሰባስበን የኢየሱስ ስራ ፣ የኢየሱስ ተልእኮና የኢየሱስ ስም መሆን አለበት፡፡ የምንስበሰበው ኢየሱስ በምድር ላይ መስራት የጀመረውን ለመጨረስ ኢየሱስን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ለመፈፀም ሊሆን ይገባዋል፡፡

ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤ ሐዋርያት 1፡1-2

የምንሰበሰበው ኢየሱስ በምድር ላይ ሰርተን እንድፈፅመው የላከንን ስራ ለመስራት መሆን አለበት፡፡ የምንሰበሰበው ኢየሱስን ወክለን መሆን አለበት፡፡ የምንሰበሰበው አብ ኢየሱስ እንደላከው ኢየሱስ የላከንን ተልእኮ ለመፈፀም መሆን አለበት፡፡

ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

ኢየሱስን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ለመስራት ባለ አንድ አላማ ከተሰበሰበን ኢየሱስ በመካከላችን ይገኛል፡፡ ለእግዚአብሄር መንግስት አላማና ኢየሱስን ወክለን ስንሰበሰብ ኢየሱስ በመካከላችን አንዲገኝ መለመንና መጨቅጨቅም እሰከማያስፈልገን ድረስ እንደቃሉ በቃሉ በመካከላችን ይገኛል፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን የሚገኘው በእርሱ ቦታ ሆነንና እርሱን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ለማስከበርና መንግስቱን ለማስፋት የምንለምነውን ሁሉ አብ እንዲያደርገው ነው፡፡ በኢየሱስ ስም ስንሰበሰብ በመካከላችን የሚገኘው ስለ እያንዳንዳችን የግል ጥቅም ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ እግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ነው፡፡

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። ማቴዎስ 16፡18-20

በኢየሱስ ስም ከተሰበሰብን መገኘቱ ይሰማንም አይሰማንም ኢየሱስ በመካከላችን የምንለምነው ይደርግልናል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መሰብሰብ #ጉባኤ #በኢየሱስስም #ተልእኮ #አላማ #የእግዚአብሄርመንግስት ##መንፈስ #መካከል  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ውክልና #እንደራሴ #አምባሳደር #ፀሎት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው

heart777.jpgነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22-27

የሰው አዋቂነት የሚለካው ጠንካራውን በመያዝ ደካማውን በመጣል አይደለም፡፡ ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን እንደሚያስፈልጉ ተፈጥሮ እንኳን ያስተምረናል፡፡

ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፡፡

በሰውነታችን የማያስፈልግ የሚመስለን ብልት ካለ ስለጥቅሙ እውቀት ይጎድላል ማለት እንጂ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ በሰውነት ክፍላችን እንኳን ስንመለከት እጅግ በጣም አስፈላጊ የአካል ብልቶች ደካማ ብልቶች ናቸው፡፡

ደካማ የሚመስሉ ብልቶች ይበልጥ እንደሚያስፈልጉ መረዳት አዋቂነት ነው፡፡ ደካማን ከላይ ከላይ የየቶ መናቅና መጣል ሞኝነት ነው፡፡ ሰው በአንድ ነገር ደካማ ነው ማለት ብርታቱ በሌላ ነው ማለት ብቻ እንጂ በአጠቃላይ ደካማ ነው ማለት በፍፁም አይደለም፡፡ የአንድ ሰው በአንድ የህይወት ክፍል ደካማነት የሚያመለክተን ያላየነው ጠንካራ የህይወት ክፍል እንዳለ ነው፡፡ በዚህ ጠንካራ አይደለም ማለት በዚያ ጠንካራ ነው ማለት ነው፡፡ በሁሉም ጠንካራ ሰው እንደሌለ ሁሉ በሁሉም ደካማ ሰው ደግሞ የለም፡፡ ከሰው ድካም ባሻገር ጥንካሬውን ማየት ጥበብ ነው፡፡ የሰውን ድካም ታግሶና ሸፍኖ በጥንካሬው መጠቀም ፍሬያማ ያደርጋል፡፡ ድካምን ብቻ የሚያይ ሰው ማንም ሳይቀረው ሁሉንም አውጥቶ ይጥላል፡፡ ከድካም ባሻገር ጥንካሬን ማየት የሚችል ሰው ደግሞ ድካምን ታግሶ በእያንዳንዱ ጥንካሬ ይጠቀማል፡፡

ለራሱ ጥቅም ለመጨመር ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለባለጠጋም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። ምሳሌ 22፡16

ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፡፡

ያልከበሩ የሚመስሉን የአካል ብልቶች ላይ ሰፊ ጊዜና ጉልበት እናፈስባቸዋለን፡፡ ያልከበሩ የሚመስሉን ብልቶችን በከበረ ነገር እንሸፍናቸዋለን፡፡ የሰው ጥበብ የሚለካው የከበረውን በማሳየት ብቻ ሳይሆን ያልከበረውን በመሸፈንም ነው፡፡ ያልከበረውን የማይሸፍን ሰው የከበረውን እንደሚደብቅ ሰው መረዳቱ ሙሉ አይደለም፡፡ ያልከበሩት ደካማ ብልቶች ይበልጥ ክብር ይለብሳሉ፡፡ ያልከበሩ ብልቶች ይበልጥ ትጋትን እናሳይባቸዋለን፡፡ ፀጋ እንኳን እጅግ የሚበዛው ይበልጥ በሃጢያት ለሚፈተን ለደካማው ሰው መሆኑን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ በቀላሉ በሃጢያት ለሚወድቅ ለደካማው ሰው እንጂ ለጠንካራው ሰው ፀጋ ወይም የሚያስችል ሃይል አይበዛም፡፡

ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ። ሮሜ 5፡15፣20-21

በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፡፡

ጠንካራን እንደሰትበታለን እንጂ እንደ ደካማው ያን ያህል ስራ አይጠይቅም፡፡ የእኛ ታላቅ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ የሚሆኑት ደካሞች ናቸው፡፡ በእኛ ውስጥ ያለው ጥንካሬ ለደካሞች ድካም መሸፈኛነት የታቀደ ነው፡፡ በእኛ ውስጥ ያለው ጥንካሬ የደካሞችን ድካም የመሸፈን ታላቅ አላማ አለው፡፡ በእኛ ውስጥ ትርፍ የሆነና ለምንም የማይጠቅም ስጦታ አልተቀመጠም፡፡ በእኛ ውስጥ ብርታት ካለ በሌላው ውስጥ የምንሸፍነው ድካም አለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ወር ትርፍ ገንዘብ ከመጣ በሌላው ወር በትርፉ የሚሞላ ጉድለት አለ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ተረፍ ብሎ ከመጣ በሌላ ጎን ፍላጎት አለ ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ደግሞ ተረፍ አድርጎ ካልመጣ እግዚአብሄር ይመስገን ፍላጎት የለም ማለት ነው፡፡

የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡14-15

ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም፡፡

ደካሞችን የሚንቅ ጠንካሮችን የሚያከብር ሰው መረዳት የጎደለው ሰው ነው፡፡ ደካሞች የሚበልጥ ክብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሰው ክብሩ ደካሞችን በማክበር ነው፡፡ ሰውን በእውነት እንደወደድነው የሚታየው ሲደክም በምናደርገው እንክብካቤ ነው፡፡ ሰውን ማክበራችን የሚፈተነው ሲዋረድ በማክበራችን ነው፡፡ ሰውን በእውነት መውደዳችን የሚፈተነው እንዳንወደው የሚፈትን ነገር ሲገጥመን ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር የሚፈተነው ሰውን ለመውደድ ምክኒያት ስናጣ ነው፡፡ ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው ሲደክም ነው፡፡ ወዳጅ የሚወለደው ለመከራ ቀን ነው፡፡ ወዳጅ በእጅጉ የሚያስፈልገው በመከራ ቀን ነው እንጂ ማንም ሰው አብሮ ሊደሰት ፈቃደኛ በሚሆንበርት በሰላም ቀን አይደለም፡፡

ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። ምሳሌ 17፡17

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልዩነት #አካል #ብልት #ህብረት #አንድነት #ክብር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #አንድነት #ፀጋ #ብልት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የአጋርነት ፈተና

GettyImages-468837861-56c5c0c93df78c763fa5d925.jpgአጋርነት እጅግ ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ በአጋርነት ውስጥ የተቀመጠው በረከት ጥልቅ ነው፡፡ በአጋርነት ውስጥ እጅግ ታላቅ በረከት እንደመቀመጡ ሁሉ ፈተናዎችም ደግሞ አሉት፡፡ መልካም ነገር ርካሽ እንዳልሆነና በቀላሉ እንደማይገኝ እንዲሁ አጋርነት ትጋትንና ትህትናን ይጠይቃል፡፡

የአጋርነት ፈተናዎች የሚመጡት አጋሩ በሚደክምበት ጊዜ ነው፡፡ የአጋርነት ትክክኛውም ፈተና ያለው በጥንካሬ ሳይሆን በድካም ወቅት ነው፡፡ የአጋርነትም ጥንካሬው በእውነት የሚፈተነው በአስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡

በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ምሳሌ 24፡10

ምክኒያቱም አጋርነት የታቀደው የሌላን ብርታት ለመድገም ሳይሆን የሌላውን ድካም ለመሸፈን ነው፡፡ የአጋርነት አላማ ሌላው በሚደክመበት ለመሙላት ነው፡፡

የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ዘፍጥረት 9፡22-23

ካም የአባቱን ራቁትነት አየ፡፡ የአባቱ ራቁትነት የራሱ ራቁትነት እንደሆነ አልተገነዘበም፡፡ የአባቱን ድክመት መሸፈን የራሱን ድክመት መሸፈን መሆኑን አልተገነዘበም፡፡ ማንም መንገደኛ የሰውን ራቁትነት መግለጥ ይችላል፡፡ የሌላውም ራቁትነት መግለጥ በጣም ቀላል ነው፡፡ የሌላውን ራቁትነት መሸፈን ግን ትጋትና ትህትናን የሚጠይቅ ጨዋነት ነው፡፡

ሴምና ያፌት የአባታቸው ራቁትነት የራሳቸው ራቁትነት መሆኑን ስለተረዱ ለመሸፈን ፈጠኑ፡፡

የአጋርን ድካም ማየት ቀላል ነው፡፡ የአጋርን ድካም መግለጥ ያን ያህል አይከብድም፡፡ ማንም መንገደኛ የአጋርን ድካም መግለጥ ይችላል፡፡ የአጋር ድካም የእኔ ድካም ነው ማለት ግን ከፍ ያለ መረዳት ነው፡፡ የአጋሬን ድካማ ያየሁት እንድሸፍነው እንጂ እንድገልጠው አይደለም ማለት ጨዋነት ነው፡፡ የአጋሬን ድካም እኔ ካልሸፈንኩ ማን ይሸፍነዋል? ማለት ቤተሰባዊነት ስሜት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ሚስት #ባል #ቤተሰብ #ወንድ #ሴት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የቤተሰብ የአጋርነት

partnershippiece.jpgበቤተሰብ አጋርነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰዎች ውስን ከመሆናቸው የተነሳ ለተሻለ ውጤት ሌላው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተሻለ ፍሬያማነት ያለው በግንኙነት አጋርነት ነው፡፡ አጋሮቻችን በበዙ ቁጥር ፍሬያማነታችን ይበዛል፡፡ እግዚአብሄር በአጋርነት ያስቀመጠውን በረከት እንዴት መጠቀም እንደምንችል በተረዳን ቁጥር በሁሉም ነገራችን እንሰፋለን እናድጋለን፡፡

ባል በረከት ነው፡፡ ወንድ በተፈጥሮው የራሱ ሞገስ አለው፡፡ ወንድ ሚስትን ሲያገኝ በረከቱ ይበዛል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገኝ ሞገሱ ይጨምራል፡፡ ወንድ ሚስት ሲያገባ ብቻውን ማድረግ ከችለው በላይ ማድረግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው በአጋርነት ውስጥ የታመቀ ታላቅ ሃይል ስላለ መፅሃፍ ቅዱስ ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ የሚለው፡፡

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22.

ቤተሰብ የሚከናወነው በሚስትና በባል አጋርነት ነው፡፡ የቤተሰብ ፍሬያማነት የሚለካው ሚስት እና ባል በተናጥል ባላቸው በረከት ሳይሆን በአጋርነታቸው በሚመጣው በረከት ነው፡፡ የቤተሰብ ስኬት የሚለካው ወንድ ወይም ሴት በተናጥል ባላቸው ስኬት ስኬት ሳይሆን በአጋርነት በሚያገኙት ስኬት ብቻ ነው፡፡ የትኛውም የተናጠል ስኬት እንደአጋርነት በቤተሰብ እንደሚገኘው ስኬት ይበልጥ የበዛ አይሆንም፡፡

ወንድ ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረው ክህሎት አለው፡፡ ወንድ ቤተሰብን እንዲያገለግልበት አብሮት የተፈጠሩ ስጦታዎች አሉት፡፡ ወንድ የተጠራው ቤተሰቡን ለመጠበቅ በመከላከል ምሪትን ለመስጠት ብሎም አስቸጋሪ ነገርን ከፊት ሆኖ ለመጋፈጥ ችግሮችን ለመጠርመስ ነው፡፡ ባል የቤተሰቡ ደህንነት ለመጠበቅ ፣ ምሪትን ለመስጠትና ዋና የገቢ ምንጭ በመሆን የቤተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አገልጋይ ነው፡፡

ሴት እንዲሁ ስትወለድ የተወለደችው ለቤተሰብ ከሚጠቅም ልዩ ክህሎት ጋር ነው፡፡ ሴት በዋነኝነት ቤተሰቡ የምታገለግለው  ቤተሰቡን በማስተዳደር ለቤተሰቡ እንክብካቤ ማድረግ ነው፡፡

ወንድ በዋነኝነት የቤተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ክህሎት ከእግዚአብሄር ተችሮታል፡፡ ወንድ ከእግዚአብሄር ስለተሰጠው የመሪነት ስጦታ  ምክኒታይ የእግዚአብሄርን ፊት በመፈለግ ቤተሰቡን በትክክለኛው መንገድ የመምራት ታላቅ ሸክም ተጥሎበታል፡፡

ሴት ደግሞ እግዚአብሔር በውስጥዋ ከፈጠረው ክህሎት የተነሳ ለቤተሰብዋ እንክብካቤ ለማድረግ ቤተሰቡ ያለውን ነገር በጥበብ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት በእርስዋ ላይ ወድቆዋል፡፡

በቤተሰብ ሙሉን የእግዚአብሄርን መልክ የሚያንፀባርቁት ወንድና ሴት ናቸው፡፡ የወንድና የሴት አጋርነት እግዚአብሄር በቤተሰብ ውስጥ ያስቀመጠው ሙሉ ሃይል እንዲወጣና ለብዙዎች በረከት እንዲሆን ያስችለዋል፡፡

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27

ሊተባበሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድ ከሴት ጋር ሊፎካከር በፍፁም አይችልም፡፡ አንዱ የሌላውን ጉድለት እንደሚሞላና የሌላውን ድካን እንዲሸፍን የተላከ አጋር የቤተሰብ አባል ለአንድ አላማ ሊሰሩ እንጂ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ወንድና ሴት ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡

የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ዘፍጥረት 9፡22-23

ወንድ ከሴት የተለየ ችሎታና ሃላፊነት አለበት፡፡ ሴትም ከወንድ የተለየ ሃላፊነትና ችሎታ ጋር ተፈጥራለች፡፡ ሁለቱም በቤተሰብ ያላቸውን ሃላፊነት ከተወጡ ቤተሰቡ እግዚአብሄር ወደዳየለት የክብር ደረጃ ይደርሳል፡፡ ሁለቱም ያላቸው ሃላፊነትና ችሎታ ክቡርና ከእግዚአብሄር የተሰጠ ነው፡፡ የሚያገለግሉበት መንገድ ይለያይ እንጂ ሁለቱም አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሚያገለግሉበት የህይወት አቅጣጫ ስልጣኑም አላቸው፡፡

እያንዳንዱ እግዚአብሄር በሰጠው የሃላፊነት ቦታ የተከበረ ነው፡፡ ባልተሰጠው ሃላፊነት አንዱ ለሌላው ይገዛል፡፡ የቤተሰቡን አጠቃላይ መሪነት በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለወንዱ ይገዛሉ፡፡ የቤተሰቡን ዝርዝር አስተዳደር በተመለከተ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለሴትዋ ይገዛሉ፡፡

ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ኤፌሶን 5፡21

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ሚስት #ባል #ቤተሰብ #ወንድ #ሴት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የአጋርነት ሃይል – በንግድ

handshake1.jpgየህይወት ስጦታ ሁሉ በአንድ ሰው ውስጥ የለም፡፡ በህይወት ስኬታማ ለመሆን እያንዳንዳችን ሌሎች ያስፈልጉናል፡፡ ስኬታማ ለመሆን በህይወታችን እኛ የሌለን ስጦታ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ የአንድን ሰው ህይወት የሚሰራው የሰዎች አስተዋፅኦ ነው፡፡ በህይወት ለመከናወን በአንዳንድ የህይወት ክፍላችን ከእኛ የተሻሉ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ላላው ከእኛ እንደሚሻል ካላወቅን በሰዎች የተሻለ ስጦታ መጠቀም ያቅተናል፡፡ ትኩረታችን በራሳችን ስጦታና ችሎታ ላይ ብቻ ከሆነ  የሌሎችን ስጦታ አስተዋፅኦ በህይወታችን እንገድላለን፡፡

ለእኛ ተራራ የሚሆንብንን ነገር በቀላሉ የሚሰራው ሌላ ሰው አለ፡፡ ለእኛ ጭንቅ የሚሆንብን ነገር ለሌላው እንደ ጨዋታ ነው፡፡ የስጦታችን መለያየት ልዩ ያደርገናል እንጂ እኛን ታናሽ ሌላውን ታላቅ አያደርገውም፡፡ በሌላው ስጦታና ክህሎት ለመጠቀም በተወሰነ የህይወት ክፍል ሌላው ከእኛ እንደሚሻል በትህትና መቁጠር ይጠይቃል፡፡

ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3

ለህይወት ስኬት አጋርነት ወሳኝ ነው፡፡

የንግዱን አለም ብንመለከት በአለም ላይ በንግድ ታላላቅ ጥርመሳዎች የመጡት በንግድ አጋርነት አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ነጋዴ ደንበኛን የማሳመንና ወጥቶ ምርቱን የመሸጥ ልዩ ችሎታ አለው፡፡ አንዳንዱ ነጋዴ ደግሞ ንግዱን ማስተዳደር የሚገባውንና የሚወጣውን እቃ መከታተል  እንዱሁም የተሸጡትን እቃዎች ተከታትሎ ገንዘቡን በመቀበል በመሳሰሉት የአስተዳደር ስራ የተካነ አለ፡፡ ስለዚህ በመሸጥ የተካነው ነጋዴና በማስተዳደር የተከናው ነጋዴ በአጋርነት ቢሰሩ ሁለቱ በተናጥል ከሚሰሩት የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ አንድ ንድግ በአንድ ሰው ክህሎት ላይ ብቻ ካልተደገፈና አጋሮቹ ሁሉ በጠንካራ ጎናቸውና በየክህሎታቸው ለድርጅቱ ጠንክረው ከሰሩ ድርጅቱ የማያድግበት ምክኒያት አይኖርም፡፡

ድርጅቱ ሲያድግ እምዲሁ አንዱ ለሌላው አስተዋፅኦ እውቅና ካልሰጠ እና ክብሩን ሁሉ ጨቅልሎ ኪሱ ከከተተ አጋርነቱ ሊቀጥል ብሎም በአጋርነቱን የሚገኘው ጥቅም ሊቀጥል አይችልም፡፡ የድርጅቱ ማደግና መስፋት እንጂ ክብሩን ማን ይወስደዋል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ካልሆነ በአጋርነት ድርጅት ያድጋል፡፡ በድርጅት እድገት ሲመጣ በአጋሮቹ ሁሉ ምክኒያት እንደመጣ እውቅና መስጠት ይጠይቃል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን በአጋርነት የመጣውን እድገት የእኛ ብቻ ለማድረግ ስንሞክርና በአጋርነት ሃይል የመጣውን ውጤት በእኛ ምክኒያት የመጣ ሲመስለን እንታለላለን፡፡ በአጋርነት የተለቀቀው ጥቅምን “ይህ አጋሬ ባይኖር ኖሮ ክንሩንና ጥቅሙ ሁሉ የኔ ይሆን ነበር” ብለን ካሰብን ነገር ይበላሻል፡፡ በአጋርነቱ ሁሉ ምክኒያት ጥቅሙ እንደመጣ ማስተዋል ነው፡፡ የመጣውን ውጤት ብቻ ሳይሆን በአጋርነቱ ላይ  የተደረገውን አስተዋፅኦ ብንመለከት አጋሬ ባይኖር ኖሮ ይህ ሁሉ የእኔ ይሆን ነበር ወደሚል አላግባብ ቁጭት ውስጥ አንገባም፡፡

ለተሻለ ጥቅም በአገፋርነት ለመስራት ራሳችንን ትሁት እናድርግ፡፡ በአጋርነት የመጣውን ድል የራሳችን ብቻ አናድርገው፡፡ እግዚአብሄር የሚባርከን አጋርነትን ሁሉ አይቶ ነው፡፡ በአጋርነት ያገኘነው ድል ብቻችንን ብንሆን ኖሮ የማናገኘው ድል ነው፡፡ ሚስት ስናገባ የሚለቀቅልን በረከት ሚስት ካላገባው ይጨምራል፡፡

ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። ምሳሌ 18፡22

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህብረት #አጋርነት #አብሮማደግ #የጋራ #ንግድ #ሚስት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ዘጠኙ የህብረት ጥቅሞች

fellowship.jpgየእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ፈፅመን እግዚአብሄርን በሚገባ እንድናከብረው እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ዋና ዋና በረከቶች አንዱ የቅዱሳን ህብረት ነው፡፡ የወንድሞች መሰብሰብና ህብረት የእግዚአብሄርን ስራ ከምንሰራበት ቁልፍ መንገዶች አንዱ ነው፡፡

እግዚአብሄር ራሱን አባት አድርጎ መስጠት ብቻ ሳይሆን እህቶችና ወንድሞች ስለሚያስፈልጉን አውቆ የቅዱሳንን ህብረት ሰጥቶናል፡፡

በመጀመሪያይቱ ቤተክርስትያን ለህብረትና ለመሰብሰብ እጅግ ልዩ ትኩረት ከመስጠታቸው የተነሳ የቤተክርስትያን ጥንካሬና በህብረት ያገኙትን ውጤት እንመለከተናል፡፡

በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር። ሐዋርያት 2፡46-47

በኢየሱስ ስም ህብረት ባደረግን መጠን ውጤታማነታችን እየጨመረ ስለሚሄድ ታላቁን ወንጌልን የመስበክ ተልእኮዋችንን በሚገባ መወጣት እንችላለን፡፡

በቅዱሳን ህብረት ብቻ ስለምናገኛቸው በሌላ በምንም መንገድ ግን ስለማናገኛቸው ታላላቅ ጥቅሞች እንመልከት፡፡

 1. የአንድነት አምልኮን ክብር የምንለማመደው ከቅዱሳን ጋር ተሰብስበን ነው፡፡

በአንድነት ሆነን እግዚአብሄርን ማምለክ እጅግ ወሳኝና የክርስትና ህይወታችን የሚያለመለም ራሳችንን እንድንረሳና በእግዚአብሄር መንፈስ እንድንረሰርስና እንድንዋጥ የሚያስችለን ልዩ ልምምድ ነው፡፡ በአምልኮ የሚመሩንን ሰዎች የሰጠን ለህብረት እንጂ በግላችን አይደለም፡፡

ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙር 96፡6-7

 1. የፀጋ ስታዎች ተጠቃሚ የምንሆነው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

በምንሰበሰብበት ጊዜ እግዚአብሄር በሌላው ወንድማችን በኩል የሚገልፀው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ህብረቱን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ይመጣል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የተሰጠው ሌላውን ለማነፅ ፣ ለማፅናናትና ለመጥቀም ነው፡፡

እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡26

ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡3

 1. የአገልግሎት ስጦታዎች የተሰጡት ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡

እግዚአብሄር ስጦታዎችን ሐዋርያትን ፣ ነቢያትን ፥ ወንጌልን ሰባኪዎችን ፥ እረኞችንና አስተማሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ህብረት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ እድገታችንና ክርስቶስን ለመምሰል ብሎም ለአገልግሎት ለመታጠቅ እግዚአብሄር ለቤተክርስትያን የሰጣቸውን የአገልግሎት ስጦታዎች የምንጠቀመው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡11-13

 1. ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎችን የሰጠው ለቤተክርስትያን ነው፡፡

እግዚአብሄር ለነፍሳችን የሚተጉትን መሪዎች የሰጠው ለቤተክርስተያን ህብረት ነው፡፡ የሚያስተምሩን የሚመክሩንና የሚገስፁን በህብረት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡

እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ቆላስይስ 1፡28

ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ዕብራዊያን 13፡17

 1. የመንፈሳዊ ህይወት ደህንነታችን የሚለካው በህብረት ውስጥ ነው፡፡

ለቅዱሳን እንደሚገባ መኖራችንን የምናወቅው በህብረት ስንሆን ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወደ መንግስተ ሰማያት እየሄድን እንደሆነ የምናውቀው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡ ለወንጌል እንደሚገባ የማይኖረውን የምናቀናው በህብረት ሲገኝ ነው፡፡ እንዳልሳትንና ወንድማችንን እንዳላሳዘንን የምናውቀው ከወንድማችን ጋር አብረን በመኖር፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል እየኖርን መሆናችንን እርግጠኛ የምንሆነው ብቻችንን በመኖር አይደለም፡፡ ትክክል መሆናችንን የምናውቀው የምንጠየቅለት ህብረት ሲኖር ነው፡፡ ስለ እውነተኝነታችንም ሰዎች የሚመሰክሩት በህብረት ስንገኝ ነው፡፡

ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-18

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ዕብራዊያን 13፡7

 1. ፍቅርን በተግባር የምንማረውና የምንረዳው ከቅዱሳን ጋር ነው፡፡

ፍቅር ለሌላው መልካም ማሰብ መናገርና ማድረግ ነው፡፡ ለብቻ ኖሮ ፍቅር አለኝ ማለት አይቻልም፡፡ የሚበድልና የሚታገሱት ባለበት ነው ፍቅርን የምንለማመደው፡፡ ከእኛ የተለየ ሰው ባለበት ህብረት ነው ፍቅርን ፣ ይቅር ማለትን እና ምህረትን የምንለማመደው የምናሳድገው፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ነው ሌላውን መቀበልና መውደድን የምንማረው፡፡

ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ኤፌሶን 3፡18-19

 1. በቅዱሳን ህብረት ስንገኝ ነው የጠፋውን የምንፈልገው፡፡

በቅዱሳን ህብረት ስንሆን ነው የጠፋውን የምናውቀው፡፡ በቅዱሳን ህብረት ስንገናኝ ነው የደከመውን ሸክም ለመሸከም መተያየት የምንችለው፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ 6፡1-2

 1. ከወንድማችን ፀጋ የምንካፈለው በመገናኘት ነው፡፡

እግዚአብሄር ባሳደገን ፀጋ ሌሎችን የምንመግበው ስንገናኝ ስናወራ ስንጫወት በቃል ነው፡፡ የእግዚአብሄን ቃል ስንጫወት ነው በቃል ፀጋን የምንለዋወጠው፡፡ እግዚአብሄር ባሳደገኝ የህይወት ክፍል በምናገረው የፀጋ ቃል ነው ሌላውን የፀጋ ሃይል የማካፍለው፡፡ በህብረት ነው ሌላውን የምረዳውና ካለበትና ከተያዘበት የሚወጣበትን ፀጋ የማካፍለው፡፡

ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

 1. ስንተያይ ነው አንዳችን አንዳችንን የምንሞርደው፡፡

በህብረት ነው ለፍቅርና ለመልካም ስራ የምንበረታታው፡፡ በህብረት ውስጥ ነው አንዳችን እንዳችንን የምንስለው፡፡ ስንገናኝ ነው አንዳችን የአንዳችንን የፍቅርና የመልካም ስራ ፍም የምናራግበው የምናነሳሳውና የምናቀጣጥለው፡፡

ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡24-25

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ዛሬ ተብሎ ሲጠራ

today2.jpgወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ ዕብራውያን 3፡12-13

ክርስትና የሰነፎች አይደለም፡፡ ክርስትና የጨካኞች ነው፡፡ ክርስትና የልፍስፍሶች አይደለም፡፡

ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ማቴዎስ 11፡12

ክርስትና ትጋትን ይጠይቃል፡፡ በክርስትና ትጋታችንን ከሚጠይቀው ነገር አንዱ ከወንድሞች ጋር ህብረት ማድረግ ነው፡፡

ሰይጣን አለ፡፡ የሚዋጋ ጠላት አለ፡፡ የሚያታልል የሚያስት ዲያቢሎስ አለ፡፡ ልባችንን የሚፈልግ ልባችንን ከእግዚአብሄር ቃል በተቃራኒ ቃል የሚደበድብ አለ፡፡ ካልተጠነቀቀን ክፉና የማያምን ልብ ሊኖረን ይችላል፡፡ ወደፊት ክፉና የማያምን ልብ ሊኖረኝ በፍፁም እይችልም ብሎ ሊዝናና የሚችል ሰው የለም፡፡

ሊስቱ አይችሉም ብለን በጣም የተማመንባቸው ሰዎች ሲስቱ አይተናል፡፡ መፍራት እንጂ በትቢት ማሰብ አያዋጣም፡፡

ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡12

ሃዋሪያው ጳውሎስ እንኳን እንዳይጣል በጥንቃቄ እንደሚኖር ያስተምራል፡፡

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27

ነገር ግን ላለመሳት ተስፋ አለ፡፡ ሰው በየእለቱ ከወንድሙ ጋር ከተመካከረ አይስትም፡፡ ሰው በየእለቱ ከወንድሙ ጋር ህብረት ካደረገ በሃጢያት መታለል አልከኛ አይሆንም፡፡ ሰው ከክርስትያን ወንድሙ ጋር በእውነት ህብረት እያደረገ እግዚአብሄርን የሚያስክድ ክፉና የማያምን ልብ ሊኖረው አይችልም፡፡

እግዚአብሄር በህብረት ውስጥ ለልባችን ጤንነትና ለእምነታችን እጅግ ጠቃሚ ነገር ካስቀመጠ እኛም በትጋት ከወንድሞቻችን ጋር በትጋት ህብረት ልናደርግ ይገባናል፡፡

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3

እኛ ካለንበት ነገር መንጥቆ ሊያወጣን የሚችን ፀጋ በሌላው ወንምድማችን ውስጥ አተቀምጧል፡፡ በወንድማችን ውሰጥ ያለውን ፀጋ የምንካፈለው በንግግርና በምክክር ነው፡፡ የወንድማችንን ቃል ስንሰማ በዚያ ፀጋን እንካፈላለን፡፡

ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ ዕብራውያን 3፡12-13

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ፀጋመካፈል #የወንድሞችህብረት #ዛሬ #እልከኛልብ #የሃጢያትመታለል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የወንድሞች ህብረት ሽቱ

thumb-350-641462.jpgወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3

ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነትና ህብረት ወሳኝ ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት ከሌለው ህይወቱን በከንቱነት ያሳልፋል፡፡

ለእግዚአብሄር ከብር የሚኖሩ ወንድሞች ደግሞ እርስ በእርሳቸው ያላቸው ግንኙነት እንዲሁ ወሳኝ ነው፡፡ የእኛ በህብረት መቀመጣችን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡እግዚአብሄር በእኛ አንድነት ደስ ይሰኛል፡፡

እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮናል፡፡ እኛ ስሜት እንዳለን ሁሉ እርሱም ስሜት አለው፡፡ እኛን ደስ የሚለን ነገር እንዳለ ሁሉ እርሱንም ደስ የሚለው ነገር አለ፡፡ እርግጥ ነው ሰውን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን ደስ አያሰኘውም ፡፡ ሰውን የሚያስደንቀው ነገር ሁሉም እግዚአብሄርን አያስደንቀውም፡፡ ሰውን የሚያምረን ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን አያምረውም፡፡

እግዚአብሄርን የሚያስደስተው ነገር የወንድሞች ህብረት ነው፡፡ ሽቱ መልካም ስሜት እንደሚፈጥር ሁሉና ደስ እንደሚያሰኝ ሁሉ የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የአርሞንዔም ጠል ምድሩን እንደሚያለመልመው ሁሉና ምድሩን እንደሚያረካው የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ያረካዋል፡፡

እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ይዘረዝርና ሰባተኛውን በወንድሞች ህብረት ላይ የሚሰራውን በደል ነፍሱ አጥብቃ እንደምትጠየፈው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡

እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ምሳሌ 6፥19

ስለዚህ ነው እግዚአብሄርን ለማስደሰትና የወንድሞችን ህብረት ለመጠበቅ ትጋት እንደሚጠይቅ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የድንጋይ ልብ

stone heart.pngወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ዕብራውያን 3፡12

ልብ በጣም ወሳኙ የሁለንተናችን ማእከላዊ ክፍል ነው፡፡ ልብ ከጠነከረ ሁሉም ነገር ይጠነክራል፡፡ ልብ ከሳሳ ደግሞ ሁሉም ነገር ይሳሳል፡፡ ልብ እግዚአብሄርን ማመን ካቃተው ነገር ሁሉ ይበላሻል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ስስ የስጋ ልብ ካለን ደግሞ ሁሉም ነገር የሰመረ ይሆናል፡፡

ስለዚህ ነው ኢየሱስን ስንቀበል ልባችን የሚለወጠውና የድንጋይ ልባችን በስጋ ልብ የሚተካው፡፡ ጭካኔን ትተን ርህራሄን የምንለብሰው ፣ ጭለማን ገፍፈን ብርሃንን የምንታጠቀው ፣ ጥላቻን ትተን ፍቅርን የምንለማመደው ልባችን በጌታ በመለወጡ ነው፡፡

የድንጋይ ልብ ደግሞ የሚባለው ለእግዚአብሄር ነገር ምንም ቅናት የሌለው ፣ እሳቱ የጠፋበት ፣ ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌለው እምነቱ የጠፋበት በጥርጥር የተሞላ ልብ ነው፡፡ ልበ ጠንካራ ሰው ትሁት መሆን ያቃተው ፣ አንገተ ደንዳና ፣ ለእግዚአብሄር እሺ የማይልና ለቃሉ የማይንቀጠቀጥ የእልከኛ ሰው ልብ ነው፡፡

ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ዕብራውያን 4፡7

የህይወት መውጫ ከእርሱ ዘንድ ነውና ልብንህን ጠብቅ ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡

አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23

ልባችንን እንዴት እንድንጠብቅ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ልባችንን የምንጠብቅበት መንገድ እለት በእለት በመትጋተ መሆኑን የእግዚአብሄር ቃል ያስተምረናል፡፡

ልቡን አለመጠበቅ ያለበት ሰው የለም፡፡ ማንም ሰው ከዚህ አደጋ ነፃ አይደለም፡፡ ከክፉና እልከኛ ልብ የምንድነው እለት በእለት በትጋት ስንሰበሰብና ስንመካከር ብቻ ነው፡፡ ማንም እኔ ይሄ አይነካኝም በሚል አጉል ትምክት በእያንዳንዱ ቀን በእግዚአብሄር ቃል መመካከሩን ቸል ቢል ሳያውቀው ክፉና እግዚአብሄርን የሚያስክድ ልብ ይኖረዋል፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤  ዕብራውያን 3፡12-13

እግዚአብሄርን የሚያምን ፣ ለእግዚአብሄር ቃል ስስ የሆነ ፣ የዋህና የስጋን ልብ ለመጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አጥብቀን እንጂ በቸልታና በስንፍና ልባችንን አንጠብቅም፡፡ ልባችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተለውጧል ፡፡ ያንን የተለወጠ የስጋ ልብ ፣ የሚያምን ልብ መጠበቅ ግን የእየለቱ ትጋታችንን ይጠይቃል፡፡

ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ተመካከሩ #ከሃዲ #እልከኛ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

ብልቶች

publication11በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ሮሜ 12:5-8
የሰው አካል ክፍሎች በአንድነትና በህብረት ተግተው ለአካሉ መልካምነት እንደሚሰሩ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖችም ብዙ አይነት የአገልግሎት ጥሪዎችና ስጦታዎችም ቢኖሩን ሁላችን ለአንድ ግብ እንደምንሰራ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
በአንድ አካል ላይ ያለን የተለያዩ ብልቶች ብንሆንም ሁላችንም ለአንድ አካል የምንሰራ የአካል ክፍሎች ነን፡፡
ለአንድ አላማ ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ስራ መስራት የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ሰዎች መሆን የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት አገልግሎት ሊኖረን አይገባም፡፡ የእምነት ደረጃችን እኩል መሆን የለበትም ለአንድ መንግስት ለመስራት፡፡ ሁላችንም አንድ አይነት ስራ ከሰራን ውበትም ውጤትምን አይኖረውም፡፡
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡17
ሁላችንም ስራችን የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም ለአንድ ግብ መስራት እንችላለን፡፡
የሁላችንም ስራ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም እጅግ አስፈላጊዎች ነን፡፡ የማያስፈልግ የአካል ብልት የለም፡፡ እንዲያውም ደካማና የማያስፈልጉ የሚመስሉት እነርሱ ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22
ማንም ከማንም ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ነው እንጂ እንዲፎካከር አልተፈቀደም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲመካ በፍፁም አልተፈቀደም፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
የአንድ አካል ብልቶች ሆናልና አንድ አካል ሲከብር ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይከብራሉ አንድ አካል ሲሰቃይ ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይሰቃያሉ፡፡
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26
እንዲያውም ደካማ ለሚመስለው የአካል ብልት ይበልጥ ክብር ይጨመርለታል፡፡ ፀጋም የሚበዛለት ለደካማው ብልት ነው፡፡
ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡23
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡27
ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። ኤፌሶን 4፡15-16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
#ኢየሱስ #ጌታ #አካል #ብልት #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

የወንድሞች ህብረት

fellowshipእግዚአብሄር በመልኩና በምሳሌው ስለፈጠረን እግዚአብሄር እንደኛው ስሜት እንዳለው እንረዳለን፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደስቱን ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሄርን የማያስደንቁት ነገሮች አሉ፡፡ እግዚአብሄር የሚወደው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር የማይወደው ነገር ደግሞ አለ፡፡ ለእግዚአብሄር መልካም የሆነ ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር መልካም የማይለው ነገር አለ፡፡
እኛን የሚያስደንቁን ነገሮች ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን አያስደንቁትም፡፡ እግዚአብሄርን የማያስደስቱት እኛን የሚያስደስቱን ነገሮች አሉ፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር የሚደነቅባቸውና መልካም ነው ያማረ ነው ብሎ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ እንዲያውም የወንድሞች ህብረት ለእግዚአብሄር የሚጣፍጥ ምርጥ ሽቱ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል፡፡ የወንድሞች መሰብሰብ ጥምን እንደሚያረካና እንደሚያለመልም ውሃ ወሳኝ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
ስንሰበሰብ እግዚአብሄር ደስ ይለዋል፡፡ በአንድነት ስንሆን ደስ ይረካል፡፡ የወንድሞች መሰብሰብ ለእግዚአበሄር እንደ ሽቱ ነው፡፡
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133:1-3 ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
#ህብረት #ወንድሞች #ሽቱ #ያማረ #እምነት #አንድነት #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ
%d bloggers like this: