Category Archives: Test

መልስ የሌለው ፈተና

mathematics-stock-picture-1958323.jpg

ፈተና ለእኛ መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ በህይወት መልስ የሌለው ጥያቄ የለም፡፡ በህይወት መውጫ የሌለው ፈተና የለም፡፡ ፈተና የለም ማለት ስህተት እንደሆነ ሁሉ ፈተናው መልስ የለውም ማለት እንዲሁ ስህተት ነው፡፡ ፈተና ፈተና የሚሆነው መውጫው ሲታጣ ነው፡፡ ፈተና ፈተና የሚሆነው መውጫውን ስለማናየው ነው፡፡

እግዚአብሄር ካለንበት ፈተና መውጣት እንደምንችል ያውቃል፡፡ በእኛ በኩል የፈተናችን መውጫ አይታይም፡፡ በእግዚአብሄር በኩል ግን የፈተናችን መውጫ ይታያል፡፡ ፈተና ከእኛ እንጂ ከእግዚአብሄር ቁጥጥር ውጭ አይደለም፡፡ በእኛ ላይ የሚደርሰው ፈተና እግዚአብሄር የፈቀደለት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያልፈቀደው ፈተና በእኛ ላይ አይደርስም፡፡ እግዚአብሄር ከምንችለው በላይ እንዳንፈተን የማይፈቅደው ስለዚህ ነው፡፡

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13

ፈተና ፈተና የሚሆነው መፍትሄው ለእኛ ስለማይታየን ነው፡፡ ፈተና የሚገድለን የሚጥለን የሚያዋርደን ይመስለናል፡፡ የማያስቸኩል እና የማያጣድፍ እንዳንታገስ የማይፈትን ፈተና ፈተና አይደለም፡፡ የፈተናን መፍትሄ የምናይበት ብቸኛው ቦታ ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ይዘግይ ይፍጠንም የፈተናው መልስ ይመጣል፡፡ ፈተናውን እንድንታገሰው የእግዚአብሄር እርዳታ ያስፈልገናል፡፡ ካለ እግዚአብሄር እርዳታ ፈተናን መታገስ አንችልም፡፡

ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13

ከፈተና ጊዜ በላይ የእግዚአብሄር ፀጋ የሚያስፈልግን ጊዜ የለም፡፡ ካለ እግዚአብሄር ፀጋ ፈተናን ማለፍ አንችልም፡፡ ፈተና ፈተና የሚሆነው መውጫው ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ፈተናን ማለፍ የምንችለው በእግዚአብሄር ፀጋ ብቻ ነው፡፡ ፈተናን ማለፍ የምንችለው በእግዚአብሄር እርዳታ ብቻ ነው፡፡

እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16

የትኛውም ፈተና ከአቅም በላየ የሚሆነው ለእኛ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ከአቅም በላይ የሆነ ፈተና የለም፡፡ በእግዚአብሄር እርዳታ የማንወጣው ተራራ የለም፡፡ በእግዚአብሄር ጥበብ የማንፈታው ቋጠሮ የለም፡፡ በእግዚአብሄር ማፅናናት የማንወጣው ሃዘን የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ የማንደርስበት ፍጥነት የለም፡፡ በእግዚአብሄር እርዳታ የማንታገሰው ጊዜ የለም፡፡ ለማንኛውም ፈተናና ችግር መፍትሄ የሆነ ፀጋ በእግዚአብሄር ዘንድ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ይመስለናል እንጂ የእግዚአብሄር ፀጋ የማይፈታው ተግዳሮት ከዚህ በፊትም አልነበረም ከዚህም በኋላ አይኖርም፡፡

እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #የሚረዳንን #ፀሎት #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በሰው የሚታመን

conscious.jpg

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። ትንቢተ ኤርምያስ 17፡5-6

እግዚአብሄር የፈጠረን በእርሱ እንድንደገፍ ነው፡፡ በእርሱ ስንደገፍ እግዚአብሄር ደስ ያሰኘዋል፡፡

ነገር ግን በእግዚአብሄር መታመን ትተን በሰዎች መታመን ስንጀምር እግዚአብሄር ያዝናል፡፡ የተፈጠርነው በእግዚአብሄር እንድንደገፍ ስለሆነ በሰው ስንደገፍ አይሳካልንም፡፡

እንኳን ለሌላ ሰው መገደፊያ ሊሆን ይቅርና ሰው ራሱ በእግዚአብሄር ላይ መገደፍ አለበት፡፡ ሰው ለሌላ ለማንም ሰው መደፊያ ሊሆን አይችልም፡፡

ብዙ ሰዎች በእግዚአብሄር መታመን ይጀምራሉ፡፡ በእግዚአብሄር በመታመን እንድንጀምር ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሄር በመታመን እንድንጨርስ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡

በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ የማያነሳ ሰው ምስጉን ነው፡፡ በክፉ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ የሚያነሳ ሰው እርጉም ነው፡፡

በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። መጽሐፈ ምሳሌ 24፡10

አስቸጋሪ ጊዜ አልፎ ደግሞ መልካም ዘመን ሲመጣ እምነቱ ከእግዚአብሄር ላይ ያነሳውና በሰው ላየ ያደረገው ሰው ይፀፀታል፡፡ መልካም ጊዜ መጥቶ የማይለወጥ የሚመስለው ነገር ሲለወጥ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ እንስቶ ወደሰው ላይ ያደረገው ሰው ለሚያልፍ ነገር ምነው በእግዚአብሄር በታመንኩኝ ኖሮ ብሎ ይቆጫል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን እግዚአብሄርን በሰው የለወጠ ሰው የእምነትን ገድል ደስታ አያገኘውም፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ እንስቶ በሰው ላይ ያደረገ ሰው ለማይረባ ነገር እግዚአብሄርን ስለለወጠው ያፍራል፡፡

በአስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ ከእግዚአብሄር ጋር የሙጥኝ ያለ ሰው በእግዚአብሄር በመታመኑና በማለፉ ብቻ እምነቱ ይጨምራል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እግዚአብሄርና ያመነና የጠበቀ ሰው እምነቱ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ጠርቶና ከብሮ ይወጣል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን በሰው ያልለወጠው ሰው ደስታው ይበዛል፡፡

በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡6-7

እምነቱን ሲፈተን የወደቀ ሰው መልካም በመጣ ጊዜ አያይም፡፡ በሰው መደገፍን ያልናቀ ሰው በእግዚአብሄር በመደገፍ ያለውን ደስታ አያይም፡፡ በሰው በመደገፍ ክፉን ጊዜ ያሳለፈ ሰው ላነሰ ጥቅም ራሱን ስለሰጠ እውነተኛውን የእግዚአብሄርን በረከት አያየውም፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። ትንቢተ ኤርምያስ 17፡5-6

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ስጋለባሽ #መታመን #መደገፍ #ልብ #የሚመልስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ክንዱ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የክብር ፈተና

video.yahoofinance.dailyticker.com@e77be9bb-de3f-3343-b93e-20611b3f7700_FULL.jpgደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፦ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ማቴዎስ 4፡8-9

ሰይጣን ሰዎችን ከሚፈትንበት መንገድ አንዱ የክብር ፈተና ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ቃል ውስጡ ከሌለ ክብር ለማግኘት ሲፈተን ይወድቃል፡፡ ለስጋችን ስልጣንና ሃይል ይጣፍጣል፡፡ ሰው ስልጣንን ለማግኘት ሃያል ሰው ለመሆን ሲመኝ በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ይወድቃል፡፡

ሰው ከስልጣንም ከክብርም ከሃይልም በላይ በእግዚአብሄር ቃል መኖር አለበት፡፡ በምንም መልኩ ስልጣን ላግኝ የሚል ሰው በሰይጣን ወጥመድ መውደቁ አይቀርም፡፡ በአራዳም በፋራም ብዬ ሃይል ላግኝ የሚል ሰው የጊዜ ጉዳይ እንጂ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡

ስጋዊ ባህያችን ክብር ፣ ስልጣንና ሃይልን ይጠማል፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን በምንም በምንም የሚመጣውን ክብርን ፣ ትልቅነትን ፣ ሃይልንና ስልጣንን ይፈልጋል፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን ሌላውን ለመብለጥ ክብርን ፣ ትልቅነትን ፣ ሃይልንና ስልጣንን ይመኛል፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን በእግዚአብሄር ላይ ላለመታመን አማራጭ ሃይልን ይፈልጋል፡፡ ስጋ እግዚአብሄርን ከመጠበቅ ይልቅ አቋራጭ ክብርን ይጠማል፡፡ ሰይጣን ደግሞ ሰውን ለማሰገድ የሰውን ስጋዊ ምኞት ይጠቀማል፡፡ ከምንም በላይ ክብርን የሚፈልግ ሰው በተዘዋዋሪ ለሰይጣን ይሰግዳል፡፡

. . . ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? ዮሃንስ 5፡44

ሰው የክብርን ፈተና የሚያልፈው በእግዚአብሄር ቃል የሚመጣውን ክብር ብቻ ሲፈልግ ነው፡፡ ሰው የክብርን ፈተና የሚያልፈው ከእግዚአብሄር ብቻ የሚገኘውን ክብር ሲፈልግ ነው፡፡ ሰው የክብርን ፈተና የሚንቀው ሰይጣን ስጋን ተጠቅሞ እንደሚመለክ ሲያውቅ ነው፡፡

ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፦ ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ሉቃስ 4፡5-7

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #አምላክ #ፈተና #ክብር #ትግስት #ስልጣን #ሃይል #ደስታ #ምስጋና #ፅናት #ጥበብ #እምነት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በፈተና ጊዜ መተው የሌለብን ስድስት ነገሮች

crisis_communication1.jpgበክርስትና ሁልጊዜ የማሸነፉ ጥበብ በሚገጥመን ማንኛውም ፈተና ማድረግ የምንችለውን አድርገን ለእግዚአብሄር ፈንታ በመስጠቱ ላይ ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገር የእግዚአብሄርና የሰው የአጋርነት ስራ ነው፡፡ እኛ መስራት የማንችለው እግዚአብሄር የሚሰራልን ነገር አለ፡፡ እኛ ደግሞ የምንሰራው ነገር አለ፡፡ ታዲያ የእኛን ስራ ሰርተን ለእግዚአብሄር ፈንታ መስጠት ብልህነት ነው፡፡

ከመጣባቸው ከታላቅ መከራ የተነሳ ወደ እግዚአብሄር የጮሁና እግዚአብሄር በድንቅ የመለሰላቸው ሰዎች ምስክርነት የተሞላ መፅሃፍ ነው መፅሃፍ ቅዱስ፡፡

በፈታኝ የውጥረት ወቅት ማድረግ የሌለብን ስድስት ነገሮች፡፡

  1. ፀሎትን አለመተው

 

እውነት ነው ሰው ወደ ውጥረት ከመግባቱና ፈተና ከመምጣቱ በፊት ነው ወደ ፈተና እንዳይገባ መፀለይ ያለበት፡፡ በሰላ ጊዜ የማይፀልይ ሰው ብርቱ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በፈተና ወቅት ለራስ ጊዜ መስጠት እና ወደ እግዚአብሄር መጮኽን መተው የለብንም፡፡ እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ስለሚሰማ በራችንን ዘግተን የምንፀልይበትም እድሉን ባናገኝ ልባችንን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሄር ማንሳት ይገባናል፡፡ መውጫ የሌለ በሚመስልበት ሁኔታ እግዚአብሄር መውጫውን በጥበብ አማካኝነት ያካፍለናል፡፡

 

ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6

 

ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት . . . ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡2-5

 

  1. እረፍትን አለመተው – አለመጨነቅ

 

ማድረግ የምንችለውንና ማድርግ የማንችለውን ለይተን ማወቅ በክርስትና ስኬታማ ያደርገናል፡፡ ሰው ማድረግ የሚችለውን አድርጎ ካላረፈና ለእግዚአብሄር ፈንታን ካልሰጠ እግዚአብሄር እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡ ሰው ማድረግ የሚችለውን ካደረገ በኋላ ማረፍ ይኖርበታል፡፡ የሚያስጨንቀንን ነገር ለእግዚአብሄር መስጠት መልሰንም አለመውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ እኛ ስናርፍና እድሉን ለእግዚአብሄር ስንሰጠው በነገራችን ላይ ይሰራል፡፡

 

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

 

  1. ምስጋናን አለመተው

በውጥረትም ጊዜ እግዚአብሄር ከእኛ ምስጋናን ይጠብቃል፡፡ እንዲያውም እውነተኛ ትህትናችን የሚለካው በፈተና ጊዜ ስናመሰግነው ነው፡፡ እውነተኛ የምስጋና መስዋእት የሚባለው ላለማመስገን ብዙ ምክኒያቶች ያገኘን ሲመሰለን ያንን የስንፍና ሃሳብ ሁሉ አልፈን የምናመሰግነው ምስጋና ለየት ያለ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ የማጉረምረም ትምክታችንን ዋጥ አድርገን የምንሰጠው በቀላሉ ያልመጣ የምስጋና መስዋእት ነው፡፡

ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ መዝሙር 50፡14

 

  1. እምነትን አለመጣል – ፍርሃትንና ጥርጥርን አለማስተናገድ

 

እምነት ብቸኛው የማሸነፊያ መንገዳችን ሰለሆነ ውጥረቶች በህይወታችን የሚመጡት እምነታችንን ሊያስጥሉ ነው፡፡ እምነታችንን ካላስጣሉን ውጥረት አይሳካለትም አላማውም ተጨናግፏል፡፡ የውጥረት አላማው ፈተናውን ማግዘፍና እግዚአብሄርንም ማሳነስ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያሳስ ሃሳብ በልባችን አለመፍቀድ ውጥረትን በአሸናፊነት እንድናልፈው ይረዳናል፡፡ ፈተና በፍርሃት ከምነሄደው ጉዞ ካስቆመን ብቻ ነው ስኬታማ የሚሆነው፡፡ ጊዞዋችንን ከቀጠልን ወደፈተና ሳንገባ እናልፈዋለን፡፡

 

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28

 

ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ፦ እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። ማርቆስ 5፡36

 

  1. የወንድሞችን ህብረት አለመተው

 

በውጥረትና በፈተና ጊዜ አብረውን ሊቆሙ የሚችሉትን የወንድሞችን ህብረት አለመተው ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ወንድሞች በሚናገሩት ቃል የሚያስችልን ሃይል በፀጋ ያካፍሉናል፡፡

 

ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

 

በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡25

 

  1. ደስታን አለመተው

 

በውጥረት ጊዜ ደስታን መተው አይገባንም፡፡ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል ትእዛዝ መተው የለብንም፡፡ ደስ ይበላችሁ ብሎ ካዘዘ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ደስታ የውሳኔ ጉዳይ እንጂ የስሜት ጉዳይ አይደለም፡፡ ደስ እንዳይለን ምንም ምክኒያት የለንም፡፡ እግዚአብሄር እረኛችን ነው የሚያሳጣንም የለም፡፡ አባታችን እግዚአብሄር ከመሆኑ በፊት ሁሉን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደንቀው ነገር የለም፡፡ ፈተናው በእኛ ላይ የሚያራግፈው የማያስፈልገውን ነገር ብቻ እንጂ እኛን አያገኘንም፡፡ በፈተና ሙሉ የሚያደርገንና ወደሚቀጥለው ደረጃ የሚያሸጋግረን እድገት ስለሚመጣ ደስ ይበለን፡፡

 

ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ያዕቆብ 1፡2-4

 

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ፈተና #ውጥረት #ፀሎት #ጥበብ #እምነት #ህብረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ደስታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምስጋና #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: