Category Archives: doubt

የጥርጥር አለም ምልክቶች

159163-bigthumbnail.jpg

የእምነት አለም አለ የጥርጥር አለም አለ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት በሚገኘው በእምነት አለም ውስጥ የሚያገኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሰው በጥርጥር አለም ውስጥ የሚያጣቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሃጢያቱ እንደሞተና እንደተነሳ የማያምን ሰው ለእምነቱ ምንም መሰረት ስለሌለው ሁሌም በጥርጥር ውስጥ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጌታን አምኖና ተከትሎ ነገር ግን እምነቱን የማያሳድግ ልቡን ከጥርጥር ፣ ካለማመን እና ፍርሃት የማይጠብቅ ሰው ደግሞ አለ፡፡ ይህ ሰው አልዳነው የዘላለም ህይወት የለውም ባይባልም ነገር ግን እግዚአብሄር በምድር እንዲሰራ ያዘጋጀለትን ስራ በእምነት መፈፀም ያቅተዋል፡፡ የእግዚአብሄር መንገድ ሁሉ በእምነት ስለሆነ እግዚአብሄርን በሙላት በመከተል ፍሬ ማፍራት ይሳነዋል፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰርት ስለማይቻል በአጠቃላይ ከእግዚአብሄር ጋር በእምነት በመገናኘት እግዚአብሄን ማስደሰት ይሳነዋል፡፡

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6

በተለይ ደግሞ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ነገር ግን አለምን መስሎ የእግዚአብሄርን ቃል ስለህይወቱ በሚለው ላይ የማይቆምና በአካሄዱ አለምን የሚመስል ሰው በጥርጥር አለም ሲኖር ምን ምልክቶች እንዳሉት እንመልከት፡፡

 1. የጥርጥር አለም የጭንቀት አለም ነው

እምነት ከጭንቀት ያሳርፋል፡፡ እምነት የሚያስጨንቀንን በሚያስብልን ላይ በመተማመን እንድንጥል ያደርገናል፡፡ እምነት በእግዚአብሄር ቃል የማይታየውን አለም ስለሚያሳይ ከጭንቀት ያሳርፋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስለህይወቱ የሚለውን ነገር ከቃሉ የማይሰማና በእርሱ ላይ የማይቆም ሰው ስለሚጠራጠር በጭንቀት ያባክናል፡፡

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡7

በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። የማቴዎስ ወንጌል 13፡22

 1. የጥርጥር አለም ያለመርካት አለም ነው

የእምነት አለም የእርካታ አለም ነው፡፡ የእምነት ሰው ባለው ይረካል ለተጨማሪ ነገር ይዘረጋል፡፡ የጥርጥር ሰው ግን ባለውም ስለማይረካ ለተጨማሪ ነገር ሲዘረጋም በእምነት ስላይደለ አይሆንለትም፡፡

ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6

 1. የጥርጥር አለም የፉክክር አለም ነው

የእምነት አለም የትኩረት አለም ነው፡፡ የእምነት አለም በአላማ ላይ ብቻ የሚያተኩር በአካባቢ ስላለ ነገር የማይጨነቁበት ከአለም ከንቱ ውድድር ራስን የሚያገሉበት የእረፍት እና የትኩረት አለም ነው፡፡ በተቃራኒው የጥርጥር አለም አላስፈላጊ የፉክክር ጦርነት ውስጥ የሚገባ ፣ የራስ ህይወት ላይ ሳይሆን የሌላ ሰው ህይወት ላይ የሚተኩር ፣ የራስ ኑሮን ዝም ብሎ ከመኖር ይልቅ ከሌሎች ኑሮ ጋር በማስተያየት የሚቀናበትና የሚያስቀናበት ከንቱ የፉክክር አለም ነው፡፡

ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12

 1. የጥርጥር አለም የፍርሃት አለም ነው

የእምነት አለምን የሚመራው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ የእምነትን አለም የሚመራው ከእግዚአብሄር ቃል የሚገኘው ተስፋ ነው፡፡ የጥርጥርን አለም የሚመራው ደግሞ በጭንቀትና ፍርሃት ነው፡፡ የጥርጥርን አለም የሚያንቀሳቅሰው ፍርሃት ነው፡፡ ሰው ደግሞ ለፍርሃት ስላልተሰራ በፍርሃት የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ትክክል አይሆኑም፡፡

እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡7

 1. የጥርጥር አለም የመናወጥ አለም ነው

የእምነት አለም የመፅናት አለም ነው፡፡ የእምነት አለም ያለመናወጥ አለም ነው፡፡ የእምነት አለም የመረጋጋተ አለም ነው፡፡ የእምነት አለም ያለመቸኮል አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የመናወጥ አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የመቅበዝበዝ ያለመፅናት ያለማረፍ አለም ነው፡፡

ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ትንቢተ ኢሳይያስ 28፡16

 

መዝሙረ ዳዊት 46፡1-2

አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።

 1. የጥርጥር አለም ያለማረፍ የጥልና የክርክር አለም ነው

የእምነት አለም የእረፍትና የሰላም አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም ሰላመ የሌለበት የረብሻ አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የጥልና የክርክር አለም ነው፡፡ የእምነት አለም እግዚአብሄርን ተስፋ ስለሚያደርግ ከሰው ተስፋ አድርጎ አያዝንም፡፡ የጥርጥር አለም እግዚአብሄርን ተስፋ ስለማያደርግ ከሰው ለማስወጣት ይጣላል ይከራከራል፡፡

በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ የያዕቆብ መልእክት 4፡1-2

 1. የጥርጥር አለም የራስ ወዳድነትና የጥላቻ አለም አይደለም፡፡

የእምነት አለም የእግዚአብሄር ቃል አለምና የእግዚአብሄር መንፈስ አለም ስለሆነ የፍቅር አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም ግን በእግዚአብሄር ቃል ስለማይመራ የራስ ወዳድነትና የጥላቻ አለም ነው፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡6

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

የእምነት አለም ፅሁፌን ማንበብ ከፈለጉ https://www.facebook.com/notes/abiy-wakuma-dinsa/%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%88%88%E1%88%9D-%E1%8A%AD%E1%89%A5%E1%88%AD/10156812620939255/

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #ደስታ #ሰላም #እርካታ #ክብር #ገድል #ነፃነት #ሞገስ #ሃይል #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በሰው የሚታመን

conscious.jpg

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። ትንቢተ ኤርምያስ 17፡5-6

እግዚአብሄር የፈጠረን በእርሱ እንድንደገፍ ነው፡፡ በእርሱ ስንደገፍ እግዚአብሄር ደስ ያሰኘዋል፡፡

ነገር ግን በእግዚአብሄር መታመን ትተን በሰዎች መታመን ስንጀምር እግዚአብሄር ያዝናል፡፡ የተፈጠርነው በእግዚአብሄር እንድንደገፍ ስለሆነ በሰው ስንደገፍ አይሳካልንም፡፡

እንኳን ለሌላ ሰው መገደፊያ ሊሆን ይቅርና ሰው ራሱ በእግዚአብሄር ላይ መገደፍ አለበት፡፡ ሰው ለሌላ ለማንም ሰው መደፊያ ሊሆን አይችልም፡፡

ብዙ ሰዎች በእግዚአብሄር መታመን ይጀምራሉ፡፡ በእግዚአብሄር በመታመን እንድንጀምር ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሄር በመታመን እንድንጨርስ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡

በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ የማያነሳ ሰው ምስጉን ነው፡፡ በክፉ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ የሚያነሳ ሰው እርጉም ነው፡፡

በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። መጽሐፈ ምሳሌ 24፡10

አስቸጋሪ ጊዜ አልፎ ደግሞ መልካም ዘመን ሲመጣ እምነቱ ከእግዚአብሄር ላይ ያነሳውና በሰው ላየ ያደረገው ሰው ይፀፀታል፡፡ መልካም ጊዜ መጥቶ የማይለወጥ የሚመስለው ነገር ሲለወጥ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ እንስቶ ወደሰው ላይ ያደረገው ሰው ለሚያልፍ ነገር ምነው በእግዚአብሄር በታመንኩኝ ኖሮ ብሎ ይቆጫል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን እግዚአብሄርን በሰው የለወጠ ሰው የእምነትን ገድል ደስታ አያገኘውም፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን ከእግዚአብሄር ላይ እንስቶ በሰው ላይ ያደረገ ሰው ለማይረባ ነገር እግዚአብሄርን ስለለወጠው ያፍራል፡፡

በአስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ ከእግዚአብሄር ጋር የሙጥኝ ያለ ሰው በእግዚአብሄር በመታመኑና በማለፉ ብቻ እምነቱ ይጨምራል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እግዚአብሄርና ያመነና የጠበቀ ሰው እምነቱ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ጠርቶና ከብሮ ይወጣል፡፡ በአስቸጋሪ ጊዜ እምነቱን በሰው ያልለወጠው ሰው ደስታው ይበዛል፡፡

በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡6-7

እምነቱን ሲፈተን የወደቀ ሰው መልካም በመጣ ጊዜ አያይም፡፡ በሰው መደገፍን ያልናቀ ሰው በእግዚአብሄር በመደገፍ ያለውን ደስታ አያይም፡፡ በሰው በመደገፍ ክፉን ጊዜ ያሳለፈ ሰው ላነሰ ጥቅም ራሱን ስለሰጠ እውነተኛውን የእግዚአብሄርን በረከት አያየውም፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። ትንቢተ ኤርምያስ 17፡5-6

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ስጋለባሽ #መታመን #መደገፍ #ልብ #የሚመልስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ክንዱ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በእምነትም ያልሆነ ሁሉ

8ccb4ec4225b290726ae9be975220ff4.jpg

የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡23

ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄርን የምናከብረው ቃሉን በመጠበቅና በቃሉ በመኖር ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሄርን የምናከብረውና የምናስደስተው በቃሉ በመኖር ፍሬ በማፍራት ብቻ ነው፡፡

በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡7-8

ካለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6

እግዚአብሄርን የምናስደስተው ከቃሉ በሆነ እምነት ኑሮ ብቻ ነው፡፡

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17

ሰው የተፈጠረው ከቃሉ በሚገኝ እምነት እንዲኖር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእምነት ከእግዚአብሄር ጋር እንዲራመድ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእምነት በሚወስደው እርምጃ እግዚአብሄርን እንዲያስደስት ነው፡፡ ሰው በእምነት ሲኖር የተፈጠረበትን አላማ ግቡን ይመታል፡፡ ሰው ከእምነት ውጭ ሲኖር የተፈጠረበትን አላማ ይስተዋል፡፡ ከቃሉ በሚመጣ እምነት እንጂ በጥርጥር እግዚአብሄር አይከብርም፡፡ ጥርጥር የተፈጠሩበትን አላማን መሳት ነው፡፡ ጥርጥር አላማን መሳት ወይም ሃጢያት ነው፡፡

ስለዚህ ነው እምነት የሚገኝበትን የእግዚአብሄር ቃል ላይ የሙጥኝ ማለት ያለብንና በእምነት እርምጃን መውሰድ ያለብን፡፡

የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡23

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ያለእምነት #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አላማ #መሳት #ሃጢያት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የእምነት ማጣት አስራ አንዱ ምልክቶች

conscious.jpgየእግዚአብሄር መንግስት የመንፈስ መንግስት ነው፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር የምናደርገው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም፡፡ ለክርስትና ህይወት እምነት ወሳኝ ነው፡፡

እግዚአብሄር የሚሰራው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠቀመው እምነት ያለውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር ለመስራት እምነት ያለውን ሰው ይፈልጋል፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን  ማስደሰት አይቻለም፡፡

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6

ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ጊዜ ምንም ታላቅ ሃይል ቢኖረውም ሰዎችን ለመርዳት ቢፈልግም እምነት ላልነበራቸው ሰዎች ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡

በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም። ማቴዎስ 13፡58

እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ ስለ ምን ትፈራላችሁ? ማቴዎስ 8:26

ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ማቴዎስ 17፡17

ሰው እግዚአብሄርን አላምንም ብሎ ላይናገር ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ስራው ይናገራል፡፡ እምነት ያለው ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች እንዳሉ ሁሉ የማያምን ሰው የሚያሳያቸው ምልከቶች አሉ፡፡

 1. የማያምን ሰው ጠማማ ነው

የማያምን ሰው ቅን ሊሆን አይችልም፡፡ የማያምን ሰው የዋህ ሊሆን አይችልም፡፡ የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን መንገድ ስለማይከተል የራሱን የጠማማነትን መንገድ ይከተላል፡፡

ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ማቴዎስ 17፡17

 1. የማያምን ሰው ኩራተኛ ሰው ነው

የሚያምን ሰው የሚታወቀው በትህትናው ሲሆን የማያምን ሰው የሚታወቀው በትእቢቱ ነው፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር ሳይሆን በራሱ ይተማመናል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ላይ ይደገፋል፡፡

እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2፡4

 1. የማያምን ሰው ፈሪ ነው

የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይደፍራል የማያምን ሰው ግን ፍርሃት አለበት፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ልቡ ስለሚጠበቅ ያርፋል፡፡ የማያምን ሰው ግን ልቡ በምንም ላይ ስለማያርፍ ይፈራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያደርገው ከፍቅር ድፍረት ሳይሆን ከፍርሃት ነው፡፡ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ ስለ ምን ትፈራላችሁ? ማቴዎስ 8:26

 1. የማያምን ሰው ፍቅር ይጎድለዋል

የሚያምን ሰው ፍቅር የሆነውን እግዚአብሄርን ስለሚያምን በፍቅር ለመኖር አይፈራም፡፡ የማምን ሰው ግን የእግዚአብሄርን ፍቅር ስለማያምን እና ስለማይቀበል ራሱም በፍቅር ለመኖር ራሱን አይሰጥም፡፡ የማምን ሰው ከፍቅር ይልቅ ሌላ የራሱን መንገድ ይፈልጋል፡፡

እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13

 1. የማያምን ሰው በምድር ጥበብ ይመላለሳል

ከእግዚአብሄር የሆነው ንፅህ ጥበብ የሚገኘው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ይህን ንፁህ ጥበብ በምድራዊ ተንኮል ይለውጠዋል፡፡

ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡14-16

 1. የማያምን ሰው ይቸኩላል

የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ጊዜ ይተማመናል፡፡ የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን እርምጃ ይታገሳል፡፡ የማያምን ሰው ግን የእግዚአብሄርን ጊዜ ስለማያምነው ይቸኩላል፡፡

በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11

የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።ምሳሌ 28፡20

 1. የማያምን ሰው ከሰው ጋር ይጣላል፡፡

የማያምን ሰው በረከቱን የያዘው ሰው ስለሚመስለው ከሰው ጋር ይጣላል፡፡ የማያምን ሰው ከሰው ስለሚጠብቅ በሰው ይሰናከላል፡፡ የመያምን ሰው መንፈሳዊውን አለም በእምነት ስለማያይ የጦር እቃው ስጋዊ ብቻ ነው፡፡ የሚያምን ሰው ግን ከእግዚአብሄር ስለሚጠብቅ በሰው አይሰናከልም፡፡ የሚያምን ሰው ከሰው ባሻገር መንፈሳዊውን አለም ስለሚያይ የጦር መሳሪያው ስጋዊ አይደለም፡፡

በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1-3

በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡3-4

 1. የማያምን ሰው በጥበቡ በሃይሉና በብልጥግናው ይመካል

የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይመካል፡፡ የማያምን ሰው ግን የእግዚአብሄር ሃብት የእኔ ሃብት ነው ስለማይል መሰብሰብ ማከማቸት ይፈልጋል፡፡ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም ስለሚል ማግበስበስ አያስፈልገውም፡፡ የማያምን ሰው ግን እረኛውን ስለማያምን እረኛ የሚያደርገው ጥበቡን ሃይሉንና ባለጠግነቱን ነው፡፡ የሚያምን ሰው የነገሮች ሁሉ ቁልፍ እግዚአብሄር ጋር እንጂ ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ጋር እንዳይደለ ያውቃል፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24

 1. የማያምን ሰው ይጨነቃል

የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅን ሲፈልግ እግዚአብሄር በምድር የሚያስፈልገው እንደሚያሟላለት ስለሚያምን አይጨነቅም፡፡ እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ግን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በመጨነቅ እግዚአብሄር ይጨመርላችኋል ያለውን በመፈልግ ህይወቱን ያባክናል፡፡

እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33

 1. የማያምን ሰው ያጉረመርማል

የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር መልካምነት ስለሚተማመን ሁልጊዜ በእግዚአብሄር ደስ ይለዋል፡፡ የማያምን ሰው ደስታው በሁኔታዎች ብቻ ስለሆነ ያጉረመርማል፡፡ የሚያምን ሰው እግዚአብሄርን መልካምነት ስለሚያይ በእግዚአብሄር ላይ ጥያቄ የለውም፡፡

ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10

 1. የማያምን ሰው ይመኛል

የሚያምን ሰው ምንም እንዳልጎደለው ራሱን ያማጥናል፡፡ የሚያምን ሰው ጉድለቱን በሚሸፍን ድካምን በሚሞላ የእግዚአብሄር ፀጋ ስለሚተማመን አይመኝም፡፡ የማያምን ሰው ግን ሁሌ እግዚአብሄር ያልሰጠውን ነገር ይመኛል፡፡ የሚያምን ሰው ራሱን በሁኔታዎች ሁሉ ራሱን ያማጥናል፡፡

ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11-13

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጭንቀት #ፍርሃት #ፍቅር #ተንኮል #ጠማማነት #ኩራት #ቅን #እምነት #ተንኮል #ምኞት #ሰላም #ኢየሱስ #ጌታ #ሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

እምነትና ጥርጥር

fear vs faith 22.jpgኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡22-23

ለእግዚአብሄር አንድን ነገር ማድረግ ከፈለግን በእምነት መሆን አለበት፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምንገናኘው በእምነት ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የምንቀበለው በእምነት ነው፡፡ ካለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡

ጥርጥር ደግሞ እግዚአብሄርን አለማመን ነው፡፡ ጥርጥር የእምነት ተቃራኒ ነው፡፡ ጥርጥር የእምነት ጠላት ነው፡፡ ጥርጥር እጃችንን ዘርግተን አንድን ነገር ከእግዚአብሄር በእምነት እንዳንቀበል እጃችንን እንድንሰበስብ ይፈታተነናል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ሲያምን የእምነት ጠላት የሆነውን ጥርጥርን መዋጋት አለበት፡፡

እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ሰው አንድን ነገር ሲያምን ያመነው ነገር እስኪሆን ደርስ በእምነቱ ፀንቶ መጠበቅ አለበት፡፡

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17

የሚታየው ነገር ሁሉ የሚመጣው ከማይታየው አለም ነው፡፡ ሰው በማይታየው አለም ውስጥ በእምነት ያየው ነገር ወደሚታየው ግኡዙ አለም እስኪመጣ መታገስ አለበት፡፡

እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ዕብራውያን 11፡1፣3

ሰው አንድን ነገር ሲያምን ያመነው ነገር ወደ ገሃዱ አለም አሰኪገለጥ ድረስ በጥርጥር ይፈተናል፡፡ ሰው ያመነው ነገር ትክክል እንዳይደለና እንዲተወው ጥርጥር ይፈትነዋል፡፡

እግዚአብሄር ሰውን የሚከፍለው በእምነቱ ብቻ ነው፡፡ የሚጠራጠር ሰው ከእግዚአብሄር አይቀበለም፡፡

ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8

መጠራጠር የለብንም ማለት ግን የጥርጥር ሃሳብ ወደ አእመሮዋችን አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ሰው ያመነው ነገር እንደማይሆን ሰይጣን የጥርጥርን ሃሳብ ይልካል፡፡ ሰው የጥርጥርን ሃሳብ ከተቃወመው በእምነቱ ከእግዚአብሄር ብድራትን ይቀበላል፡፡ ሰው ግን የጥርጥርን ሃሳብ ከተቀበለው እምነቱ ያለፍሬ ይቀራል፡፡

ሰው መጀመሪያ ማመኑ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው ሲያምን ጥርጥርን በሚገባ መቃወም አለበት፡፡

ጴጥሮስ የጌታን ቃል እምኖ በውሃ ላይ መራመድ ጀምሮ ነበር ፡፡ ነገር ግን ጥርጥር በውሃ ላይ መራመድ የጀመረውን ጴጥሮስን አሰመጠው፡፡ ጴጥሮስ አይኑን ና ከሚለው ከኢየሱስ ቃል ላይ እንስቶ ወደወጀቡ ላይ ሲያደርግ መስመጥ ጀመረ፡፡

እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ማቴዎስ 14፡29-30

ጥርጥርን የምንዋጋው የእግዚአብሄርን ቃል በቀጣይነት በመስማት በማሰላሰልና በመናገር ነው፡፡ ጥርጥርን የምንዋጋው ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ነገር ባለመስማትና ባለመከተል ነው፡፡

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17

ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡22-23

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

%d bloggers like this: