Category Archives: worry

ለጭንቀት ጥያቄ አምስቱ የተሳሳቱ መልሶች

Worry-2 (1).jpgሰይጣን ሰውን የሚያጠቃው በጭንቀት ነው፡፡ ሰይጣን ሃሳብን በመላክ ሰውን ያስጨንቃል፡፡ ሰይጣን ወደ ሰው አእምሮ ሃሳብን በመላክ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡

ሰይጣን እንደዚሁ አይነት ንግግር ጀምሮ ነው ሄዋንን የጣላት፡፡ ሰይጣን ሃሳብን ያስገባል፡፡ ሰይጣን ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡

እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ዘፍጥረት 3፡1

ሰይጣን ኢየሱስንም ሊጥለው የነበረው በተመሳይ መንገድ ነበር፡፡ ሰይጣን ጥያቄን ይጠይቃል፡፡ ለጥያቄው መልስ ከሌለን ሰይጣን ያስጨነቀናል፡፡ ለጥያቄው የተሳሳተ መልስ ከሰጠን እንጨነቃለን እንደክማለን ሰላማዊ ህይወታችን መኖር ያቅተናል፡፡

ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴዎስ 4፡3

አሁንም ሰይጣን የሚዋጋን በዚሁ መልክ ነው፡፡ ሃሳብን ይልካል ፡፡ ሰይጣን ቅን ያልሆኑ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡ መልስ ካላገኘን ያስጨንቀለናል፡፡ ትክክለፃውን መልስ ካልሰጠን ያዋርደነባል፡፡

በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3

ሰይጣን ምንም ይበል ምንም ሰይጣን የተለያየ ርእስ ያምጣ የሰይጣን የጭንቀት ጥያቄ ሲጨመቅ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡

 1. አንተ አታውቅም

ሰይጣን አንተ አታውቅም የሚል እንደምታ ሊሰጠን ሲሞክር እኔ አውቃልሁ ብለን ከተንፈራገጥን ይጥለናል፡፡ አውቃለሁ ብለን ስላልተገለጠልን ወደፊት ማስረዳት ከሞከርን እንስታለን፡፡ ወይም ያልተገለጠልንን ወደፊት እኛ ራሳችን ፈልገን ለመድረስና ለመረዳትና ለማስረዳት ከሞከርን እንሳሳታለን፡፡ ሰይጣን አታውቅም ሲለን ራሳችንን ትሁት ማድረግ አለብን፡፡ የማናውቀውን አናውቅም ማለት ትህትና ነው፡፡ አዎ ስለ ወደፊቴ ሁሉንም ዝርዝር አላውቅም ማወቅም አያስፈልገኝም መልስ ነው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ የሚመራኝ አባት አለኝ ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ሁሉን የሚያውቀው ይጠነቀቅልኛል ይመራኛል፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

 1. አንተ አትችልም

ሌላው ሰይጣን የሚልከው የጭንቀት ጥያቄ ሲጨመቅ የምናገኘው ሌላው መልክት አንተ አትችልም የሚል ነው፡፡ እችላለሁ ብለን ከተከራከርነው የማንችልበትን ብዙ ተፈጥሮአዊ ምክኒያቶች ደርድሮ ያዳክመናል፡፡ አትችልም ለሚለው መልሱ አዎ በራሴ አልችልም የሚል ነው፡፡ አዎ በራሴ ጉልበት የለኝም ነገር ግን አንተን በመስቀል ላይ ድል የነሳህ ኢየሱስ ጉልበቴ ነው ማለት ይጠበቅብናል፡፡

ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡13

 1. ለእግዚአብሄር እየኖርክ አይደለም

ሌላው ከተቀበልነው ጭንቀት ውስጥ የሚያስገነባን ሰይጣን የሚልከው ሃሳብ ለጌታ እየኖርክ አይደለም የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ እግዚአብሄር በክርስቶስ ወዶኛል፡፡ ምንም ሳልሆነ ፣ ምንም ሳላደርግለትና ምንም ሳይኖረኝ ጠላት ሳለሁ ወዶኛል፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ደስ ተሰኝቶብኛል፡፡ እግዚአብሄር የማይፈልገው ነገር ካለ ደግሞ ይነግረኛል፡፡ አንተ የምን ቤት ነህ፡፡ አጥፍቼ ከሆነ ከእርሱ ጋር እጨርሳለሁ ፡፡ ይህ የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በቤተሰብ ጉዳይ ጣልቃ አትግባ ማለት ይጠበቅብናል፡፡

 1. ይህ እና ያ የለህም

ሌላው ሰይጣንን የሚልከውን ሃሳብ እህ ብለን ከሰማነው ሊያሳምነን የሚሞከረው የሚያስፈልግህ የለህም የሚል ነው፡፡ ይህ እና ይህ ላይኖረኝ ይችላል፡፡ የሚያስፈክልገኝ ግን አለኝ፡፡ ይህ እና ይህ አሁን ላይኖረኝ ይችላል በሚያስፈልገኝ ሰአት ግን ይኖረኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የሌላኝ ግን የማያስፈልገኝነው፡፡ እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም፡፡ የሌለኝ ነገር ካለ አያስፈልገኝም ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 23፡1

 1. ይህ ጉድለት አለብህ

አዎ ይህ ጉድለት አለብኝ፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሄ ፀጋ የተዘጋጀው፡፡ የማልችለውን ሊያስችል ጉድለቴን ሊሞላ ድካሜን ሊያበረታ ክፍተቴን ሊሸፍን የሚያስችል የእግዚአብሄር ፀጋ ተሰጥቶኛል፡፡

ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡4-6

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ማረፍ #ፀጋ #ቅንነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Advertisements

ለነገ (ለሚመጣው አመት) አትጨነቁ

worry not.jpgነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34

በጌታ ለመኖርና ኢየሱስን ለመከተል እያንዳንዱ ቀን ተግዳሮት አለው፡፡ እያንዳንዱ ቀን የሚመጣው ከተወሰነ ተግዳሮት ጋር ነው፡፡ ይብዛም ይነስም ተግዳሮት ይዞ የማይመጣ ቀን የለም፡፡ ሁሉም ቀን የሚመጣው የራሱ የተግዳሮት ድርሻን ይዞ ነው፡፡

ቀን ይዞ ለሚመጣው ተግዳሮት የሚመጥን ፀጋ በቀን ውስጥ ይለቀቃል፡፡ ለእያንዳንዱ ቀን ተግዳሮት የሚበቃ የእግዚአብሄር ፀጋ በእያንዳንዱ ቀን ውስጥ አለ፡፡ እያንዳንዱ ቀን የራሱ ድርሻ ተግዳሮትና ለዚያ ተግዳሮት የሚበቃ የራሱ ድርሻ የሚያስችል ሃይል አለው፡፡

በነገ ውስጥ የሚለቀቀውን ፀጋ ዛሬ ማየትና መለማመድ አንችልም፡፡ ወይም ዛሬ ላይ ቆመን ነገር መኖር ወይም ማስተካካል ወይም ደህና ማድረግ አንችልም፡፡ በዛሬ የሚለቀቀው የሚያስችል የእግዚአብሄር ሃይልን የምንለማመደው በዛሬ ውስጥ ያለውን ተግዳሮት ለማለፍ ብቻ ነው፡፡

ሰው የነገን ተግዳሮት በዛሬ ፀጋ ሊጋፈጠው በመሞከር ይጨነቃል፡፡ የዛሬን ተግዳሮት ብቻ ለመኖር ከነገ ተግዳሮት ጋር ላለመቀላቀል  መረጋጋት ይጠይቃል፡፡ የዛሬን ተግዳሮት በዛሬ ፀጋ ተወጣውና ለጥ በል፡፡ ስለነገ አትጨነቅ፡፡ ስለነገ ባልተለቀቀ ፀጋ ውስጥ ሆነህ ስነገ መጨነቅ ከንቱ ነው፡፡  ስለነገ ለማሰብ ትክክለኛው ጊዜ ነገ ነው፡፡ ነገ ላይ ተግዳሮቱም ይታወቃል ፀጋውም ይገለጣል፡፡ ነገ ላይ ስለነገ ማሰብ ውጤታማ እቅድ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ስለነገ መጨነቅ ብክነት ነው፡፡

ነገ የሚመጣው በሬሱ ጊዜ ነው፡፡ ነገ የሚመጣው ከራሱ ተግዳሮትና ከራሱ ፀጋ ጋር ነው፡፡ ነገ ሲመጣ ለነገ የሚሆን እምነት አብሮት ይመጣል፡፡ ነገ ሲሆን ለነገ ተግዳሮት የሚሆን ፀጋ ይለቀቃል፡፡ ለዚያም ነው ብዙ ጊዜ የተጨነቅንበት ነገር ጊዜው ሲደርስ ሸክሙ የሚበነው፡፡

እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ገላትያ 3፡25

ስለነገ ማድረግ የምትችለው አንድ ነገር የሚያስጨንቅህን በጌታ ላይ መጣል ብቻ ነው፡፡ ስለነገ የሚያስጨንቅህን በእርሱ በእግዚአብሄር ላይ ከመጣል ውጪ ውጤታማ ነገር የለም፡፡ አባታችን እግዚአብሄር አንደሆነ እንደ እኛ የታደለና መጨነቅ የሌለበት ሰው የለም፡፡

ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡34

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ነገ #ማረፍ #ጣሉ #ክፋት #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰው ልዩ ምልክት

o-TRUST-facebook.jpgካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መስራት አይቻልም፡፡ እግዚአብሄር እምነትን ከእኛ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር ቃሉን እንድናምን ይፈልጋል፡፡ ከደህንነት ቀጥሎ መሰረታዊው እምነት ደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልገን ሁሉ እንደሚያውቅና እንደሚጨምር ማመን ነው፡፡

ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33

ሰው ስለሚበላው ስለሚጠጣውና ስለሚለብሰው ካመነ በነፃነት ለእግዚአብሔር መኖር ይችላል፡፡ ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካመነ በሁለንተናው እግዚአብሄርን ለማገልገል ይለቀቃል፡፡

እምነት የልብ ስለሆነ አንድ ሰው ማመኑና አለማመኑን ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰውም ምልክቶች ከእግዚአብሄር ቃል መመልከት እንችላለን፡፡

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይጨነቅም፡፡

ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ጉልበቱን የእግዚአብሄርን ነገር በመፈለግ ላይ እንጂ በጭንቀት ላይ አያፈስም፡፡ የሚያምን ሰው የጭንቀትን ፍሬ ቢስነት ይረዳል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን በመፈለግ ላይ ሙሉ በሙሉ ከመጠመዱ የተነሳ ለጭንቀት የሚተርፍ ትርፍ ጊዜና ጉልበት የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ጭንቀት ጉልበቱን እንዲበላ አይደፈቅድለትም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የማያምን ሰው የእግዚአብሄርን ስራ በሚሰራበት ጊዜና ጉልበቱ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱን በትክክለኛው በእግዚአብሄር መንግስት ላይ ማፍሰስን አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው  ምንም ነገር በትክክል መስራት ሳይችል በጭንቀት ብቻ ካለፍሬ ይቀራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያስጨንቀው ነገር ጌታ እንዲሆንበት ይፈቅድለታል፡፡ ስለመሰረታዊ ግፍላጎቱ የማያምን ሰው ይጨነቃል በጭንቀትም ውድ ህይወቱን ያባክናል፡፡

ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ማቴዎስ 6፡25

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይፀልያል፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ይፀልያል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ይፀልያል በእምነትም ያመሰግናል፡፡ አማኝ የሚያስጨንቀውን ይጥላል በእግዚአብሄር ላይ መልሶም አይወስደውም፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይተማመናል ያርፋል፡፡

የማያምን ሰው በመጨነቁ ትልቅ ስራ እንደሰራ ያስባል፡፡ የማያምን ሰው መፀለይ በሚገባው ጊዜ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱንና ጊዜውን በጭንቀት ላይ ያሳልፋል፡፡ የማያምን ሰው ቢፀልይም  ጭንቀቱን መልሶ ይወስደዋል፡፡ የማያመን ሰው መጨነቁ የህይወት አንዱ ስራ ይመስለዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው ሸክሙን  በእግዚአብሄር ላይ እንዴት እንደሚጥለው አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር እንዴት እንሚያርፍ አያውቅም፡፡

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴዎስ 11፡28

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ልቡን ይሰማል፡፡

እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሞትክ አለቀልህ ጠፋህ የሚለውን የውጭውንና የአእምሮውን ድምፅ ሳይሆን የልቡን ድምፅ በዝምታ ይሰማል፡፡

በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው በአእምሮ የሚመጣውን ሃሳብ ሁሉ ያስተናግዳል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ይታወካል ሰላም የለውም፡፡

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃነስ 14፡27

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይወራረዳል፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይህን ካላገኘሁ አይሆንም የሚለው ፍላጎት የለም፡፡ የሚያምነ ሰው በምንም ነገር ውስጥ እግዚአብሄር እንደሚያስችለው ያምናል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በከፍታም በዝቅታም በምንም ነገር ውስጥ በክርስቶስ እንደሚበረታ ያውቃል፡፡

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-23

ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሰው በእግዚአብሄር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ያውቃል፡፡

እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው የሌለኝ ነገር የማያስፈልገኝ ነው ብሎ በእግዚአብሄር እረኝነትና  አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ይታመናል፡፡

እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡10-11

ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር በሰጠው ነገር ብቻ መኖር እንደሚችል ያውቃል፡፡ ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር የሰጠው ነገር ለአላማው በቂ እንደሆነ ያምናል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር እቅርቦት ላይ ምንም ትችት የለውም፡፡

ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማየታመን ሰው ገንዘቡ ተቆጥሮ እሰካልገባ አያምንም፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሚያየውን ብቻ ያምናል፡፡

ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡7-8

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከአለም ፉክክር ራሱ ያገላል፡፡

እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው በአለም ካለ ክፉ የፉክክር መንፈስ በፈቃዱ ራሱን ያገላል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው ከሌላው ጋር ተፎካክሮም ለእግዚአብሄር ኖሮም እንደማይችል ይረዳል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው የፉክክርን ክፋትና አታላይነት ይረዳል፡፡

ስለፍላጎቱ ጌታን የማያምን ግን ሰው የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ይጥራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው በሰው ፊት ሙሉ መስሎ ለመታየትና ላለመበለጥ ይዳክራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሰውን ደረጃ ለማሟላት ህይወቱን ያባክናል፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ከጭንቀት አርፎ እግዚአብሄርን ማገልገል ያቅተዋል፡፡

በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፡22

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው የተረጋጋ ህይወት አለው፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከማረፍ ውጭ ሲቅበዘበዝ አይታይም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይናወጥም፡፡ ጌታን የሚያምን ሰው ለጌታ ሙሉ ለሙሉ ለመኖር ነፃ ነው፡፡ በጌታ የሚታመን ሰው የረካ በመሆኑ ሌላውን ለማርካት ይሮጣል፡፡

የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25

ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ምሳሌ 17፡22

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ ሰላም ያለው ሰው ለሌላው ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍለጎቱ የረካ ሰው ትኩረቱ አንድ ስለሆነ ሰላሙን ሊወስድ የሚችል ምንም ሃይል አይኖርም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ያልረካ ሰው ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ለማድረግ ስለሚሞክር ሁለቱንም ማድረግ ያቅተዋል፡፡ ስለፍላጎቱ በጌታ ያልታመነ ሰው ሌሎችን ስለማገልገልና ሌሎችን ስለመጥቀም ሲሰማ ቁጣ ቁጣ ይለዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው “ምስኪን እኔ” አስተሳብ “ለእኔስ ማን አለኝ?” የሚል ምስኪንነት አስተሳሰብ አለው፡፡

ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ኢሳያስ 28፡16

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያመን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው አይጣላም አይጨቃጨቅም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው የእርሱን ነገር ከሰው ጋር አያያይዘውም፡፡

በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?ያዕቆብ 4፡1

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡

ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያመን ሰው ሰውን ለመጥቀም ሳይሆን በሰው ለመጠቀም ያስባል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያንምን ሰው ከዚህ የምጠቀመው ምንድነው ብሎ ስለግል ጥቅሙ ሁሌ ያስባል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ የማይታመን ሰው የእግዚአብሄርን አቅርቦት ስለማያይ አገልግሎትን የጥቅም ማግኛ መንገድ ያደርገዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን የፀጋ ስጦታ በጥቅም ይቸረችረዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን ነገር ሁሉ ወደግል ስሙ ያዞረዋል፡፡ ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው በግል በማይጠቀምበት ምንም ነገር ውስጥ የመሳተፍ ሃሞቱ የለውም፡፡

ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ማቴዎስ 10፡8

 1. ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚታመን ሰው ነውረኛ ረብን ይጠላል፡፡

ስለፍላጎቱ በአግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክቡርና ነውረኛን ጥቅምን ይለያል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው በፊቱ የመጣውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡ ስለፍላጎቱ የሚታመን ሰው ኩሩ ነው፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው ለቀቅ ብሎ ይኖራል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክብር ከእግዚአብሄር ብቻ እንደሚመጣ ይረዳል፡፡

ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7

ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9

ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው የጥቅም ደረጃ የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የማይታመን ሰው የህይወት መርህ የለውም ወደተመቸው ይገለባበጣል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው ጥቅም ይሁን እንጂ የሚንቀውና እንቢ የሚለው ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው እግዚአብሄር በክብር እንደሚባረክ አይረዳም፡፡

አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19

 

የክርስትናም የመጨረሻ ደረጃና የስኬት ጣራ ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡

 

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እግዚአብሔር የሚያደርግልኝ አያሳስበኝም

channel-partner-puzzle.jpgክርስትና የእግዚአብሔርና የህዝቡ የቃል ኪዳን ግንኙነት ነው፡፡ በማንኛውም ቃል ኪዳን እያንዳንዱ ወገን የሚወጣው ድርሻ እንዳለ ሁሉ በክርስትናም እኛ እንደ ህዝብ የምንወጣው ድርሻ አለ እግዚአብሔር ደግሞ እንደ አምላክ የሚወጣው የራሱ ድርሻ አለው፡፡ እኛ እንደ አባት የማናደርገው የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ደርሻ አለ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ እንደ ልጅ የማያደርገው እኛ ብቻ የምናደርገው ድርሻ ደግሞ አለ፡፡

ለምሳሌ ወታደርና ገበሬ ቃልኪዳን ቢገቡ ወታደር የገበሬውን ደህንነት የመጠበቅ ሙሉ ሃላፊነት ይወስዳል ገበሬው ደግሞ ወታደሩን የመመገብ ሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ቃልኪዳኑ እንዲሰራና ሁለቱም የቃልኪዳኑ ሙሉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ገበሬው በእርሻው ላይ ወታደሩ ደግሞ በጥበቃው ላይ ብቻ ማተኮር አለባቸው፡፡

ነገር ግን ወታደሩ የጥበቃ ስራውን ትቶ በየጊዜው እየመጣ ገበሬው በትክክል ያርስ ይሆን? ብሎ ቢጨነቅና ስለሌላው ወገን ድርሻ በመጨነቅ የራሱን ድርሻ የጥበቃውን ስራ ቢያጎድል ሃላፊነቱን አይወጣም፡፡ ገበሬውም ይህ ወታደር በትክክል ይጠብቀኝ ይሆን ብሎ በማይመለከተው በጥበቃ ስራ ላይ ቢጨነቅና ጊዜውን በጭንቀት ቢያጠፋ የቃልኪዳን ሃላፊነቱን መወጣት አይችልም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ  ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ቃልኪዳን የእኛ ድርሻ አለ የእግዚአብሔር ደግሞ ድርሻ አለ፡፡ እኛ ማተኮር ያለብን በእኛና በእኛ ድርሻ ላይ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለምንበላው ስለምንጠጣው ስለምንለብሰው መጨነቅ በፍፁም የእኛ ስራ አይደለም፡፡

እግዚአብሔር አቢይን በትክክል ይይዘው ይሆን ? የሚያስፈልገውን ያሟላለት ይሆን? እግዚአብሔር አቢይን መንከባከቡን ያውቅበት ይሆን? እግዚአብሔር ድርሻውን በትክክል ይወጣ ይሆን? እያልኩ ብንጨነቅ ህይወቴን አባክነዋለሁ፡፡

እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ቃል በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ የእኛን እና የራሱን ድርሻ በሚገባ ለያይቶ አስቀምጦታል፡፡ እንዲያውም የእርሱን ድርሻ ለመስራት እንዳንሞክር ከሞከርን እንዳማይሳካልን በከንቱም እንደምንደክም አስረድቶናል፡፡ እኛ ግን በራሳችን ድርሻ ላይ ካተኮርን የቃልኪዳን አጋራችን እግዚአብሔር የራሱን ድርሻ በሚገባ እንደሚወጣ አስረድቶናል፡፡

እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33

የቃልኪዳን ድርሻዬን ስላወቅኩ ፣ የምችለውንና የማልችለውን ስለተረዳሁ ፣ ድንበሬምን ስላወቅኩ በህይወቴ የሚያሳስበኝ እኔ ለእግዚአብሔር የማደርግለት ነገር ብቻ ነው፡፡

ለእግዚአብሔር መንግስት የማደርገው ነገር ያሳስበኛል፡፡ የእግዚአብሔርን ፅድቁንና መንግስቱን እንዴት እንደምፈልግ አስባለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክል ሆኜ የመገኘትን ሃላፊነቴን ለመወጣት ቃሉን አሰላስላለሁ፡፡ ለመንግስቱ በጎነት እንዴት እንደምሰራ አወጣለሁ አወርዳለሁ፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት የማደርገው አስተዋፅኦ ያሳስበኛል፡፡

የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28

ምኔን ልስጠው ? እንዴት ልኑርለት? እንዴት ላስብ ? እንዴት ልናገር? እንዴት ልኑርለት የሚለው ያሳስበኛል፡፡

ከራሴ ድርሻ አልፌ እግዚአብሔር ለእኔ ስለሚያደርግልኝ ነገር ለማሰብ የሚተርፍ አቅምም ጉልበትም የለኝም፡፡ እግዚአብሔር ለእኔ የሚያደርግለኝ ነገር አያሳስበኝም፡፡ እግዚአብሔር ድርሻውን ይወጣል፡፡ እግዚአብሔር ልጁን እንዴት እንዲይዘው ያውቅበታል፡፡ እግዚአብሔርን ማንንም አያማክረውም፡፡ እግዚአብሔ ልጁንም እንዴት እንዲመራው ያውቃል፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11

እኔ ደርሼ ለእግዚአብሔር ልጨነቅለት አይገባም፡፡ እግዚአብሔር እኔን የመንከባከብ ሃላፊነቱን ተወጥቶ ይሆን ብዬ ልስጋ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር አያያዙን አውቆበት ይሆን ብዬ ልሰልልው አልሞክርም፡፡ እግዚአብሔርን አያያዙን እንዲረዳ ላግዘው አልሞክርም፡፡

ሃላፊነቴን ለመወጣት እተጋለሁ እርሱ ስለእናንተ ያስባልበና የሚለውን ቃል አምኜ እርፍ እላለሁ፡፡ የእኔ ድርሻ የሚያስጨንቀኝን በእርሱ ላይ መጣል ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ ስለእኔ ማሰብ ማቀድና መፈፀም ነው፡፡

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

የእኔ ድርሻ መፀለይ እና ማስታወቅ ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ ለህይወቴ ማቀድ የፈጠረኝን አላማ በህይወቴ ማከናወን ነው፡፡

ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6

የእኔ ድርሻ የእርሱ አላማ በህይወቴ ላይ ማድረግ ነው፡፡ የእርሱ ድርሻ የሰራሁትን ነገር ወደፍፃሜ ማምጣትና ፍሬያማ ማድረግ ነው፡፡

እኔም መልሼ፦። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው። ነህምያ 2፡20

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ማረፍ #ፀጋ #መንግስት #ቃልኪዳን #ድርሻ #ሃላፊነት #ፅድቅ #ፀሎት #ምልጃ #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

%d bloggers like this: