Category Archives: Authority

ለእግዚአብሄር ፈንታ ስጡ እንጂ

jones-natasha-111123-8col.jpgእግዚአብሄርን የመራንን ነገሮች ስናደርግ አንዳንዴ ሰዎች ላይረዱን ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው ሰዎች ካልተረዱን ደግሞ በራሳችን ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ አብረናቸው የእግዚአብሄርን ስራ እንድንሰራ የተሰጡን ሰዎች ካልተረዱን ለእግዚአብሄር መልቀቅ አለብን፡፡ የራሳችንን ድርሻ ከተወጣን በኋላ ለእግዚአብሄር አሰራር ደግሞ ጊዜና ስፍራ መስጠት አለብን፡፡ ለእግዚአብሄር አንድ እያንዳንዱ ሰው ነገር ለማድረግ ራሱ አጥብቆ መረዳት አለብት፡፡

ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ ሮሜ 4፡20

እግዚአብሄርም ሰዎች ያላወቁትንና ያልተረዱትን ነገር እንዲያደርጉ አይጠብቅም፡፡ እኛን እግዚአብሄር ተናገረን ብለን ሰዎችን ማስገደድ አንችልም፡፡ እኛ ነፃ ፈቃድ እንዳለን ሁሉ ሌሎች ሰዎችም አይ አይደለም ለማለት ፈቃድ እንዳላቸው ማወቅና መቀበል ይገባናል፡፡ ከእግዚአብሄር የሆነውን ለሚመለከታቸው ሰዎች ከተናገርን በኋላ ራሳችን ለማስፈፀም መሞከር በእግዚአብሄር ሳይሆን በራስ መተማመን ነው፡፡

ድርሻችንን ከተወጣን በኋላ ማረፍና ለእኛ እንደተናገረን እግዚአብሄር ራሱ እንዲናገራቸው ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ እኛን እንደተናገረን ራሱ እግዚአብሄር እንዲናገራቸው እድሉን ካልሰጠን ሰዎች የተናገርነው ነገር የእኛን የራስ ወዳድነት ፍላጎት አድርገው ሊረዱት ይችላሉ፡፡ ይዘን የመጣነው ሃሳብ የእኛ የግላችን ሃሳብ እንዳልሆነና የሃሳቡ ዋናው ባለቤት እግዚአብሄር እንደሆነ ለማሳየት እኛ ዝም ማለት ይገባናል፡፡ እኛ ዝም ካላልንና ሰዎች የእግዚአብሄርን ድምፅ አጥርተው ካልሰሙ የእግዚአብሄርና የእኛን ድምፅ ይቀላቀልባቸዋል፡፡ ስለአንድ ነገር የእግዚአብሄርን ድምፅ ለራሳቸው መስማት የሚችሉት እኛ ዝም ስንልና ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡

ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19

እግዚአብሄር ከግርግር ባሻገር ለራሳቸው የሚናገራቸው ስንታገስና ጊዜ ስንሰጥ ነው፡፡ ሰዎች የራሳችንን ጥቅም እንደምናሳድንድ ካሰቡ ስሜታቸው ይረበሻል፡፡ በዚህም ሁኔታ ጌታን በትክክል መስማት ይሳናቸዋል፡፡ እኛ ዝም በምንልበት ጊዜ ግን እግዚአብሄር ራሱ በዝምታ እንዲናገራቸው ምቹ ሁኔታን እንፈጥርላቸዋለን፡፡

ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ሆሴዕ 2፡16

በአለም ላይ በአማኞች ብዛት ታላቁን ቤተክርስትያን የመሩት መጋቢ ዲቪድ ዮንጊ ቾ በኮሪያ የኢኮኖሚ ውጥረት ጊዜ እግዚአብሄር 10 ሺህ ሰው የሚይዝ ቤተክርትስትያን እንዲሰሩ እንደተናገራቸው ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚያም እያፀለዩ እያሉ እግዚአብሄር ለሚስታቸው ቤት መስሪያ ያጠራቀሙትን ገንዘብ የመጀመሪያው መዋጮ አድርገው እንዲሰጡት ይናገራቸዋል፡፡ በእጃቸው የነበረው ብቻኛው ገንዘብ የሚስታቸው ገንዘብ ነበር፡፡ በኮሪያ ባህል ባል ለሚስቱ ቤት ይገዛ ስለነበር እሳቸው ለሚስታቸው ቤት ለመግዛት ያጠራቀሙት የሚስታቸው ቤት መግዣ ገንዘብ ነበር፡፡ እሳቸው ለሚስታቸው እግዚአብሄር ገንዘቡን እንዲሰጡ እንደተናገራቸው ይነግሩዋታል፡፡  የሚስታቸው መለስ ግን ያንን ገንዘብ ለመስጠት በፍፁም እንዳታስብ የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ያለችውን ሰምተሃል ብለው ፀልየው ይተዉታል፡፡

ሚስታቸው ግን ልትትወው አልቻለችም፡፡ ሚስታቸው እንቅልፍ አጣች፡፡ እኔ ተኝቼ እነሳለሁ እርስዋ ግን ሌሊቱን ሙሉ ትገላበጣለች እንጂ እንቅልፍ በአይኑዋ አልዞረም ይላሉ፡፡ በእንቅልፍ ማጣት አይንዋ እያበጠ ሄደች፡፡ በሰባተኛው ቀን ይላሉ ቾ ያንን ገንዘብ ውሰደው አለችኝ ብለው ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ በሰጡ ጊዜ እግዚአብሄር ከሚመለከተው ሰው ጋር ነገሮችን እንደጨረሰ ይመሰክራሉ፡፡

እግዚአብሄር የተናገረንን ለሚመለከታቸው ሰዎች ካሳየን በኋላ መታገስ እና ጊዜ መስጠት እግዚአብሄር ደግሞ በራሱ መንገድ እንዲናገራቸው እድልን ይሰጠዋል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ ካልሰጠን የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት ስንሮጥ እንደ ራስ ወዳድ ሰዎች ለጥቅማችን የምንከራከር ይመስላል፡፡ ስለዚህ ነው ከቤተክርስትያን መሪነት መመዘኛዎች አንዱ አለመከራከርና አለመጨቃጨቅ የሆነው፡፡

የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡3

ስለዚህ ነው ሰው ካንተ ጋር ቦክስ ወይም ቡጢ ሊገጥምህ ሲፈልግ አንተ ከቦክሱ ሜዳ ውጣና ባንተ ፋንታ እግዚአብሄርን ወደ ቦክሱ ሜዳው አስገባው የሚባለው፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ፋንታ የሚዋጋው እኛ ከሰዎች ጋር ውጊያን ስናቆም ብቻ ነው፡፡ እራሳችንን የምናየውና ከተሳሳትን የምንታረመው ለእገዚአብሄር አሰራር ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርም በማሸነፋችን ክብሩን የሚወስደው እኛ ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜና እድል ስንሰጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። ዘፀአት 14፡14

እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው። 2ኛ ዜና 20፡17

እግዚአብሄር የመራንን ከተናገርን በኋላና እግዚአብሄር ያለንን ካደረግን በኋላ ካላረፍን በስተቀር የእኛ ስራ እንጂ የእግዚአብሄ ስራ አይሆንም ፣ የእኛ ሃይል እንጀ የእግዚአብሄር ሃይል አይሆንም እንዲሁም የእኛ ጥበብ እንጂ የእግዚአብሄር ጥበብን አይሆንም፡፡

ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ፦ ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው። መሣፍንት 6፡31

እኛ ከእግዚአብሄር ጋር አብረን ሰራተኛ ነን እንጂ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የእግዚአብሄርን ስራ የምንሰራ ብቸኛ ባለቤቶች እና ተሟጋቾች አይደለንም፡፡ መስራት የምንችለውን ካደረግን በኋላ ለዋናው ባለቤት ጊዜውንና ስፍራውን እንለቃለን፡፡

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ስፍራ #እውቀት #ጥበብ #ቦክስ #ቡጢ #የማይጨቃጨቅ #ገር #የማይከራከር #ክርስትያን #አማርኛ #ፍጥነት #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ፈንታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #እድል #ጊዜ

Advertisements

መመላለስ ከመቀመጥ ይጀምራል

sit.jpgለእግዚአብሄር እንደሚገባ መመላለስ በሰው ጉልበት የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ልጅ መመላለስ የእግዚአብሄር ሃይልና አሰራርን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ነው ከመመላለስ በፊት መቀመጥ ይቀድማል የሚባለው፡፡

በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ በተቀመጥንበት ሃይልና ምሪት ለእግዚአብሄር እንደሚገባ መኖር እንችላለን፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ባለንበት ስልጣን የምድር ህይወታችንን ሃላፊነት በስኬት እንወጣለን፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ በናለን ልዩ ስፍራ በምደር ላይ ነገሮችን ተቋቁመን እናልፋለን፡፡

በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ኤፌሶን 1፡3

በእግዚአብሄር ዘንድ ያለን ስፍራ በምድር ስፍራ እንዳንፈልግ ይረዳናል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለብ ስልጣን በሰይጣን ፊት እንዳንዋረድ ያስችለናል፡፡ በእግዚአብሄር ልብ ያለን ስፍራ ስንረዳ ከእግዚአብሄር ውጭ በምድር ምንም ነገር በልባች የመጀመሪያውን ስፍራ እንዳይዝ ያደርገናል፡ በእግዚአብሄ ዘንድ ያለን ከፍታ ስንረዳ በምድር ያለ ምንም ዝቅታ አያስደነግጠንም፡፡ በእግዚአብሄር እንደነገስን ስንረዳ ከጌታ ውጭ ምንም ነገር ንጉስ እንዳይሆንብን ያደርጋል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ያለን ከፍታ በምድር ራሳችንን እንድናዋርድ ያስታጥቀና፡፡ በሰማያዊ ያለን ስፍራ ለምድር ስፍራ እንዳንፎካከር ያግዘናል፡፡ በእግዚአብሄር ያለንን ክብር ስንረዳ የምድሩን ክብር እንድንቀው ያስችለናል፡፡

ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-4

ለእርሱ ለመኖራችን የሚያስፈልገውን ነገር ሳያዘጋጅ እግዚአብሄር አልጠራንም፡፡  ለእርሱ ለመኖርና ለእርሱ በሚገባ ለመመላለስ እግዚአብሄር የጠራን ለክርስትና ህይወት ሁሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሰጥቶን ነው፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

በሰማያዊ ስፍራ ሳያስቀምጠን በፊት እንደ ልጅ ለእርሱ እንድንመላለስ አልጠየቀንም፡፡

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6-7

በክርስቶስ ያለንን ስፍራ ፣ ስልጣንና ክብር ካላወቅን ለጥሪያችን እንደሚገባ መኖር አንችልም፡፡ በክርስቶስ ያለንን አቅርቦት ካለተረዳን በአቅርቦቱ በድል መመላለስ አንችልም፡፡

ለምሳሌ መኪና የተሰራው ለመነዳት ነው፡፡ መኪና ለመገፋት አልተሰራም፡፡ መኪና የሚነዳውም ሰው ይሁን የሚገፋውም ሰው ሁለቱም መኪናውን አንድ ቦታ ቢያደርሱትም መኪና መንዳትና መግፋት ግን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ስልጣን በተረዳን ቁጥር ክርስትና እንደ መኪና መንዳት እንጂ እንደ መኪና መግፋት አይሆንብንም፡፡

እግዚአብሄር በክርስቶስ ባዘጋጀው ጥቅምና መብት ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን እግዚአብሄርን በማወቅ ማደግ አለብን፡፡ እግዚአብሄር በልቡ እንዳለው ለመመላለስ በቃሉ አማካኝነት ክርስቶስን ማጥናትና መማር አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በሙላት ሊኖርብንና በክርስቶስ እውቀት ማደግ ይገባናል፡፡

በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡3

እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን እንዴት ከእግዚአብሄር ጋር በሰላም እንደምንኖር እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰላማችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄርን በተረዳነው መጠን የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን በሙላት መፍሰስ ይጀምራል፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ሰውን እንዴት እንደምንይዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ነገሮችን እንዴት እንደምንዝ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ የሰጠንን ቦታ ስንረዳ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በሙላት ፈፅመን እናልፋለን፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #መቀመጥ #ሰማያዊ #በክርስቶስ #በጌታ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን

eag.jpgያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡27-31 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

በአለም የሚያደክም ብዙ ነገር አለ፡፡

ጎበዝ የተባለ ፣ ጠንካራ የተባለና ሃያል የተባለ ሰው በራሱ አይቆምም፡፡ ይወድቃል ብለን የማናስበው ሰው ወድቆ እናገኘዋለን፡፡ ማንም ሰው ላለመውደቅ መተማመኛ የለውም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄርን የሚጠብቁ ሰዎች አይደክሙም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የሚራመዱ ሰዎች በድካም አይሸነፉም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የሚኖሩ ሰዎች ከድካም በላይ ናቸው፡፡ ሰው ሳይደክም እንደበረታ የሚኖረው እግዚአብሄርን ሲጠብቅ ብቻ ነው፡፡ ሰው ከድካም በላይ የሚኖረው ከእግዚአብሄር ጋር ሲራመድ ብቻ ነው፡፡

ሰው ሃይሉን የሚያድሰው እግዚአብሄርን ካልቀደመው ነው፡፡ ሰው ሃያል የሚሆነው በእግዚአብሄር ፍጥነት ለመኖር ራሱን ትሁት ካደረገ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ከኖረ የእግዚአብሄር ሃይል በእርሱ ላይ ይሆናል፡፡ ሰው በራሱ ከሮጠ ይደክማል ይወድቃል፡፡

እግዚአብሄር የሚያነሳበት ጥበብ አለው፡፡ አግዚአብሄር የሚያሻግርበት መንገድ አለው፡፡ እግዚአብሄር የሚክስበት መንገድ አለው፡፡ እውቀት በሌለን ነገር በእግዚአብሄር ልንታመንና ልንደገፍ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን አሰራር ልንታገስ ይገባል፡፡ የእግዚአብሄርን ፍጥነት ልንጠብቅ ይገባናል፡፡

ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡27-31

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #መጠበት #መተማመን #እምነት #ያድሳሉ #ይወጣሉ #አይደክሙም #አይታክቱም #እግዚአብሔር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

አምላክ የመሆኑ ትርጉም

highway.jpgእግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።  መዝሙር 33፡12

ነገር ግን አምላኩ የመሆን ትርጉም ምንድነው፡፡ ወይም እግዚአብሄር ለህዝብ አምላኩ ሆነ ማለት ምን ማለት ነው፡፡

እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ኤርሚያስ 11፡4

እግዚአብሄር አምላኩ የሆነለት ማለት ፡-

 1. በእግዚአብሄር ፍቅር ካለምክኒያት ተወደናል ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ሮሜ 5፡8

 1. እግዚአብሄር ስለእኛ ሃላፊነት ይወስዳል ይመራናል ማለት ነው፡፡

ጌታን ለመከተል በወሰንን በዚያን ጊዜ እግዚአብሄር በእኛ አምኖዋል፡፡ ልጆቼ ናቸው ብሎዋል፡፡ ስለእነርሱ ሃላፊነት እወስዳለሁ፡፡ ስለእነሱ እጠየቃለሁ ብሎዋል፡፡

ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7

 1. እግዚአብሄር ስለእኛ ተጠሪ ነው ማለት ነው፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራውያን 2፡13

መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡11

 1. እግዚአብሄር ስለእኛ ያቅዳል በእቅዱም ይመራናል ማለት ነው፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11

 1. እኛ የእግዚአብሄር ነን ማለት ነው፡፡

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ። ሚልክያስ 3፡17

በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳይያስ 43፡7

 1. ከእግዚአብሄር እጅ ሊነጥቀን የሚችል የለም ማለት ነው፡፡

እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። ዮሃንስ 10፡28-29

 1. እግዚአብሄር በእኛ ፋንታ ሃይሉን ይገልጣል ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል፥ ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል። 2ኛ ዜና 16፡9

 1. እግዚአብሄር ከፊታችን ይወጣል ማለት ነው፡፡

እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። ዘጸአት 33፡15-16

 1. ለክብሩ የፈጠረን ለክብሩ የሚጠቀምብን ነን ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን። መዝሙር 100፡3

 1. የእግዚአብሄር የሆነውን ተካፍለናል ማለት ነው፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ የጴጥሮስ 1፡2-3

ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡23

#እግዚአብሔር #አምላክ #የተባረከ #የተመሰገነ #የታደለ #የተሞገሰ #የተወደደ #የተከናወነ #የተሳካ #የተለየ #የከበረ #የሚቀናበት #የተጠቀመ #እድለኛ #ክብር #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ኢየሱስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ

in christ.jpgስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡16

ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቀውም ይላል ሃዋሪያው፡፡ ግን ክርስቶስንም በስጋ አናውቀውም ማለት ምን ማለት ነው? ማንንም  በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለትስ?

ሃዋሪያው ቀድሞ ክርስቶስን በስጋ ያውቀው ነበር፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ አንድ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ አንድ ያገሩ ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ነበር የኢየሱስን ተከታዮች እንደሳቱ በማመን ሊገድልና ሊያስር ደብዳቤ ተቀብሎ ይሄድ የነበረው፡፡

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሐዋርያት 9፡1-2

ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ክርስቶስን ከእግዚአብሄር እንዳልተላከ እንደተራ ሰው ማየት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት በእግዚአብሄር መመዘኛ  ሳይሆን በሰው መመዘኛ ኢየሱስን መመዘን ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት የኢየሱስን የዘር ግንዱን አይቶ መጣል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ኢየሱስ የሰው ልጅነቱን እንጂ የእግዚአብሄ ልጅነቱን አለማየት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት የሃገር ልጅ መሆኑን እንጂ ከእግዚአብሄር መላኩን አለመቀበል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት በእግዚአብሄር ዘንድ ያለውን ስፍራ አለማወቅ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ ማለት ምክኒያት ፈልጎ መሰናከል ማለት ነው፡፡

ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። ማቴዎስ 13፡55-56

ጌታ ጳውሎስን በብርሃን ከተገናኘው በኋላ ግን ኢየሱስን በስጋ እንደሚሆን ማወቅ አቆመ፡፡ ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ እንድ አይሁዳዊ ሳይሆን እንደ ጌታ ነው፡፡ አሁን ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ ተራ ሰው ሳይሆን እንደ አዳኝ ነው፡፡ አሁን ክርስቶስን የሚያውቀው እንደ ማሪያም ልጅ ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡

እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፦ ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው። ሐዋርያት 9፡6

ሃዋሪያው ይቀጥልና ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ይላል፡፡ ክርስቶስን ብቻ አይደለም ማንምም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ይላል፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በእግዚአብሄር መመዘኛ እንጂ በሰው መመዘኛ እንመዝንም፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በስጋ ማዕረጉ ሳይሆን በእግዚአብሄር ዘንድ ባለው የልጅነት ማዕረጉ ነው የምናውቀው ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በዘር ፣ ፆታና ቀለም አንለካም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በስጋ ባለው ክብር አናከብርም ፣ በስጋ ባለው ድካም አንንቅም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት ማንንም በምድራዊ መመዘኛ አናነሳምምም አንጥልምም ማለት ነው፡፡ ማንንም በስጋ እንደሚሆን አናውቅም ማለት እግዚአብሄር እንደሚያይ እንጂ ሰው እንደሚያይ አናይም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡16-17

ሰውን ሁሉ የምናውቀው በክርስቶስ ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምንመዝነው በክርስቶስ ባለው ስፍራ ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምንቀበለው በክርስቶስ አቀባበል ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምናከብረው በክርስቶስ ክብር ነው፡፡ ሰውን ሁሉ የምናውቀው ክርስቶስ በሚያውቀው እውቀት ነው፡፡ ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡7

ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፡፡

ማንም ማንም ማንም

በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። ገላትያ 3፡26-28

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #ማንነት #የእግዚአብሄርንእይታ #በስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #በስጋደረጃ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ስፍራ #ማእረግ #ስልጣን

እጅግ ውጤታማው የጦር መሳሪያ

weapon.jpgበሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡3-5

ስልጣን እስከሚሰራ ድረስ አይታይም፡፡ ስልጣን የሚታየው ሲሰራና እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው፡፡

እኛ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች ደግሞ እንደማንኛውም የምድር ነዋሪወች ነው የምንኖረው፡፡ የምንኖረው እንደሰው ልማድ ነው፡፡ እንደ ሰው እንበላለን ፣ እንደሰው እንለብሳለን ፣ እንደሰው እንተኛለን፡፡ ያ ማለት ግን መንፈሳዊ ስልጣን የሌለን ተራ ሰዎች ነን ማለት አይደለንም፡፡

እኛ የእግዚአብሄ ልጆች የሆንን ሁሉ ታላቅ ስልጣን አለን፡፡ (ዮሃንስ 1፡12) እንደ ሰው ልማድ ብንመላለስም ወደ ስልጣን ወደ ውጊያ ወደ ማሸነፍ ሲመጣ ግን እንደሰው ልማድ አንዋጋም፡፡ የጦር እቃችንም ስጋን ብቻ መግደል የሚችል ስጋዊና ምድራዊ አይደለም፡፡ የጦር እቃችን በምድር ላይ እጅግ ከተራቀቀ ከባድ የጦር መሳሪያ ይልቅ እጅግ ውጤታማ ነው፡፡

የጦር እቃችን ማንኛውንም ነገር መለወጥ የሚችል በእግዚአብሄር ፊት ብርቱ ነው፡፡ የጦር እቃችንን ሊቋቋም የሚችል ጠላት የለም፡፡ ስልጣናችንን ስንጠቀም ፊታችን ሊቆም የሚችል ማንም አይኖርም፡፡

የጦር እቃችን ምሽግን ለመስበር በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፡፡ በሰው ፊት ምንም ላይመስል ይችላል በእግዚአብሄር ዘንድ ግን ሃያል ነው፡፡ ሰው ሊንቀው ይችላል በእግዚአብሄር ፊት ግን ብርቱ ነው፡፡ በምድራዊ አለም ምንም ላይመስል ይችላል በሰማያዊው አለም ግን እጅግ የተከበረ ነው፡፡

ምሽግ በጦርነት ሜዳ ለማሸነፍ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ጠላት ከመሸገ ለመሸነፍ ያለው እድል ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን የጦር እቃችን ምሽግን ለመስበር ብርቱ ነው፡፡ የጦር እቃችን የሚስተው የጠላት ኢላማ የለም፡፡ የጦር እቃችን የማይደመስሰው የተመሸገ የጠላት ጦር የለም፡፡

የሰይጣን ትልቁ ምሽግ ደግሞ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ክፉ ሃሳብን የሚያስተናግድ የሰው አእምሮ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ የጦር መሳሪያ የሰው ሃሳብ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ መደበቂያ ምሽግ የሰው አእምሮ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ ምሽግ በእግዚአብሄር ቃል ያልታደሰ ፣ ስርአት የሌለውና እንዳመጣለት የሚያስብ አእምሮ ነው፡፡

ሰይጣን የሰው ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ወደ ሰው ሲመጣ የሚመጣው ወይ ለመስረቅ ወይ ለማረድ ወይ ለማጥፋት ነው፡፡ (ዮሃንስ 10፡10) ሰይጣን ከዚህ ውጭ ምንም አላማ የለውም፡፡ ሰይጣን የሰውን ህይወት የማጥፋት አላውን የሚፈፅምበት ብቸኛው መንገድ ሃሳቡን ወደሰው አአምሮ በመላክ በመመሸግ ነው፡፡

ሰይጣን በኢየሱስ ሞት ሙሉ ለሙሉ ድል ተነስቷል፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ ሰዎች 2፡15

ሰይጣን ድል ስለተነሳ በማታለል እንጂ በግድ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ሰይጣን ድል ስለተነሳ አሁን የቀረው መሳሪያ ሃሳብን ወደሰው አእምሮ መላክና የሚቀበለው ሰው ካገኘ በአእምሮ በመመሸግ የሰውን ህይወት ማጥቃት ነው፡፡

ሰይጣን ሃሳቡ ተቀባይነት ካላገኘ ሰውን ሊያጠቃ በፍፁም አይችልም፡፡ ሰይጣን ደግሞ በሰው ውስጥ ሃሳቡን ልኮ ተቀባይነት ካገኘ ሰውን እንደልቡ ማጥቃት የሰውን ህይወት መስረቅ ማረድና ማጥፋት ትችላል፡፡

ይህ እግዚአብሄር የሰጠን ስልጣን የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ ለማፍረስ ብቁ ነው፡፡

በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡3-5

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #የጦርመሳሪያ #ምሽግ #አእምሮ #ሃሳብ #ማታለል #ብርቱ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

 

 

 

ከአሸናፊዎች እንበልጣለን

SoldierKneeling320.jpgበአለም ላይ ብዙ ሃያላንና አሸናፊዎች አሉ፡፡ አለም ሰዎችን በሚያንበረክኩ ብዙ አዋራጆች የተሞላች ነች፡፡ በአለማችን ደካሞች በሃያላን ሲሸነፉ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ሰዎች በአሸናፊዎች በየእለቱ ይሸነፋሉ፡፡

ሌሎችን ተሸነፉ ማለት እኛ እንሸነፋለን ማለት አይደለም፡፡ ለእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ሽንፈት የእኛ እጣ ፋንታ አይደለም፡፡ አሸናፊነት እጣ ፈንታችን ነው፡፡ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከእኛ ጋር ሆኖ ፣ ለእኛ ሆኖ እና በእኛ ውስጥ ሆኖ ከማሸነፍ ውጭ ምንም ሊታሰብ አይችልም፡፡

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡37-39

እርግጥ ነው እግዚአብሄር ለአሸናፊነት ጠርቶናል ስንል በአለም ላይ ያለውን ሁኔታ እየካድን አይደለም፡፡ እኛ ክርስቶስን የምንከተል የበላይ ነን የምንለው በራሳችን ጉልበት ሳይሆን በእግዚአብሄር ስለተወደድን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በራሳችን ጥረትና መንገድ ሳይሆን በወደደን በእርሱ በክርስቶስ ነው፡፡ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ስንል እስከመጨረሻው በሚያፀናን በክርስቶስ ፍቅር ተመክተን ነው፡፡

በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ ፊልጵስዩስ 1፡6

እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። ዮሐንስ 10፡28

ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አለምን ያሸነፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለምንከተል ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞቱ በሻረው በኢየሱስ ነፃ ስለወጣን ነው፡፡

እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ ዕብራውያን 2፡14-15

ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው ክርስቶስ የአሸናፊውን ስልጣን ስለገፈፈው ነው፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15

ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ የሚንበረከኩለት ክርስቶስ ጌታችን ስለሆነ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ ፊልጵስዩስ 2፡9-10

ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡

ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡10

ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አሸናፊውን አለም ባሸነፈው በክርስቶስ ስለምንታመን ነው፡፡

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃያል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አሸናፊ #አለቅነት #ስልጣናት #ስልጣን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የሰይጣን ብቸኛው መሳሪያ

Masking-Pain.jpgየዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። ኤፌሶን 6፡11

የጠላት የዲያብሎስ አላማ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ዲያቢሎስ የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን በመስቀል ላይ ድል ነስቷል፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15

ሰይጣን የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ማንንም በግድ ጎትቶ ሃጢያት ሊያሰራ አይችልም፡፡ ሰይጣን እንደታሰረ ውሻ ነው፡፡ የታሰረ ውሻ እንደሚጮህና እንደሚረብሽ ሁሉ ሰይጣንም መሳሪያው ጩኸት ፣ ማስፈራራትና ማታለል ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን የጥርጥርን ሃሳብ ወደ አእምሮዋችን ልኮ ከተቀበልነው ከእምነት መንገድ እንስታለን፡፡

ሰይጣን ሃሳብን ወደ አእምሮው ልኮ በሰይጣን ሽንገላ የተሸነፈ ሰው የሰይጣንን ማስፈራሪያ ፈርቶ ከመንገዱ ይመለሳል፡፡ በሰይጣን ሽንገላ የተታለለ ሰው በኑሮ ፍርሃት እግዚአብሄርን ከማገልገል ይመለሳል፡፡

የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡19

በሰይጣን የሃጢያት ሽንገላ የተታለለ ሰው ለእግዚአብሄር በቅድስና መኖር አይቻልም ብሎ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በሰይጣን ሽንገላ የተሸነፈ ሰው አለምን ማሸነፍ አይቻልም ብሎ ለአለም አሰራር እጅ ይሰጣል፡፡

ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16

ሰይጣን ስልጣኑ ስለተገፈፈ ብቸኛው መሳሪያው ማታለል ነው፡፡ ሰይጣን ካታለለን ክፋት ያሰራናል፡፡ ሽንገላውን ከተቃወምን እግዘኢአብሄርን አገልግለን እናልፋለን፡፡

ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ከማታለሉ እንድንጠበቅ የሚመክረን፡፡ ከማታለሉ የምንጠበቀው የእግዚአብሄርን ቃል ስንረዳ ብቻ ነው፡፡ ከሰይጣን ማታለል የምንጠበቀው በእግዚአብሄር ጥበብ ብቻ ነው፡፡

የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። ኤፌሶን 6፡11

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #አእምሮ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የልጅነትን ስልጣን መረዳት

police-clip-art-1194984609285255522police_man_ganson.svg.med.pngሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር ክብር ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው ሲፈጠር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ በመስቀል ላይ በመሞት ለመክፈል ወደ ምድር መጣ፡፡

ኢየሱስ የሞተውና ከሙታን የተነሳው ስለእኔ ሃጢያት ነው ብሎ ኢየሱስን እንደ አዳኙና የህይወቱ ጌታ አድርጎ የሚቀበለውን ማንኛውም ሰው እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ወደ ቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡ የልጅነት ስልጣኑን ይመልስለታል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐንስ 1፡12

ግን የእግዚአብሄ ልጅነት ስልጣን ምንድነው?

 1. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም የመኖር ስልጣን ነው፡፡

ሃጢያት የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር ተልይቶዋል፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ሞት በመሆኑ ሰው ከእግዚአብሄር ለዘላለም ተለይቶዋል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ በሃጢያት ውጤት በዘላለም ሞት ፍርድ ስር ወድቆዋል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው እግዚአብሄር ስለሚቀበለው ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር የመኖር ስልጣን አለው፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንሰ 3፡16

 1. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የእግዚአብሄር መኖሪያ የመሆን ስልጣን ነው፡፡

 

ኢየሱስን በተቀበለ ሰው ውስጥ እግዚአብሄር ይኖራል፡፡ ኢየሱስን የሚከተለ ሰው መንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነው፡፡

 

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16

 

 1. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን የመንፈሱን መያዣ የመቀበያ ስልጣን ነው፡፡

 

ሰው አንድ እቃ ለመግዛት ፈልጎ ገንዘብ ቢጎድለው እቃውን መግዛት እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ቀብድ ይከፍላል፡፡ ቀብድ የከፈለው ሰው እያለ እቃው ለሌላ ሰው አይሸጥም፡፡ ያን ቀብድ የከፈለ ሰው ሌላ ጊዜ መጥቶ የቀረውን ዋጋ ሲከፍል እቃው የእርሱ ይሆናል፡፡

 

ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡5

 

እንዲሁንም እኛ የእግዚአብሄር መሆናንችንን ደግሞም በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሄር ጠቅልሎ የራሱ እንደሚያደርገንም ማረጋገጫ መንፈሱን እንደቅድሚያ ክፍያ ቀብድ ሰጭጥቶናል፡፡ የእግዚአብሄ ልጅ የሆነ ሰው የቤተሰቡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስን የመሞላት ስልጣን አለው፡፡

 

 1. ለሚበላና ለሚጠጣ ከመጨነቅ በላይ እንድንኖር ስልጣን ተሰጥቶናል

 

እግዚአብሄር  አባታችን ነው፡፡ አባታችን እግዚአብሄ ከእኛ የሚፈልገው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን እንድንፈልግ ነው፡፡ አህዛብ የሚፈልጉትን እንዳንፈልግ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡ እኛ እንድንፈልግ የታዘዝነው የእግዘኢአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ነው፡፡ ሌላው እንዲጨመርልን ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

 

 1. በእግዚአብሄር ልጅነታችን በሃጢያት ላይ ስለጣን ተሰጥቶናል

 

የእግዚአብሄር ልጆች ከሆንን በኋላ ሃጢያት አይገዛንም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የሃጢያተኛ ስጋችንን በመስቀል ላይ ሰቅሎታል፡፡ ስለዚህ አሁን ከሃጢያት ሃይል ነፃ ወጥተናል፡፡ በሃጢያት ላይ ሃይል ተሰጥቶናል፡፡

 

ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14

 

 1. በሰይጣል ላይ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን አለን

 

ኢየሱስ በምድር ላይ ሰይጣንን ድል ነስቶታል፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን ድል የነሳው በእኛ ምትክ ለእኛ ነው፡፡

 

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15

 

እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10፡18-19

 

 1. የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ከሁኔታዎች በላይ እንድኖር የሚያስችል ታላቅ ስልጣን ነው፡፡

 

እግዚአብሄር በህይወታችን ካስቀመጠው አላማ ሊያደናቅፈን በሚመጣ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

 

በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።  ሮሜ ሰዎች 8፡37-39

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ስልጣን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ሃይል #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

አቤት ውሸት?

publication1የጠላት ዲያቢሎስ አላማ ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት አይዘልም፡፡ ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሐንስ 10፡10

የህይወት ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያቢሎስ ከሚታወቅባቸው ስሞቹ አንዱ የውሸት አባት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሰይጣን ይዋሻል፡፡ ሰይጣን በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለተሸነፈና ስልጣኑን ስለአጣ አሁን የቀረው መሳሪያ መዋሸትና ማታለል ብቻ ነው፡፡

እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሐንስ 8፡44

በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3

ሰይጣን የሚዋሸው በእግዚአብሄር ቃል ላይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በውስጣችን ከሌለ ሊያሳስተን ሁሌ ይመጣል፡፡ ሰዎች ይህን የሰይጣንን ውሸት ሲያምኑ በዚህም ህይወታቸው ሲበላሽ እናያለን፡፡ ሰይጣን እንዴት እንደሚዋሽ እንመልከት

 • · እየጠፋህ ነው ዋጋ የለህም ትወድቃለህ ካለህ የሰይጣን ማታለል መሆኑን አውቀህ በእግዚአብሄር ቃል ፀንተህ ተቃወመው፡፡ ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11

የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። ምሳሌ 4፡18

 • · ሰይጣን በሃጢያት ውስጥ ደስታ ይገኛል አለምህን ቅጭ እንጂ ለምን ጊዜ ያልፍብሃል? ካለ ሰይጣን እየዋሸህ ነው፡፡ በአለም የቀረብህ ነገር ቢኖር አሳፋሪ ፣ ፍሬቢስና መጨረሻው ሞት የሆነ ነገር ብቻ ነው፡፡

እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። ሮሜ 6፡21

ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። ዕብራውያን 11፡25-26

 • · ሃብታም የሆነው ሰው ሁሉ ሃብት ያገኘው በማጭበርበር ነው ካለ አንተም ካላጭበረበርክ መበልፀግ አትችልም ስለዚህ አጭበርብር እያለህ ነው፡፡ ይህ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰው በታማኝነት በእግዚአብሄር ሊበለፅግ ይችላል፡፡

የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20

 • · እግዚአብሄር ለአንተ ግድ የለውም እራስህን አድን ፡፡ እግዚአብሄርን አትጠብቅ የራስህን መንገድ ሂድ የሚለው ድምፅ የሰይጣን ድምፅ ነው፡፡ ሰይጣን ሄዋንንም ተመሳሳይ ነገር ብሎዋት ነበር፡፡

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

 • · ማንንም አታገልግል ሰዎች ይጠቀሙብሃል ፡፡ ስለዚህ ከቤተክርስቲያን ሽሽ አምልጥ የሚልህ ሰይጣን ሲሆን ለምታገለግለው ለእግዚአብሄር ያለህን አመለካከት እያበላሸ ነው፡፡

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ማቴዎስ 25፡24-26

 • · ሌላው ሰው አያስፈልግህም አንተ ብቻ በቂ ነህ ከአለህ ሰይጣን በትእቢት ሊጥልህ እያናገረህ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3

 • · ካልተጨነቅህ ጤነኛ ሰው አይደለህም፡፡ አለመጨነቅ አይቻልም የሚለው የጠላት ድምፅ ነው፡፡ አንተ በቂ ጭንቀት አለህ እግዚአብሄርን ማምለክና ማገልገል የምትለውን ነገር ትተህ ለኑሮህ በመጨነቅ ህይወትህን ግፋ የሚለው ሰይጣን ዲያቢሎስ ነው፡፡

እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33

 • · አንተ ምስኪን ነህ ለእግዚአብሄር የምትሰጠው ምንም ነገር የለህም የሚለው ሰይጣን ለብዙዎች በረከት እንዳትሆን ሊያደርግ ነው፡፡

ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10

 • · ለማንም ቤተክርስቲያን አትገዛ ፣ በየትኛውም ስልጣን ስር አትሁን ፣ በግልህ ኑር አገልግል ካለህ ሰይጣን ነው፡፡

እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5

 • · አንተ ብቻ ነህ በመከራ ውስጥ የምታልፈው ካለአንተ በስተቀር ሰው ሁሉ ኑሮ ቀሎለት እየኖረ ነው ካለህ ይህ ንግግር ከሰይጣን እንደሆነ እወቅበት፡፡ ሰይጣን ሁሉም ሰው ጋር እየሄደ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡

በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8-9

 • · አንተ በሃጢያት ከመውደቅ አልፈሃል ምንም መጠንቀቅ የለብህም ካለህ ይህ ሃሳብ ከሰይጣን ነው፡፡

ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡12

 • · በእኔ ላይ የደረሰው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ነው፡፡ ከዚህ የምወጣበት ምንም መንገድ የለም ካልክ የሰይጣንን ንግግር አምነሃል ማለት ነው፡፡

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ውሸት #ሀሰት #ሰይጣን #ዲያቢሎስ #ጠላት #ማታለል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

%d bloggers like this: