Category Archives: Ethernal Life

ስንሞት ምን እንሆናለን ?

angeles carried lazarus.jpgሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡የሰው መኖሪያ ቤቱ እና ስጋው ከምድር አፈር ቢበጅም ሰው ግን አፈር አይደለም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ በስጋ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 2፡7

እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ስጋውን ከምድር አፈር አበጀው፡፡ የሰው ስጋ ከምድር አፈር ስለተበጀ የህይወት እስትንፋስ እፍ እስኪባልበት ጊዜ ድረስ ስጋው ሙት ነበር፡፡ እግዚአብሄር የህይወት እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት የሰው ስጋ ስሜት ያለው ፣ ፈቃድ ያለውና ሃሳብ ያለው አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር በሰው ስጋ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት የሰው ስጋ ግኡዝ አካል ነበር፡፡ እግዚአብሄር በሰው ስጋ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ከማለቱ በፊት ሰው ህያው ነፍስ ያለው አልነበረም፡፡

እግዚአብሄር በፈጠረው የሰው አካል አፍንጫ ላይ የህይወትን እስትንፋስ እፍ ካለበት በኋላ ሰው ህያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡

ሰው ሲሞት አይጠፋም፡፡ ሰው ሲሞት አይበንም፡፡ ሰው  ሲሞት መንፈሱ ከስጋ ይለያል፡፡ የማንኛውም ሰው በስጋ መሞት ከስጋ መለየት ነው፡፡ የውስጠኛው ሰው መንፈስ ከስጋ ተለይቶ ወደ መንፈሳዊው አለም ይሄዳል፡፡ የውጭው ሰው ስጋው ከመንፈስ ተለይቶ ወደ መቃብር ይገባል፡፡

ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ሉቃስ 16፡22

ሰው  ወዲህና ወዲያ ለመሄድ ፈቃድ ያለው በምድር ላይ ብቻ ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ሲኖር ብቻ ነው የፈለገበት የሚሄደው ያልገፈልገበት የማይሄደው ፡፡ ሰው በስጋ ሲሞት መንፈሱ ከስጋው ሲለይ ግን በመላእክት ይወሰዳል እንጂ ራሱን የትም አይወስድም፡፡ ሰው በስጋ ሲሞት ራሱ ወደፈለገበት ቦታ አይሄድም፡፡

ሰው የተገኘው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ሲሞት መኖሪያ ስጋው ወደ ነበረበት ምድር ይመለሳል፡፡ ሰው ግን ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሄር ይመለሳል፡፡

አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። መክብብ 12፡7

ሰው ሲሞት ከስጋ ስለሚለይ በስጋ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሰው መንቀሳቀስ ስለማይችእል መላእክት ይወስዱታል፡፡

ለሰው አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም ፍርድ ይጠብቀዋል፡፡ ሰው የኢየሱስን አዳኝነት የሚቀበለው በስጋ ውስጥ እያለ ነው፡፡ ሰው ከስጋ ከተለየ መላእከት ወደሚወስዱት ቦታ ይሄዳል እንጂ ጌታን ለመከተል ወይም ላለመከተል መወሰን አይችልም፡፡

ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እብራዊያን 9፡27

በምድር ላይ ጌታ ኢየሱስን አንደ አዳኙ የተቀበለ ሰው ሁሉ ወደዘላለም እረፍት ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ሃጢያት በመስቀል ላይ እንደዲሞት የሰጠውን ኢየሱስን በምድር ላይ ያልተቀበለ ሰው ለዘላም ከእግዚአብሄር ይለያያል፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #አፈር #ስጋ #ቤት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ

ስንፈጠር ምን ነበርን?

god created.jpgስለ አንድ ነገር ትክክለኛውን ነገር ለመረዳት ካስቸገረ ስለዚያ ነገር ለመረዳት ወደ ቀድሞው ነገሩ መመለስ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ስለአንድ ነገር ክርክር ከተነሳ ቀድሞ ምን እንደነበረ ማወቅ ለክርክሩ መቋጫ ያደርግለታል፡፡

ደቀመዛሙርቱ በጊዜ ሂደት ውስጥ ስለተለወጠው የትዳር ህግ ኢየሱስን ሲጠይቁት የመለሰላቸው መልስ ይህ ነበር፡፡ አዎ የምትሉት እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ከመጀመሪያ እንደዚህ አልበነረም፡፡

የእግዚአብሄርን የመጀመሪያውን ሃሳብ ለመረዳት ወደ መጀመሪያ ታሪኩ መመለስ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

እነርሱም፦ እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። እርሱም፦ ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። ማቴዎስ 19፡7-8

በየጊዜው ስለሰው ማንነት የተለያ አወዛጋቢ ትንታኔዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ሰው ከየት እንደመጣና ወደፊት ምን እንደሚሆን የተለያዩ መላምቶች ይሰጣሉ፡፡ ስለሰው ማንነት ለማወቅ በመጀመሪያ የነበረውን ታሪክ መመልከት እውነተኛውን እውቀት ይሰጠናል፡፡

ሰው እንዴት እንደተፈጠረ መመልከት ሰው ከየት እንደመጣ ማን እንደሆነ እውቀትን ያስጨብጠናል፡፡

እግዚአብሄር ሰውን በድንገት አልፈጠረውም፡፡ እግዚአብሄር በድንገት ሰው የሚባለ ፍጥረት አላገኘም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ምን አይነት ፍጥረት መፍጠር እንደሚፈልግ አስቦበት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ፍጥረቱን ከመፍጠሩ በፊት ይህ ፍጥረት ምንን መስሎ እንደሚፈጠር ፣ በምን ሁኔታ እንደሚፈጠር ፣ ምን እንደሚያደርግለት ሁሉንም ነገር አስቀድሞ አቅዶና አስቦበት ነው ሰውን የፈጠረው፡፡

እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ዘፍጥረት 1፡26

ሰው ሲፈጠር እግዚአብሄር ያየውን ነገር እንዲሰራ ለዚያው ለተፈጠረበት አላማ ዲዛይን ተደርጎ ነው የተፈጠረው፡፡

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡26-27

እግዚአብሄር ሰውን እንዴት እንደ ፈጠረው ከቃሉ በመረዳት ሰው ከየት እንደመጣና ወደየት እንደሚሄድ መረዳትን ማግኘት እንችላለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 1፡7

እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በምድር ላየ እንበዲኖር በመሆኑ ለምድር የሚስማማ ቤትን ፈጠረለት፡፡ እግዚአብሄ ሰውን የላከው በምድር ላይ በመሆኑ ለምድር ኑሮ የሚስማማ መኖሪያን ከምድር አዘጋጀለት፡፡ እግዚአብሄር የሰውን መኖሪያ ቤት የሰውን ስጋ ከምድር አፈር አበጀው፡፡ እግዚአብሄር ከምድር አፈር ያበጀው የሰው በምድር ላይ መኖሪያ ቤት ነው፡፡

እግዚአብሄር ከምድር ያዘጋጀው የሰው መኖሪያ ቤት ሰው ዝንደሌለበት ቤት ባዶ ነበር፡፡ እግዚአብሄ ከምደር አፈር ያበጀው የሰው ስጋ በሰው እንዳልተለበሰ ልብስ ባዶ እና የሞተ ነበር፡፡

እግዚአብሄር የፈጠረው የሰው ስጋ ስሜት ያለው ፈቃድ ያለው ሃሳብ ያለው አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር ያበጀው የሰው ስጋ ሙት ነበር፡፡ ሰው ስጋ ስላይደለ እግዚአብሄር ያበጀው የሰው ስጋ የምድር አካል የሆነ አፈር ብቻ ነበር፡፡ ስጋ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል አልተፈጠረም፡፡ ስጋ በእግዚአብሄር መልክና አምሳሉ የተፈጠረ የሰው መኖሪያ እንጂ ሰው አይደለም፡፡

ከምድር አፈር የተበጀውን የሰው ስጋ እንዲሆን ያደረገው እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ዘፍጥረት 1፡7

እግዚአብሄር የህይወትን እስትንፋስ እፍ እስካለበት ጊዜ ድረስ ከምድር የተበጀው ቢያነሱት ተመልሶ የሚወድቅ ፣ ቢያቆሙት የማይቆም ፣ ስሜት የሌለው ፣ ሃሳብ የሌለውና ፈቃድ የሌለው ሬሳ ብቻ ነበር፡፡

የህይወት እስትንፋስ እፍ ካለበት በኋላ ብቻ ነበር ሰው ህያው ነፍስ ሆነ ተብሎ የተፃፈው፡፡

ሰው የተገኘው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ስጋው ወደነበረበት ምድር ይመለሳል፡፡ ሰው ግን ወደሰጠው ወደ እግዚአብሄር ይመለሳል፡፡ 7

አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። መክብብ 12፡7

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #አፈር #ስጋ #ቤት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ

የዘላለም አምላክ

eternal.jpgእግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም እስከዘላለም ነው፡፡ እግዚአብሄር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም እግዚአብሄር አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡

አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ራእይ 22፡13

የእግዚአብሄር ከዘላለም እስከ ዘላለም መሆኑ በአእምሮዋችን እየመረመርም፡፡ የእግዚአብሄር ዘላለማዊነት በአእምሮዋችን ከመረዳት ያለፈ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ዘለዓለማዊነት ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ያልፋል፡፡

እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። ኢዮብ 36፡26

እግዚአብሄር የዘላለም አምላክነቱና እንደማይመረመርና ሰዎችም ሁሌ በእርሱ እንዲታመኑ የሚያዘው፡፡

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡28

እግዚአብሄር የዘላለም አምላክና ማስተዋሉም የማይመረመር ስለሆነ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ የተሻለ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር  የዘላለም አምላከ ነው፡፡ የዘላለም ክንዶች ከእኛ በታች ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ የሚያኮራና ሳንናወጥ ረጋ ብለን እንንድንኖር የሚያደርግን እውቀት የለም፡፡

መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡27

እግዚአብሄር በድንገት በህዝብ ድምፅ ብልጫ የተመረጠ ፕሬዝዳንት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም ንጉስ ነው፡፡

መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። መዝሙር 145፡13

እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። ኤርምያስ 10፡10

ከእግዚአብሄር ከዘላለም ከመኖር አንፃር የሰው በምድር ላይ ቆይታው እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ የሰውን በስጋ ቆይታ መፅሃፍ ቅዱስ ከእንፍዋለት ጋር ያነፃፅረዋል፡፡ የምድር ህይወት እጅግ አጭር በመሆኑ በራስ ላይ ከመደገፍ በላይ አክሳሪ ነገር የለም፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ከመደገፍ በላይ ጥበብ የለም፡፡

ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14

ከእግዚአብሄር ዘላለማዊነት አንፃር የምድር ቆይታችን ነጥብ አትሞላም፡፡ የዘላለም አምላከ እግዚአብሄር አምባችን ነው፡፡

ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። ኢሳያስ 26፡4

ሰው ማንንም ባያምን እግዚአብሄርን ማመን ግን ግዴታ ነው፡፡ በዘላለም አምላክ በእግዚአብሄር ላይ ካልተደገፍን በማንም ላይ መገደፍ አንችልም፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መኖሪያህእግዚአብሄር #እውቀት #ጥበብ #ሃይል #እንፍዋለት #አልፋ #ኦሜጋ #መጀመሪያ #መጨረሻ #ክርስትያን #አማርኛ #መደገፍ #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ፅድቅ #ማመን #አምባ #ስልጣን

የዘላለም አምላክ

 

psalm 31 9.pngአላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28

አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሄ ፊት የምናገራቸው ነገሮች እግዚአብሄርን የማያከብሩ አላዋቂነታችንን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሄር በላይ ያወቅን ይመስለናል፡፡ ለእግዚአብሄር ምክር መለገስ የምንችል ይመስለናል፡፡ ስንደክም እግዚአብሄርም አብሮን የሚደክም የቆሎ ጓደኛችን ይመስለናል፡፡ እግዚአብሄር አባታችንም ቢሆን የቆሎ ጓደኛችን ግን አይደለም፡፡

ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት በጥንቃቄ ልናደርገው ይገባል፡፡ አክብሮት የጎደላቸውና ንግግሮችና ዝንባሌዎች ከህይወታችን ልናስወግድና በትህትና ከእግዚአብሄር ጋር ልንኖር ይገባል፡፡

ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ሚክያስ 6፡8

ልትሰማና ልታውቅ ይገባል ይላል እግዚአብሄር፡፡ የዚህ ሁሉ ንግግር ምንጩ አለማወቅ ነው፡፡

እግዚአብሄ የዘላለም አምላክ ነው

አግዚአብሄር ተለማማጅ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አንተን እንዴት እንደሚመራ ፣ አንተን እንዴት እንደሚይዝህና እንደሚንከባከብህ ፣ አንተን እንዴት እንደሚያስተዳድርህ ከጊዜ ወደጊዜ ልምድን እያካበተ የሚሄድ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም የነበረ መሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘመናት ጀምሮ ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ ነው፡፡

እግዚአብሄር እንዴት ሊይዝህ እንደሚገባው ለመምከር ከዳዳህ እባክህ አፍህን አታበላሽ፡፡ እግዚአብሄርን አትመክረውም፡፡

የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ሮሜ 11፡34-35

እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው

እግዚአብሄር ሃያል ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለውን የሃይል መጠን ተረድተን አንጨርሰውም፡፡ እግዚአብሄር በምድር ውስጥ እንዳንድ ነገሮችን ያገኘ ሳይንቲስት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በቀናት የፈጠራቸውን ነገሮች የአለም ምርጥ ሳይንቲስቶች በክፍለ ዘመናት ሁሉ ተማራምረው ተመራምረው ተመራምረው አልጨረሱትም፡፡

የእግዚአብሄር ማስተዋል አይመረመርም

እግዚአብሄርን ተረድተን ለመጨረስ መሞከር የውድቀት መጀመሪያ ነው፡፡ ማድረግ የምንችለው የተሻለው ነገር በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ማረፍ ብልህነት ነው፡፡ በእግዚአብሄር በጎነት ላይ መደገፍ ጥበብ ነው፡፡ የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ መጣል የአባት ነው፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡11-13

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #የዘላለምአምላክ #የምድርዳርቻ #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ምን ብዬ ልጩኽ?

World-in-Gods-Hands 1.jpgጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ኢሳይያስ 40፡6-8

የሰው ህይወት በምድር ላይ አጭር ነው፡፡ ሰው ሃላፊ ነው፡፡ የሰው ህይወቱ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ነው፡፡

ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14

ሰው ሰማይና ምድርን ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖር የሚችለው የእግዚአብሄርን የመዳኛ መንገድ ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖር የሚችለው የማይጠፋውን የእግዚአብሄርን ቃል ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው የዘላለም ህይወት የሚኖረው እግዚአብሄር ስለመዳኑ ያዘጋጀውን የኢየሱስን የመስቀል ስራ ለእኔ ነው የሞተውና የተነሳው ብሎ ብቻ ነው፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16

ሰው ዘላለማዊ ህይወትን የሚያገኘው ከእግዚአብሄር ቃል ዳግመኛ ሲወለድ ብቻ ነው፡፡

ሰማይና ምድር ያልፋሉ ከማይጠፋው ለዘላለም ከሚኖረው ከእግዚአብሄር ቃል የተወለደ ሰው ግን አያልፍም፡፡

ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።  1ኛ ጴጥሮስ 1፡23-25

ኢየሱስ ስለሃጢያቱ እንደሞተለትና ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ የሚያምን ሰው ይድናል፡፡

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10

ሰማይና ምድር ያልፋሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ግን አያልፍም፡፡

ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ማቴዎስ 24፡35

የሚታየው ሁሉ የጊዜው ነው፡፡ የማይታየው ሁሉ ዘላለማዊ ነው፡፡

የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡18

ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሃንስ 2፡17

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የጌታቃል #ዘላለም #የዘላለምህይወት #የእግዚአብሄርፈቃድ #የጊዜው #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የዘላለምን ሕይወት ያዝ

lay-22መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
የዘላለም ህይወት የእግዚአብሄር ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ይህን ታላቅ ስጦታ እንደመቀበላችን መጠን ህይወታችን ሁሉ በዚያ ስጦታ መቃኘት አለበት፡፡
ምንም ነገር ስናስብ ከዘላለማዊ ህይወት እይታ እንፃር ማሰብ አለብን ፣ ምንም ነገር ስንወስን ከዘላለም ህይወት አንፃር ልንወስን ይገባል ፣ ምንም ነገር ስናደርግ ዘላለም እንደሚኖር ሰው ማድረግ አለብን፡፡
በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። ያዕቆብ 2፡12
ሰው ዘላለማዊ ህይወትን ካልያዘና የሚያደርገውን ሁሉ ከዘላለማዊ ህይወት አንፃር ካልመዘነውና ካላደረገው እይታው የቅርብና የአሁኑን ብቻ ያያል፡፡
እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፤ እናንተ፦ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል። ኢሳይያስ 22፡13
ሰው ትክክለኛ እይታ አለው የሚባለው ነገሮችን ሁሉ በዘላለም እይታ ማየት ሲችል ብቻ ነው፡፡ እይታው ዘላለምን ካላሳየው የቅርቡን ብቻ የሚያይ እውር ሰው ነው፡፡
እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡9
ከምድር ምንም አይነት ስኬትና ክንውን ጋር ሲነፃፀር የዘላለምን ህይወት የሚያክለው የለም፡፡ በእይታችን የዘላለም ህይወት ከሌለና እግዚአብሄርን ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ለምድራዊ ህይወት ብቻ ከሆነ ምስኪኖች ነን፡፡
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡19
እያንዳንዱ እርምጃችን ዘላለም ለሚኖር ሰው የሚገባ መሆን አለበት፡፡ ከምንም ነገር በላይ የዘላለምን ህይወት በትጋት መጠባበቅ አለብን፡፡ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ ፊልጵስዩስ 3፡20
በምድር ላይ የምናደርገው ማንኛውም ነገር በነፃነት ህግ እንደሚፈረድባቸው በጌታ ዙፋን ፊት እንደሚቀርቡ ሰዎች መሆን ይኖርበታል፡፡
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። ቆላስይስ 3፡1-4
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#የዘላለምህይወት #ሰማይ #ዘላለም #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
%d bloggers like this: