Category Archives: godliness

የክርስቶስም ሙላቱ ልክ እስክንደርስ

church leader.jpgሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡12-13

የክርስትና ጉዞ የእድገት ጉዞ ነው፡፡ የክርስትና ጉዞ መነሻ ያለው መድረሻም ያለው ጉዞ ነው፡፡

የክርስትና ጉዞ ሲጀመር የሚታወቅ ግቡም የሚታወቅ ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የማይታወቅ የግምት ረቂቅ ጉዞ አይደለም፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የሚገመት ባዶ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የማይታወቅ የወግና የስርአት ብዛት አይደለም፡፡

ክርስትና የሚጀመረው በንስሃ ከአሮጌ ኑሮ ፍጹም ወደኋላ በመመለስ ነው፡፡ ክርስትና የሚጀመረው ዳግም ከመወለድ ነው፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው ደግሞ ያድጋል፡፡

የክርስትና እድገት ወግና ስርአት መፈፀም አይደለም፡፡ የክርስትና እድገት የውጫዊ ስርአትን መጠበቅ አይደለም፡፡

ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡18-19

የክርስትና እድገት ጣራው የክርስቶስ ሙላት ልክ ነው፡፡ የክርስትና መጨረሻው ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ የክርስትና መጨረሻው የክርስቶስ ሙላት ልክ ነው፡፡ የክርስትና ግቡ ክርስቶስን ሙሉ ለሙሉ መከተልና መምሰል ነው፡፡

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡12-13

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #ክርስቶስእስኪሳል #መምሰል #ክርስቶስንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Advertisements

የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ

maxresdefault (5).jpgከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴዎስ 4፡1-3

ሰይጣን አላማው አልተለወጠም፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ ሊርድ ሊያጠፋ እንጂ ስለሌላ አይመጣም፡፡ ሰይጣን እኛንም የሚፈትነን ኢየሱስን በፈተነበትን ፈተና ነው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ባየ ጊዜ ሰይጣን የኢየሱስን የእግዚአብሄር ልጅነት ዝቅ ዝቅ የሚያደርግበት እድል ያገኘ መሰለው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ሲያየው ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅነቱን ሊያስክደው የሚችልበት በቂ ምክኒያት ያገኘ መሰለው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ያገኘው ሰይጣን የመንፈሳዊነትን ትኩረት ሊያስለውጠው ፈለገ፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሄር ቃልን የተሞላ ስለነበረ ለሰይጣን ፈተና በቂን መልስ መለሰ፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር ቃል ካለን ከፈተና እናመልጣለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ከሌለን ግን በሰይጣን ማታለል እንወድቃለን፡፡

የሰይጣን ፈተና ኢየሱስ ከደረሰበት ነገርና ካለበት የህይወት ሁኔታ አንፃር አይ ተሳሰቼ ነው የእግዚአብሄር ልጅ አይደለሁም ብሎ እንዲክድ ማድረግ ነበር፡፡ አሁንም ሰይጣን እኛን የሚፈትነን እንደዚሁ ነው፡፡

ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ብሎ ኢየሱስን እንደፈተነው እኛንም ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ውድ መኪና አትነዳም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን በመከራ ውስጥ ታልፋለህ? የእግዚአብሄር ልጅህ ከሆንክ ለምን ትደክማለህ? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ሰው ይጠላሃል? የእግዚአብሄ ልጅ ከሆንክ ለምን ትልቅ ቤት ውስጥ አትኖርም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንል ለምን በገንዘብ ሚሊየነር አልሆንክም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ዝነኛ አትሆንም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን በከፍታና በዝቅታ ውስጥ ታልፋለህ ? ነው የሚለን፡፡

ጥያቄው እነዚህ ከሌሉህ የእግዚአብሄር ልጅ አይደለህም የሚል መልእክትን የያዘ ነው፡፡ ጥያቄው ሰው የሚኖረው በዝናና በሃብት ነው የሚል መልእክት ያዘለ ነው፡፡ ጥያቄው ሰዎች በምድር ላይ የሚሮጡላቸው ነገሮች ከሌለህ ዋጋ የለህም የሚል መልእክት ያለው ነው፡፡

ኢየሱስ የሰይጣንን ጥያቄ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በማለት በሚገባ መልሶታል፡፡

ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች በምድር ላይ የሚፈልጓቸው ዝና ፣ ክብርና ሃብት ሰውን ሊያኖሩ የሚበቁ አይደሉም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እንዲያደርግ በመልኩና በአምሳሉ የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን እየሰማና እየታተዘ እንዲኖር የተፈጠረ ነው፡፡

ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡  ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሄር ጋር በሚያደርገው ህብረት ነው፡፡ ሰው የሚኖረው ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የሚኖረው እግዚአብሄርን በመስማትና በመታዘዝ ነው፡፡

የሰይጣን አላማ ሰው የሚኖረው በምን እንደሆነ በመዋሸትና የሰውን ትኩረት በማስለወጥ ነው፡ሸ የሰይጣን አላማ ሰው እነዚህ ነገሮች ከሌሉኝ ብሎ ራሱን እንዲንቅና እንዲያንቋሽሽ ማድረግ ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው ድንጋዩን ዳቦ ባለማድረጉ እውነትም የእግዚአብሄር ልጅ አይደለሁም ማለት ነው እንዲል ማድረግ ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው የሚኖርበትን የእግዚአብሄርን ቃል በቂ እንዳይደለ ማጣጣል ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው በእርሱ ብቻ የማይኖርበትን ሃብት ክብርና ዝና ላይ ብቻ እንዲያተኩትር ማሳሳት ነው፡፡ የሰጣን አላማ ክቡር የሆነው ሰው መኖር የማይችለበት ነገር ላይ አተኩሮ የሚኖርበትን ነገር እንዲተው ትኩረቱን ማዛባት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #የንጉስልጅ #ልጅነት ##መንፈስ #ነፍስ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

እግዚአብሔር ታላቅ

b6a876de530fd337727b3e2affa565a8እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። 1ኛ ዜና መዋዕል 16:25

እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው። መዝሙር 48:1

አባታችን አግዚአብሄር ትልቅ ነው፡፡

እግዚአብሄር ትልቅ  ብቻ ሳይሆን ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም፡፡ እግዚአብሄር ታላቅ ነው የምንለው ታላቅ ወንድም እንደምንለው ከታናሽ ወንድም ጋር አስተያይተን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ታላቅ ነው የምንለው ከሌላ የምንገልፅበት ቃል ስለሌለን ነው፡፡

እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም። ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ። መዝሙር 145፡3-4

እግዚአብሄርን እናምነዋለን እንጂ እግዚአብሄር እጅግ ታላቅ ስለሆነ በፍጥረት አቅም ተረድተን አንጨርሰውም፡፡

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡28

መፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ታላቅ ነው እኛም አናውቀውም የሚለው እግዚአብሄርን አውቀን ስለማንጨርስ ነው፡፡

እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። ኢዮብ 36፡26

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መኖሪያህእግዚአብሄር #እግዚአብሄርታላቅ #እውቀት #ጥበብ #ሃይል #አይመረመርም #አልፋ #ኦሜጋ #መጀመሪያ #መጨረሻ #ክርስትያን #አማርኛ #መደገፍ #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ፅድቅ #ማመን #አምባ #ስልጣን

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል

form of godliness.jpgነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-5

የአምልኮ መልክ ኖሮዋቸው የእግዚአብሄርን ሃይል የካዱ ሰዎች በጣም የሚያሳዝኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ሃይሉን የካዱ ሰዎች በእግዚአብሄር ሃይል ስለማይታመኑ የራሳቸውን መንገድ ይሄዳሉ፡፡ በሃይሉ ስለማይታሙና የእግዚአብሄር ሃይሉ ይህን ያደርግልኛል ብለው ተስፋ ስለማያደጉ ማስመሰዩውን መንገድ ይሄዳሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ሃትል ስለካዱ የስጋን ሃይል ይጠቀማሉ፡፡ በፍቀር ስለማያምኑ ፍቅር የሌላቸው ሆነው ይመላለሳሉ፡፡ በእግዚአብሄር ሃየለ ስለማያምኑ በራሳቸው ቅልጥፍና ይታመናሉ፡፡ ራሰብን በመካድ ስለማያምኑ በ ስግብግብነት ይመላለሳሉ፡፡ በእግዚአብሄር ስለማያምኑ በረሳቸው ብልጠይት ይደገፋሉ፡፡

ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ

ሰዎች እግዚአብሄር እንደሚወዳቸው እርግጠኛ ስላይደሉ ደስተኞች አይደሉም፡፡ እግዚአብሄር እንደሚወደው የሚያውቅ ሰው ያርፋል ራስ ወዳድ አይሆንም፡፡ ሰዎች ራሳቸው ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሌላውን መድረስ ፣ ሌላውን መጥቀም ፣ ማካፈል ፣ ለሌላው መኖር ፣ ሌላውን ማንሳት የሚባሉ ነገሮች ከራስ ወዳድንት ከፍ ያለ የከበረ ደረጃ እንደሆነ አያውቁም፡፡

ገንዘብን የሚወዱ፥

ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ጌታን ይንቃሉ፡፡ ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ሰውን አይወዱም፡፡ ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ይሰርቃሉ ፣ ይዋሻሉ ፣ ያጭበረብራሉ ፣ ይክዳሉ ፣ ሰዎችን ይጠላሉ፡፡ ገንዘብን መውደድ የክፋይ ሁሉ ስር እንደመሆኑ ገንዘብን የሚወድ ሰው እግዚአብሄርንም ሰውንም ስለማይወድ ምንም ክፋት ሊያደርግ ይችላል፡፡ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10

ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24

ትምክህተኞች፥

በገንዘብና በተለያዩ ጉሳቁሶች ይመካሉ፡፡ በራሳቸው ችሎታ ይመካሉ፡፡ ባላቸው ዝምድና በሚያውቁት ሰው በአራድነታቸው ይመካሉ፡፡

ትዕቢተኞች፥

ሰውን ሁሉ ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ባልጀራዬ ከእኔ ይሻላል አይሉም፡፡ ሰውን የሚፈልጉት ለጥቅማቸው ብቻ ነው፡፡ ካልጠቀማቸው ለሌላ ለምንም ነገር አይፈልጉትም፡፡ ከሁሉም የሚሻሉበትን መንገድ ባገኙት አጋጣሚ ያሳያሉ፡፡ ሁሉም እነርሱን ለመጥቀም የተሰራ እንጂ ልናገለግለው የሚገባ እንደሆነ አያውቁም፡፡

ተሳዳቢዎች፥

በታላቅ ቃል ይሳደባሉ፡፡ ሲሳደቡ ለነገ አይሉም፡፡ ለመሳደብ አይፈሩም፡፡ ሲናገሩ ደፋሮች ናቸው፡፡ በድፍረት ንግግር ሁሉንም ለመብለጥ የሚፈልጉ ይመስላሉ፡፡ በፊታቸው የተከበረ የማይሰደብ ሰው የለም፡፡ በግል ጥቅማቸው ፊት የቆመን ማንም ሰው ለማዋረድ ወደኋላ አይሉም፡፡ በግል ጥቅማቸው ፊት የቆመን ሰው ለማዋረድ ያለችውን ተሰሚነት ሁሉ ለክፋት ይጠቀሙበታል፡፡

ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥

ስልጣንን አያከብሩም፡፡ የሚሰሙት ምንም ስልጣን የለም፡፡ ለእነርሱ ሁሉም ሰው አልገባውም፡፡ እነርሱ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ከመስቀላቸው አንፃር ማንም ሊሰሙት የተገባ አይደለም፡፡ ለማንም አይታዘዙም፡፡ ማንንም አይሰሙም፡፡ ለሁለም ሰው የሚያወጡት አቃቂር አለ፡፡ ሁሉም ሰው እነርሱም የሚሰማ እንጂ እነርሱ የሚሰሙት አንድም ሰው የለም፡፡

 

ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እርሱም፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። ማቴዎስ 11፡16-19

የማያመሰግኑ፥

ራሳቸውን ከመስቀላቸ አንፃር ይህ የሚኖሩበት ኑሮ የሚገባቸው እንደሆነ አያስቡም፡፡ ለአነርሱ የቱም ደረጃ አይመጥናቸውም፡፡ በየትኛውም ህይወት አይረኩም፡፡ በየትኛውም የህይወት ደረጃ ራሳቸውን ለማማጠን አይፈልጉም፡፡ ምንም ከፍ ያለ ደረጃ ለእነርሱ አይበቃል፡፡ እጅግ የተከበሩ ስለሆኑ ለክብራቸው የሚበቃ የህይወት ደረጃ የለም፡፡ ስለዚህ አያመሰግኑም፡፡ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉት ከምስጋና ልብና በደስታ አይደለም፡፡

ቅድስና የሌላቸው፥

ህይወታቸው በመርህ አይመራም፡፡ ደስ ካላቸው የፈለጉትን ያደርጋሉ፡፡ ለእግዚአብሄር ነገሮችን መተው ፣ ከአለም እርኩሰት መለየት ፣ ራስን መካድ የሚሉት ቃላቶች በህይወታቸው የሉም፡፡ በቃሉ ሳይሆን በሁኔታው ነው የሚመሩት፡፡ የተሻለ ጥቅም ካስገኘላቸው ይዋሻሉ፡፡

ፍቅር የሌላቸው፥

እግዚአብሄርን አያውቁም፡፡ እግዚአብሄርን አይወዱም ሰውን አይወዱም፡፡ ፍቅር የላቸውም፡፡ ሌላውም መጥቀም ፣ ለሌላው ማካፈል ፣ አብሮ ማደግ የሚባሉት ሃሳቦች ለእነርሱ እንግዳና የሞኝነት ሃሳቦች ናቸው፡፡

ዕርቅን የማይሰሙ፥

የራሳቸውን ሃሳብ እንጂ የማንንም ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡እነርሱ ሃሳብ ብቻ ትክክል የሌላው ሃሳብ ሁሉ ስህተት ነው፡፡ ለሌላው ብለው ምንም ነገር ለመተው ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እውቅና የሚሰጡት ለራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ የሚያርፉት የራሳቸውን ሃሳብ ሲያስፈፅሙ ብቻ ነው፡፡ ለጥቅማቸው እንጂ ለሰላም ምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡

ሐሜተኞች፥

የሰውን ገመና ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ማንንም ሰው እንደ ቤተሰብ አያዩም፡፡ ማንም ሰው በፊታቸው የከበረ አይደለም፡፡ ሰውን በሌላ ሰው ፊት ዝቅ ዝቅ ለማድረግ አይፈሩም፡፡ የአንዱን ገመና በሌላው ሰው ፊት ለመግለጥ አይፈሩም፡፡ የሌላውን ስም ለማጥፋት ጨካኞች ናቸው፡፡ ሌላውን ለማዋረድና ስሙን ለማጥፋት ፈጥረውም በውሸት ያወራሉ፡፡ ሌላውን ሰውን ማጣጣል እነርሱን ከፍ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል፡፡

ራሳቸውን የማይገዙ፥

የፈሉትን ነገር በፈለጉት ጊዜ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ትእግስት ፣ መጠበቅ ፣ መተው የሚሉትን መርሆች አያውቋቸውም፡፡ ከስጋቸው የሚሰሙት ድምፅ ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ራስን መግዛት ፣ ስጋ መጎሸም ፣ ስጋን መከልከል የሚሉት ሃሳቦት በፍፁም አይገባቸውም፡፡

ጨካኞች፥

ምህረትና ርህራሄ የላቸውም፡፡ ለጥቅም ሲባል ምንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ በጥቅም ላይ እነጂ በማንም ላይ ይጨክናሉ፡፡ ለእነርሱ ትክክል ጥቅም ማግኘት ነው፡፡ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ማንኛውም ነገር በምንም ይምጣ በምንም ትክክል ነው፡፡

መልካም የሆነውን የማይወዱ፥

ትክክለኛው ህይወት  ከእነርሱ ስለሚለይ ይጠሉታል፡፡ ቀስ ብላ የምትከማቸውን ሃብት ያላዋቂ ያደርጉታል፡፡ ራሱን የሚገዛ ሰው ሲያዩ ያልገባው እውቀት ያነሰው ይመስላቸዋል፡፡ እንደ እነርሱ የማይሄድ ማንም ሰውን ይጠላሉ፡፡ መልካመ የሆነው ህይወት የእነርሱን ህይወት ስለሚያጋልጥ አይወዱትም፡፡

ከዳተኞች፥

በቃላቸው አይታመኑም፡፡ ለመካድ ቅርብ ናቸው፡፡ ታማኝነት ስለሌላቸው ከተመቻቸው ቅጥፍ አድርገው ይክዳሉ፡፡ የተሻለ ነገር ሲያገኙ ወዲያው ተገልብጠው ይገኛሉ፡፡ ቀድመው የገቡትን ቃል በቀላሉ ያፈርሳሉ፡፡ ስለቃሌ ልታገስ የሚል ነገር የላቸውም፡፡

ችኩሎች፥

ሁሉ ነገር በፍጥነት እንዲሆንላቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ ነገር በፍጥነት ካልሆነላቸው ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡ መጠበቅን ይፈሩታል፡፡ መታገስ አለማወቅ አለመረዳት ደካምነት ነው የሚመስላቸው፡፡

በትዕቢት የተነፉ፥

ማንም ሊያስተምራቸውና ሊመክራቸው አይችልም፡፡ ሁሉንም ያውቃሉ፡፡ አውቀውት ጨርሰዋል፡፡ ሌላው ሁሉ ሰው እንጂ እነርሱ መማር መለወጥ አያስፈልጋቸውም፡፡ ለመማር ለመለወጥ ዝግ ናቸው፡፡ በማንም ስልጣን ስር መግባት አይፈልሀጉም፡፡ ማንም እንዲያዛቸው አይፈልጉም፡፡ ማንንም መስማት አይፈልጉም፡፡

ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ

ደስታ መዝናናት የህይወታቸው ከፍተኛው አላማ ነው፡፡ የሚያስደስታቸውን ምንም ነገር ይቀበሉታል፡፡ የማያስደስታቸውን ምንም ነገር አይቀበሉትም፡፡ ህይወታቸውን በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ሳይሆን በቅንጦት ላይ ያባክኑታል፡፡ በህይወታቸው የሚመራቸው ደስታ ተድላ እንጂ ጌታ አይደለም፡፡

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል

የክርስትና ቋንቋው ሁሉ አላቸው፡፡ ንግግሩ ቃላቶቹ ሁሉ አላቸው፡፡ መልኩ ሁሉ አላቸው፡፡ ለውጭው መልካቸው በጣም ይጠነቀቃሉ፡፡ ሁሉንም ነገር ከላይ ከላይ ትክክል ለማድረግ እጅግ ይጠነቀቃሉ፡፡ የውጭውን ነገር ሁሉ በደንብ ይይዙታል ለልባቸው ግን ግድ የላቸውም፡፡ ዋናው የውጭው ይመስላቸዋል፡፡ ከሰው የሚመጣውን ክብር እንጂ ከእግዚአብሄር የሚመጣውን ክብር አይፈልጉም፡፡ ልባቸው ግን ክፋትና ቅሚያ ሞልቶባቸዋል፡፡

ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ዮሃንስ 12፡43

ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-5

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገንዘብን የሚወዱ #ትምክህተኞች #ትዕቢተኞች #ተሳዳቢዎች #ለወላጆቻቸውየማይታዘዙ #የማያመሰግኑ፥ #ቅድስና የሌላቸው #ፍቅርየሌላቸው #ዕርቅንየማይሰሙ #ሐሜተኞች #ራሳቸውን የማይገዙ #ጨካኞች #የማይወዱ #ከዳተኞች #ችኩሎች #በትዕቢትየተነፉ #ተድላን #እውቀት #ጥበብ #ማስተዋል #ቃል #መልካም #መታመን #መደገፍ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት  #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ማትረፊያ ነው ኑሮዬ ይበቃኛል

061-1024x768-300x225.jpgኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6

እግዚአብሄርን መምሰል ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል በራሱ የከበረ ግብ ነው፡፡ ጌታን መከተል ምንም ምንም ሳይጨምር በረከት ነው፡፡

ለጌታ መኖራችን ሙሉ እንዲሆን በዚያ ምክኒያት የምናገኘው ጥቅም መኖር የለበትም፡፡ ጌታን መከተላችን ትክክል መሆኑን ለማሳየት ብዙ ገንዘብ አያስፈልገንም፡፡ ለጌታ መኖራችን በብዙ ሃብትና ሃይል አይደገፍም አይታወቀም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል ጥሩ ሆኖ እንዲታይ የሚጣፍበት ምንም ዝና አያስፈልገውም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል በራ ሙሉ ከመሆኑ የተነሳ በየትም ሃብትና ዝና አይሟላም፡፡

እግዚአብሄርን መምሰል የመጨረሻ ግብ ነው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰልን የሚበልጠው ሌላ ከፍ ያል ግብ የለም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል የክብር ጥግ ነው፡፡

ሰይጣን ይህንን ያውቀዋል፡፡ ሰይጣን ጌታን መከተላችን ብቻ የክብር ጣራ መሆኑን ያውቀዋል፡፡ ሰይጣን ውሸታም ስለሆነ እኛ ጋር ሲመጣ ግን ጌታን ብለሽ ምን አገኘሽ በማለት እግዚአብሄርን መምሰል በራሱ ማትረፊያ እንዳልሆነ ሌላ ትርፍ እንደሚያስፈልገው ይዋሻል፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሄርን መምሰል በላይ የክብር ደረጃ እንደሌላ ያውቃል እኛ ጋር ግን ሲመጣ እግዚአብሄርን መምሰል የማትረፊያ መንገድ እንጂ በራሱ ትርፍ እንዳልሆነ በክፋት ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡ ሰይጣን እግዚአብሄርን ከመምሰላችን በላይ የሚረብሸው ነገር የለም ነገር ግን ወደእኛ ሲመጣ እግዚአብሄርን መምሰል ያጣጥለዋል፡፡ ሰይጣን ወደ እኛ ሲመጣ ግን እግዚአብሄርን መምሰል በራሱ ግብ እንዳይደለ ግን ወደግብ መድረሻ መንገድ ብቻ እንደሆነ ሊያሳምነን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

በመፅሃፈ አስቴር ውስጥ ሃማ ለቤተሰቦቹ እንዴት ንጉሱ እንዳከበረው ዘርዝሮ ነገራቸው፡፡ ነገር ግን አለ መርዶኪዮስ ሳይሰግድለይት ባለመናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ያ መርዶኪየፐስ እያለ ምን ክብር ይሆንልኛል ብሎ ተናገረ፡፡

በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ። ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ልኮም ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠራ። ሐማም የሀብቱን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ንጉሡም ያከበረበትን ክብር ሁሉ፥ በንጉሡም አዛውንትና ባሪያዎች ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው። ሐማም፦ ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ። ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንምን አይጠቅምም አለ። አስቴር 5፡9-13

ሰይጣንም እንደዚሁ ነው አከሌን አስገዝቻለሁ እከሌ በእኔ ቁጥጥር ስር ነው ነገር ግን እከሌ ኢየሱስን እየተከተለ ምን ይጠቅመኛል ነው፡፡ ሰይጣን የእኛ እግዚአብሄርንም መምሰል ለእርሱ ፍፁም ሽንፈት እንደሆነ ያውቃዋል፡፡

ሰይጣን ግን ወደእኛ ሲመጣ ስለእኛ እግዚአብሄርን መምሰል የሆነ ተጨማሪ ጥቅም ካላስገኘልን እንደሳትን ነው የሚከሰን፡፡ ሰይጣን እኛጋ ሲመጣ እሺ ክርስትያን ሆነህ ምን አገኘህ ክርስትናህ ምን ጠቀመህ ነው የሚለው፡፡ መልሱ ግን ክርስትናዬ ራሱ ጥቅም ነው፡፡ ክርስትናዬ ሙሉ እንዲሆን በብዙ ገንዘብ እና በዝና መጣፍ የለበትም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል የመጨረሻ የክብር ጣራ ነው፡፡

የክርስትና የመጨረሻው ደረጃ ቢሊየነርነት ወይም ትሪሊየነርነት በመሰረታዊ ፍላጎት ረክቶና ራስን አማጥኖ ጌታን መከተል ነው፡፡

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ማትረፊያ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እንኳን ለጥምቀት ህይወት አደረሳችሁ

36759-baptism.630w.tn.jpgጥምቀት በአመት አንድ ቀን የምናስታውሰው በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ህይወት ነው፡፡ ጥምቀት የክርስትና ህይወይ ዘይቤ ነው፡፡

ኢየሱስ የሞተውና የተነሳው ስለእኛ ሃጢያት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተውና የተቀበረው እኛን ወክሎ ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተውና የተቀበረው በእኛ ፋንታ ነው፡፡

ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እንደሞተና እንደተቀበረ እውቅና ስንሰጥ በውሃ እንጠመቃለን፡፡ በውሃ የመጠመቃችን ትርጉሙ ኢየሱስ ስለእኛ እንደሞተ እንደተቀበረ ማሳይ ነው፡፡ በውሃ የመጠመቃችን ትርጉሙ ኢየሱስ ስለሃጢያቴ እንደሞተልኝ እኔም ለሃጢያትና ለአለም ክፉ ምኞት ሞቻለሁ ማለት ነው፡፡

ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ሮሜ 6፡3

በውሃ ስንጠመቅ ከውሃ ስር እንድምንሆንና ውሃው እኛንና ሌላውን አለም እንደሚለይ ሁሉ የጥምቀት ምሳሌነቱ ከሃጢያት መገላገላችንና መለያየታችን ሃጢያት እንደማይገዛንና ከሃጢያት ሃይል ነፃ መውጣታችን ማሳያ መንገድ ነው፡፡

እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሮሜ 6፡4

ጥምቀት ከሃጢያት ሃይል ነፃ የወጣንበት የእግዚአብሄር አሰራር እንጂ የሃጢያት በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ቅድስናን የተቀበልንበት የእግዚአብሄር አሰራር እንጂ ሃጢያት የሚነግስበት በአል አይደለም፡፡ ጥምቀት ከሃጢያት ሃይል ነፃ የወጣንበት አሰራር እንጂ ሃጢያት የሚስፋፋበት በአለ አይደለም፡፡ ጥምቀት እግዚአብሄር የሚፈራበትና የሚከበርበት በአል እንጂ የሰይጣን ስራ ሃጢያትና እርኩሰት የሚስፋፋበት በአል አይደለም፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥምቀት #ሞት #ትንሳኤ #መቀበር #አዲስህይወት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እግዚአብሔርን የሚመስሉ የሚሰደዱበት ምክኒያት

inline_image_preview.jpgበእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡12

እግዚአብሔርን መስለው ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ፡፡ የስደቱን ምክኒያት ማወቅ በስደት እንድንፀና ያስችለናል፡፡

ህይወታችን እንግዳ ስለሚሆን ነው፡፡

እግዚአብሔርን መምሰላችን የሚታወቀው አስተሳሰባችን ፣ አነጋገራችን ፣ ፍቅራችንና ኑሮዋችን ለአለም እንግዳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች የለመዱት ስለስጋ ማሰብን ነው፡፡ ከጠዋት እስከማታ ስጋቸውን እንዴት እንደሚያስደስቱ ያስባሉ፡፡ እኛ ደግሞ እግዚአብሄርን በኑሮዋችን እንዴት እንደምናስደስተው የመንፈስን ነገር እናስባለን፡፡ የእነርሱ ፍላጎትና የእኛ ፍላጎት እጅግ ይለያያል፡፡ እነርሱ ዋጋ የሚሰጡትን ነገር እኛ እንንቀዋልን፡፡ ስለዚህ ይቃወሙናል ያሳድዱናል፡፡

እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ሮሜ 8፡5-6

አለምን ስለማንመስል ከአለም ስለምንለይ ነው፡፡

በአለም ያለው ባህል በስጋ ምኞት መመራት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚመስል ሰው የሚመራው በመንፈስ ፍቃድ ነው፡፡ አለምን ስለማንመስል በዚህም ከሰዎች ስለምንለይ ከሌላ አለም እንደመጡ ሰዎች እንደ እንግዳና መጤ በመታየታችን እንሰደዳለን፡፡

ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሃንስ 2፡15-16

ብርሃናችን ጨለማውን ስለሚገልጠው ነው

በብርሃን ስንኖር ጨለማውን እንገልጠዋለን፡፡ ሃጢያትን የሚወዱ ሰዎች ደግሞ ጨለማቸው ሲገለጥ ደስ አይላቸውም፡፡ ስለዚህ ይቃወሙናል ያሳድዱናል፡፡

ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ ዮሃንስ 3፡19-20

ከፍ ያለው ህይወታችን ሲያዩ ስለሚሳቀቁ ነው፡፡

እግዚአብሔር የሚመስሉ ሰዎች የሚሰደዱት ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ስለሚኖሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሃጢተያት ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ውርደት ያጋልጣል፡፡ ክርስትና ምንም የሚወጣለት ነገር የለም ፡፡ እግዚአብሔርን መምሰል ምንም አይወጣለትም፡፡ እግዚአብሔርን በመምሰል በንፅህና የሚኖር ሰው ሲያዩ አለማዊያን ጉድለታቸ ይታያቸዋል፡፡ ንስሃ ገብተው ተዋርደው እነርሱም እግዚአብሔርን ለመምሰል እስካልወሰኑ ድረስ በቅናት እግዚአብሔርን የሚመስሉትን ይቃወማሉ ያሳድዳሉ፡፡

የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና። በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡3-4

ወደመንግስተሰማያት አትሄዱም የሚል መልክት ስለሚሰጣቸው ነው፡፡

እግዚአብሄርን መፍራታችን እነርሱ አለመፍራታቸው ያስፈራቸዋል፡፡ በንፅህና መኖራችን እነርሱ በንፅህና አለመኖራቸው ያሳቅቃቸዋል፡፡ የኑሮዋችን ንፅህናን አይተውና የእነርሱን ኑሮ አይተው በራሳቸው እኔስ ወደ መንግስተሰማያት አልሄድም ብለው በራሳቸው ይፈርዳሉ፡፡ ኑሮዋችን ተመልሱ በእንደዚህ አይነት ኑሮ ወደ መንግስተሰማያት አትሄዱም ብሎ በዝምታ ይወቅሳቸዋል፡፡

በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡14-16

ሰይጣን ስለማይታገሰን ነው፡፡

ሰይጣን የእግዚአብሔር ጠላት የህይወት ጠላት የእኛ ጠላት ስለሆነ የእግዚአብሔርንመለክ በምድር ከላይት ማየት አይፈልግም፡፡  ሃብታም ብንሆን ወይም ዝነኛ ብንሆን ሰይጣን አይደንቀውም እግዚአብሔርን መምሰላችን ግን እረፍት አይሰጠውም፡፡ ሃብታችንን ግን እግዚአብሔርን መምሰል ላይ ካዋልነው አይታገሰውም፡፡

ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። 1ኛ ዮሃንስ 5፡19

እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። ዮሃንስ 8፡ 44-45

ያም ሆነ ይህ ሰይጣን ስለፈቀድል “አስኮናኞች ኑሩ” ስላለን ሳይሆን የምንኖረው በግድ ነው፡፡ ሰይጣን ወደደም ጠላም በአሸናፊነት እንኖራለን፡፡

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #ስደት #መከራ #ብርሃን #ጨለማ #ንፅህና #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በተግባር እግዚአብሔርን መምሰል

34554-womanpraising-praise-prayer-worship.1200w.tn.jpgእግዚአብሔርን መምሰል እንደ እግዚአብሔር ማሰብ ነው

አንድ ሰው ሲናገር የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው እንደእግዚአብሔር ያስባል በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ማሰብ እግዚአብሔርን እንደምንመስል እንዴት እንደሚረዳን ተናገረ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2

በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ኤፌሶን 4፡23-24

እግዚአብሔርን መምሰል እግዚአብሔር እንደሚያየው ማየት ነው

እግዚአብሔርን የምንመስለው በእይታችን ነው፡፡ አግዚአብሔር የሚያየውን ካየን እግዚአብሔርን እንደምሳለን፡፡ የእግዚአብሔር እይታ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ የእግዚአብሔር እይታ የእግዚአብሔር ቃል እይታ ነው፡፡ ነገሮችን እንደእግዚአብሔር ቃል ካየን እግዚአብሔር የሚየየውን በማየት እግዚአብሔርን እንመስላለን፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያየው ካላየን እግዚአብሔርን መምሰል በፍጹም አንችልም፡፡

እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-7

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17

እግዚአብሔርን መምሰል እግዚአብሔር እንደሚወደው መውደድ ነው

የእግዚአብሔር ፍቅር የእንካ በእንካ ፍቅር አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚሰጥ የሚያካፍል የሚራራ ጠላቶቹን የሚወድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለመምሰል በፍቅሩ እርሱን መምሰል አለብን፡፡

የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ማቴዎስ 5፡46-48

ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። 1ኛ ዮሃንስ 4፡11-12

እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ ኤፌሶን 5፡1

እግዚአብሔርን መምሰል እግዚአብሔር እንደሚናገረው መናገር ነው፡፡

ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ . . . ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 1ኛ ጴጥሮስ 4፡11

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር

Hawaii-Beach-Wallpaper-HD.jpgእግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡

እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡26-27

ሰው በሃጢያት ምክኒያት ያጣው በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነገር የእግዚአብሄርን መልክና ክብር ነው፡፡

ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ሮሜ 3፡23

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በሃጢያት ምክኒያት የጠፋውን የእግዚአብሄርን መልክ ለመመለስ ነው፡፡

ኢየሱስን የተቀበልን ሁላችን ከሁሉም ነገር በላይ አላማችን እና ግባችን እግዚአብሄርን መምሰል መሆን አለበት፡፡

የእግዚአብሄር ፀጋ ለሁላችን የተዘጋጀው እግዚአብሄርን እንድንመስል ነው፡፡

ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ ቲቶ 2፡11-13

እግዚአብሄርን እንድንመስል የሚያስፈልገን ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

የማንኛውም አገልጋይ ተልእኮ ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲመስሉ ማስተማርና መርዳት ነው፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ የተላከው ሰዎችን እግዚአብሄርን ወደ መምሰል እንዲመራ መሆኑን ስለአገልግሎቱ ይመሰክራል፡፡

የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ቲቶ 1፡1

መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስጠነቅቀው የአምልኮ መልክ ያላቸውን ሃይሉን ግን የካዱትን ነው፡፡

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡5

እግዚአብሄርን መስለው የሚኖሩ ሰዎች እንደሚሰደዱ መኝሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ እግዚአብሄርን መሰለው ለሚኖሩ ሰዎች ነገሮች ቀላል አይሆኑም፡፡

በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡12

እግዚአብሄርን መምሰል ነገሮችን የማግኛ መንገድ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል የመጠቀሚያ መንገድ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል በራሱ ግብ ነው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል ወደ ጥቅም መሸጋገሪያ መንገድ ሳይሆን ራሱ ጥቅም ነው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰል ወደ እድል መተላለፊያ መንገድ ሳይሆን ራሱ እድል ነው፡፡

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የእግዚአብሔር ምስል

Publication1.jpgእግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር እርሱን የመሰለ እንደ እርሱ አድጎ ምድርን እንዲያስተዳድራት ሰውን በመኩና በአምሳሉ ፈጠረ፡፡

አዳም ሃጥያትን በመስራቱ የተነሳና አታድርግ የተባለውን ያንኑ ነገር በማድረግ በእግዚአብሄር ላይ ስላመፀ የእግዚአብሄርን መልክ አጣው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰሉ በሃጢያት ምክኒያት ተበላሸ፡፡

እግዚአብሄር በሰው ህይወት ላይ መልኩን የመመለስ አላማውን አልቀየረውም፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር አላማ ሰውን ወደ እግዚአብሄርን መምሰል መመለስ ነው፡፡

የእግዚአብሄር በሰዎች ላይ ያለው ብቸኛ አላማ ሰው ተመልሶ እግዚአብሄርን መስሎ እንዲኖር ነው፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ሰዎች ከሃጢያት ባርነት ነፃ ወጥተው እግዚአብሄርን የመምሰል ነፃነት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡

ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ ቲቶ 2፡12-13

ብዙ ሰዎች ለብዙ አይነት ጥቅም ህይወታችውን ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን ከመምሰል በላይ ጥቅምና ሐብት የለም፡፡ እግዚአብሄርንም ከሁሉም ነገራችን በላይ እርሱን መምሰላችን ያስደስተዋል፡፡

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6

ሰይጣን በምንም ብልፅግናችን ፊት ለፊት ላይላተመን ይችላል እግዚአብሄርን መልክ በእኛ ውስጥ ሲበዛ ሲያይ ግን ያንገሸግሸዋል፡፡ ሰይጣንም ምንም ስኬታችን ላያስደነግጠው ይችላል እግዚአብሄርን መምሰላችንን ግን ሊቋቋመው አይችልም፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሄር መልክ የሚታይባቸውን ሰዎች የተለያየ ዘዴ ተጠቅሞ የሚያሳድደው፡፡

በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡12

የክርስትና ትርፋችን እግዚአብሄርን መምሰል መሆኑን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ እግዚአብሄርን ከመምሰል በላይ ክብር የለም፡፡

እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16

ፀሎት

እግዚአብሄር ሆይ ስለሰጠኸኝ ቃል አመሰግንሃለሁ፡፡ ቃልህን ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በህይወቴ የአንተ አላማ የራስህን ምስል ማየት መሆኑን መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ቃልህን በመስማትና በመታዘዝ አንተን ለመምሰል ራሴን እሰጣለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ሰዎች የሚከተሉዋቸውን አንተን እንድመስል የማይረዱትን ነገሮች ሁሉ እንቃለሁ፡፡ አንተን እንድመስል የሚያደርጉትን ነገሮች ሁሉ ዋጋ ቢያስከፍለኝም ለማድርግ ራሴን እሰጣለሁ፡፡ ጌታ ሆይ አንተን እንድመስል እየሰራኽኝ ስለሆነ አመሰግንሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው

10286_1661478280743686_67154726575587222_n.jpgመኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡27

መኖሪያችን ገንዘባችን አይደለም፡፡

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ሉቃስ 12፡15

መኖሪያችን እውቀታችን አይደለም፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤   ኤርምያስ 9፡23

መኖሪያችን ፍጥነታችንና ቅልጥፍናችንም አይደለም፡፡

እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11

መኖሪያችን ሃይላችንና ብርታታችን አይደለም፡፡

መልሶም፦ ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ ዘካርያስ 4፡6

መኖሪያህ የምህረት አምላክ እግዚአብሄር ነው፡፡

ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡24

መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ዘዳግም 33፡27

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መኖሪያህእግዚአብሄር #እውቀት #ጥበብ #ሃይል #ክርስትያን #አማርኛ #ፍጥነት #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ፅድቅ #ፍርድን #ምህረት #ስልጣን

ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ

publication122አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። መዝሙር 132፡1-6
ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። 1ኛ ዜና 29፡3
እግዚአብሄር እንደልቤ ያለው በዘመኑ የእግዚአብሄርን ሃሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ የተባለለት ሰው ነው-ዳዊት፡፡ ዳዊት እንደልቤ ያስባለውን ስለ እግዚአብሄር ቤት ያለውን ቅናት በሚናገረው ንግግሩና በድርጊቱ በቀላሉ ልንመለከት እንችላለን፡፡
ዳዊት ንጉስ ነው፡፡ ነገር ግን ለእግዚአብሄር ቤት ስራ የሚሆነውን ዛፍ ለመምረጥ በዱር ውስጥ ይዞር ነበር፡፡ ዳዊት የእግዚአብሄርን ስራ እስከሚሰራ አያርፍም ነበር፡፡ እጅግም ይተጋ ነበር፡፡
ዳዊት የሚያደርጋቸው ነገሮች ለቤቱ ስራ ያለውን ቅናት ያሳያል፡፡ ሲፀልይም የዳዊትን ገርነቱን መሰጠቱን ትጋቱን አስብ ይል ነበር፡፡ ገርነትና ለእግዚአብሄር ስራ ራስን መካድ እግዚአብሄር በእርግጥ የሚከፍለው ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ገርነትን አይቶ አያልፈውም፡፡
ለእግዚአብሄር በነገር ሮጦ የሚበዛ እንጂ ሊከስር የሚችል ሰው የለም፡፡ በመስጠት እግዚአብሄርን አንበልጠውም፡፡ ለእግዚአብሄር በመስጠት እግዚአብሄርን አናስደነግጠውም፡፡
ዳዊት ለእግዚአብሄር ቤት ስራ የዋህ ነበር፡፡ ዳዊት በእግዚአብሄር ቤት ስራ ብልጣ ብልጥ አልነበረም፡፡ ለእግዚአብሄር ቤት ስራ የሚሰጠው በስሌት አልነበረም፡፡ ዳዊት ለጌታ በገርነትና በመሰጠት ራስን በመካድ ቆንጠጥ የሚያደርግ ስጦታን ነበር የሚያደርገው፡፡ ዳዊት ጌታን ስለሚወድ ምንም መስዋእትነት ለጌታ ብዙ አይደለም፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡24-25
አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦ በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። መዝሙር 132፡1-6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ገርነት #መሰጠት #የዋህ #ራስንመካድ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው

44265123-beautiful-wallpapers.jpgነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡11 ፣ 1
ምንም ነገር ውብ የመሆን እምቅ ጉልበት ቢኖረውም በእርግጥ ውብ የሚሆነው በራሱ ጊዜ ነው፡፡
የህይወታችን እቅድ ሁሉ ቀድሞውንም በእግዚአብሄር ዘንድ አለ፡፡ እግዚአብሄር የህይወት ንድፋችንን የሚሰራው በየጊዜው የምንፀልየውን የፀሎት ርእስ ሰብስቦ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን የሚሰራበትን ሃሳብ በየጊዜው አንሰጠውም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ለእግዚአብሄር በትልቁ አናልምለትም፡፡ ወይም በጥሩ ሃሳብ እግዚአብሄርን አናስደንቀውም፡፡
የእያንዳንዳችን የህይወት እቅድ በእግዚአብሄር ዘንድ ቀድሞውንም አለ፡፡ ወደዚህ ምድር የተወለድነው በምድር ላይ ልንሰራ ያለው የተለየ ነገር ስላለ ነው፡፡
ስለተወለድንበት የህይወት እቅድና ዲዛይን መሰረት እግዚአብሄር በህይወታችን እየሰራ ነው፡፡ እኛ ማድረግ የምችለው የተሻለ ነገር እግዚአብሄር በህይወታችን በጊዜው የሚሰራውን ተከትለን አብረነው መስራት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሐንስ 5፡17
እግዚአብሄር የሚሰራውን ስራ ሁሉ የሚሰራው በጊዜውና በዘመኑ ነው ፡፡ እግዚአብሄር አይቸኩልም፡፡ እግዚአብሄር በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለመስራት አይሞክርም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን አንድን ነገር የሚሰራበት የራሱ ዘመንና ጊዜ አለው፡፡ በሰማይ እኛ እንዳለን አይነት ዘመንና ጊዜ የለም፡፡ ሰማይ በእኛ አይነት ዘመንና ጊዜ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከሰማይ በታች ያለው ነገር ሁሉ ግን በጊዜና በዘመን ውስጥ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
· ትላንት
ትላንት አልፎዋል ያንተም አይደለም፡፡ ባለፈው ስኬትህም ሆነ ውድቀትህ በፍፁም አትያዝ፡፡ ጆይስ ሜይር ስታስተምር በትላልቱ ላይ በጣም የሚቆይና በጣም የሚያሰላስለው ሰው ከነገ ይበልጥ ትላንት ይሻላል እያለ ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ በትላንትህ ላይ በጣም የምታተኩር ከሆንክ ሳታውቀው ትላንት እንደገና ትኖረዋለህ፡፡ ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። መክብብ 7፡10
ትላንትን ግን መኖር የለብህም፡፡ እግዚአብሄር ላንተ ዛሬ አዲስ ነገር አለው፡፡ ከዛሬ ይልቅ ትላንት በፍፁም አይሻልም፡፡
ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22-23
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ፊልጵስዩስ 3፡13
· ዛሬ
ያለህ እድል ዛሬ ነው፡፡ ለመስራት ለመሮጥ ለመድከም ለመትጋት ያለህ እድል ዛሬ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ መስራት ያለብህን ነገር ለነገ አታስተላልፍ፡፡
አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። መክብብ 9፡10 ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። መዝሙር 27፡1
ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። ዮሃንስ 9፡4
ደስታህንም ለነገ አታስተላልፍ፡፡ ደስተኛ ለመሆን በፍፁም ነገን አትጠብቅ፡፡ ደስተኛ ለመሆን በህይወትህ የሆነ ነገር እስኪሆን አትጠብቅ፡፡ ነገ እንዲሆኑልህ የምትፈልጋቸ ነገሮች በጊዜው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዛሬን ግን ባለህበት ደረጃ አክብረህ ተደስተህበት ካላከለፍክ ተመለሰህ አታገኘውም፡፡ ጊዜ ወደኋላ ተመልሶ አይጠነጠንም፡፡
ህይወት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ዛሬ እንድንደሰትበት የተሰጠን ስጦታም ነው፡፡ በህይወት ተደሰትበት፡፡ ስለነገ ተስፋ ብለህ ዛሬን አታጣጣል፡፡ ዛሬ ባለበት ደረጃና ሁኔታ ልንደሰትበት የሚገባ እግዚአብሄር ክቡር ስጦታ ነው፡፡
ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መክብብ 3፡12-13
· ነገ
ነገ የራሱ ጊዜና ዘመን አለው፡፡ የነገን ስራና ሃላፊነት ደግሞ ዛሬ ለመስራት አትሞክር፡፡ የዛሬን ስራ ሰርተህ ዘና በል፡፡
የነገን ስራ በዛሬ ጉልበት ልንሰራው ስንሞክር ስለማንችለው ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ዛሬ እንደተራራ የሆነብህን በነገ ጉልበት ግን ትገፋዋለህ፡፡ ጊዜ አለህ እስከ ነገ ታገስ፡፡ ዛሬ የማይለቀቅ ሲነጋ ብቻ የሚለቀቅ እምነትና ፀጋ አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆነህ ስለነገ አትፍራ፡፡ ዛሬን ብቻ በትክክል መኖርህን እርግጠኛ ሁን፡፡ ለነገ አትጨነቅ፡፡ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ ወንጌል 6፡34
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡11 ፣ 1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

የሚበልጥ የባህሪ ለውጥ

Publication2.jpgእግዚአብሄርን መምሰል ወይም መንፈሳዊ ባህሪ ከእግዚአብሄር ጋር ኖረንና ቃሉን ታዘን በትእግስት በህይወታችን የምንገነባው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ትክክለኛ የትጋታችን ውጤት የባህሪያችን መሰራት ነው እንጂ በህይወታችን ያለው ስጦታ እንዳልሆነ መፅሃፍ ቅዱሳችን ያስተምረናል፡፡
ባህሪያችን የራሳችን መንፈስ ፍሬ ነው፡፡ ስጦታ ግን ሰጭው እንደ ወደደ የሚሰጠንና የምንቀበለው ነገር ነው፡፡ ባህሪያችን እንደ ዛፍ ፍሬ ሲሆን ከችግኝነት ጀምሮ አድጎ ተጠብቆ በትጋት የሚያፈራ ሃብት ነው፡፡ ስጦታ ግን የገና ዛፍ ላይ እንደሚንጠለጠር ከረሜላ እና ቸኮላት ነው፡፡
በእርግጥም ደግሞ የሰውን ብስለት የሚናገርው ባህሪው እንጂ ስጦታው አይደለም፡፡ የሰውን መስዋእትነት ፣ መታዘዙን ፣ የሰውን ለጌታ መሰጠት የሚናገረው ባህሪ እንጂ ስጦታ አይደለም፡፡
ስጦታችን እንደ ድግስ ቤት ምግብ ሲሆን ባህሪያችን ግን የራሳችንን ሙያ ማደግ የሚያሳይ ሽንኩርት ከመክተፍ ጀምረን በቤታችን የምናበስለው ምግብን ይመስላል፡፡ የድግስ ቤት ምግብ የእኛን ታማኝነትና ትጋት የማይጠይቅ የሌላ ሰውና ጊዜያዊ ስጦታ ነው፡፡ የራሳችን የምግብ ሙያ ግን በፈለግን ጊዜ የምንጠቀምበት ሁሌ አብሮን የሚኖር የራሳችን ሃብት ነው፡፡ እግዚአብሄር ስጦታን ለመስጠት ሰከንድ አይፈጅበትም፡፡ ስጦታውን እንደ እግዚአብሄር ልብ በትክክል የምናስተዳድርበትን ባህሪያችን ለመሰራት ግን ወራትና አመታት ይፈጅብናል፡፡
ከሃብቱ ይልቅ ባህሪው ስለሚበልጥ ጌታ ሃብቱን ከመስጠቱ በፊት አስተዳዳሪውን ለመስራት ይፈልጋል፡፡ ሃብቱን የሚያስተዳድረውንም ሰው ለመስራት እና ለመቅረፅ እግዚአብሄር ጊዜ ወስዶ ይተጋል፡፡
  • ከምቾታችን ይልቅ የባህሪያችን መሰራት ይበልጣል እግዚአብሄር እምነታችን እንዲፈተን የሚፈቅደው መከራው እኛን ስለማያገኘንና እግዚአብሄርን የሚያሳዝነውን የስጋችንን ባህሪ ከእኛ ለማስወገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር በመከራ ውስጥ እንድንታገስ የሚፈልገው በባህሪ ሙሉ ሰዎች እንድንሆን ለማድረግ ነው፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ያዕቆብ 1፡2-4
ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ ሮሜ 5፡3-4
  • ከሃብታችን ይልቅ ባህሪያችን ይበልጣል እግዚአብሄር ሃብታችንን ከመጨመሩ በፊት በታማኝነት ማደጋችንን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ በታማኝነት ባደግን መጠን ሃብታችን ይበዛል፡፡
ሃብቱን የሚሸከመው ልባችን ካልሰፋና በባህሪ ካላደግን በስተቀር ሃብቱም ቢመጣም ሃብቱን የምንይዝበት ልቡ ስለሚጎድለን ፈጥኖ ይበተናል፡፡ ዘይቱን የሚይዘው ገንቦ ቀዳዳው ካልተደፈነ የሚቀመጥበት ዘይት ፈስሶ ያልቃል፡፡ ለሚፈለገውም አላማ መዋል አይችልም፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም። ምሳሌ 20፡21
  • ከስጦታችን ይልቅ በባህሪ ማደጋችን ይበልጣል
ምንም ድንቅ ስጦታ ቢኖረን በፍቅር መነሻ ሃሳብ /ሞቲቭ/ ካላደረግነው አይጠቅምም፡፡ ምንም አገልግሎት ቢኖረን በፍቅር ካልተመራ ለትክክለኛው አላማ መዋል አይችልም፡፡
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡1-3፣13
  • ከውጭ ውበታችን ይልቅ የባህሪያችን ውበት ይበልጣል
የውጭው ውበታችን ጊዜያዊ ነው፡፡ የውስጥ ውበታችን ግን ዋጋው እጅግ የከበረና ዘላቂ ነው፡፡
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
%d bloggers like this: