Category Archives: Judge

ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር

conscious.jpgራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡31

በሌላ ሰው እጅ ከመውደቅ ይልቅ ቀላሉ በራስ እጅ መውደቅ ነው፡፡ በሌላ ሰው ከመፈረድ የሚቀለው ራስ ላይ መፍረድ ነው፡፡ ሌላ ሰው ከሚቀጣን ራሳችንን መቅጣት ይቀላል፡፡

እግዚአብሄር የመርህ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብሮ የማይኖራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ክፋት መፈረዱ አይቀርም፡፡ ትእቢት መዋረዱ አይቀርም፡፡ ትእቢት መዋረዱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ክፋት መፈረዱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀር ነው፡፡

የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። የሉቃስ ወንጌል 8፡17

ሰው በእግዚአብሄር እንዳይጣል ስጋውን መጎሸም አለበት፡፡ ሃዋሪያው በእግዚአብሄር ከሚፈረድበት ይልቅ ራሱ ስጋው ላይ መፍረድን መርጧል፡፡

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27

በተለይ ደግሞ እግዚአብሄር እጅ ከመውደቅ እና በእግዚአብሄር ከመዋረድ ራስን ማዋረድ ይሻላል፡፡

እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡6

በሌላ ሰው ከማዋረድ ራስን ማዋረድ ይቀላል፡፡ በሌላ ሰው ከመጋፈጥ ራስን መጋፈጥ ይቀላል፡፡ በሌላ ሰው ከመፈተሽ ራስን መፈተሽ ይቀላል፡፡ ሌላ ሰው ከሚያየን ራሳችንን ማየት ይሻላል፡፡ ሌላ ሰው ከሚገዳደረን ራሳችንን መገዳደር ይሻላል፡፡

ስለዚህ ነው ኢየሱስ ፈጥነህ ተስማማ እያለ የሚያስተምረው፡፡

አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤

አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም። የማቴዎስ ወንጌል 5፡25-26

ራስን መርምሮ በድብቅ ራስን ማስተካከል የመሰለ ነገር የለም፡፡ ልብን መርምሮ ንስሃ መግባትን የመሰለ ነገር ጣፋጭ ነገር የለም፡፡ ራስን ማዋረድን የመሰለ ፍሬያማነት የለም፡፡

ራሳችንን ካላዋረድን የምንዋረድበት መድረኩ እየሰፋ ነው የሚሄደው ፡፡ ራሳችንን ካላዋረድን የምንዋረድበት መዋረድ እየከፋና እየመረረ ነው የሚሄደው፡፡

ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። የማቴዎስ ወንጌል 18፡15-17

በድብቅ ራሳችንን መርምረን ካልተመለስን በወንድማችን ፊት መዋረድ ይሻላል፡፡ ወንድማችን ፊት ካልተዋረድን በሁለት ወይም በሶስት ምስክር ፊት እንዋረድ፡፡ እምቢ ካልን ግን በቤተክርስትያን ፊት እንዋረዳለን፡፡ በቤተክርስትያን ፊት ካልተዋረድን ደግሞ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ በመሆን እንዋረዳለን፡፡

ከዚህ ሁሉ የሚቀለው የውርደታችንን አድማስ የሚያጠበው ራሳችንን ማዋረድ ነው፡፡ በራሳችን ፊት ለመዋረድ ከፈቀድን ፍሬያችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ በራሳችን ፊት ለመዋረድ ግልፅ ከሆንንና ጊዜ ከሰጠን ለእግዚአብሄር የምንጠቅም የክብር እቃዎች እንሆናለን፡፡

ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡ ለራሳችን ታማኝ ከሆንን ራሳችንን ስራችንን እናውቀዋለን፡፡ ለራሳችን ታማኝ ከሆንን ስራችንን እንደ እግዚአብሄር ቃል እንመዝነዋለን፡፡ ለራሳችን ታማኝና ግልፅ ከሆንን ያደረግነውን ነገር ያደረግነው በምን መነሻ ሃሳብ /motive/ ሞቲቭ መሆኑን እናውቀዋለን፡፡

አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡3-4

ከሰው ፊት ከዋረድ ሁሉ ደግሞ የከፋው በእግዚአብሄር መዋረድ ነው፡፡ በሰው ከመፈረድ የከፋው በእግዚአብሄር መፈረድ ነው፡፡

በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ወደ ዕብራውያን 10፡30-31

ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡31

ፀሎት

እግዚአብሄር ሆይ ስላስተማርክኝ ትምህርት አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ለአንተ ብቻ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ራስን የመመርምር እና የመመለስ የሰጠኸኝን እድል መጠቀም እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ሰው እኔን ከማዋረዱ በፊት የውርደቴ አድማሱ ከመስፋቱ በፊት ራሴን ለማዋረድ ራሴን ለመመርመር ጊዜ እሰጣለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ራሴን ለመመርመር ታማኝ እሆናለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ በአንተ ከመዋረድ አስቀድሜ ራሴን አዋርዳለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ራሴን ለመመርመር ስለሰጠኸኝ እድል አመሰግንሃለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #ራስንማዋረድ #ራስንመመርመር #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ

conscious.jpgእንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን፦ ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። ማቴዎስ 7፡1-5

አትፍረዱ ማለት አታመዛዝኑ ማለት አይደለም፡፡ አትፈረዱ ማለት ሳትለዩ ሳትፈትኑ ሁሉን ተቀበሉ ማለት አይደለም፡፡

አትፍረዱ ማለት በክፉ ሃሳብ አትፍረዱ ማለት ነው፡፡

አትፍረዱ ማለት በጥላቻ ፣ በቅናት ወይም በትእቢት ተነሳሰታቸሁ አትፍረዱ ማለት ነው፡፡ የምትጠሉትን ሰው በትክክል ልትፈርዱበት አትችሉም፡፡ በምትጠሉት ሰው ላየ የምትሰጡት የፍርድ አስተያየታችሁ ስለሚበላሽ ትክክለኛ ፍርድን መፍረድ አትችሉም፡፡ የምትጠሉትን ሰው በትክክለኛ መነፅር ማየት አትችሉም፡፡ በቅናት መነፅር የምታዩትን ሰው ደግሞ በትክክለ ልታዩት አትችሉም፡፡ ዝቅ አድርጋችሁ በትእቢት የምታዩት ሰው ላይ የምትፈርዱት ፍርድ ቅን ፍርድ የማይሆነው እይታችሁ ስለደበዘዘ በቀጥታ ማየት ስለማትችሉ ነው፡፡ በፉክክርና በትእቢት የምታዩት ሰው ላይ የሚኖራችሁ አስተያየት እና ፍርድ የተዛበ ነው፡፡

ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? ያዕቆብ 2፡1-4

አትፍረዱ ማለት የምትፈርዱበት ሚዛን ይስተካከል ማለት ነው፡፡

አትፍረዱ ማለት የምትፈርዱበት ሚዛን ካልተስተካከለ በስተቀር የምትፈርዱት ፍርድ ትክክል አይሆንም ማት ነው፡፡ አትፍረዱ ማለት ከራሳችሁ ጥቅም አንፃር ነገሮችን አትመልከቱ ማለት ነው፡፡ አትፍረዱ ማለት ከስጋዊ ፍላጎት አንፃር አትፍረዱ ማለት ነው፡፡ አትፍረዱ ማለት ከመንፈስ ሳይሆን ከክፉ የስጋ ፍላጎት አንፃር አትፍረዱ ማት ነው፡፡

እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። ዮሃንስ 8፡15

አትፍረዱ ማለት በትክክለኛ እይታ ብቻ ፍረዱ ማለት ነው፡፡

አትፍረዱ ማለት በአድልዎ አትፍረዱ ማለት ነው፡፡ አትፍረዱ ማለት በመልክ አትፍረዱ ማለት ነው፡፡ አትድፍረዱ ማለት አይናችሁ እንዳየ አትፍረዱ ማለት ነው፡፡ አትፍረዱ ማለት እግዚአብሄር እንደሚያይ ፍረዱ ማለት ነው፡፡

ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። ዮሃንስ 7፡24

አትፍረዱ ማለት ከእግዚአብሄር ቃል መመዘኛ ውጭ አትፍረዱ ማለት እንጂ በእግዚአብሄር ቃል አትፍረዱ ማለት አይደለም፡፡ አትፍረዱ ማለት በፅድቅ ፍረዱ ማለት እንጂ አትመዝኑ አትፈትሹ አትፍረዱ ማለት አይደለም፡፡

ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤ ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፥ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ ኢሳያስ 11፡3-4

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የችግሩ ስርና መሰረት

your will.jpgወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ 4፡11

ወንድሙን የሚያማ ሰው ችግሩ ወንድሙ ይመስለዋል፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ዋናው ችግሩ ወንድሙ አይደለም፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው የችግሩ ስርና መሰረት ቢጠና ወንድሙ ሳይሆን ወንደሙን የሚያማ ሰው ችግሩ ህጉ ራሱ ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው እውነተኛ ችግሩ ከወንድሙ ጋረ ሳይሆን ከህጉ ጋረ ነው፡፡

ወንደሙን የሚያማ ሰው ህጉን ያማል፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው በቀጥታ ወንደሙን በተዘዋዋሪ ህጉን ያማል፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ህጉ አስቸጋሪ እንደሆነ ፣ ህጉ ቀላል እንዳይደለና ህጉ ለመፈፀም እንደሚከብድ ህጉን እያማው ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው በህጉ ላይ ያለውን ተቀባይነት እያማ ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ህጉ ችግር አለበት እያለ ነው፡፡

ወንድሙን የሚያማ ሰው ህጉን ስለሚያማ ዛሬ ህጉን በተዘዋዋሪ እንደተቃወመው ሁሉ ነገ ደግሞ ህጉን ላይ በቀጥታ ይቃወመዋል፡፡ ወንድሙን የሚያማ በተዘዋዋሪ ህጉን ስለሚያማ እና በተዘዋዋሪ ወንድሙን ስለሚደግፍ ነገ ህጉን ለመቃወም ለራሱ እያመቻቸ ነው፡፡ ዛሬ ወንድሙን የሚያማ ውስጥ ሰው ውስጡን ህጉን ስለሚያማ ህጉን ለመፈፀም አቅም እያጣ ይሄዳል፡፡

በጣም ሰውን የሚያሙ ሰዎችን ስትመለከቱ ብዙ ጊዜ በሚያሙበት በዚያው ነገር ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ምክኒያቱም ሰውን የሚያሙ ሰዎች ያን ወንድም ሃጢያት ያሰራው ያው ስጋ በእነርሱ እንደሚኖር አይረዱትም፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ወንድሙን የሚያማው በትምክት ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ወንድሙን የሚያማው እኔ እበልጣለሁ ከሚል የትምክት ስሜት ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ወንድሙን የሚያማው በጭካኔ ነው፡፡ በርህራሄ ወንድሙን የሚያማ ሰው የለም፡፡ በትህትና ወንድሙን የሚደግፍ የሚያነሳ የሚረዳ እንጂ ወንድሙን እንደ ባዕድ የሚያማ ሰው የለም፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። ገላትያ ሰዎች 6፡1-2

ወንድሙን የሚያማ ሰው ወንድሙ ህጉን እንዲጠብቅ የሚያደረገው ምንም አስተዋፅኦ የለም፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው የቤተሰብነት ስሜት የጠፋበት ሰው ነው፡፡ ወንደሙን የሚያማ ሰው ለቤተሰቡ ህጉን መጠበቅ የሚያደርገው አስተዋፅኦ የለም፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ወንድሙ ህጉን እንዲጠብቅ የሚረዳው ምንም ነገር የለም፡፡

ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።  ገላትያ ሰዎች 5፡13-15

ወንድሙን የሚያማ ሰው ቤተሰቡን እንደ እንግዳ እያየው ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው የወንድሜ ገመና የእኔ ገመና ነው አይልም፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው ከራሱ የቤተሰብ አባል ጋር ከንቱ ፉክክር ውስጥ ገብቶዋል፡፡

አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26

ወንድሙን የሚያማ ሰው ላይላዩን በወንድሙ መውደቅ የተናደደ ይመስላል እንጂ ውስጥ ውስጡን በወንድሙ መውደቅ ደስ ብሎታል፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው በወንድሙ መውደቅ ራሱን ከፍ ሊያደርግ እየሞከረ ነው፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው የወንድሙ መውደቅ የእርሱ መክበር ይመስለዋል፡፡ ወንድሙን የሚያማ ሰው በወንድሙ መውደቅ አብሮ እንደወደቀ አያስበውም፡፡

አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ገላትያ 6፡3-4

የሃሜት አላማ ሌላውን ማንሳት ፣ ሌላውን መጥቀም እና ሌላውን መርዳት አይደለም፡፡ የሃሜት ብቸኛው አላማ ሌላውን ማዋረድ ራስን ማክበር ስለሆነ በእግዚአብሄር ፊት አስፀጸያፊ ነው፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ያዕቆብ 4፡11

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: