Category Archives: grace

እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን

eag.jpgያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ? አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡27-31 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

በአለም የሚያደክም ብዙ ነገር አለ፡፡

ጎበዝ የተባለ ፣ ጠንካራ የተባለና ሃያል የተባለ ሰው በራሱ አይቆምም፡፡ ይወድቃል ብለን የማናስበው ሰው ወድቆ እናገኘዋለን፡፡ ማንም ሰው ላለመውደቅ መተማመኛ የለውም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄርን የሚጠብቁ ሰዎች አይደክሙም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የሚራመዱ ሰዎች በድካም አይሸነፉም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የሚኖሩ ሰዎች ከድካም በላይ ናቸው፡፡ ሰው ሳይደክም እንደበረታ የሚኖረው እግዚአብሄርን ሲጠብቅ ብቻ ነው፡፡ ሰው ከድካም በላይ የሚኖረው ከእግዚአብሄር ጋር ሲራመድ ብቻ ነው፡፡

ሰው ሃይሉን የሚያድሰው እግዚአብሄርን ካልቀደመው ነው፡፡ ሰው ሃያል የሚሆነው በእግዚአብሄር ፍጥነት ለመኖር ራሱን ትሁት ካደረገ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ከኖረ የእግዚአብሄር ሃይል በእርሱ ላይ ይሆናል፡፡ ሰው በራሱ ከሮጠ ይደክማል ይወድቃል፡፡

እግዚአብሄር የሚያነሳበት ጥበብ አለው፡፡ አግዚአብሄር የሚያሻግርበት መንገድ አለው፡፡ እግዚአብሄር የሚክስበት መንገድ አለው፡፡ እውቀት በሌለን ነገር በእግዚአብሄር ልንታመንና ልንደገፍ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሄርን አሰራር ልንታገስ ይገባል፡፡ የእግዚአብሄርን ፍጥነት ልንጠብቅ ይገባናል፡፡

ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡27-31

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #መጠበት #መተማመን #እምነት #ያድሳሉ #ይወጣሉ #አይደክሙም #አይታክቱም #እግዚአብሔር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል

grace abound.jpgእግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9

እግዚአብሄር ሙሉ ነው፡፡ እኛ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት የተቀበልን ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ሙሉ እንደሆነ ሁሉ በነገር ሁሉ ሙሉ ሊያደርገን ይችላል፡፡

ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ ዮሃንስ 1፡14

ሁልጊዜ

እግዚአብሄር ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እኛ እንኳን ንቁ ባልሆንበት ጊዜ እግዚአብሄር ግን ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሰው አይተኛም አያንቀላፋም፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ በስራ ላይ ነው፡፡

ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17

በነገር ሁሉ

እግዚአብሄር ስለዝርዝር ጉዳያችን ግድ ይለዋል፡፡ እኛ አንኳን አንዳንድ ጊዜ ስለምንረሳው ጥቃቅን ጉዳያችን እግዚአብሄር ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ የተሳካለት ስለሆነ እኛ ልጆቹ በነገር ሁሉ እንዲሳካልን ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን ስላለው ስለእያንዳንዱ ሃላፊነት ሁሉ ጌታ ግድ ይለዋል፡፡ ይህ አይመለከተኝም የሚለው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ብቃትን ሊያበዛልን ይችላል፡፡

አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። ሉቃስ 12፡6-7

ብቃትን ሁሉ

ህይወት ብዙ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ህይወት አንድ መልስ የለውም፡፡ የተለያየ የህይወት አቅጣጫ የተለያየ መልስ ይፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ሃላፊነት ሃይልና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ የትኛው ጥያቄ በሃይል የትኛው ጥያቄ ደግሞ በጥበብ እንደሚመለስ ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርም በምድር ላይ አላማውን በሚገባ እንፈፅም ዘንድ ብቃትን ሁሉ ሊሰጠን ይችላል፡፡

ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ኤፌሶን 3፡10

ለበጎ ስራ ሁሉ

እግዚአብሄር እንድንሰራው ያዘጋጀውን መልካም ስራ ሁሉ መፈፀም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ወደምድር ያመጣን ስራውን ለመፈፀም የሚያስችልን ሃይል አዘጋጅቶ ነው ፡፡ በምድር ስንኖር እግዚአብሄር ካዘጋጀልን በጎ ስራ አንጎድልም፡፡ ለበጎ ስራ ሁሉ የሚያስፈልገው ብቃት በእኛ ውስጥ አለ፡፡ በጎ ስራ ከሆነ ልንፈፅመው እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ላዘጋጀው በምድር ላይ ሰርተን ለምናልፈው በጎ ስራ ሁሉ ብቃቱ አለን፡፡

እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10

ፀጋን ሁሉ

ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ካለሃይል ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ በሃይል ደግሞ ማድረግ የማይቻል ምንም ነገር የለም፡፡ በፀጋ ሁሉም ይቻላል፡፡ በእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል ሁለም ይከናወናል፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ ሁሉ ይሳካል፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡10

እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #እውቀት #ምስጋና #ሁልጊዜ #ልብ #በነገርሁሉ #ብቃትንሁሉ #ለበጎስራሁሉ #ፀጋንሁሉ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በአስሩ የድህነት አስተሳሰብ ምልክቶች ዛሬ ህይወትዎን ይመዝኑ

mindብልፅግና የሚመነጨው ከእግዚአብሄር ሲሆን ድህነት የሚመነጨው ከሰይጣን ነው፡፡ ድህነትም ብልፅግናም የሚያልፈው በሰው አእምሮ ነው፡፡ ሰው የሚበለፅገው አእምሮው ነው፡፡ አእምሮው የበለፀገ ሰው ደሃ መሆን አይችልም፡፡ አእምሮው ደሃ የሆነ ሰው ሊበለፅግ አይችልም፡፡

የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ደሃ ነው፡፡ የብልፅግና አስተሳሰብ ያለው ሰው ባለጠጋ ነው፡፡

በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7

 • ምስኪን እኔ – የድህነት አስተሳሰብ

ሰው ራሱን እግዚአብሄር በክርስቶስ እንደሚያየው ካላየና ሰው በሚታይ ነገር ብቻ ራሱን ከመዘነ ድሃ ሰው ነው፡፡ ድሃ ለመሆን ገንዘብ ማጣት አያስፈልግም፡፡ ገንዘብ ኖሮት የእግዚአብሄር አቅርቦት የማይታየውና የእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል መረዳት የሌለው ሰው አስተሳሰቡ ያልበለፀገ ሰው ደሃ ሰው ነው፡፡

 • እንድበለፅግ ሰው ያስፈልገኛል የሚል የድህነት አስተሳሰብ

እኔን ለማንሳት ሃብታም ሰው ይጠይቃል የሚል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እኔን ለማንሳት የሚያስፈልገው እግዚአብሄር ብቻ ነው የሚል ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ለመበልፀግ ሰው አያስፈልግህም፡፡ ለመበልፀግ የሚያስፈልግህ ባለጠጋውን እግዚአብሄን ማወቅና ከእርሱ ጋር እንዴት መኖር እንዳለብህ መረዳት ነው፡፡ ሰው ግን ለብልፅግናውና ስለ እድገቱ አይኑን ከእግዚአብሄር ላይ ካነሳ ደሃ ሰው ነው፡፡ ደሃ ለመሆን ገንዘብ ማጣት የለበትም፡፡

ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7

 • ያለማመስገን – የድህነት አስተሳሰብ

የማያመሰግን ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄርን ላለማመስገን ምክኒያት የሚያገኝ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ምንም ቢደረግለት የማይበቃው ሰው ደሃ ሰው ነው፡፡ ለአንዳንድ ሰው ምንም ነገር የሚበቃ አይደለም፡፡ ድሃ ሰው ሁል ጊዜ ጎረቤቱን ያያል ፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለበት ሰው ከጎረቤቱ የሚመኘው ነገር አያጣም፡፡ አንዳንድ ሰው እግዚአብሔር በቤቱ የሚሰራውን ድንቅ ስለማያይ አይኑ ወደጎረቤቱ ይቀላውጣል፡፡ ለመኖር እጅግ ብዙ ነው የሚያስፈልገው ደሃ ሰው ነው፡፡ ድሃ ሰው ይህ ይህ ይህ ከሌለኝ ዋጋ የለኝም የሚል አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው፡፡  ድሃ ሰው ምንም ቢሆንለት ምኞት ቱን መቆጣጠር ስለማያውቅ ይሰቃያል፡፡

ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። ምሳሌ 21፡26

ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10

 • ድህነትን መፍራት – የድህነት አስተሳሰብ

አንዳንድ ሰው ድህነትን በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ድሃ ላለመሆን ምንም ነገር ያደርገሃል፡፡ ድህነት የሚያስፈራራህ ከሆንክ ከድህነት ፍርሃት ነጻ መውጣት አለብህ፡፡ ድህነትን የሚፈራ ሰው እግዚአብሔን አይፈራም፡፡ የድህነት ፍርሃት የሚመራው ሰው እግዚአብሄር ሊመራው አይችልም፡፡ ማጣትን አይቶ ምንም እንደማያመጣ የተረዳ ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ድህነትን አልፎበት ልኩን ያየና የናቀው ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ፀጋ እንደሆነ እንጂ በማግኘት እንዳልሆነ የተረዳ ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡

ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡11-12

 • ማግኘትን ማክበር – የድህነት አስተሳሰብ

ሰው ሃብታምም ባይሆን ሃብትን በተሳሳተ መልኩ የሚረዳ ሰው በድህነት እስራት ውስጥ ይኖተራል፡፡ ሃብታም ቢሆን ደስታ እንደሚያስገኝ ማሰብ የድህነት ምልክት ነው፡፡ ሃብት ቢያገኝ እንደሚሳካለት ማሰብ ድህነት ነው፡፡ ሃብት ማድረግ የማይችለው ብዙ ነገር እያለ ሃብት መስራት የማይችለውን ነገር ይሰራል የሚል የተሳተ ግምት ድህነት ነው፡፡ ለሃብት የተሳሳተ ግምት መኖር ድህነት ነው፡፡ እግዚአብር ብቻ የሚሰራውን ነገር ሃብት ይሰራል ብሎ መጠበቅ የድህነት አስተሳሰብ ነው፡፡

እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24

 • ቅንጦት – የድህነት አስተሳሳብ

ደሃ ሰው ራሱን መግዛት ስለማይችል ያለውን ነገር በማያስፈልግ ነገር ላይ ያባክናል፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ያለውን ጥሪት በሚያስፈልገው ነገር ላይ ሳይሆን በምኞቱ ላይ በማዋል ሃብቱን ያባክናል፡፡ ድሃ ሰው ያለውን ነገር በማያስፈልግ በቅንጦት ነገር ላይ ያባክናል፡፡ የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ያለውን ነገር በአላስፈላጊ ነገር ላይ ስለሚያጠፋው በሚያስፈልገው ነገር ይቸገራል፡፡

ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6

 • አልችልም – የድህነት አስተሳሰብ

ድሃ ሰው እችላለሁ የማይል ሰው ነው፡፡ ሁሌ አልችልም የሚል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ የሰጠኝን ስራ ሁሉ ሰርቼ ማለፍ እችላለሁ የሚል ሰው ባለጠጋ ሰው ነው፡፡ ሲደክም እንኳን የእግዚአብሄር ፀጋ ድካሜን ይሸፍናል የማይል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ በመከራ ውስጥ ሲያልፍ እጅ የሚሰጥ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ በድካሜ የእግዚአብሄር ፀጋ ድካሜን ይፈፅመዋል የማይል ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ከራሱ አልፎ የሚያስችልን የእግዚአብሄርን ሃይል የማያይ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡1፣4-5

 • ይቅር አለማለት – የድህነት አስተሳሰብ

ሰው የበደሉትን ይቅር ካላለ ፣ ካልቀቀና የሙጥኝ ካለ ደሃ ሰው ነው፡፡ መበደል የለብኝም ብሎ ካሰበ እና ለመበደል ምንም ቦታ የማይሰጥ ሰው ቋጣሪ ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር በብዙ ይቅር ብሎት ሌላውን ይቅር ማለት የማይችል ደሃ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄን ይቅርታ ውጦ ሌላን ይቅር የማይል ሰው ስስታም ሰው ነው፡፡

ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡32-33

 • አለመስጠት – የድህነት አስተሳሰብ

ሰው የተፈጠረው ለመስጠትና ለመባረከ ነው፡፡ ሃብቱን ራሱ ላይ ብቻ የሚያፈስ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ መሰብሰብ እንጂ መስጠትና መባረክ የማያውቅ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ስለሌላው ግድ የማይለው ሰው ምንም ያህል ሃብት ቢኖረው ድሃ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሰጠው ገንዘብ የዘላለምን ወንጌልን የማይሰራ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ሰው ባለጠግነቱ የሚለካው በሚያከማቸው ሳይሆን ባከማቸው ባለጠግነት በሚሰራው መልካም ስራ ነው፡፡

ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ 12፡21

እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9

በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19

 • አለመተው – የድህነት አስተሳሰብ

የድህነት አስተሳሰብ ያለው ሰው በህይወቱ ለቀቅ ያለ አይደለም፡፡ የእርሱ ነገር ወደሌላ ሰው እንዲያልፍ አይፈልግም፡፡ ለሳንቲምም ቢሆን ይጨቃጨቃል፡፡ መብቱን በፍፁም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ንጥቂያን በቀላሉ አያየውም፡፡ ይሁን አይልም አይተውም፡፡ እኔን ድሃ ሊያደርገኝ የሚችል ሰው የለም አይልም፡፡ እያንዳንዷን ስንጣሪ አንቆ ነው የሚቀበለው፡፡ ይህ ሰው ድሃ ሰው ነው፡፡ ለቀቅ ያለ አስተሳሰብ የለውም፡፡ በውስጡ ባለው በእግዚአብሄር ፀጋ አይመካም፡፡

የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። ዕብራውያን 10፡34

እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ማቴዎስ 5፡40-41

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል  #በረከት #ስኬት #የድህነትአስተሳሰብ #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የፀጋው ክብር

eagle11111111.jpgፀጋ ነፃ ስጦታ ነው፡፡ ፀጋ በነፃ ከእግዚአብሄር የሚሰጥ ችሎታ ነው፡፡ ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ፀጋ የሚያስልች ብቃት ነው፡፡ ፀጋ የሚያስችል ችሎታ ነው፡፡

ፀጋ እግዚአብሄር በህይወታችን እንድንሆን የፈለገውን እንድሆን የሚያስችል ሃይል ነው፡፡

ፀጋ በህይወታቸነ እንድናገኝ የፈለገው ነገር ሁሉ እንድናገኝ የሚያስችል የእግዚአብሄር ድጋፍ ነው፡፡

ፀጋ እግዚአብሄር በህይወታችን እንድናደርገው የፈለገውን ነገር ሁሉ እንድናደርግ የሚያስታጥቀን ችሎታ ነው፡፡

የዳንነው በፀጋው እንደመሆኑ መጠን ለእግዚአብሄር የምንኖረው በፀጋው እንጂ በስጋ ክንድ አይደለም፡፡ የዳንነው በራሱ ችሎታና አሰራር እንደመሆኑ ለእግዚአብሄር እንድ ነገር ካደረግንለት በራሱ ችሎታ ነው፡፡ የዳንነው በፀጋ እንደመሆኑ መጠን እግዚአብሄር የሚፈልገውን ነገር ከሆንንለት በእግዚአብሄ የሚያስችል ችሎታ ነው እንጂ በራሳችን ጉልበት አይደለም፡፡

ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡30-31

ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ ቲቶ 2፡11-14

 1. የዳነው በፀጋው ነው፡፡

ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንድንችል እግዚአብቭጌር ሞገሱን ሰጥቶናል፡፡ ጠላቶች የበነበረነውን ልጆች እንድባል ፀጋው አብቅቶናል፡፡

 1. የተቀደስነው በፀጋው ነው፡፡

በቅድስና ለእግዚአብሄር የምንለየው በእግዚአብሄር ችሎታ ነው፡፡ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞትን የምንክደው በእግዚአብሄር ችሎታ ነው፡፡ ቲቶ 2፡12

 1. ራሳችንን የምንገዛው በፀጋው ነው

የስጋን ክፉ ምኞት ተቋቁመን ራሳችንን በመግዛት በቅድስና ለእግዚአብሄር ብቻ የምንኖረቅው በራሳችን ችሎታ አይደለም በፀጋው ነው፡፡ ቲቶ 2፡12

 1. እግዚአብሄርን የምንመስለው በፀጋው ነው፡፡

እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስችል የእግዚአብሄር ሃይል ይጠይቃል፡፡ ካለ እግዚአብሄር ሃይል እግዚአብሄርን መምሰል እንችልም፡፡ የእግዚአብሄር ችሎታ በእኛ ውስጥ ሲሰራ ነው እግዚአብሄርን መምሰል የምንችለው፡፡ ቲቶ 2፡12

 1. በአለም ውጣ ውረድ የምንበረታው በፀጋው ነው፡፡

አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡1፣3-5

 1. እግዚአብሄርን የምናገለግለው በፀጋው ነው

ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡1

 1. የሚጠሉንን የምንወደው ፣ የሚረግሙንን የምንመርቀውና ለሚያሳድዱን የምንፀልየው በእግዚአብሄር ፀጋ ነው

እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ ማቴዎስ 5፡44-45

 1. ሌሎችን የምናገለግለው በእግዚአብሄር ችሎታ ነው

ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10

 1. እግዚአብሄር የጠራንን አገልግሎት ሁሉ የምናደርገው በፀጋው ነው

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

 1. በድካም የምንበረታው በእግዚአብሄር ማስቻል ነው

ከድካማችን አልፈን የእግዚአብሄርን አላማ በህይወታችን የምናስፈፅጽመው በእግዚአብሄር ሃይል ነው፡፡

ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡7

ኢየሱስ ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው የእኛን ሃጢያት ይቅር ሊለን ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሄር የሚጠቅሙ ሰዎች አድርጎ በራሱ ችሎታ ሊያስታጥቀን ነው፡፡ ለመዳን በፀጋው ጀምረን መሃል ላይ ተቀብለነው በጉልበታችን እንጨርስም፡፡ የእግዚአብሄር ፀጋ መዳናችን ላይ አያበቃም፡፡ የእግዚአብሄር ፀጋ ከመዳናችን ጀምሮ ወደሰማይ እስከምንሄድ ደረስ አንዳች ትርጉም ያለው ነገር ካደረግን በፀጋው ብቻ ነው፡፡

መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡14

ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ 11፡36

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ

የፀጋ ቃል

grace word.jpgለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

ፀጋ የሚያስችል ነፃ ስጦታ ነው፡፡ ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ፀጋ የሚያበቃ ችሎታ ነው፡፡ ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን የፀጋ ቃል ብቻ ከአፋችንም እንዲወጣ ታዘናል፡፡

እግዚአብሄር በመንፈሱ በተለያየ ፀጋ አሳድጎናል፡፡ እግዚአብሄር በፀጋው ለውጦናል፡፡ እግዚአብሄር በፀጋው ካለንበት አውጥቶናል፡፡ በፀጋው ከብዙ ነገር አሻግሮናል፡፡

እግዚአብሄር በቃላችን ውስጥ ታላቅ ሃይልን አስቀምጧል፡፡ እኛ ውስጥ የተጠራቀመው ፀጋ በቃላችን በኩል ሌሎችን በህይወታቸው ካለው ነገር እንዲያወጣቸው ያስፈልጋል፡፡ በቃላችን ውስጥ ያለው ፀጋ መንፈሳዊ ጉልበትን የሚሰጥ ምግብ ነው፡፡ የሚሰሙን በቃላችን በኩል የእግዚአብሄርን ፀጋ ይመገባሉ፡፡ እኛን ያበረታን ፀጋ በቃላችን በኩል ለሌሎች ይተላለፋል፡፡ የሆነውን የሆንበትን ፀጋን ለሌሎች ማካፈል እንችላለን፡፡

ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ንግግር #ቃል #አንደበት #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

 

የእግዚአብሄር ፀጋ እንዲሰራልን የሚያደርጉ ቁልፎች

fatherson-moab.jpgየእግዚአብሄር ፀጋ በሰው ህይወት የሚገለፅ የእግዚአብሄር ችሎታ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፀጋ በሰው የማንችለውን የሚያስችል የእግዚአብሄር ሃይል ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፀጋ በሰው ህይወት ውስጥ የሚሰራ የእግዚአብሄር ብቃት ነው፡፡ እግዚአብሄር ለጠራን ለማንኛውም ነገር ብቁ የሚያደርገን የእግዚአብሄር ችሎታ ፀጋ ነው፡፡

ሐዋሪያው ጳውሎስ ያንን ሁሉ የእግዚአብሄር ስራ የሰራው በእግዚአብሄር ፀጋ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንዲያውም ከሁሉ በላይ ደከምኩ ይልና የደከምኩት እኔ አይደለሁም የእግዚአብሄር ፀጋ ነው እንጂ ይላል፡፡

ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡10

በህይወታችን የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት የምንችለው በራስ ችሎታ ሳይሆን በእግዚአብሄር ፀጋ ነው፡፡

በእውነት እግዚአብሄር በህይታችን የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ የእግዚአብሄር ፀጋ ይጠይቃል፡፡ ካለ እግዚአብሄር ፀጋ የሚደረግ ምንም የእግዚአብሄር ስራ የለም፡፡ እንዲሁም በእግዚአብሄር ፀጋ ደግሞ የማይቻል ምንም አስቸጋሪ ነገር የለም፡፡

በእኛ ፋንታ ይህ ፀጋ እንዲሰራልን ማድረግ የምንችልባቸው መንገዶች

 1. ትህትና

 

የእግዚአብሄር ፀጋ በእኛ ፋንታ እንዲደክም ለማድረግ ትህትና ይጠይቃል፡፡ ፀጋን የተሞላ ትእቢተኛ ሰው የለም፡፡ ፀጋ የጎደለው ትሁት ሰው ደግሞ አይገኝም፡፡ ከእግዚአብሄር እና ከሰው ጋር በትህትና የሚኖር ሰው የእግዚአብሄር ችሎታ በእርሱ ፋንታ እንዲሰራ እያደረገ ነው፡፡ ትሁት ሰው በእርሱ ሃይል ፋንታ የእግዚአብሄር ፀጋ ተራራውን እንዲነቅለው ለጌታ ችሎታ ስፍራን እየሰጠ ነው፡፡ ትሁት ሰው በእርሱ ምትክ እግዚአብሄር እንዲሰራ ፋንታን እየሰጠውና መንገድን እየለቀቀለት ነው፡፡

 

እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5

 

 1. እምነት

 

የእግዚአብሄር ፀጋ በህዬታችን የሚፈሰው በእምነት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አሰራር ከተረዳንና ለአግዚአብሄር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ካወቅን እግዚአብሄር የተናገረንን ነገር እናደርገዋለን፡፡ እግዚአብሄር እንድናደርግ የሚናገረን ነገር በሰው ችሎታ የሚቻል ስላልሆነ የእግዚአብሄር ችሎታ በህይወታችን አንዲሰራ እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ የተናገረውን በተቀበልን መጠን የእግዚአብሄር የሚያስችል ብቃት በስራችን ሁሉ ያልፋል፡፡ ለመዳን የእግዚአበሄርን ቃል እንዳመንን ሁሉ በህይወት አሸናፊ ለመሆን የእግዚአብሄርን ቃል በማመን የእግዚአብሄርን ችሎታ በእኛ ፋንታ እንዲሰራ መልቀቅ ይኖርብናል፡፡

 

ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ኤፌሶን ሰዎች 2፡8

 

 1. ራስን ማማጠን

 

የእግዚአብሄርን ፀጋ ተቀብለን እንዳልተቀበልን በሽንፈት መኖር እንችላለን፡፡ ይህ የሚሆነው ድካማችንን የሚሞላ የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታችን እያለ ነገር ግን እንደሚጎድለን እንደ ደካማ ስንኖር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ በከንቱ መቀበል ማለት የእግዚአብሄርን ፀጋ ተቀብለን ግን እንዳልተቀበለ በስንፍና በመኖር ሃይሉን ማባከን ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ በከንቱ መቀበል ማለት አልችልም ብሎ እግዚአብሄር በህይወታችን የሰጠንን ሃላፊነት አለመወጣት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ በከንቱ መቀበል ማለት አብሮን የሚሰራ የእግዚአብሄር ፀጋ አብሮን እያለ ብቻችንን እንደምንሰራ እንደ ደካማና እንደተሸናፊ ሰዎች ራስን ማየት ማለት ነው፡፡

 

አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡1፣3-4

 

 1. እውቀት

 

ኢየሱስን ባወቅነው መጠን ምንም ያልተሰጠን ነገር እንደሌለ እንረዳለን፡፡ ኢየሱስን ባወቅነው መጠን በመስቀል ላይ ያልተሰራ ስራ እንደሌለ እናስተውላለን፡፡ የእግዚአብሄር እውቀት የእግዚአብሄር ፀጋ በእኛ ፋንታ እንዲሰራ እድልን እንድንሰጠው ያደርገናል፡፡ የእግዚአብሄር እውቀት በራሳችን ጉልበት እንዳንታገልና ለእግዚአብሄር ፀጋ እድሉን እንድንሰጥ ያስተምረናል፡፡

 

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

 

 1. ፀሎት

 

የእግዚአብሄርን ፀጋ ለእኛ እንዲሰራልን የምናደርግበት መንገድ ፀጸሎት ነው፡፡ ስንፀልይ እግዚአብሄ ምሪትን ይሰጠናል፡፡ ስንፀልይ እግዚአብሄር እየሰራ ያለውን ያሳየናል፡፡ ስንፀልይ እግዚአብሄር የሚሰራውን በመረዳት ከእግዚአብሄር ጋር አብረን እንሰራለን፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ ልባችንን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሄር ካነሳን የእግዚአብሄር ሃይል በእኛ ፋንታ ይሰራል፡፡

 

እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።

 

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የበይ ተመልካች

o-DAVID-CAMERON-facebook (1).jpgእናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ኢሳይያስ 55፡1-2

እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር ለሁላችንም እኩል እድል ሰጥቶናል፡፡ እስኪ ግን እነዚህን ሁለት አይነት ሰዎች እንመልከት፡፡ እኛንስ ራሳችንን ከሁለቱ አይነት ሰዎች በየትኛው ነው የምንመድበው?

አንዱ በገና ኢየሱስ ተወለደ ፣ በስቅለት ኢየሱስ ሞተ ፣ በትንሳኤ ደግሞ ኢየሱስ ከሞት ተነሳ እያለ እንደ ታሪክ በአመት ሶስቴ እያስታወሰ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ ከዚህ ከኢየሱስ ከከፈለው የሃጢያት እዳ ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ በመሆን በአመት 365 ቀን ከሃጢያት እስራት ነፃ ወጥቶ ይኖራል፡፡

አንዱ ለሁሉ ሰው በተገለጠው በዚህ የነፃ ስጦታ ተጠቃሚ በመሆን የእግዚአብሄር ልጅ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ኢየሱስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ እያለ እንደታሪክ እያወራ ከዚህ ነፃ ስጦታ አንዳች ተጠቃሚ ሳይሆን የበይ ተመልካች ይሆናል፡፡

አንዱ በዚህ በሚያስችል የእግዚአብሄር ፀጋ ስጦታ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት በመካድ ከሃጢያት የበላይነትን ኑሮ ያጣጥማል፡፡ ሌላው ደግሞ ነፃነት በኢየሱስ ተዘጋጅቶ እያለ በሃጢያት እስራት ተተብትቦ የሃጢያት መጫወቻ ሆኖ ዘመኑን ይፈጃል፡፡

አንዱ በእግዚአብሄር ፀጋ ራስን የመግዛትን ፍሬ በህይወቱ ይጠግባል፡፡ ሌላው ደግሞ በእግዚአብሄር ፀጋ ራሱን እንዴት እንደሚገዛ ባለማወቅ የሰይጣን ጥቃት ሰለባ ሆኖ ይኖራል፡፡

አንዱ እግዚአብሄርን በመምሰል እግዚአብሄርን ደስ እያሰኘ በእግዚአብሄርም ደስ እየተሰኘ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ እግዚአብሄርን መምሰል እንደ ሰማይ ርቆበት ተስፋ ይቆርጣል፡፡

እግዚአብሄር ግን ለሁሉም ግብዣን አዘጋጅቷል፡፡ እግዚአብሄር ልዩ ልጅ የለውም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡

ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡11-14

ኢየሱስ ስለሃጢያትችን በመሞቱና የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመክፈሉ ሁላችንም በነፃነት መኖር እንችላለን፡፡ ሰዎችን ከባርነት ቀንበርት የሚያድን የእግዚአብሄር ፀጋ ለሁሉም ሰው ተዘጋጅቷል፡፡

አንዱ ኢየሱስ የሞተበትን ምክኒያት ሙሉ በሙሉ በመረዳት 365 ቀን የበረከቱ ተካፋይ ሲሆን ሌላው ግን እንደ ባህል በአመት አንዴ በማስታወስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞት ዋጋ የከፈለበት አላማ በህየወቱ ሳይፈፀም ይቀራል፡፡

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአመፃ ሁሉ እንዲቤዠን ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ አሁንም ከሃጢያት ካልዳንክ ኢየሱስ የሞተበት አላማ በህይወትህ ገና አልተፈፀመም፡፡

በአሉን ልታከብር ስትዘጋጅ እኔስ የኢየሱስ ሞት ተጠቃሚ ሆኛለሁ ወይስ እንደ ወግ በአመት አንዴ ነው የማስታውሰው ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ኢየሱስ የሞተበት አላማ በህይወትህ ካልተፈፀመ በአመት አንዴ በአሉን ማስታወስህ የበይ ተመልካች ወይም ቲፎዞ እንጂ ሌላ ምንም አያደርግህም፡፡

መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡14

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መቤትዠት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት

የእግዚአብሔርን ፀጋ የምንጥልባቸው አራቱ መንገዶች

reject grace.jpgእኛን ያቆመን የእግዚአብሄር ፀጋ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ፀጋ ውጭ እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ሁሉ በእግዚአብሄር ሃይልና ፀጋ ስለሆነ በክርስትና ታላቁ ሰው ማለት ነው የሚችለው የሆንኩትን የሆንኩት በእግዚአብሄር ፀጋ ነው ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡10

የእግዚአብሄርን ፀጋ ስንጥል ማደግ እናቆማለን፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ ከጣልን መውደቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ፀጋን የምንጥልበትና ማደግ የምናቆምበት ብሎም በክርስትና የምንወድቅበት ሶስት ዋና ዋና መንገዶች አሉ፡፡

የእግዚአብሄርን ፀጋ የምናጣበት ሃይል አልባ የሚያደርጉን አራቱ መንገዶች

ትህትናን መጣል

ሰው ትህትናን ከጣለ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንደሚወድቅ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ከሰጠው ደረጃ በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ ሲያይ ከእግዚአብሄር ጋር ይተላለፋል፡፡ እግዚአብሄር ፀጋን መስጠትና ማንሳት ከፍ ማድረግ እየፈለገ በራሱ ነገሮችን ማደርግ እንደሚችል የሚያስበውን ትእቢተኛን ሰው ግን ከመቃወም ውጭ ምንም ሊያደርገው አይችልም፡፡

ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። ያዕቆብ 4፡6

እውቀትን መጣል

ሰው ከመሬት ተነስቶ አውቆ የጨረሰ ከመሰለው በህይወቱ ማደግና መለወጥ አቁሟል ማለት ነው፡፡ ይህ ሰው ለአዲስ ተግዳሮት በእውቀት ራሱን ካላስታጠቀ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሰው ያወቀና የጨረሰ ከመሰለው እጅግ አሰቃቂ ነው፡፡

ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1-2

ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ ሆሴዕ 4፡6

በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2

እምነትን መጣል

ሰው በእግዚአብሄር ላይ መደገፍን ትቶ በራሱ ስራ ላይ ሲደገፍ ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡ ሰው ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ ለመቀደስ ፣ ለእግዚአብሄር መንግስት ለመስራትና እግዚአብሄርን ለማስደሰት በራሱ ጉልበትና ቅልጥፍና ላይ ሲደገፍ ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡

በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ገላትያ 5፡4

ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡30-31

ምስጋናን መጣል

ሰው ምንም ከማይወጣለት መልካም አምላክ ጋር እየኖረ ካጉረመረመና ማመስገን ካቃተው ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አሰራር ላይ አቃቂር ማውጣት ከቻለ የሆነ የሳተው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር በላይ የሚያውቅ ከመሰለው የሆነ የተዛባ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አሰራር ካልታመነ ከእግዚአብሄር ጋር በየዋህነት መኖር ፣ ራሱን መስጠት ፣ ለእግዚአብሄር በየዋህነት መስራትና ፍሬያማ መሆን ያቅተዋል፡፡

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡24-25

ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት

በመዋረዳችን እንጠቀማለን

croppedimage720520-glasses-of-waterጌታን ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን በእግዚአብሄር ፊት የከበርን ነን፡፡

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

ስለዚህ ነው በምድር ላይ የምናልፍባቸው ከፍታዎችና ዝቅታዎች ሊያሸንፉን የማይችሉት፡፡ ጠላት እኛን ለመጣል የሚያመጣውን እንኳን እግዚአብሄ ለከፍታችን ይጠቀምበታል፡፡

በአንድም በሌላም መልኩ የሚዋርዱ ነገሮች በህይወታችን ይመጣሉ፡፡ ነገሮች ሊያዋርዱን በጉድለት በመጡ መጠን እግዚአብሄር የሚክስበት የራሱ መንገድ አለው፡፡ በጎደለን ቅፅበት የሚሞላ የእግዚአብሄር ፀጋ በህይወታቸን ይሰራል፡፡

በሳይንስ ስንማር አንድ ምንም ውሃ ያልያዘ ብርጭቆ ባዶ አይደለም ተብለን ተምረናል፡፡ ባዶው ብርጭቆ ውሃ ባይኖረውም ውሃው የጎደለበትን ቦታ ሁሉ የሚሞላ በባዶ አይናችን የማናየው አየር አለ፡፡

የእግዚአብሄርም አሰራር እንዲዚሁ ነው፡፡ ሰይጣን ሊያጠቃን የሚችለው በሚታየው ነገር ብቻ ነው፡፡ በሚታየው ነገር ሊያዋርደን ሲመጣ እግዚአብሄር በማይታየው በከበረው በተሻለው ነገር ጉድለታችንን ይሞላል፡፡ በሚታየው ነገር ተዋረድን ማለት በማይታየው ነገር ከበርን ማለት ነው፡፡

በሚታይ ነገር 100 እጅ ሞልቶልኛል የሚያዋርደኝ ምንም ነገር የለም የሚል ማንም ሰው እንደሌለ ሁሉ ሁላችንም ዘወትር የሚያበረታውን የእግዚአብሄርን ፀጋ እንፈልጋለን፡፡ በጎደለን በማንኛውም እጅ የእግዚአብሄ ፀጋ ስለሚሞላብን ሁልጊዜ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ለእኛ መዋረዳችን እንኳን በሌላ መልኩ ጥቅም ነው፡፡

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

አዳምና ሄዋን በሃጢያት ከመውደቃቸው በፊት ምንም ልብስ ባይለብሱም ራቁትነታቸው አይታይም ነበር፡፡ ራቁትነታቸውን የሚሸፍን የእግዚአብሄርምን ፀጋ ለብሰው ነበር፡፡

የሚታይ ነገር ሲጎድል የእግዚአብሄር ፀጋ የሚያስችለን ሃይሉ ቦታውን እየያዘ ይመጣል፡፡ የሚታይ ነገር ሲጎድል የማይታየው የእግዚአብሄር ሃይል እያበረታን ይመጣል፡፡ በነገሮች ስንዋረድ በእግዚአብሄር አሰራር ከፍ ከፍ እንላለን፡፡ በመዋረዳችን በሚያበረታ ፀጋ ለእኛ ማሸነፍ ሁልጊዜ ነው፡፡

ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 2፡14

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ጸጋዬ ይበቃሃል !

publication1በክርስትና ህይወታችን ብዙ የሆኑልን መልካም ነገሮች አሉ፡፡ ስለሆነልን ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን ሁል ጊዜ እናመሰግነዋለን፡፡ ብዙም እንዲሆኑልን የምንፈልጋቸው ነገሮች ደግሞ አሉ፡፡ ደግሞም ጸልየን ለምነን እንደጠበቅነው ያልሆኑልን ነገሮች ደግሞ እንዳሉ ማመንም ወሳኝ ነው፡፡

በህይወታችን እንዲሆኑልን ጠይቀን እንዳሰብነው ስላልሆኑ ነገሮች ምን ማድረግ እንደሚገባን የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚል ማወቅ ያሳርፈናል፡፡

ሃዋሪያው ጳውሎስ በህይወቱ ስለነበረው ድካም እንደፀለየ እንደለመነ እንመለከታለን፡፡ ምንም ቢለምን ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ደጋግሞ ስለዚያ ነገር እግዚአብሄርን ሲለምን እናየዋለን፡፡

ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡8

ደስ የሚለው ነገር ግን ለምነን ነገሩ ባይሆንም እንኳን በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሁል ጊዜ መንገድ አለ፡፡ እግዚአብሄር ለሁሉ መፍትሄ አለው፡፡ ከፊታችን ያላነሳውን ተራራ እንዴት እንደምናልፈው የሚያበረታበት መንገድ አለው፡፡

በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያበቃና የተቆረጠ ተስፋ የሌለው ነገር የለም፡፡ ወደ እግዚአብሄር ፀልየን የማይመለስ መልስ የለም፡፡ እግዚአብሄር ሁሉንም ይመልሳል፡፡ እግዚአብሄር ግን የሚመልሰው እኛ በጠበቅነው መንገድ ላይሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር ግን ሁሌ ይመልሳል፡፡

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

በእግዚአብሄር ዘንድ የማይቻል ፣ የማይታለፍና የማይሆን ነገር የለም፡፡ ከፊታችን ያለውን ውሃ ካላደረቀው በውሃ ውስጥ ባለፍን ጊዜ በውሃው የማንሰጥምበትን ፀጋ ሰጥቶናል ማለት ነው፡፡ የእሳቱን ነበልባል ካላጠፋው በእሳት ውስጥ ሳንቃጠል የምናልፍበት ፀጋ በውስጣችን አለ ማለት ነው፡፡ ተራራውን ዘወር ካላደረገው ተራራውን የምንወጣበትና የምናልፍበት የሚያስችል ሃይል ተሰጥቶናል ማለት ነው፡፡

እንደ እኛ አጠባበቅ እግዚአብሄር ላልመለሳቸው ፀሎቶች የእግዚአብሄ አምላካዊ መልስ “ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማል” የሚል ነው፡፡

ደስ የሚለው ነገር በሁለቱም አሸናፊው እኛ ነን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር ባእኛ  ወስጥ ነው፡፡

ጸጋዬ ይበቃሃል!

ጸጋዬ ይበቃሃል!

ጸጋዬ ይበቃሃል!

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ

%d bloggers like this: