Category Archives: Politics

የምሁራኖቻችን ተግዳሮት

1 (3).jpg

ምሁራን ለአገር እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ የእውቀትና የመረጃ አለም ካለምሁራን ንቁ ተሳትፎ አገር የሚገባውን ያህል ታድጋለች ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡

ባደጉት አገሮች በአብዛኛው ፖለቲካና ሙያ ድንበራቸውን አውቀው ተከባብረው ይኖራሉ፡፡ ፖለቲከኛው ዋና ፖሊሲን የሚመለከት  ነገር ካልሆነ በስተቀር የሙያውን ስራ የሚተወው ለምሁራኑ ነው፡፡ ምሁራኑም ሙሉ በሙሉ የማይደግፉት ፖሊሲም ቢሆን ከፖለቲካ ውጭ አገሪቱን በሙያቸው ያገለግላሉ፡፡ እኔ የምስማማበት ፖሊሲ ካልገሆነ ብለው ራሳችውን ከሙያው አያገሉም፡፡

ባደጉት አገሮች የአገር መዋቅር በሚገባ ስለተገነባ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ሙያውን ደግሞ ለምሁራኑ የሚሰጥበትና አንዱ ከአንዱ የድንበር መስመር እንዳያልፍ የሚያደርግበት በአመታት የዳበር ስርአት አለ፡፡ ስርአቱ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኛውም በአብዛኛው ድንበሩን አውቆ ወደሙያው ድንበር ዘልቆ የባለሙያውን ቦታ አይገዛም፡፡ ምሁሩም እንዲሁ በአብዛኛው ድንበሩን አውቆ ወደ ፖለቲከኛው ድንበር ሳያልፍ በሙያው ብቻ አገርን ያገለግላል፡፡

በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ግን በዚህ ዘርፍ ትልቅ ተግዳሮት አለ፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ብዙ ፖለቲከኞች ስጋት አለባቸው፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ስልጫን ሲይዝ ከእርሱ የተለየን ሰው ማቅረብ አይፈልግም፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ የሚያምነው ዝለል ሲባል ምን ያህል ከፍታ ልዝለል ብሎ ብቻ የሚጠይቅ ተከታይን ነው፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ በራሱ ስለማይተማመን ከእርሱ ለየት ያለ ሃሳብ የሚያመጣ ሰው ጠላቱ እንጂ ወዳጁ አይደለም፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ራሱን በታማኝ ሎሌዎች ይከባል፡፡ ስጋት ያለበት ፖለቲከኛ ከስሩ የሚሾመው ሙያ ያለውና በሙያውና በእውቀቱ  ህዝብን የሚያገለግለውን ሳይሆን ለእርሱ ታማኝ ሎሌ የሆነውን በሙያው እውቀት የሌለውን ሰው ብቻ ነው፡፡

ስጋት ባለበት ፖለቲከኛ የተመረጡና የተሾሙ ፖለቲከኞች ለፖለቲካው ታማኝ ሎሌን ብቻ በመሾም ዋናውን መሪ ይከተላሉ፡፡ ስጋት ባለበት ፖለቲከኛ የተሾሙ መሪዎች እንዲሁ ከስራቸው ታማኝ ሎሌ የሆነውን ምንም ጥያቄ ሳይጠይቅ ክፉም ይሁን መልካም የሚታዘዘውን ሰው ከስራቸው ይሾማሉ፡፡ እንደዚህ እያለ ከላይ ለጠቅላይ ሚንስትር እስከ ቀበሌ ከፕሬዝዳንት እስከ ፅዳት ሰራተኛ ድረስ በሙያ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት ይሾማሉ፡፡ ይህ ሲሆን ሙያው ለሙያተኞች ስላልተሰጠ በአገልግሎት እጦት ሳቢያ ህዝብ ይሰቃያል፡፡

በማደግ ላይ ያሉ ሃገሮች ተግዳሮት አንዳንድ ስጋት ያለባቸው ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ምሁራኑም ናቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራን የፖለቲካውን ስልጣን ለፖለቲከኛው ለመተው አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ ምሁራን የፖለቲከኛውን እጅ በጉልበት ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ድንበራቸውን አላግባብ ይጥሳሉ፡፡ ይህ ፖሊሲ ካልተለወጠ አገራችንን አናገልግልም ብለው ያኮርፋሉ የግል ድርጅቶችን ያገለግላ ወይም አገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ እውነት ነው አይን ያወጣ ግፍ ሲፈፀም ከፖለቲከኛው ጋር አብሮ ክፋትን መዋጋት ካለተቻለ ከክፋት ጋር ላለመተባበር ራስን ማግለል ወሳኝ ነው፡፡

ነገር ግን አብሮ መስራት ውስጥ ሆኖ መለወጥ ከተቻለ አብሮ ለመስራት እና ህዝቡን በሙያ ለማገልገል ልብን ማስፋት አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ህሊናዬን ጠብቄ ከፖለቲከኛው ጋር አገልግላለሁ ካለ ምሁሩ በሙያው ህዝቡን ቢያገለግል አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ምሁር የሚስማማበትን ፖሊሲ እየደገፈ ስለማይስማማበት ፖሊሲ ድምፁን እያሰማ ህዝቡን በሙያው ለማገልገል ለአገር እድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ መታገስ አለበት፡፡

ፖለቲከኛውም በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሰዎችን መሾሙን ትቶ ለሙያተኛው ምሁር ልቡን ቢያሰፋ ምሁሩም የሚነቅፈውም ፖሊሲ ቢኖርም ህዝቡን ግን በሙያው ለማገልገል ተጨማሪ ምእራፍ ቢሄድ አገር ታርፋለች፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍትህ #ፍርድ #ሙያ #እውቀት #ዲሞክራሲ #ታማኝነት #ፖለቲካ #አገር #እድገት #ድንበር #ኢትዮጲያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ምሁር #ፍቅር #ልብ #መሪ

ከጫጉላው መልስ

P-.jpg

ብዙዎቻችን በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ፍትሃዊ አመለካከት ሁላችንም ተደስተናል፡፡ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር አብሮ መቆም ወሳኝ ነው፡፡

መሪን የምንከተለው እግዚአብሄር ይመራዋል ብለን በእግዚአብሄር አምነን እንጂ እያንዳንዱ እርምጃውን ተከታተልን አጣርትን ተስማምቶን አይደለም፡፡ መሪን የምንከተለው እያንዳንዱን የሚወስነውን ውሳኔ ሁሉ ወደነው ላይሆን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ካደረገ እኛ እንጂ እርሱ መሪ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ነገ ከነገ ወዲያ ይህንን ባያደርግ ጥሩ ነበረ የምንለውን ውሳኔ ሊወስን ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድና በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ፈቃድህ ቢሆን ይህችህ ፅዋ ከእኔ ትለፍ የምንልበት አንዳንድ ውሳኔዎች ሊወስን ይችላል ብለን ካልጠበቅን እና ልባችንን ካላዘጋጀን ብስለት የጎደለው ህዝብ እንሆናለን፡፡

ታዲያ የህዝብ ብስለት የሚለካው በምንስማማበት ውሳኔዎቹ እየተደስትንበት በማንስማማው ውሳኔዎቹ ድምፃችንን እያሰማን በአጠቃላይ ግን መሪን መከተል ነው፡፡ የእያንዳንዳችንን ሃሳብ ሳይሆን መሪን በመከተል ብቻ ነው አገር ወደ አንድነት የሚመጣው፡፡

መሪን የምንከተለው እኛ የምንፈልገውን እንዳንዱን ነገር ያደርጋል ብለን አይደለም፡፡ መሪን የምንከተለው ከእኛ ይበልጥ ትልቁን ምስል ያያል ብለን ነው፡፡ መሪን የምንከተለው የአገሪቱን መሪነትን በተመለከተ እግዚአብሄር ከእኛ ይበልጥ መሪውን ይመራል ብለን ነው፡፡

የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። መጽሐፈ ምሳሌ 21፡1

ጠቅላይ ሚንስትሩ ነገ ከነገ ወዲያ ቅር የሚለንን ነገር ሊወስን ይችላል፡፡ ለዚያ ምን ያህል ተዘጋጅተናል፡፡ ይሄ ሰው አይሆንም ብለን እርግፍ አድርገን ትተን ሌላ ሰው ለመፈለግ እንሄዳለን? ወይስ የምንስማማበትን ዋና ነገር እየተደሰትንበት የማንስማማውን ነገር በማለፍ የአገር ሃላፊነታችንን እየተወጣን ለአገር ብልፅግና በአንድነት እንሰራለን፡፡

ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡1-7

ሰው እንኳን በሰው መሪነት በእግዚአብሄር መሪነት እንኳን እንዲህ ቢያደርግልፅ ኖሮ የሚለው ነገር አለ፡፡ ሰው እንኳን በሰው መሪነት በእግዚአብሄር መሪነት ፈቃድህ ቢሆን ይህች ፅዋ ከእኔ ትለፍ የሚለው ነገር ይኖራል፡፡

ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 22፡42

ባል ከሚስቴ ጋር የማልስማበት ነገር አለ ቢል አያስገርምም፡፡ ሁለት ሰዎች የማይስማሙበት ነገር ቢኖር ይደንቃል? እንዲያውም ታእምር የሚሆነው የማይሳማሙበት ነገር ባይኖር ነው፡፡ ባል የሚስቴን ሁሉንም ነገር እወደዋለሁ እንድትለውጥ የምፈልገው ነገር የለም ቢል ይዋሻል፡፡ ሚስት ባልዋን የምትወድበት ዋና ምክኒያት አለ ሌላውን ግን ትታገሰዋለች፡፡ ሚስት ባልዋን በፍቅር የምትከተለው እግዚአብሄር ይመራዋል ብላ እግዚአብሄርን ታምና እንጂ እኔ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል ብላ አይደለም፡፡

ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡21-22

ፓስተሩ የሚናገረው ነገር ሁሉ ይስማማኛል እኔ የማስበውን ነገር ሁሉ ነው የሚያስበው የሚል ሰው ካለ ከገሃዱ አለም የራቀ ሰው ነው፡፡ ፓስተሩ ባለው ዋና አቋም ከተስማማ ሌላውን ነገር ወደጎን በመተው ለቤተክርስትያን እንድነት ይሰራል፡፡

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡1-2

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍትህ #ፍርድ #አናሳ #አብላጫ #ዲሞክራሲ #ባል #አምባገነን #ሚስት #ድሃ #ኢትዮጲያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ

ወደ ኬንያ የተሰማው ወሬ

democracy.jpgሰሞኑን ወደ ኬንያ እንግዳ ወሬ ተሰምቶዋል፡፡ የነበረውን የፕሬዝዳንትነት ምርጫ ውጤት በተመለከተ የኬንያ ፍርድ ቤት ያልተለመደ አንድ ውሳኔ አስተላልፎዋል፡፡ በውሳኔውም የኬንያ ፕሬዝዳንትነት ምርጫ የጉድለት እንደነበረውና የነበረው የፕሬዝዳንት አመራረጥ ዲሞክራሲያዊ ነፃና ፍትሃዊ መንገድን አካሄድ ያልተከተለ አልነበረም በማለት የምርጫው ውጤት ውድቅ እንዲሆንና አዲስ ምርጫ በ 60 ቀን ውስጥ እንዲካሄድ ወስኖዋል፡፡

ይህ የዲሞክራሲ አንዱ ምልክት ነው፡፡

ዲሞክራሲ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ አውጪ ምክር ቤቶች ፣ ህግ ተርጉዋሚው ፍርድ ቤት እና ህግ አስፈፃሚው የመንግስት አካል እርስ በእርሳቸው መፈታተሻቸው ፣ መጠበባበቃቸውና አንዱ የሌላው ሚዛን መጠበቃቸው ነው፡፡

መንግስት አንድ ወጥ ቢሆን ስልጣኑን ያለአግባብ ቢጠቀም የሚመለከተው ክፍል እየኖርም፡፡ መንግስት በሶስት ክፍሎች በህግ አውጪ ፣ በህግ ተርጉዋሚና በህግ አስፈፃሚ ባይከፋፈል  በህዝብ ላይ ሃይሉን ያለአግባብ ሊጠቀም ይችላል፡፡ መንግስት አንድ ወጥ ከሆነና በሶስቱ የመንግስት ክፍሎች ካልተከፋፈለ የመንግት አካሎች እርስ በእርሳቸውን የሚቆጣጠሩበት መንገድ አይኖርም፡፡ መንግስት አንድ ወጥ ከሆነና በመንግስት አካሎች ካልተከፋፈለ በስተቀር አንዱ የመንግስት አካል ህግ ማውጣቱንም ፣ ህግ መተርጎሙንም ሆነ ህግ ማስፈፀሙንም ራሱ ካደረገው ስልጣኑ ካለአግባብ ቢጠቀም የሚያየው የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው አካል አይኖርም፡፡

ለምሳሌ አንዱ የመንግስት አካል አስፈፃሚው ክፍል ወይም ፖሊስ አንድን ሰው ራሱ ከከሰሰ ፣ ያው ፖሊስ የከሰሰውን ሰው ራሱ ከፈረደበትና ያው ፖሊስ ፍርዱን ከፈፀመበት ዲሞክራሲ ሳይሆን አምባ ገነንነት ነው፡፡

አንድ ፖሊስ ሰውን ጠረጠረ ወይም ከሰሰ ማለት መንግስት ጠረጠረው ወይም ከሰሰው ማለት አይደለም፡፡ አንድ ፖሊስ ሰውን ጠረጠረ ማለት አንዱ የመንግስት አካል ብቻ ጠረጠረው ማለት ነው፡፡ ፖሊስ እንደ ህግ አስፈፃሚነቱ ሰውን ጠረጠረ ወይም ከሰሰ ማለት ከሰሰ ወይም ጠረጠረ ማለት ብቻ እንጂ ሰው ተፈረደበት ማለት አይደለም፡፡ ፖሊስ አስፈፃሚነቱን ስልጣኑን አልፎ ሌላ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ፖሊሱ ሊያደርግ የሚችለው ብቸኛ ነገር ህግ ተርጓሚው ፍርድ ቤት ጋር ማቅረብ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ደግሞ ስራው ህጉን መተርጎም ነው፡፡ ህጉምን በመተርጎም ይህን ሰው ያስጠይቀዋል ወይስ አያስጠይቀውም የሚለውን የሚስነው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤቱ ፊት ፖሊስም ተጠርጣሪው እኩል ናቸው፡፡ ሰው በፍርድ ቤት ተከራክሮ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ በደለኛ አይደለም፡፡ ፖሊስም ተጠርጣሪው ሰውም ስለህጉ አተረጓጎም እኩል ይከራከለራሉ፡፡ ህግ አስፈፃሚው ፖሊሱና ተከሳሹ በህግ ተርጓሚው ፊት እኩል ናቸው፡፡ ህግ አስፈፃሚው እንደ መንግስር ሳይሆን እንደ አንድ የመንግስት አካል ክፍል ተጠርጣሪውን የሚቀርበበው ሌላው የመንግስት አካል ክፍል ጋር ነው፡፡

ህግ አውጪው ምክር ቤት እንዲሁ ህግ የማውጣት ስራውን በነፃነት ይሰራል፡፡ ነገር ግን ህግ አውጪ እንጂ ህግ ተርጉዋሚም ሆነ ህግ አስፈፀጻሚ አይደለም፡፡ ህግ አውጪው ህግ በማውጣት ብቻ ህግ ተርጓሚውንም ሆነ ህግ አስፈፃሚውን ይፈትሻቸዋል ሚዛናቸውን ይጠብቃል፡፡

ፍርድ ቤቱም እንዲሁ የራሱ ስልጣን እንዲሁም ለስልጣኑ የራሱም ገደብ አለው፡፡ ፍርድ ቤቱ ስልጣኑ እና ሃላፊነቱ በህግ አውጪው የተሰጠውን ህግ መተርጎም ነው፡፡ ነገር ግን ህግ ተርጓሚው ፍርድ ቤት ህጉን መተርጎም እንጂ የሌሎቹን የመንግስት አካላት የህግ አውጪውንም ሆነ የህግ አስፈፃሚነትን ስራ አይሰራም፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ህጉን በመተርጎሙ ሂደት የህግ አስፈፃሚው ሆነ የህግ አውጭው ምክር ቤት ጣልቃ አይገቡበትም፡፡ ህግ ተርጉዋሚውም ህግ አውጭውንና ህግ አስፈፃሚውን ድንበራቸውን እንዳይስቱና ካለአግባብ በስልጣናቸው እንዳይጠቀሙ ህጉን በመተርጎምና በመወሰን ይጠብቃቸዋል፡፡

መንግስት ሃይሉን ካለአግባብ እንዳይጠቀም በሶስት ዋና ዋና የመንግስት ክፍሎች በህግ አውጪ ምክር ቤት ፣ በህግ ተርጓሚ ፍርድ ቤትና በህግ አስፈፃሚ ተከፋፍሏል፡፡ አንዱ የመንግስት ክፍል ሌላው የመንግስት ክፍል ከስልጣን ከድንበሩ እንዳያልፍ ይጠብቀዋል ይፈትሸዋል ይቆጣጠረዋል፡፡ አንዱ የመንግስት አካል የሌላውን የመንግስት አካል ሚዛን ይጠብቃል፡፡

በኬንያ የሆነውም ነገር ይህ ነው፡፡ ስለምርጫው ውዝግብ ሲነሳ አንዱ የመንግስት አካል ህግ ተርጉዋሚው ጋር በመድረሱ ህግ ተርጉዋሚው በህጉ መሰረት ያልተገበሩ ነገሮች አሉ በማለት የምርጫውን ውጤት ውድቅ ከማድረጉም በላይ በ60 ቀን ውስጥ አሰዲስ ምርጫ እንዲደረግ ወስኖዋል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ፍርድቤት #ህግአውጪ #ህግአስፈፃሚ #ምክርቤት #ፖሊስ #ዲሞክራሲ #ህግተርጉዋሚ #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

5 things Christian shouldn’t do during political tensions

stop-shutterstock_69015226For Christians, the word of God is the only council as what to and what not to do during political tension. If we walk in biblical manners, we will fulfil our calling on earth. People look up to us as role models. And this is high time that we testify for Jesus Christ behaving ourselves in a decent way.
• Don’t reject wisdom
We have a calling to be witnesses for Christ. The character we show must be used for testimony for Christ and His kingdom. We have to behave in a way that will not spoil our testimony. We have to do it wisely and in gentleness.
Be wise in the way you act toward outsiders; make the most of every opportunity. 6 Let your conversation be always full of grace, seasoned with salt, so that you may know how to answer everyone. Colossians 4:5-6
• Guarding self from hatred
The only party benefited from hatred is the devil. Guard yourself from hatred. “In your anger do not sin” Do not let the sun go down while you are still angry, and do not give the devil a foothold. Ephesians 4: 26-27
• Don’t cease to pray for the country
Sometimes there are easier things to do than prayer. But let’s intercede before God to intervene in the situation. And resist the devil not to take advantage of this situation to steal, kill and destroy.
I urge, then, first of all, that petitions, prayers, intercession and thanksgiving be made for all people— for kings and all those in authority, that we may live peaceful and quiet lives in all godliness and holiness. This is good, and pleases God our Savior, who wants all people to be saved and to come to a knowledge of the truth. 1 Timothy 2:1-4
• Avoid Division
Accept that other Christians can have a different political view from yours. Have a large heart to accommodate them. And focus on the things that unify you, not divide for the kingdom work.
Be completely humble and gentle; be patient, bearing with one another in love. Make every effort to keep the unity of the Spirit through the bond of peace. Ephesians 4:2-3
• Give priority to Christianity
Even if we have to fully take part in political activities as citizens, we have to know that we don’t do any of them at the cost of our Christian calling. We don’t give priority for temporary thing over the eternal things of the kingdom.
Share this article to share with others

በፖለቲካ ውጥረት ወቅት ክርስቲያን ማድረግ የሌለበት 5 ነገሮች

stop-shutterstock_69015226ፖለቲካ ውጥረት ሲነግስ ክርስቲያኑ ምን ማድርግ እንዳለበት የሚመክረው ብቸኛ መካሪ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ድርጊቶችን ብቻ በማድረግ በዚህ ጊዜ ለሌሎች መልካም ምሳሌ ለመሆን ይህን እድል መጠቀም ይኖርብናል፡፡
  • ጥበብን አለመጣል
እንደ ክርስቲያን እያንዳንዱ ነገሮቻችን በሌሎች ሰዎች እንደሚታይና በዚህ ጊዜ ለሌሎች በጎ ወይም ክፉ ምሳሌ እንደምንሆን በማወቅ የምናደርገውን ነገር ሁሉ በእርጋታና በጥበብ ማድረግ፡፡ ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። ቆላስይስ 4፡5-6
  •  ራስን ከጥላቻ መጠበቅ፡፡
በጥላቻ መስፋፋት የሚጠቀመው ሰይጣን ብቻ መሆኑን አውቆ ከጥላቻ ራስን መጠበቅ፡፡ ለዚህም ጥላቻን የሚያሰራጩ ንግግሮችን በማስተዋል መስማት፡፡ ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡26-27
  • ሰለአገር መፀለይን አለመተው
በዚህ ሁኔታ ሁሉ እግዚአብሄር ጣልቃ እንዲገባና ከሁሉም በላይ የእግዚአብሄር ፈቃድ በምድሪቱ ላይ እንዲፈፀም መፀለይ፡፡ እንዲሁም ሰይጣን ምንም እድል ፈንታ እንዳይኖረው አጥብቆ መፀለይ፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
  • በፖለቲካ ከወንድም አለመለየት
ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ሌላው ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋም ይኖረዋል ብሎ አለመጠበቅ፡፡ ለተለዩ የፖለቲካ አቋሞች ልብን ማስፋት በዚህም የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡2-3
  • ክርስትናን ማስቀደም
እንደ ህዝብ በፖለቲካ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ቢጠበቅብንም የክርስትናን ባህሪ እስከመጣል ድረስ በፖለቲካ አለመወሰድ ይጠይቃል፡፡ ለምንም የፖለቲካ አስተሳሰብ የማያልፈውን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ አለመተው፡፡ የዘላለሙን የጌታን አገልግሎት በፖለቲካ አቋም አለመለወጥ፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum…

ከዋናተኛው ሮቤል ምን እንማራለን ?

robel kiros habte.jpgዛሬ ኢትዮጲያን ወክሎ ስልተወዳደረ ዋናተኛ ብዙ ተብሎዋል፡፡ ይህን አስቂኝ ዜና ከ ዴይሊ ሜይል እስከ ዋሽንግተን ፖስት በግርምታ ዘግበውታል፡፡

 

ይህንን ዜና የስፖርትና ሌሎችም ጋዜጠኞች በፌስቡክና በትዊተር ገፆቻቸው ተችተውበታል፡፡ በርግጥ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖዋል፡፡ ሁኔታው ያስቃልም ያስቆጫልም፡፡ እያንዳንዳችን ግን ከዚህ ምን እንማራለን የሚለው መጠየቅና ከስህተት መማር ብልህነት ነው፡፡

 

ምክኒያቱም ይህ ክስተት በዚህ በ24 ዓመት ወጣት ላይ ወደቀበት እንጂ ይህ ክስተት ከዚህ ያለፈ ነው፡፡ ወጣቱ ለየት ያለ ነገር መስራት እፈልጋለሁ ብሎ ነው የሄደው ከዚያም በውጤቴ ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡

 

ከእርሱ በላይ ስልጣን ያላቸው መሪዎች ልከውታል ፡፡ ለዚህም ውሳኔያቸው ሃላፊነቱንም መውሰድ ያለባቸው መሪዎቹ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በዚህ በዋና ፌዴሬሽኑ አይወሰንም፡፡ ሌሎችም ፌዴሬሽኖች በዚህ አጋጣሚ ራሳቸውን ሊያዩ ይገባል፡፡

 

በአጠቃላይ መንግስትም በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ራሳቸውን ከአድሎ እንዲጠብቁ ክትትልና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ መንግስት በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ተመሳሳይ ነገር እንዳያደርጉ ስልቶችን መፍጠርና መድሎንና ሙስናን መከላከል እንዳለበት ራሱን የሚያይበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

 

ይህ በአለም መድረክ የተደረገው ነገር በየመስሪያ ቤቱ እንዳይደረግ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣኖች ወደራሳቸው የሚያዩበትና አሰራራቸውን የሚፈትሹበት እንዲሁም አድሎን ለመዋጋት በትጋት ለመስራት የሚወስኑበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

 

ግልፅነትና ተጠያቂነት በአግባቡ ካልሰፈነ እንደዚህ የሚያዋርድ ነገር ይከሰታል፡፡ ከዚህም በላይ አድሎ የሚደረግባቸውን ሰዎች ልብ ያሳዝናል፡፡

 

መንግስት ብቻ ሳይሆን እኛም እያንዳንዳችን ባለንበት ስልጣንና የመሪነት ደረጃ ይህን አይነት ስህተት ላለመስራት ወደ ራሳችን ማየት ይኖርብናል፡፡ በጓዳ የምንሰራው በደል በአደባባይ ሊያጋልጠን እንደሚችል ማሰብ አለብን፡፡

 

ይገርማል ብለን ስቀንና ተቆጭተን ብቻ ብናልፍና እያንዳንዱ የህይወት ክፍላችንን ለመፈተሽ ይህን አጋጣሚ ካልተጠቀምንበት እና በእውነት ለመኖር ካልወሰንን ይህን አጋጣሚ በከንቱ እናባክነዋለን፡፡

 

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ

 

ለተጨማሪ ፅሁፎች

የህዝብ ድምፅ የመንግስት ሃብት ነው

abebe-Gelaw 222.jpgህዝብ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ያለውን ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ሰው የፖለቲካ መሪዎች መልካምን ሲያደርጉ ሊያመሰግናቸውና ሊያበረታታቸው ይገባል፡፡ ፍትህ ሲዛባ ደግሞ ይህ ትክክል አይደለም እንደዚህ መሆን የለበትም ብሎ ድምፁን በማሰማት በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣኖችን ማሳሰብ ይኖርበታል፡፡

የሰው ሃሳብና አስተያየት የሃገር ሃብት እንደመሆኑ መጠን መንግስትም ሃገር የሚገነባው ከህዝብ ጋር አብሮ እንደሆነ ተረድቶ ህዝብን በማክበር ለህዝብ ድምጽ ጆሮ መስጠት አለበት፡፡ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በቅንነት መስማትና ራሱን በሚገባ መፈተሽ  እንጂ ህዝብን ሁልጊዜ በጥርጣሬ ማየት የህዝብ የመንግስት ግንኙነት የሰመረ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ መንግስት ግን የህዝብ ድምፅ አያስፈልገኝም ካለ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል፡፡

ህዝብም የህሊና ነፃነትና ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ ለአገር ግንባታ እንደሚጠቅም ተረድቶ ሃሳቡን መስጠት አለበት፡፡ እንዲሁም ህዝብም ሃገር ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነ ተረድቶ በትእግስት ፍላጎቱን ለመሪዎቹ ሊያስረዳቸው ትኩረታቸውን ሊስብ ያስፈልጋል፡፡

መንግስት የህዝብ አገልጋይ ነው፡፡ የመንግስት አላማ ህዝብን በሚገባ በማስተዳደር ወደ ብልፅግና ማድረስ ነው፡፡ መንግስት ህዝብን በሚገባ ካላስተዳደረ በሰዎች መካከል የሚያደላ ከሆነ ፣ መንግስት ለህዝቡ የሚገባውን አክብሮት ካልሰጠ ፣ መንግስት ህዝብን ማገልገል ላይ ካላተኮረና ህዝብን በፍትህ ካላስተዳደረ የህዝብን ልብ እያጣው ይሄዳል፡፡

የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። ምሳሌ 14፡28

በተሉያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚፈልጉ ከሆነና ህዝብን ከማገልገል ይልቅ የራሳቸው ጥቅምና ስልጣናቸውን ማስጠበቅ ላይ ካተኮሩ ስልጣናቸውን መጠበቅ ከባድ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚያድጉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ከሆኑና አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል እየከበደው ከሄደ የሃብታምና የደሃው ልዩነት እየሰፋ ከሄደ መንግስት እንደሚናወጥ ለመናገር አይቸግርም፡፡

ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና። ምሳሌ 10፡12

ረብሻንና መቁሰልንና መሞትን የሚፈልግ ማንም ሰው የለም፡፡ መንግስት እንደ አባት ልጆቹን በእኩልነት እያየ ሁሉም የሚያድጉበትና የሚለወጡበትን መንገድ ከቀየሰና ከተገበረ በዚህ የህዝብን አመኔታ ካተረፈ ህዝብ በደስታ ከመንግስት ጋር ይሰራል፡፡

መንግስት ይበልጥ የሚፈለገውና የሚከበረው እንዲሁም እየጠነከረ የሚሄደው ህዝብ ሲረካበት ብቻ ነው፡፡ የህዝብ ልብ ከመንግስት ጋር ካልሆነ ተሰሚነቱ እየጠፋ ይሄዳል፡፡

ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥ ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል። ምሳሌ 29፡14

እኛ ደግሞ የመንግስት መሪዎች ሃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡና ህዝቡም በሰላም እንዲኖር እንዲሁም ሰው ሁሉ ከዚህ ሁሉ በላይ የሆነውን የነፍስ ከሃጢያት ነፃነት እንዲያገኝ ለመንግስት ባለስልጣኖችና ለህዝቡ ሁሉ እንድንፀልይ ተጠርተናል፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች

#ፀሎት #አማርኛ #ቤተክርስትያን #ኢትዮጲያ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: