Category Archives: Identity sonship

ሰውን በክርስቶስ ማወቅ

different-eyeglass-lenses-ti-c-s-d-prescription-contact-lenses-for-astigmatism.jpg

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16

ሰው የሚያይበትና እግዚአብሄር የሚያይበት አስተያየት ይለያያል፡፡

እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7

የሰውን እውነተኛ ማንነት ሊነግረን የሚችለው የፈጠረው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ሰው ስለሰው ማንነት ቢነግረን ሊሳሳት ይችላል፡፡

ሰውን በክርስቶስ ማየት ማለት ሰውን እግዚአብሄር እንደሚያየው ማየት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚያየው ካላየ በስተቀር ሰው ሰውን በትክክል ሊረዳው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር እንደሚያየው ካላየ በስተቀር ሰው ከሰው ጋር በትክክል ህብረት ሊያደርግ አይችልም፡፡

ሰውን በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ሰውን የምናውቅው በክርስቶስ ነው ማለት ምንድነው?

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስትያንን እግዚአብሄር እንደሚወደው እንጂ ሰው እንደሚያየው አላየውም፡፡

 

ሰው በሰው ላይ ብዙ አቃቂር ሊያወጣ ይችላል፡፡ ሰው እንኳን በሰው ላይ በራሱ ላይ እንኳን እንከን ያገኛል፡፡ የሰው ፍርድ ትክክል የማይሆነው ሰው አይኑ እንዳየ ጆሮው እንደሰማ ከፈረደ ነው፡፡ የሰው ፍርድ ትክክል የሚሆነው ሰው እግዚአብሄር አንደሚያየው አይቶ በፅድቅ ከፈረደ ነው፡፡ በፅድቅ መፍረድ ማለትደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያየው አይቶ መፍረድ ማለት ነው፡፡

ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። የዮሐንስ ወንጌል 7፡24

 

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስትያን በክርስቶስ በመሆኑ ያለውን ቦታ እንጂ ሌሎች ነገሮችን አላይም ማለት ነው

ክርስትያን በእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ባለው ቦታ እንጂ በስሜታችን ልናየው አይገባም፡፡ ክርስትያን በእግዚአብሄር መንግስት ባለው ቦታ ብቻ ክብር አለው፡፡ ክርስትያን ቦታው የሚጠይቀውን ክብር ማግኘት አለበት፡፡

ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡7

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ክርስቲያን በክርስቶስ ባለው እምቅ ሃይል እንጂ በውጭ በሚታየው ድካም አላየውም፡፡

 

ክርስትያን የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ ቢደክም ድካሙን የሚሸፍን የእግዚአብሄር ፀጋ ተገልጦዋል፡፡ ስለዚህ ድካምን ብቻ አይቶ የሚያበረታውን ፀጋ አለማየት ፍርዳችንን ፍርደ ገምድል ያደረገዋል፡፡

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡9-10

 

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን በስጋ ያሉትን ነገሮች አልቆጥራቸውም

ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን ዘሩን አላይም፣  ተፈጥሮአዊ ድካሙን አላይም ፣ ፆታውን አላይም የመጣበትን የኋላ ታሪክ አላይም ማለት ነው፡፡

አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ ወደ ገላትያ ሰዎች 2፡6

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን እግዚአብሄር እንደሚያየው እንጂ ሰው እንደሚያየው አላየውም፡፡

ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት እግዚአብሄር ኢየሱስን ፍፁም አድርጎ እንደሚመለከተው እግዚአብሄር ሰውን ፍጹም አድርጎ እንደሚመለከተው መመልከት ማለት ነው፡፡

አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። ወደ ዕብራውያን 10፡14

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት እግዚአብሄር ኢየሱስን እንደወደደው ሰውን እንደሚወደው ማወቅ ነው፡፡

 

እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 17፡22-23

 

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት እግዚአብሄር ኢየሱስን በሚያይበት መነፅር ሰውን እንደሚያይ ማወቅ ነው፡፡

 

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ የዮሐንስ ወንጌል 17፡22-23

 

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት እግዚአብሄር ሰዎችን ለመገሰፅ ካልተጠቀመብን በስተቀር በራሳችን አነሳሽነት ብቻ በሰዎች ላይ እንፈርድም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3

 • ሰውን በክርስቶስ እንጂ በስጋ እንደሚሆን አላውቀውም ማለት ሰውን በክቡር ደሙ እንደተዋጀ ክቡር ፍጥረት እንጂ እንደተራ ሰው አላየውም ማለት ነው፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡18-19

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #ማንነት #የእግዚአብሄርንእይታ #በስጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #በስጋደረጃ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ስፍራ #ማእረግ #ስልጣን

Advertisements

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና

pride

አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። መዝሙረ ዳዊት 139፡13-16

እግዚአብሄርን ከማወቅ ቀጥሎ ራስን ማወቅ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄርን አውቀን በመልኩና በአምሳሉ የሰራንን ራሳችንን ካላወቅን በእርሱና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት ሊሳካ አይችልም፡፡ ራሳችንን ካላወቅን ከእግዚአብሄር ጋርና ከሌላው ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

በመድር ላይ ያሉ አብዛኛው ችግሮች መንስኤ የሰው እግዚአብሄርን ያለማወቅና ራስን ያለማወቅ ችግር ነው፡፡

ሰው ራሱን ካላወቀና እግዚአብሄር እንደሚያየው አድርጎ ካላየ ከእግዚአብሄር ጋርም ከሰውም ጋርም እንዴት እንደሚኖር ማወቅ አይችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄር እንደሚያየው ራሱን ካላየ እግዚአብሄር በህይወቱ ያለውን አላማ ለመፈፀም አይችልም፡፡

እግዚአብሄር ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር በመድር ላየ እንድንሰራ ለፈለገው ነገር በቂ ነገር በእኛ ውስጥ ፈጥሮአል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ሊፈፅም ላሰበው ነገር የሚጎድለን ምንም እምቅ ሃይል የለም፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3

ሰይጣንም በመጀመሪያ የሰው ልጅን የተዋጋው ሰው ያለውን ማንነት በማበላሸትና ለራሱ ያለውን መረዳት በማሳሳት ነው፡፡

እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡4-5

አሁንም ሰይጣን የሚጎድልህ ነገር አለ ፣ እግዚአብሄር የደበቀህ ነገር አለ ወይም እግዚአብሄር ከሚያስፈልግህ ነገር አጉድሎብሃል ብሎ በውሸት ካሳመነህ ትወድቃለህ፡፡

ነገር ግን ውብና ድንቅ አድርጎ ሰርቶኛል፡፡ እኔ የእርሱ የፈጠራ ውጤት ማሳያ ነኝ፡፡ እኔ የእግዚአብሄር የእጅ ስራ ነኝ፡፡ እኔ በህይወት ያለኝን አላማ ለመፈፀም ፍፁም ተደርጌ ተፈጥሬያለሁ ካልክ ታሸንፋለህ፡፡

እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡10

እግዚአብሄር ውብና ድንቅ አድርጎ እንደሰራኝ ራሴን ከተቀበልኩ አሸንፋለሁ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር የፈጠረኝ አፈጣጠር ላይ የማወጣው አቃቂር ካለ የህይወት አላዬን መፈፀም ያቅተኛል እሸነፋለሁም፡፡

ራሱን ያልተቀበለ ሰው ሌላውን ሊቀበል አይችልም፡፡ ሌላውን ያለመቀበል ችግር ወደኋላ ቢጠና ራስን ያለመቀበል ችግር መንስአኤ ነው፡፡

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙረ ዳዊት 139፡14

ምንም ሳላሻሽልና ሳልቀንስ ሳልጨምር ራሴን እቀበለዋለሁ፡፡ ማንም በፍጥረቴ ላይ ጥያቄ ቢኖረው ምንም ማድረግ አልችልም አዝናለሁ፡፡ እኔ ግን ፍጥረቴን እወደዋለሁ፡፡ እኔ ግን በፍጥረቴ ላይ ምንም የማወጣው እንከን የለም፡፡

እግዚአብሄር የፈጠረው የቆዳዬ ቀለም ፣ ቁመቴ ፣ ዘሬ ፣ መልኬ ፣ አስተዳደጌና ባህሪዬ ምንም አይወጣለትም፡፡ ስለ ቆዳዬ ቀለም ፣ ስለ ቁመቴ ፣ ስለ ዘሬ ፣ ስለ መልኬ ፣ ስለ አስተዳደጌና ስለ ባህሪዬ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም፡፡ ማንም በአፈጣጠሬ ላይ እንከን ያገኘበት ካለ ንስሃ ይግባና ይመለስ፡፡ ማንም ሰው አይኑ ተለቅ ቢል ኖሮ ጥሩ ነበር ቢል ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን የእጅ ስራ የማስተካክል እኔ ማነ ነኝ?

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ግሩም #ድንቅ #በክርስቶስ #መንፈስ #ማንነት #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ክብር  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ከፍታ

የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ

maxresdefault (5).jpgከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴዎስ 4፡1-3

ሰይጣን አላማው አልተለወጠም፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ ሊርድ ሊያጠፋ እንጂ ስለሌላ አይመጣም፡፡ ሰይጣን እኛንም የሚፈትነን ኢየሱስን በፈተነበትን ፈተና ነው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ባየ ጊዜ ሰይጣን የኢየሱስን የእግዚአብሄር ልጅነት ዝቅ ዝቅ የሚያደርግበት እድል ያገኘ መሰለው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ሲያየው ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅነቱን ሊያስክደው የሚችልበት በቂ ምክኒያት ያገኘ መሰለው፡፡ ኢየሱስ ተርቦ ያገኘው ሰይጣን የመንፈሳዊነትን ትኩረት ሊያስለውጠው ፈለገ፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሄር ቃልን የተሞላ ስለነበረ ለሰይጣን ፈተና በቂን መልስ መለሰ፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር ቃል ካለን ከፈተና እናመልጣለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ከሌለን ግን በሰይጣን ማታለል እንወድቃለን፡፡

የሰይጣን ፈተና ኢየሱስ ከደረሰበት ነገርና ካለበት የህይወት ሁኔታ አንፃር አይ ተሳሰቼ ነው የእግዚአብሄር ልጅ አይደለሁም ብሎ እንዲክድ ማድረግ ነበር፡፡ አሁንም ሰይጣን እኛን የሚፈትነን እንደዚሁ ነው፡፡

ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ብሎ ኢየሱስን እንደፈተነው እኛንም ሰይጣን የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ውድ መኪና አትነዳም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን በመከራ ውስጥ ታልፋለህ? የእግዚአብሄር ልጅህ ከሆንክ ለምን ትደክማለህ? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ሰው ይጠላሃል? የእግዚአብሄ ልጅ ከሆንክ ለምን ትልቅ ቤት ውስጥ አትኖርም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንል ለምን በገንዘብ ሚሊየነር አልሆንክም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን ዝነኛ አትሆንም? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ለምን በከፍታና በዝቅታ ውስጥ ታልፋለህ ? ነው የሚለን፡፡

ጥያቄው እነዚህ ከሌሉህ የእግዚአብሄር ልጅ አይደለህም የሚል መልእክትን የያዘ ነው፡፡ ጥያቄው ሰው የሚኖረው በዝናና በሃብት ነው የሚል መልእክት ያዘለ ነው፡፡ ጥያቄው ሰዎች በምድር ላይ የሚሮጡላቸው ነገሮች ከሌለህ ዋጋ የለህም የሚል መልእክት ያለው ነው፡፡

ኢየሱስ የሰይጣንን ጥያቄ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በማለት በሚገባ መልሶታል፡፡

ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች በምድር ላይ የሚፈልጓቸው ዝና ፣ ክብርና ሃብት ሰውን ሊያኖሩ የሚበቁ አይደሉም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እንዲያደርግ በመልኩና በአምሳሉ የተፈጠረ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን እየሰማና እየታተዘ እንዲኖር የተፈጠረ ነው፡፡

ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡  ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሄር ጋር በሚያደርገው ህብረት ነው፡፡ ሰው የሚኖረው ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የሚኖረው እግዚአብሄርን በመስማትና በመታዘዝ ነው፡፡

የሰይጣን አላማ ሰው የሚኖረው በምን እንደሆነ በመዋሸትና የሰውን ትኩረት በማስለወጥ ነው፡ሸ የሰይጣን አላማ ሰው እነዚህ ነገሮች ከሌሉኝ ብሎ ራሱን እንዲንቅና እንዲያንቋሽሽ ማድረግ ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው ድንጋዩን ዳቦ ባለማድረጉ እውነትም የእግዚአብሄር ልጅ አይደለሁም ማለት ነው እንዲል ማድረግ ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው የሚኖርበትን የእግዚአብሄርን ቃል በቂ እንዳይደለ ማጣጣል ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰው በእርሱ ብቻ የማይኖርበትን ሃብት ክብርና ዝና ላይ ብቻ እንዲያተኩትር ማሳሳት ነው፡፡ የሰጣን አላማ ክቡር የሆነው ሰው መኖር የማይችለበት ነገር ላይ አተኩሮ የሚኖርበትን ነገር እንዲተው ትኩረቱን ማዛባት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #የንጉስልጅ #ልጅነት ##መንፈስ #ነፍስ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

የኢየሱስና የእኛ ልጅነት እንድነት እና ልዩነት

sonship_toga_virilus (2).jpgሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ፅሁፌን ከሚከታተሉ ቅዱሳን መካከል በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ስላለ ልዩነት ብታስረዳ የሚል ጥያቄ ተቀብያለሁ፡፡ እኔም ይህ ለትምህርት ለሁላችን ይጠቅማለ ብዬ ስላሰብኩ ዛሬ ስለዚህ ሃሳብ በአጭሩ አንዳንድ ነገሮችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ ትምህርቱ በጣም ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ ናቸው የምናለውን ብቻ ስለዚህ በጣምአስረዳለሁ፡፡

የኢየሱስንና የእኛን የልጅነት አንድነትና ልዩነት ለመረዳት መጀመሪያ አንድነታችንን ብንመለከት ጥሩ መንደርደሪያ ይሰጠናል፡፡

የኢየሱስና የእኛ አንድነት

 1. ኢየሱስ በስጋ ነው የተወለደው እኛም በስጋ ነው የተወለድነው፡፡

ኢየሱስ የእኛን ስጋ ነው የለበሰው፡፡ የኢየሱስ ስጋ ከእኛ ስጋ በምንም አይለይም፡፡

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ . . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራዊያን 2፡14-15

 1. ኢየሱስ እኛ በምንፈተንበት ፈተና ሁሉ ተፈትኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ስጋ ሃጢያትን የሚያሙዋልጭ ስጋ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አልስማማም፡፡ ኢየሱስ በስጋው ሃጢያት መስራት ባይችል ኖሮ አይፈተንም ነበር፡፡ ፈተና ያለው መውደቅ ስላለ ነው፡፡ አግዚአብሄር ይመስን ኢየሱስ ግን በሃጢያት ተፈተነ እንጂ በሃጢያት አልወደቀም፡፡

ኢየሱስ በሃጢያት የማይወድቅ ስጋ ቢኖረው ኖሮ ለእኛ የቅድስና ምሳሌ ሊሆንልን አይችልም ነበር፡፡

ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። ዕብራዊያን 4፡15

 1. ኢየሱስ በተፈጥሮአዊ መንገድ በጥበብ እና በሞገስ ያደግ ነበር እኛም እናድጋለን

እኛ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ብለን ተምረን በእግዚአብሄር ነገር እንደምናድግ ሁሉ ኢየሱስን ወደምድር ሲመጣ ራሱን ባዶ በማድረጉ የተነሳ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ሁለት ብሎ መማርና ማደግ ነበረበት፡፡

ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ሉቃስ 2፡52

 1. ኢየሱስ የሚያበረታው መንፈስ ቅዱስን መቀበል ነበረበት

በስጋው ወራት ካለመንፈስ ቅዱስ አሸናፊ የእግዚአብሄ ልጅ ሆኖ ማለፍ ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን መሞላት አስፈልጎታል፡፡

ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ሉቃስ 4፡1

 1. በእግዚአብሄር ከኢየሱስ ጋር እኩል ተወደናል

እግዚአብሄር ኢየሱስን ከሚወደው ያነሰ እኛን አይወደንም፡፡

እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23

 1. ከኢየሱስ ጋር ወንድማማቾች ነን

ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው እኛም የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ኢየሱስ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም፡፡

የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13

 1. ኢየሱስን እንድንመስል ነው የተወሰንነው

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ሮሜ 8፡29

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ምሳሌ ሊያሳየን ናሙና ሊሆንልን ነው፡፡ አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር ሊያሳየን ነው፡፡

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14

 1. ኢየሱስ በምድር ላይ እንደተላከ እኛም ተልከናል፡፡

ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

 

በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነገሮች መመልከት ይጠቅመናል፡፡

የኢየሱስና የእኛ ልዩነት

 1. ኢየሱስ ሃጢያት ሰርቶ አያውቅም እኛ ግን በንስሃ ከሃጢያታችን ተመልሰን ነው፡፡

እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21

 1. ኢየሱስ የሞተ መንፈስ ኖሮት አያውቅም እኛ ግን በአዳም በሃጢያት ከእግዚአብሄር የተለየው መንፈሳችን ዳግመኛ ተወልዶ ነው፡፡

ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3

 1. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የእግዚአብሄር ብቸኛ ልጁ ነበር፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃነስ 3፡16

 1. እኛ ከዳንን በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል

ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ እና እኛም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበለው የእግዚአብሄር ልጆች በመሆናችን የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ የነበረው ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል፡፡ አሁን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንጂ አንድያ ልጅ አይደለም፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃነስ 1፡12

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

 1. ኢየሱስ አዳኛችንና ቀዳሻችን ነው

ሁላችንም በሃጢያት እስራት ውስጥ ወድቀን በነበርን ጊዜ ስለሃጢያታችን እዳ መስዋእት የሆነልን ኢየሱስ ነው፡፡

የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13

 1. ኢየሱስ ጌታችን ነው እኛ ተከታዮቹ ነን

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሮሜ 10፡9

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ናሙና #አንድያ #በኩር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የማንነት ጥያቄ ሲመለስ- ሰው ገዢ ተደርጎ ተፈጥሮአል

identity.jpgየእግዚአብሄርን የጥንቱን አላማ የምናውቀው ወደ ጥንት አፈጣጠሩ ተመልሰን የእግዚአብሄርን ቃል ስናጠና ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ሲመለስ ብዙ የህይወት ጥያቄዎቻችን ይመለሳሉ፡፡

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም ንጉስ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረው እንዲገዛ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን ወክሎ በእግዚአብሄር ቦታ በስልጣን እንዲገዛ ነው፡፡

እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ዘፍጥረት 1፡26

ሰው የተባረከው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተለቀቀው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የታጠቀው ለገዢነት ነው፡፡ ፈቃድ የተሰጠው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው ብቁ የተደረገው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተላከው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተወከለው ለገዢነት ነው፡፡ የተባረከው ሞገስ የተሰጠው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተቀባው ለገዢነት ነው፡፡

እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡26-28

ህዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት እግዚአብሄር ሙሴን ሲጠራው ለነፃነት አላማው የሚያስፈልገውን ስልጣን ሁሉ ሰጥቶት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን ሲጠራው ማንም እንዳያቆመው በፈርኦን ላይ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶት ነው፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሄር ሙሴን እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ ያለው፡፡

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። ዘጸአት 7፡1

እኛንም ሲጠራን እግዚአብሄር አልሰሰተም፡፡ እግዚአብሄር የጠራን የመለኮታዊ ባህሪው ተካፋዮች እንድንሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር የጠራን በህይወት በአሸናፊነት እግዚአብሄር የጠራንን ስራ ፈፅምን እንድናከብረው ነው፡፡ እግዚአብሄር የጠራን ምንም ሃይል እስከማያደናቅፈን ድረስ የሚያስፈልገንን የገዢነት ስልጣን ሁሉ ሰጥቶን ነው፡፡

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3

ኢየሱስ በምድር ሲመላለስ የዘመኑ ሃይማኖት መሪዎች ሊወግሩት በፈለጉ ጊዜ ሃጢያት ስለሰራ እንደማይወግሩት ነገር ግን የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ በማለቱ እንደሚወግሩት ነገሩት፡፡

ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ዮሃንስ 10፡32-33

እርሱ ግን ለሰው ልጅ ገዢ ወይም አምላክ መባል ብርቅ እንዳይደለ አስረዳቸው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የመጣላቸው ሰዎች እግዚአብሄር ቃል በመጣላቸው ክልል ገዢዎችና አማልክት እንደሆኑ በመፅሀፍ ቅዱስ እንደተፃፈ ኢየሱስ ቃሉን ጠቅሶ አስታወሳቸው፡፡ ኢየሱስ ስለማንም ሰው አመለካከት የእግዚአብሄር ቃል እንደማይሻር አስረዳቸው፡፡

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? ዮሃንስ 10፡34-36

አንዳንድ ሰው ለእግዚአብሔር ከአግዚአብሄር በላይ ፃዲቅ ሊሆን ሲሞክር የእግዚአብሄርን ቃል የሚለውን ለማለት እንኳን ይሳሳል፡፡ ከእግዚአብሄር በላይ ለእግዚአብሄር ልንቀናለት አንችልም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ካለስስት በመልኩና በአምሳሉ ስለፈጠረ በመልኩና በአምሳሉ ተፈጥሬያለሁ ማለት መፍራት የለብንም፡፡

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና የሚለውን እንዳለ መቀበል እንጂ ለእግዚአብሄር ካለእውቀት በመቅናት ለማሻሻል መሞከር የለብንም፡፡

 

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙር 139፡14

ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል እንዳለ ካልተቀበሉትና በሰው ትምህርት ለማሻል ከሞከሩ ሃይሉን ያሳጡታል፡፡

ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ማርቆስ 7፡13

ሰዎች ለእግዚአብሄር ከራሱ ከእግዚአብሄር በላይ ሲጠነቀቁለት ይስታሉ፡፡ ጌታን ማምለክ ማለት እግዚአብሄር በቃሉ ናችሁ ያለንን ነን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት እግዚአብሄር በቃሉ አይደለህም ያለኝን አይደለሁም ብሎ መቆም ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር የእግዚአብሄርን ቃል ሳያሻሽሉ ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ አንዳለ አሜን ብሎ መቀበል ነው፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ ያለውን ላለማለት ሰዎች አጉል ትህትና ሲይዛቸው ከእግዚአብሄር በረከት ይጎድላሉ፡፡ ሰዎች ቃሉ ያለውን ለማለት ካልፈለጉ ትህትና ሳይሆን ትእቢት ነው፡፡ ትህትና እንደ ማሪያም የእግዚአብሄርን ቃል አሜን ብሎ መቀበል ነው፡፡ ሉቃስ 1፡38

ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። ቆላስይስ 2፡18

መፅሃፍ ቅዱስ የመለኮት ሙላት በተሞላ ኢየሱስ ተሞልታችኋል ሲል ትሁት ሰው አሜን ይላል፡፡

በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡9-10

እግዚአብሄርን የምናመለከው በእውነትና በመንፈስ እንጂ በራሳችን አነሳሽነት በገዛ ፈቃዳችን እና ፍልስፍናችን አይደለም፡፡

ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም። ቆላስይስ 2፡23

በእውነትና እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆነን አምልኮ እንጂ በገዛ ፈቃዳችን ራሳችንን ቃሉ እንደማይለው ማዋረድ “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” 2ኛ ጢሞ 3፡5 የተባሉ ባዶ የሃይማኖት መልክ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ክርስትና እግዚአብሄር ምንም ይሁን በቃሉ ነህ ያለውን ነኝ ብሎ መቀበል ነው፡፡ ክርስትና በቃሉ እግዚአብሄር አይደለህም ያለውን አይደለሁም ብሎ ለመቀበል ትሁት መሆን ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #የንጉስልጅ #ልጅነት ##መንፈስ #ነፍስ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

የማንነት አንገብጋቢ ጥያቄ ሲመለስ

identity question.jpgየማንነት ጥያቄ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ መመለስ ሁሉም ባይሆንም አብዛኛው የህይወት ጥያቄ ይመልሳል፡፡ የማንነት ጥያቄ መመለስ እንደ ደረጃችን መኖርን ያስችለናል፡፡ ምክኒያቱም ሰው እንደሚያስበው እንደዚሁ ነውና፡፡

የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ የሚያስብ እንደ እግዚአብሄር ልጅ ይኖራል፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ የማያስብ የእግዚአብሄር ልጅ እንዳልሆነ ከደረጃ በታች የሆነ የሰው ብቻ ኑሮ ይኖራል፡፡

አንዱ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም፦ እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡4

የማንነት ጥያቄ የፍጥረት ጥያቄ ነበር፡፡

እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27

ሰው እንደተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ይኖር ነበር፡፡ አትብላ የተባለውን በመብላት እግዚአብሄር ላይ በማመፅ በሃጢያት እስከወደቀ ድረስ በእግዚአብሄር ክብር ይኖር ነበር፡፡ ሰው በሃጢያት ሲወድቅ ብቻ ነበር የእግዚአብሄር የእግዚአብሄር ክብር የጎደለው፡፡

ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ሮሜ 3፡23

ሰይጣንም በመጀመሪያ ጥቃት የሰነዘረው የሰው የማንነት ምስል ላይ ነው፡፡ የማንነት ምስሉ ከተበላሸ ሰው ይበለሻል፡፡ የማንነት ምስሉ ካልተበላሸ ሰውን ማበላሸት በፍፁም አይቻለም፡፡ የሰው ማንነት መስተካካለ ካለበት የሰው ማንነት ምስል ወደ ቀደመው ወደጥንቱ ምስሉ መመለስና መስተካከሉ አለበት፡፡

የማንነት ጥያቄ የሰይጣን ፈተና መሳሪያ ነበር

ይህ የማንነት ጥያቄ በኢየሱስም የአገልግሎት ዘመን ቀጥሎዋል፡፡ ሰይጣን ኢየሱስን የፈተነው በማንነት ዙሪያ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ” የሚለው የሰይጣን ንግግር የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ ትላለህ እንጂ አይደለህም የሚልን ተዘዋዋሪ መልክት ያስተላልፋል፡፡

ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴዎስ 4፡3

የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ የሚለው ሌላው ንግግር የሰይጣንን በማንነት ላይ ያነጣጠረ ግልፅ ጥቃትን ያሳያል፡፡

ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ፦ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ማቴዎስ 4፡5-6

ሌላው ሰይጣን ያነሳው ጉዳይ የእግዚአብሄር ቃል እውነት አይደለም የሚል መልክትን ያዘለ ነው፡፡ ስለማንነታችን የእግዚአብሄርን ቃል ካላመንን የማመን እድላችንን ጨርሰናል ማለት ነው፡፡ በውስኑ አእምሮዋችን ባንረዳውም እንኳን የእግዚአብሄር ቃል ነህ የሚለንን ነኝ ለማለት ፣ የእግዚአብሄር ቃል አለህ የሚለንን አለኝ ለማለትና የእግዚአብሄር ቃል ታደርጋለህ የሚለንን አደርጋለሁ ለማለት መፍራት የለብንም፡፡ እንዲያውም መፍራት ያለብን የእግዚአብሄር ቃል የማይለንን ለማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚለንን ማለት ትእቢት ሳይሆን ትህትና ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚለንን አለማለት ደግሞ ትህትና ሳይሆን ትእቢት ነው፡፡ የሆነውን አይደለሁም ማለት በአጉል ትህትና ከእግዚአብሄር በላይ ፃዲቅ ለመሆን መሞከር ነው፡፡

ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። ቆላስይስ 2፡18

ማንነታችንን አውቀን አናውቅም ብንል ስህተተኛ እንሆናለን፡፡ ኢየሱስ ስለማንነቱ እንዲክድና ንስሃ እንዲገባ የወቅቱ የሃይማኖት መሪዎች ሲያዋክበት እናንት የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ በማለት እንደምትዋሹ ሁሉ እኔ እንደሆንኩ የማውቀውን ነገር አላውቅም ብል ውሸተኛ እሆናለሁ አላቸው፡፡

አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ ቃሉንም እጠብቃለሁ። ዮሃንስ 8፡55

የማንነት ጥያቄ የኢየሱስ አገልግሎት ጥያቄ ነበር

ኢየሱስን ለመውገር የተነሱ የወቅቱ የሃይማኖት መሪዎች ስለማናቸው ሃጢያት ነው የምትወግሩኝ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የመለሱለት ስለ የትኛውም ሃጢያት ሳይሆን አንተ ሰው ስትሆን የእግዚአብሄ ልጅ ነኝ በማለትህ ነው በማለት ሊገድሉት የሚፈልጉ በማንነት ጥያቄ ዙሪያ እንደሆነ በግልፅ መልሰዋል፡፡

ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ዮሃነስ 10፡32-33

አይሁዳዊያን የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ ማለት የአምላከ ቤተሰብ ነኝ ማለት ፣ የነገስታት ቤተሰብ አባል ነኝ ማለትና የአምላክ የቤተሰብ አባል ነኝ ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?  ዮሃንስ 10፡34-36

የተሃድሶ ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ነበር

ማርቲን ሉተር የዛሬ 500 አመት የበተራለት የሰው የማንነት ጥያቄ እና የደህንነት ጥያቄ መልስ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ህዝቡ ምንም እንዳይደለ ፣ በነፃ መዳን እንዳደማይችል ፣ ከእግዚአብሄር ጋር በቀጥታ ሊገናኝ የሚችልበት ማንነት እንደሌለው ፣ መፅሃፍ ቅዱስን አንብቦ መረዳት እንዳይችል ፣ ለምንም ነገር ካህን እንደሚያስፈልገው የማንነት ምስሉን አጥፍተውበት በእስራት እና በጨለማ ያኖሩት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ማርቲን ሉተር ስለደህንነቱ የእግዚአብሄርን ቃል ተረድቶ ስላስረዳና የእግዚአብሄር ቃል የሚለውን ስላለ እጅግ ያሳድዱት ነበር፡፡

የማንነት ጥያቄ የእኛም ዘመን ጥያቄ ነው

አሁንም ቢሆን አንገብጋቢው ጥያቄ ይህ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” 2ኛ ጢሞ 3፡5 የተባሉ ባዶ ሃይማኖተኞችንና የእግዚአብሄርን ቃል የተረዱ ሰዎችን የሚያጋጨው ይህ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኙ የተቀበለ ሰውን የእግዚአብሄር ቃል ፀድቋል ሲል የዳነ ፃዲቅ ነን ሲል ማን ስለሆንክ ነው የሚል ጥያቄ እና ስደት ይነሳል፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ ነን የኢየሱስ ወንድም ነን ስንል በፍፁም ሊሆን አይችልም የሚል ተቃውሞ አለ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚለንን ለማለት አንፍራ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ያላለንን ለማለት አንድፈር፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ያላለንን በማለት ልንስት እንችላለን፡፡  የእግዚአብሄር ቃል ያለንን በማለት ግን ልንስት አንችልም፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #የንጉስልጅ #ልጅነት ##መንፈስ #ነፍስ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

የስኬት መለኪያው

success.jpg

በህይወታችን ስኬት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ህይወታችን በስኬት ካልተለካ ብክነት ነው፡፡ ህይወቴ በስኬት ጎዳና ላይ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በትክክል ካልተመለሰ ህይወታችን ካለፍሬና ውጤት አለመቅረቱ ምንም ማረጋገጫ አይኖረውም፡፡ ስኬት ደግሞ በአጋጣሚ የሚመጣ እድል አይደለም፡፡ ስለስኬት በሙሉ ስልጣን የሚነግረን የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡

ስኬት ደግሞ የሚለካው የተፈጠርንበትን አላማ በመፈፀም ነው፡፡ ስኬት የሚለካው እግዚአብሄር እንደፈጠረን ንድፍ ወይም ዲዛይን መኖራችንን በመለካት ነው፡፡ ግን ጥያቄው ስኬት በምን ይለካል? ነው፡፡

ስኬት የሚለካው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን ለመፈፀም የሚያስችለን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ይታያል ወይ? የሚለውን ጥያቄ በታማኝነት በመመለስ ነው፡፡ በክርስትያና ስኬትን እንደኪሎና ርዝመት መለካት ቀላል ባይሆንም ነገር ግን ስኬት የሚለካባቸውን መመዘኛዎች ከእግዚአብሄር ቃል በመመልከት በስኬት ጎዳና ላይ መሆናችንና አለመሆናችንን መመዘን እንችላለን፡፡

እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ጥሪ ለመፈፀም የክርስቶስ ባህሪ ይጠይቃል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረውን አላማ ለመፈፀም የጠየቀው ባህሪ ነበር፡፡ አሁንም እኛ የእግዚአብሄር አላማ በህይወታችን ሙሉ ለሙሉ እንዲፈፀም የሚጠይቀን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ላይ መታየቱ ነው፡፡

ሰዎች የሚያከብሩዋቸውና የሚሰግዱላቸው ነውር የሚባሉ ነገሮችን መናቅ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን መሉ ለሙሉ እንድንፈፅም ይረዳናል፡፡ የሰው አስተያየት ሳይሆን የእግዚአብሄር ቃል የህይወታችን መመዘኛ ከሆነ በስኬት ጎዳና ላይ ነን፡፡

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2

ሩጥ ተቀደምክ ታለፍክ የሚለውን የአለም የፉክክር ድምፅ ችላ ብለንና በፈቃደኝነት ራሳችንን ከፉክክር አግለን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም በትግስት ከሮጥን የተሳካልን ሰዎች እንደሆንን ሌላ ማርጋገጫ አያስፈልግም፡፡

ስኬታማ እንዳንሆን የሚያግደን የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ውስጥ አለመታየቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ባህሪ የማይታይበት ሰው ስኬታማ ነኝ ቢል ከንቱ ራሱን ያታልላል፡፡ የክርስቶስ ባህሪ የማይታየበት ሰው በሌላ በሁሉም ነገር ስኬታማ እንደሆነ ቢመስለው ስኬታማ አይደለም፡፡ የክርስቶስን ባህሪ በህይወቱ ለመገንባት ቅድሚያ የማይሰጥ ሰው ህይወቱን በከንቱ ያባክናል፡፡

እውነተኛ የስኬት መመዘኛ የክርስቶስ ባህሪ በእኛ ውስጥ መታየቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ባህሪ በህይወቱ የተገነባ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ እየፈፀመ ነው፡፡ የክርስቶስን ባህሪ የተላበሰ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ላለመፈፀም የሚያግደው ምንም ሃይል አይኖርም፡፡ የክርስቶስን ባህሪ በሚኖር ሰው ላይ የሚሰራ ህግ የለም፡፡

የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። ገላትያ 5፡22-23

የክርስቶስ ባህሪ ያለው ሰው ህጉን ፈፅሞታል፡፡ የክርስቶስ ባህሪ ካለው ሰው ውጭ የእግዚአብሄርን አላማ በህይወቱ ፈፅሞ ለማለፍ ብቃቱ ያለው ሰው የለም፡፡

ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ገላትያ 5፡14

በየደረጃው ላለው ለእግዚአብሄር አሰራር ራሱን ትሁት ከሚያደርግ ሰው በላይ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈፀም የሚያስችል ስልጣን ያለው ሰው የለም፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ፊልጵስዩስ 2፡5-8

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ትህትና #ትእግስት #መከተል #ክርስቶስእስኪሳል #መምሰል #ክርስቶስንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር

sonship 777.jpgአንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ 1፡15

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለክብሩ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄ ክብር ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ክብር የጎደለው በሃጢያት ሲወድቅ ነው፡፡

ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ በመክፈሉ ኢየሱስን የሚቀበል ሰው ሁሉ እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ይቀበለዋል፡፡

ኢየሱስን የተቀበለ ሰው ሁሉ የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡

ግን የእግዚአብሄር ልጅ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር እስካላወቅን ድረስ የልጅነት ጥሪያችንን መረዳት አንችልም፡፡ የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር እስካልተረዳን ድረስ ልጆች ሆነን መመላለስ አንችልም፡፡ የእግዚአብሄር ልጅነትን ክብር እስካልተረዳን ድረስ በልጅነት መብትና ስልጣን መኖር ያቅተናል፡፡ የእግዚአብሄርን ልጅነት ክብር እስካልተረዳን ድረስ በእግዚአብሄር ልጅነት ደረጃ በመኖር እግዚአብሄር በህይወታችን ላይ ያለውን አላማ መፈፀም አንችልም፡፡

ልጅ ላልሆኑት የልጅነትን ክብር ሊያሳይ የሚችለ ልጅ የሆነ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ልጅነት  ክብር የምናየው የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ከነበረው ከኢየሱስ ነው፡፡ አሁን ኢየሱስ የእግዚአብሄር አንድያል ልጅ አይደለም፡፡ በኢየሱስ የሚያምኑትን እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ስለተቀበላቸው እግዚአብሄር ብዙ ልጆች አሉት፡፡ አሁን ኢየሱስ የበኩር ልጅ ነው፡፡

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ስለሃጢያታችን በመስቀል ላይ ዋጋ ለመክፈል ብቻ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የሃጢያታቸውን መስዋእት ኢየሱስን የተቀበሉ ሰዎች የእግዚአብሄር ልጅ ሲሆኑ እንዴት እንደሚኖሩ ለማሳየት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣውና የተመላለሰው የእግዚአብሄር ልጅ ክብር ምን እንደሆነ ለሚመጡት ልጆች ለማሳየት ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ እንደሰው የተመላለሰው ለተከታይ የእግዚአዘብሄር ልጆች የእግዚአብሄር ልጅነትን የክብር ደረጃ ሊያሳየን ነው፡፡

ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ እኛ የእየሱስ ተከታዮች ሁለተኛ ሶስተኛ አራተኛ ሚሊዮነኛ . . . ልጆች ነን፡፡

ከኢየሱስ በፊት የእግዚአብሄር ልጅ በምድር ላይ ስላልነበረ የእግዚአብሄር ልጅነት ደረጃ ምን እንደሆነ አንረዳም ነበር፡፡ ከኢየሱስ በፊት የእግዚአብሄር ልጅነት ክብር ምን አይነት ክብር እንደሆነ አናውቅም ነበር፡፡ ኢየሱስን እስከምናየው ድረስ የእግዚአብሄር ልጅነት ማእረግ ደረጃውን አናውቅም ነበር፡፡ በኢየሱስ ካልሆነ በስተቀር የእግዚአብሄር ልጅነትን መብት የምናውቅበት ምንም መንገድ አልነበረም፡፡

ኢየሱስ ሲመጣ ግን የእግዚአብሄር ልጅነትን መብት አሳየን፡፡ ኢየሱስ በምድር ሲመለስ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ማእረግ አሳየን፡፡ ስንፈጠር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል እንደፈጠርን ሁሉ የተጠራነው የልጁን የኢየሱስን መልክ እንድንመስል ነው፡፡

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

አባት ልጁን እንዴት እንደሚሰማው ያየነው በኢየሱስ ነው፡፡ አባት ልጁን እንዴት እንደሚወደው ያለየነው በኢየሱስ ነው፡፡

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሐንስ 17፡22-23

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ናሙና #መልክ #አምሳል #ልጅ #አባት #ክብር #ማእረግ #መብት #ስልጣን #ስፍራ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የልጅነት መንገድ

son afther.jpg22.jpgእግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው የቤተሰቡ አባል እንዲሆንና ከእርሱ ጋር የአባትና የልጅ ህብረት እንዲኖረው ነው ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ልጁ እንዲሆን ነው፡፡ ሰውን የፈጠረው እግዚአብሔር ለሰው አባቱ ሊሆነው ነው፡፡

እግዚአብሔር ለሰው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአምስት ቀን ውስጥ ሰርቶ በስድስተኛው ቀን ሰውን ፈጠረው፡፡ ሰው በስድስተኛው ቀን የተፈጠረው እንደ ልጅ ከአባቱ ጋር በሰባተኛው ቀን እንዲያርፍ ነው፡፡

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር የቤተሰብ አባልነቱና በልጅነቱ ለዘላለም እንዲኖር ነበር፡፡ ስለዚህ ነው እግዚአብሔር የተከለከለውን እንዳይበላ ሰውን ሲያዘው የምንመለከተው፡፡ እግዚአብሔር ለሰውን ልጅ ሆኖ ለዘላለም የሚኖርበትን መንገድ አሳየው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሰው ካልታዘዘ ከልጅነቱ እንደሚሻር ከእግዚአብሔር ጋር ያለው የአባትና የልጅ ግንኙነት እንደሚቋረጥ አስጠነቀቀው፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17

ሰው እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ በመንፈሱ ሞተ፡፡ ሰው እግዚአብሔር ላይ በማመፁ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው የአባትነት እና የልጅነት ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ቤት ወጣ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ከአባቱ ጋር ተጣልቶ በመንፈሳዊ አነጋገር ጎዳና ተዳዳሪ ሆነ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር የሚመጡለት የቤተሰብ አባል መብቶችና ጥቅሞች ሁሉ ተቋረጡበት፡፡

ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላ፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ላይ አመፀ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ህልውና ራቀ፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ተለየ፡፡ ሰው በራሱ ሆነ፡፡ በአዳም ሃጢያት ምክኒያት ሃጢያት በሰው ልጆች ላይ ሁሉ ወደቀ፡፡

እግዚአብሔር ለዘላለም አብሮት እንዲኖር የፈጠረው ሰው ከእርሱ ለዘላለም እንዲለይና እንዲጠፋ አልወደደም፡፡ ኢየሱስን ወደምድር በመላክ የሃጢያትን እዳ ሁሉ እንዲከፍል አደረገው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የአባትነትና የልጅ ግንኙነት እንዲቋረጥ ያደረገውን የሃጢያትን እዳ በመስቀል ላይ በመሞት ሙሉ ለሙሉ እንዲከፍል አደረገው፡፡

አሁን የሃጢያት እዳ ሁሉ ተከፍሎዋል፡፡ አሁን እንደገና መታረቅ እንችላለን፡፡ አሁን ወደ ቤተሰቡ መመለስ እንችላለን፡፡

ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡18-19

ኢየሱስን እንደ አዳኛችንና እንደ ህይወታችን ጌታ ከተቀበልነው እግዚአብሔር መልሶ ልጅ አድርጎ ይቀበለናል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 1ኛ ዮሐንስ 4፡10

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። 1ኛ ዮሐንስ 3፡1

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #አቅርቦት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ጥሪ #ክህንነት #ስራ #መልክተኛ #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: