Category Archives: Vision and Leading

አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን

your will.jpgጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ማቴዎስ 26፡39

ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42

አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ማርቆስ 14፡36

እኛ ለእግዚአብሄር ክብር ለመኖር የተጠራን ሁላችን ለእግዚአብሄር መኖር እንፈልጋላን፡፡ ኢየሱስን ስንከተል ለክብሩ ለመኖር ወስነን ነው፡፡ ኢየሱስን የተከተልነው ለሞተልንና ለተነሳው ለኢየሱስ እንጂ ወደፊት ለራሳችን ላለመኖር ነው፡፡

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።  2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15

በተለያየ ጊዜያት በህይወታችን የተለያዩ ምርጫዎች ይቀርቡልናል፡፡ በተለይ ኢየሱስን በሁለንተናችን ለመከተል የወሰንንእኛ ክርስትያኖች በየጊዜው የእኛ ፍላጎትና የእግዚአብሄር ፍላጎት ሲለያይ እንመለከታለን፡፡ በህይወት ጉዞዋችን እኛ የምንፈቅደውና እግዚአብሄር የሚፈቅደው በፊታችን እንደምርጫ ሲቀርብልን እናገኛለን፡፡፡ እኛ በህይወታችን እንዲሆን የምንወደው ነገር እግዚአብሄር የማይወደው ነገር ይሆንና እጅግ እንጨነቃለን፡፡ ወይም እኛ የማንወደው ነገርን እግዚአብሄር ይህንን እወዳለሁ ሲለን የእግዚአብሄርን ወይም የእኛን ለመምረጥ በውሳኔ መካከል ራሳችንን እናገኛለን፡፡

የራሳችንን ፈቃድ መከተል ለጊዜው ደስ ይል ይሆናል እንጂ ዘለቄታዊነት የለውም፡፡ የራሳችንን ፍላጎት መከተል እኛን ከእግዚአብሄር ፈቃድ በረከቶች ውጭ ያደርገናል፡፡ የራሳችን ፈቃድ መከተል በምድር ላይ ያለንን አንድ የህይወት እድል እንድናባክነው ያደርገናል፡፡  የራሳችንን ፍላጎት መከተል የእግዚአብሄር አብሮነት ያሳጣናል፡፡ የራሳችን ፍላጎት መከተል ክስረት ያመጣብናል፡፡ የራሳችንን ፍላጎት መከተል በእግዚአብሄር ፊት ያለንን ድፍረት ያሳጣናል፡፡

የእኛ ምርጫ ችግር አለበት፡፡ የእኛ ምርጫ ሁሉን የማያውቅ ሰው ምርጫ ነው፡፡ የእኛ ምርጫ እውቀት የጎደለው ሰው ምርጫ ነው፡፡ የእኛ መርጫ እንከን አያጣውም፡፡ በአለም ላይ የእጅግ ጥበበኛው ሰው ምርጫ ፍፁም አይደለም ጉድለት አለበት፡፡

የእግዚአብሄር ምርጫ ሁሉ የሚችል አምላክ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ የቅዱስ አምላክ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ የፍቅር አምላክ ምርጫ ነው፡፡

ስለዚህ ነው በራሳችን ፈቃድና በእግዚአብሄር ፈቃድ መካካል የምንጨነቀው፡፡ የእኛ ምርጫ ምን ያህን እንከን እንዳበት ስለምናውቅ በራሳችን መንገድ ላመሄድ ከራሳችን ጋር እንከራከራለን፡፡ በራሳችን ማስተዋል መደገፍ ስለማንፈልግ ነው ሁልጊዜ የእግዚአብሄርን ምርጫ መከተል የምንፈልገው፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ምሳሌ 3፡5

የእግዚአብሄር ምርጫ የተሳሳተና የማይመስል ብዙዎች የማይደግፉት ቢሆን እንኳን የእርሱ ምርጫ ከየትኛውም መርጫችን የተሻለ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ ሞኝነት ቢመስል እንኳን የእግዚአብሄር ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይጠበባል፡፡

ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25

ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42

ፀሎት

እግዚአብሄር ሆይ ስለተናገርከኝ ስለዚህ ቃል አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በሁለንተናዬ ለአንተ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ የአንተን ፈቃድ ብቻ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ፈቃድህን ስለምትገልጥልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ፈቃድህን እንድከተል ሃይል ስለምትሆነኝ ፀጋህን ስለምታበዛልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አንተን በሁለንተናዬ እስከመጨረሻው ተከትዬህ ስለማልፍ አመሰግንሃለሁ፡፡ ስለ ሁሉም ተመስገን ፡፡ በኢየሱስ ስም ፡፡ አሜን

Advertisements

በተጠራችሁበት መጠራታችሁ

Lord-calling.jpgእንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ኤፌሶን 4፡1

እግዚአብሄር ለክብሩ ፈጥሮናል፡፡ ወደዚህ መደር ከመፈጠራችን በፊት በምድር ላይ እንድናደርገው የታቀደው ነገር ስለነበረ ወደዚህ ምድር ተፈጥረናል፡፡ ወገጌታ መነግስት ከመጣረራታችን ባሻገር እንወቀውም አንወቀውንም ወደምድር የመጣንበት ምክኒያት አለ፡፡ እያንዳንዳችን በምድር ላይ ልንሰራው የሚገባው ስራ ወይም ጥሪ አለን፡፡

በራሳችን አነሳሽነት ለእግዚአብሄር ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት ጥሪዬ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ወሳኝ ነው፡፡ በምድር ላይ ያለን ህይወት አንድ ህይወት ነው፡፡ ይህንን ህይወት እግዚአብሄር ለጠራን መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ ይህን ህይወት እግዚአብሄር ላልጠራን ነገር ላይ ማዋል ብክነት ነው፡፡

የአካል ብልቶቻችን እያንዳንዳቸው የተለየ ስራና ጥሪ እንዳለቸው ሁሉ እያንዳንዳችን በምድር ላይ እንድንሰራው የተላክነው የተለያየ ስራና ጥሪ አለን፡፡ ያንን ጥሪ ማግኘትና መከተል የእኛ ሃላፊነት ነው፡፡

ጥሪ ከጎረቤት አይኮረጅም፡፡ ጥሪ የሚገኘው ከጠራን ከእግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሀር ለእያንዳንዳችን ጥሪ አለው፡፡ የእኛ ሃላፊነት እግዚአብሄን መፈለግና ጥሪያችንን ማወቅ ነው፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርሚያስ 29፡11-13

በምድር ላይ ያለሁት ለምን አላማና ጥሪ ነው? ብሎ መጠየቅ ፣ ጥሪን አውቆ በትጋት መከተል ከምንም ነገር በላይ ስኬታማ ያደርገናል፡፡

ጥሪያችንን ስንከተል ከጥሪያችን መንገድ ሊስወጡ የሚመጡ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡ የጥሪያችን አንዱ ክፍል ነውና እንታገሰዋለን፡፡

የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡21

ከጥሪያችን ውጭ መኖር ምንም ዋስትና የለንም፡፡ በጥሪያችን ላይ መኖራችን ግን ክፉ ነገር እንኳን ቢሆን ለመልካምነታችን እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡

እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28

ሰዎች ከተለያየ ቦታ ሽልማትን ያገኛሉ፡፡ ከእግዚአብሄር የሆነ ሽልማት ያለው ጥሪን በመከተል ውስጥ ብቻ ነው፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። ፊልጵስዩስ 3፡14

የጠራንን ጥሪ ለማድረግ ስንተጋ እርሱ የእኛን ነገር ለመስራት ታማኝ ነው፡፡

የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡24

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥሪ #ምስክር #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ

pride.jpgከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ቆላስይስ 2፡20-21

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሚል ትእዛዝ ለእኛ በክርስቶስ አምነን ለዳንን አይገባንም፡፡ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሚል ትእዛዝ ለእኛ የማይመጥንበትን ምክነቢያቶች እንመልከት

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ አለማዊ ስርአት ነው

በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄር መንፈስ በውስጣቸው አይኖርም፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄርን ፍቅር አልተረዱም፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄር ፍቅር አይመራቸውም፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች መንፈሳቸው ሙት ነው፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች በእግዚአብሄር መንፈስ ህያው አልሆኑም፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄር ቃል በውስጣቸው የለም፡፡ ስለዚህ  አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ትእዛዝ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ ኤፌሶ 2፡1

በአለም ያሉ ሰዎች የሚመሩት አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ  ስርአት ብቻ ነው፡፡ ሌላ የሚያሸንፍ መንፈስ በውስጣቸው ስለሌለ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ትእዛዝ ብቻ ነው በአለም ያሉትን ሰዎች የሚያሸንፋቸው፡፡ ለእኛ ግን መንፈሳችን ህያው ስለሆነ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ትእዛዝ አያስፈልገንም፡፡ እኛ በኢየሱስ ስለምንኖር ቃሎቹም በውስጣችን ስለሚኖር እግዚአብሄር በመንፈሱ አማካኝነት ይመራናል፡፡

በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ዮሃንስ 15፡7

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የመጀመሪያ ትምህርት ነው

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የመጀመሪያ ትምህርት ነው፡፡ ልጅ መጀመሪያ የነገሮችን ጉዳትና ጥቅም በራሱ ስለማይረዳ ትእዛዘ ይሰጠዋል፡፡ ልጅ በራሱ አነሳሽነት ነገሮችን ለማድርግ ብቃቱን ስላዳበረ ትእዛዝ በትእዛዝ ይሰጠዋል፡፡ ልጅ እራሱ አውቆ ነገሮችን ስለማይሰራ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ተብሎ ይታዘዛል፡፡

ጎልማሳ ሰው ግን ይህ አያስፈልገውም፡፡ የነገሮችን ጥቅምና ጉዳት ስለሚያመዛዘን በራሱ ይወስናል፡፡ በተመሳይ መልኩ በክርስትና የምንመራው በህጉ መንፈስ እንጂ በህጉ ፊደል አይደለም፡፡ ህጉን ተረድተን በገባነ መንገድ እንተረጉመዋለን እንጂ ሰዎች ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ እያሉ እንደህፃን ልጅ እንዲመሩን እንጠብቅም፡፡  ቃሉን ሰምተን የታዘዘው ትእዛዝ ለምን እንደታዘዘ ተረድተን እናደርገዋለን እንጂ በእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን ይህን አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሚለን ሌላ ሰው እንጠብቅም፡፡

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሰው ስርአት ነው

አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ የሰው ስርአት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስርአት አንድ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስርአት ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስርአት እግዚአብሄርን እና ባልንጀራህን ውደድ ነው፡፡ ትእዛዛት ሁሉ በሁለቱ ትእዛዛት ይጠቃለላሉ፡፡

እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። ሮሜ 12፡8-10

የትእዛዛት ሁሉ አላማ እኛ በፍቅር እንድንኖር መርዳት ነው፡፡

የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5

ከፍቅር ህግ በላይ የሚጨምር ግን ህጉን ይሽረዋል፡፡

ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ማርቆስ 7፡13

ለእኛ ግን የእግዚአብሄር ምንፈስ በእናንት ውስጥ ይኖራል እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ ነው የምንባለው፡፡

እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሃንስ 2፡20-27

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አትያዝ #አትቅመስ #አትንካ #አለማዊ #ስርአት #መጀመሪያ #ፅድቅ ሰላም #መንፈስቅዱስ #ደስታ #መብል #መጠጥ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አለም #ድምፅ #ቅባት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መሪ

የእግዚአብሔር ሶስቱ የምሪት ደረጃዎች

leading.jpgአስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ። መዝሙር 32፡8

የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል እንደማወቅ የሚያሳርፍና የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር የተስፋ ቃሎች ንፁህ ናቸው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የነጠረ ነው፡፡

በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው። መዝሙር 12፡6

የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው። ምሳሌ 30፡5-6

እግዚአብሄር በተስፋ ቃሉ እንዲህ ይላል፡፡

  • አስተምርሃለሁ

እግዚአብሄር የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄ የፈጠረን ለአላማው ነው፡፡ ከመፈጠራችን በፊት በምድር ላይ ይምንሰራው ስራ ነበር፡፡ የተፈጠረንው እኛ የምንሰራው ስራ ስልነበረ ነው፡፡ ያንን ስራ ሊያሳየን ሊያስተምረን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡

በእግዚአብሄር ካልተማርንና ካለ እውቀት ከሆንን እንደምንጠፋ እግዚአብሄር ያውቃል፡፡ በእግዚአብሄር ካልተማርን የተፈጠረንበትን አላማ መፈፀም አንደማንችልና ሰላም እንደማይኖረን እግዚአብሄር ያውቃል፡፡

ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። ኢሳያስ 54፡13

እኛ መማር ከምንፈልግው በላይ እግዚአብሄር እንድንማርለት ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በመረጠው መንገድ ሃሳቡን ይገልጣል ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በተለያየ መንገድ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር ሲናገር እናውቃለን፡፡ እግዚአብሄ ይናገር እንጂ የማናውቅው የእገዚአብሄ ንግግር የለም፡፡ እግዚአብሄር ሲያስተምር ልባችን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ደረጃ ወርዶ በሚገባን ቋንቋ ያስተምረናል፡፡

እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ኢዮብ 33፡14

  • በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤

ያስተማረንን እንዴት እንደምንተገብረው ደግሞ ያሳየናል፡፡ አስተምሮን ብቻ ዘወር አይልም፡፡ ያስተማረንን እንዴት እንደምንለማመደው ያሳየናል፡፡ እግዚአብሄ ማስተማር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር ይመራናል፡፡ ስንለማመድ አብሮን ይሆናል፡፡ ማስተማር ብቻ ሳይሆን መንገዱን ያሳየናል፡፡ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በተግባር ይመራናል፡፡ መንፈሱ የተማርነውን ያሳሳበናል፡፡ ያ በሃሳብ ደረጃ የተማራችሁት በተግባር ይህ ነው ይለናል፡፡

አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። ዮሃንስ 14፡26

  • ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ

እግዚአብሄ ማስተማርና መምራት ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻው መሄዳችንን ይከታተለናል፡፡ እግዚአብሄር አይኑን ከእኛ ላይ አይነቅልም፡፡ እግዚአብሄር በመንገዳችን ይከታተለናል፡፡ እግዚአብሄር ከመንገዱ አለመውጣታችንንና በመንገዱ ውስጥ መሆናችንን ይከታተለናል፡፡

ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ። መዝሙር 23፡6

እግዚአብሄር በቸርነቱና በምህረቱ በህይወታችን ዘመን ሁሉ ይከታተለናል፡፡ እግዚአብሄር ስለእኛ አይተኛም አያንቀላፋም፡፡

እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። መዝሙር 121፡3-4

አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ። መዝሙር 32፡8

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #አስተምርሃለሁ #መንገድ #እመራሃለሁ #ዓይኖቼን #አጠናለሁ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የልብ ዓይን መብራት ሶስቱ ጣምራ ፋይዳዎች

eyes.jpgስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡16-19

በምድር ላይ የአይናችን ወሳኝ ጤንነት ወሳኝ ነው፡፡ አይናችን በትክክል ሲያይ ከብዙ ችግሮች እናመልጣለን፡፡ አይናቸው አጥርቶ ማየት የማይችሉ ሰዎች ከብዙ ነገር ይጎድላሉ፡፡ አይኑ የበራለለት ሰው ራሱን ችሎ ውሳኔዎችን መወሰን ይችላል፡፡ አይኑ የበራለት ሰው ስለሚያይ ትክክለኛ ውሳኔን እንዲወስን ያስችለዋል፡፡

በተፈጥሮአዊ አይናችን ወሳኝ አንደሆነ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የልባችን አይን ጤንነትነ አጥርቶ ማየት ለክርስትና ፍሬያማነት ወሳኝ ነው፡፡ አይኑ የተከፈተለት ሰው እድልን ማየት ይችላል፡፡ አይኑ የተከፈተለት ሰው በረከቱን አይቶ መጠቀም ይችላል፡፡ እይታችን የህይወታችንን ጥራትና ልቀት ይወስነዋል፡፡

እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 2ኛ የጴጥሮስ 1፡9

ሃዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስትያኖች ይፀልይ የነበረውና እግዚአብሄርን ማሳሰብ አልተውም አላቆምም የሚለው የልቦናቸው አይኖች እንዲበሩ ነበር፡፡

የልቦናችን አይኖች ሲበሩ የምናውቃቸው ወይም በትክክል የምናስተውላቸው ሶስቱ የእግዚአብሄር ታላላቅ ስጦታዎች

የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን

እግዚአብሄር ወደምን ተስፋ እንደጠራን ማወቅ ህይወታችንን ያሳርፋል፡፡ ተስፋ ያለን ሰዎች ነን፡፡ እንደ እኛ ታላቅ ተስፋ ያለው ሰው የለም፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፡፡ ከሞት ወደ ህይወት ተሸጋገረናል፡፡ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንኖራለን፡፡

በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን

በክርስቶስ ወራሾች ተደርገናል፡፡ የእግዚአብሄር ወራሾች ነን፡፡ የወረስነው እግዚአብሄርን ነው፡፡ የወረስነው ብርና ወርቅ አይደለም፡፡ ያለን ርስት እጅግ የከበረ ነው፡፡

ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ሮሜ 8፡17

የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ወራች ነን፡፡

ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። ኤፌሶን 3፡5-6

በብርሃን ርስትን እንድንካፈል ያበቃንን እግዚአብሄርን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። ቆላስይስ 1፡12

ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን

በምድር ላይ ሞት ሃያል ነበር፡፡ የእግዚአብሄር የሃይል ታላቅነት የተገለጠው ኢየሱስን ከሙታን በማስነሳት ነው፡፡ የመጨረሻው ሃይል ሞት በክርስቶስ ትንሳኤ ድል ተነስቶዋል፡፡ ይህ ታላቅ ሃይል በህይወታችን አለ፡፡ ይህን ታላቅ ሃይል ማየት ከቻልን አለምን እናሸንፋለን፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #አይን #ቃል #የጠራ #ኩል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ምን ታያለህ?

see.jpg

ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል። ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ። እግዚአብሔርም፦ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ። ኤርሚያስ 1፡11-12

እግዚአብሄር የፈጠረን ለአላማው ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን በክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ከእርሱ ጋር አብሮ እንዲሰራ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ለአብሮ ሰራተኝነት ነው፡፡

የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡9

አብሮን ሊሰራ ከሚፈልገው ከእግዚአብሄር ጋር ተስማምተን አብረን መስራት የምንችለው እርሱ የሚያየውን ስናይ ብቻ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሚሰራውን ማየት ካልቻለ በስተቀር ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ ሊሰራ አይችልም፡፡

አብሮት የሚሰራውን ሰው እርሱ የሚያየውን አብሮ እንዲያይ እግዚአብሄር የሚፈልገው ለዚህ ነው፡፡

እግዚአብሄር የሚሰራውን ማየት ካልቻልን በራሳችን ብቻችንን ሰርተን ውጤት ላይ መድረስ እንችልም፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራውን ማየት ካልቻልን ከእግዚአብሄር ጋር አብረን ልንሰራ አንችልም፡፡ አግዚአብሄር ሲሰራ ካላየን ከእርሱ ጋር ተባብረን ፍሬያማ መሆን አንችልም፡፡

ኢየሱስ በምድር በነበረ ጊዜ አብ የሚሰራውን ያይ አብሮም ይሰራ ነበር፡፡ አብ የሚሰራወነ ያይና ከእርሱ ሃር ይተበናበር ስለነበረ ኢየሱስ በምድር ላይ በአገልግሎቱ ስኬታማ ነበር፡፡

ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17

ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። ዮሃንስ 5፡19-20

አሁንም እግዚአብሄር በየጊዜው የሚጠይቀው ይህንኑ ጥያቄ ነው፡፡

አብሮን ሊሰራ ሲፈልግ ምን ታያለህ ይለናል፡፡ ውጤታማ እንድንሆን ስለሚፈለግ ምን እንዳየን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ምክኒያቱም ባየነው መጠን ብቻ ነው አብረነው የምንሰራውና ውጤታማ የምንሆነው፡፡

የእግዚአብሄርን መንግስት እና የእግዚአብሄርን አሰራር የምናየው በቃሉ ነው፡፡

ቃሉን በሚገባ ካየን እግዚአብሄርን እናየዋለን፡፡ ቃሉን ካየን የእግዚአብሄርን መንግስት አሰራር እንረዳለን፡፡ ቃሉን ካየን እግዚአብሄር ሲሰራ እናየዋለን አብረንም በመስራት ውጤታማ መሆን እንችላለን፡፡

እግዚአብሄር በህይወታችን የሚሰራውን ካየን እግዚአብሄር በህይወታችን ሊፈፅም ያሰበውን አላማ በሚገባ መፈፀም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን የሚሰራውን ካየን ከእርሱ ጋር ተባበረን ስኬታማ መሆን እንችላለን፡፡

ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል። ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ። እግዚአብሔርም፦ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ። ኤርሚያስ 1፡11-12

ፀሎት

እግዚአብሄር ሆይ ስለአባትነትህ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አይኖቼን ክፈት፡፡ እግዚአብሄር ሆይ አንተ በክርስቶስ ያደረክልኝን ሁሉ መረዳት እንድችል  የጥበብና የመገለጥን መንፈስ ስጠኝ፡፡ አንተ በህይወቴ የምታየውን ማየት አችል ዘንድ አይኖቼን ክፈት፡፡ አንተ የምትሰራወነ አይቼ እተባበርክህ ዘንድ አይኔን ክፈት፡፡ ከአንት ጋር በትክክል መራመድ እንድችል አንተ ስለህይወቴ የምታየውን ሁሉ ልይ፡፡ አይኔን ስለምትከፍት ስራህን በህይወቴ ሰለማይ አመሰግንሃለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #አይን #እይታ #ተኣምራት #እድል #ዘመን #እድል #ዋጁ #ጥበብ #መተርጎም #ይሳኮር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ

after you .jpgከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና

ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25

የሰው ጥበብ ሲጨርስ የእግዚአብሄር ጥበብ ይጀምራል፡፡ የእግዚአብሄር ሞኝነት የሰውን እጅግ ታላቅ ጥበብ ይበልጠዋል፡፡ የእግዚአብሄር ድካም ከሰውን እጅግ ታላቅ ሃይል ይበረታል፡፡

ከሰው እጅግ ታላቅ ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሄር ሞኝነት ይሻላል፡፡ በሰው እጅግ ታላቅ ጥበብ ከመደገፍ ይልቅ በእግዚአብሄር ሞኝነት መደገፍ ይሻላል፡፡

የእግዚአብሄር ማስተዋል ጥልቅ ነው፡፡

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ 40፡28

ስለዚህ ነው ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም የሚለው፡፡

ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1

በራስ ማስተዋል እንደመደገፍ አደገኛ ነገር የለም፡፡ የእኛ ማስተዋል ልንደገፍበት የሚበቃ አይደለም፡፡ ሰው በሸንበቆ ላየ ዘና ብሎ እንደማይደገፍ ሁሉ የእኛ ማስተዋል ለመደገፍ የማይበቃ ደካማ ነው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ የሚለው፡፡ የትኛውም የእኛ ማስተዋል ልንደገፍበት በቂ አይደለም፡፡ የእኛ እጅግ ታላቁ ማስተዋል የእግዚአብሄርን ጥበብ አይደለም ሞኝነቱን አይደርስበትም፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። ምሳሌ 3፡5-6

ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ በመንገድህ ሁሉ አርሱን እወቅ የሚለው፡፡ በመንገድህ ሁሉ ለእርሱ አዋቂነት እውቅና ስጥ፡፡ በመንገድህ ሁሉ እኔ ለራሴ ከማውቀው በላይ እርሱ ለእኔ ያውቃል በል፡፡ በመንገድህ ሁሉ እኔ የማላውቀው ነገር አለ እርሱ ሁሉን ያውቃል በል፡፡ በመንገድህ ሁሉ እኔ ልሳሳት እችላሁ አርሱ ግን አይሳሳትም በል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ማስተዋል #ቃል #መልካም #መታመን #መደገፍ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት  #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ለአንድ ጥሪ አልተጠራንም

calling.jpgሁላችንም ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር በእያንዳንዳችን ህይወት ሊሰራ ያለው ልዩ አላማ አለ፡፡ ለዚያ አላማ ተጠርተናል፡፡ እግዚአብሄር ለምን አላማ እና አገልግሎት እንደጠራን ማወቅን የመሰለ በህይወት የሚያሳርፍና የሚያረጋጋ ነገር የለም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በጥሪያችን ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ የተከፈቱ እጅግ ብዙ በሮች ውስጥ አንገባም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከሙከራ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ህይወትን መኖር እንጀምራለን፡፡

ጥሪያችን የሆነውን ነገር ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ መጠን ጥሪያችን ያልሆነውን ነገር ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነውን እንለያለን፡፡ ማን እንደሆንን ስንረዳ መን እንዳልሆንን ይገባናል፡፡ እሺ የምንለውን ስናውቅ እምቢ የምንለውን እናውቃለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ውስን የሆነውን ጊዜያችንን ጉልበታችንን እውቀታችንን ገንዘባችንን ባልተጠራንበት ነገር ላይ ከማፍሰስ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ምንም ብንጥር ፍሬ ከማናፈራበት ቦታ እንርቃለን፡፡

እውነተኛ ፍሬ የሚፈራው በእድል አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው በቅልጥፍና አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው ጥሪን አውቆ በመከተል ነው፡፡

ጥሪያችንን ስናውቅ ማድረግ የማንችለውን እንድናውቅ ለዚያ ለተጠሩት እንድንተወው ያስችለናል፡፡ ጥሪያችን ስናውቅ ራሳችንን ትሁት አድርገን ለተጠሩት ሰዎች እንድንተው ይረዳናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከእኛ የተሻለ ለሚሰሩት በመተው በራሳችን ጥሪ ላይ እንድናተኩር ያስችለናል፡፡

ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው ከሆኑ ሰዎች ጋር እንዳንጣላ ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው የሆኑትን ሰዎች እንዳናስተጓጉል ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በራሳችን ጥሪ ላይ አተኩረን ጥሪያችንን በትጋት እንድንፈፅም ያደርገናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ለጥሪያችን ብቻ ተለክቶ የተሰጠንን የእግዚአብሄር ፀጋ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ያደርገናል፡፡

ጥሪያችንን በሚገባ ካልተረዳንና ያየነውና የሰማነው ጥሪ ሁሉ የሚያመረን ከሆነ መኪናን እንደመንዳት ሳይሆን እንደመግፋት ይሆንብናል፡፡ በህይወታቸን የሚለቀቀው የእግዚአብሄር ፀጋ የጥሪያችን አይነትና ልክ ስለሆነ የእግዚአብሄርን ስራ በጭንቀት ሳይሆን በደስታ እናደርገዋለን፡፡ በህይወታችን ያለው የእግዚአብሄር ፀጋ ስለማያንስና ስለማይበዛ ለጥሪያችን ብቻ የሚበቃ ስለሆነ የሚረዳንና የሚያከናውንልን በጥሪያችን ላይ ብቻ ስንቆም ነው፡፡ ባለተጠራንበት ቦታ ቆመን የእግዚአብሄር ፀጋ ይደግፈናል ማለት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡

ሰው እግዚአብሄር እንደሚያስችለው እና እንደሚያበረታው እንደሚያውቀው ሁሉ ለሁሉም ነገር ደግሞ እንዳልተጠራ ማወቁ ወሳኝ ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በጣም ልዩ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል የሚመስለው ሰው ተታሏል፡፡ በእግዚአብሄር ነገር እየበሰለን ስንሄድ የምንረዳው በጣም አስፈላጊ ነገር ማድረግ የምንችለው በጣም ውስን ነገር ብቻ እንደሆነ መረዳት ነው፡፡ በዚያ በተጠራንበት ውስን ነገር ላይ ከተወሰንን ፍሬያማ እንሆናለን፡፡

በጥሪያችን ስትቆም እርሱ መሰረታዊ ፍላጎታችን ነው ፣ ሞገሳችን ነው ፣ ውበታችን ነው ፣ ዝናችን ነው ፣ እውቅናችን ነው ፣ እርካታችን  ነው እንዲሁም ደስታችን ነው፡፡ የተሳካልህ ለመሆን የራስህ ጥሪ ማድርግ በቂ ነው፡፡ እንዲከናወንልህ የሌላን ሰው ጥሪ ማድረግ እና እንደምትችለው ማሳየት የለብህም፡፡

ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡17

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥሪ #ምስክር #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ

moved by compassion.jpgብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። ማቴዎስ 9፡36

ኢየሱስ በምድር ላይ ያገለገለው ብዙዎችን ነፃ ያወጣው በአዘኔታና በርህራሄ ተመርቶ ነው፡፡ ርህራሄ ወደ ትክክለኛው አገልግሎት ይመራል፡፡ ርህራሄ ወደ እግዚአብሄር ሃሳብ ይመራል፡፡ ርህራሄ ወደፈውስ ወደነኛ ማውጣት ወደአገልግሎት ይመራል፡፡

እግዚአብሄር የሚሰራው በፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚንቀሳቀሰው በርህራሄ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሲራራላችሁ ህይወታችሁን ይለውጣል፡፡ እግዚአብሄር ህይወታችሁን እንዲለወጥ ሲፈልግ ለሚያገለግላችሁ አገልጋይ ርህራሄውን ያካፍለዋል፡፡

እግዚአብሄር አገልጋዩን ለፈውስና ለነፃ ማውጣት ሊጠቀም ሲል ለአገልጋዩ ርህራሄ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር እንዲጠቀምብህ ካስፈለገ ርህራሄ ያስፈልግሃል፡፡ ለምታገለግለው ህዝብ ርህራሄ ከሌለህ በከንቱ ትለፋለህ፡፡ የምታገለግለውን ህዝብ የምታገለገልው ካለፍቅርና ካለርህራሔ እንደስራ ከሆነ አገልግሎቱ ቢቀርብህ ይሻላል፡፡

በፍቅር የማይደረግ አገልግሎትም እንኳን ቢሆን አይጠቅምም፡፡ ካለ ምህረትና ርህራሄ የሚደረግ አገልግሎት ሁሉ ከንቱ ነው፡፡

በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ  ቆሮንቶስ 13፡1-3

የምታገለግላቸውንና የምትጠቅማቸውን ሰዎች ለማገልገል ፍቅር ያስፈልግሃል፡፡ ፍቅር ከሌለህ እግዚአብሄር አይጠቀምብህም፡፡ ፍቅርና ርህራሄ ካልመራህ እግዚአብሄር አልመራህም፡፡ ፍቅር ሃይልህ ካልሆነ እግዚአብሄር ሃይል አይሆንም፡፡ በፍቅርና በርህራሄ ካልሆነ እግዚአብሄር ካንተ ጋር አይሆንም፡፡

አለምን የምናሸንፍበት እምነት የሚሰራው በፍቅር ነው፡፡ እምነት እንዲሰራና በእምነት ሰዎችን ለመጥቀምና ለማገለግል ፍቅር ይጠይቃል፡፡ እምነት ከፍቅር ተለይቶ አይሰራም፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። ገላትያ 5፡6

ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። ማቴዎስ 14፡14

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ምህረት #ርህራሄ #ፍቅር #መውደድ  #አዘነላቸው #ነፃማውጣት #አገልግሎት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል

jesus.jpgሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ . . . የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9፡6

የአለቅነት ብቸኛው ጥቅም ሰዎች ሲገለገሉና ሲጠቀሙ ማየት ነው፡፡ አለቅነት በራሱ ጥቅም አይደለም፡፡ የአለቅነት ጥቅም ሰዎች ካሉበት እግዚአብሄር ወደ አየላቸው ደረጃ ሲደርሱ ማየት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎች ከታሰሩበት ነገር ተፈትተው በነፃነት እግዚአብሄርን ሲያገለግሉ ማየት ነው፡፡

አለቅነትን ለራሳቸው ጥቅም የሚጠቀሙበት ሰዎች በአለም ላይ ስላሉ አለቅነት ከጥቅም ጋር ተያይዞዋል፡፡ በአገራችንም ያለውም አባባል ሲሺም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው አባባል የመጣው አለቅነትን ከተጠቃሙነት ጋር አያይዞ ነው፡፡ ነግር ግን አባባሉ መሆን የነበረበት “ሲሾም በትጋትና በታማኝነት ህዝብን ያላገለገለ ሲሻር ይቆጨዋል” መሆን ነበረበት፡፡ አለቅነት ሰውን ከመጥቀም ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡ አለቅነት ግን እግዚአብሄርን አገልግሎ ከእግዚአብሄር ሽልማትን ከመቀበል ውጭ ጥቅማ ጥቅም የለውም፡፡

የአለቅነትን ሃላፊነት የተረዱ ሰዎች አለቅነትን እንደ ጥቅም አይጓጉለትም፡፡ የአለቅነት ሃላፊነትን የተረዱ ሰዎች ሸክሙ እንጂ ጥቅሙ ትዝ አይላቸውም፡፡ የአለቅነትን ሸክም የተረዱ ሰዎች አላቅነትን እንደጥቅም አይፈልጉትም፡፡

እርግጥ ነው በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን እንደመጠቀሚያ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች ከሰው ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለመጠቀም የአለቅነትን ስልጣን በጭካኔ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ብዙ አለቅነት ያለው ብዙ ይጠቀማል ትንሽ አለቅነት ያለው ትንሽ ይጠቀማል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን ሰውን ለመበዝበዝ ይጠቀሙበታል፡፡

ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። ማቴዎስ 20፡25-26

አለቅነትን ለራስ ጥቅም መጠቀሚያ ማድረግ የእግዚአብሄር ሃሳብ አይደለም፡፡ አለቅነት የመጠቀሚያ መንገድ አይደለም፡፡

በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3

አለቅነት ሃላፊነት ነው፡፡ አለቅነት ሸክም ነው፡፡ አለቅነት የትጋት ስራ ነው፡፡ አለቅነት ታማኝነት ነው፡፡ አለቅነት መሰጠት ነው፡፡ አለቅነት ፊት ቀዳሚነት ነው፡፡ አለቅነት ማንም ባያደርገው እኔ አደርገዋለሁ ማለት ሃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ አለቅነት ምሪትን በየጊዜው በመስጠት የመጥቀም የማገልገል መንገድ ነው፡፡

በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ማቴዎስ 20፡26-28

አለቅነት ሰላምን መስጠት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎችን ወደ ሰላም ምንም ወዳልጎደለበትና ምንም ወዳልተበላሸበት ቦታ መርቶ ማድረስ ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ሰላም #ድንቅመካር #ሃያልአምላክ #የሰላምአለቃ #የዘላለምአባት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ማገልገል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አለቅነት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: