Category Archives: cross

መስቀልን መሸከም

representation-of-christ-carrying-the-cross-road-to-calvary-hill_bol4x4-z__F0000.pngኢየሱስ በማያወላዳ ሁኔታ ሊከተሉት የሚወዱ ሁሉ መስቀላቸውን ተሸክመው እንዲከተሉት አስተምሮዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለው ሰው ለእርሱ ሊሆን እንደመይገባው በግልፅ ተናግሮዋል፡፡

የደቀመዝሙርነት መመዘኛው የራሰን መስቀል ተሸክሞ ጌታን መከተል ነው፡፡

ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ሉቃስ 14፡27

ኢየሱስን ለመከረተል ራስን መካድ ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስን ጌታ ለማድርግ ከራስ ጌትነት መውረድ ያስፈልጋል፡፡ ጌታንም ነፍሳችንም ማስደሰት አንችልም፡፡ ራሱን የካደ ሰው ብቻ ነው መስቀሉን ተሸክሞ ሊከተል የሚችለው፡፡

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ማቴዎስ 16፡24

መስቀል ግን ምንድነው ብለን መረዳት እየሱስ ያዘዘን ትእዛዝ በሚገባ ፈፅመን ጌታን እንዳከብረው ይረዳናል፡፡ እንድንሸከመው የታዘዝነው መስቀል በእንጨት የተሰራ ግኡዝ ነገር እንዳይደለ እናውቃለን፡፡

መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ማቴዎስ 10፡38

መስቀል እንደእግዚአብሄር ቃል የመኖር ሃላፊነት ነው፡፡ መስቀልን መሸከም ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ ላለመኖር የመወሰን ሃላፊነት ነው፡፡ መስቀል እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ሃላፊነትን እንጂ የፈለግነውን ነገር ያለማድረግ ሃላፊነት ነው፡፡ መስቀልን መሸከም ራስን የመካድ ሃላፊነት ነው፡፡ መስቀልን መሸከም የሚመቸንን ነገር ሳይሆን ጌታ ያዘዘንን ነገር ለማድረግ መጨከን ነው፡፡ መስቀልን መሸከም የተሻለን ነገር ሳይሆን የእግዚአብሄርን ነገር ለማድረግ መቁረጥ ነው፡፡ መስቀልን መሸከም የእግዚአብሄርን ነገር ለማድረግ የሚመጣብንን ማንኛውንም መከራ መቀበል ነው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር መስቀል የህይወት ሃላፊነት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #መስቀል #ስቅለት #ሃላፊነት #ውሳኔ #መጨከን #መከራ #ፈተና #መካድ #ደቀመዝሙር #ጌታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተፈፀመ #ቤተመቅደስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም

the cross.jpgበዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

በሰው ህይወት የባለቤትነት ጥያቄ ሲመለስ ብዙ ጥያቄዎች ይመለሳሉ፡፡ የባለቤትነት ጥያቄ ሲመለስ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች  ይመለሳሉ፡፡

አንድ ነገር የማን ነው የሚለው ጥያቄ ሲመለስ ማን መብት አለው የሚለውም ጠያቄ አብሮ ይመለሳል፡፡ አንድ ነገር ባለቤቱ ማን አንደሆነ ጥርት ያለ ነገር ከሌለ በነገሩ ላይ ማን ምን መብት አለው የሚለው ጥያቄ ሊመለስ አይችልም፡፡

እግዚአብሄር እኛን የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኛን የፈጠረን ለራሱ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ለእኛ ለራሳችን አይደለም፡፡ ይህን እውነት ካልተረዳን ሌላ ምንም እውነት ልንረዳ አንችልም፡፡ በዚህ ካልተግባባን በሌላ በምንም ልንግባባ አንችልም፡፡ እኛ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ እኛ የእግዚአብሄር የፈጠረን ፍጡሮች ነን፡፡ የህይወታችን ባለቤት እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙር 95፡7

እግዚአብሄር ለክብሩ ፈጥሮናል፡፡ እኛ የእርሱ ነን፡፡ እኛ የራሳችን አይደለንም፡፡

በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳያስ 43፡6-7

እግዚአብሄር በእኛ ላይ ሙሉ ባለመብት ነው፡፡ እኛ በራሳችን ላይ መብት የለንም፡፡

እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ አታስተውልም ይለዋልን? ኢሳያስ 29፡16

ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ፦ እጅ የለውም ይላልን? ኢሳያስ 45፡9

ሰው እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ነገር በማድረግ በማመፁ ለሃጢያትና ለሰይጣን ተሽጦ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን በመስቀል ላይ መስዋእት እንዲሆንልን በማድረግ እኛን በደሙ መልሶ ገዛን፡፡

በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ኤፌሶን 1፡7

አሁን ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ያመንን ሁላችን  በክርስቶስ ኢየሱስ ደም በከበረ ዋጋ ተገዝተናል፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

ከአሁን በኋላ ለራሳችን በመሞት ህይወት ለሰጠን ለእርሱ እንኖራለን፡፡

ስለዚህ የራሳችን አይደለንም፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለራሳችን እንድንሞት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለሞተልን ለእርሱ እንድንኖር ነው እንጂ ወደፊት ለራሳችን እንዳንኖር ነው፡፡

ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡14-15

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ባለቤት #ዋጋ #መዋጀት #ብር #ወርቅ #ደም #ክብር #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን

come out of the cross.jpgአንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ሉቃስ 23፡37

የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። ማርቆስ 15፡29-30

ኢየሱስ ለሃጢያታችን ሊሞት ወደ ምድር ሲመጣ የእኛን ስጋ ለብሶ ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ በሁሉ ነገር እንደኛ ተፈትኖዋል፡፡

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ከመስቀል እንዲወርድና ሃይሉን እንዲያሳይ ተፈትኖዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሃይሉን ከማሳየት ይልቅ ባሀሪን ማሳየት መረጠ፡፡ ኢየሱስ ሃይሉን ከማሳየት ይልቅ ሃይሉን ላለማሳየት መረጠ፡፡ ኢየሱስ ሃይሉን ለማሳየት ከመስቀል ከመውረድ ይልቅ በመስቀል በመቆየት በትግስት ደህንነታችንን መፈፀም መረጠ፡፡ ኢየሱስ ሃይሉን ከማሳየት ይልቅ እንደደካማ ተቆጠረ፡፡

ኢየሰስ ሃይሉን በማሳየትከሚገኝ እርካታ ይልቅ ሃይሉን ላለማሳየት ትህትናን መረጠ፡፡ ኢየሱስ ሃይሉን በማሳየት ዝነኛ ከመሆን ይልቅ በመስቀል የመሞትን ነውርን መረጠ፡፡ ኢየሱስ ነውርን አክብሮ በመስቀል ላይ ላለመሰቀል ሃይሉን ከማሳየት ይልቅ በመስቀል የመሞትን ነውርን ንቆ በመስቀል ላይ ለመሞት ታገሰ፡፡ ኢየሱስ ራሱን ለማዳን ሳይሆን ሰውን ለማዳን ነው ወደ ምድር የመጣው፡፡ ኢየሱስ ለራሱ ክብር ሳይሆን ሰውን ሊያከብር ነው በመስቀል ላይ የተዋረደው፡፡

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2

አሁንም እኛን ለአለም ሞተናል ተሰቅለናል ብለን ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን ከመስቀል ውረድ እና ሃይልህን አሳየን የሚሉ ብዙ ነገሮች በህይወታችን ያጋጠሙናል፡፡ ስጋችን ፍቀድልኝ አንዴ ሃይሌን ላሳያቸው ይለናል፡፡

እኛ ግን ሃይላችንን ከማሳየት ይልቅ የእግዚአብሄርን አላማ በህይወታችን ለመፈፀም መዋረድን እንመርጣለን፡፡ እኛ ሃይላችንን ከማሳየት ይልቅ ለእግዚአብሄር ሃሳብ መሸነፍን እንመርጣለን፡፡ ሃይላችንን አሳይተን በሰው ፊት ጎሽ ከመባል ይልቅ ሃይላችንን ላለማሳየት በመታገስ በእግዚአብሄር ፊት ብቻ ጎሽ መባልን እንመርጣለን፡፡

ሁልጊዜ ከመስቀል ወረድ የሚለውን የፉክክር ጥሪ እንቢ ባልን መጠን እንደ ስንዴ ቅንጣት ተዘርተን ሞተን ብዙ ፍሬ ማፍራት እንችላለን፡፡

እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ዮሃንሰ 12፡24

ከመስቀል ውረድ የሚለውን ሰምተን በታዘዘን መጠን ስጋችን ሞቶ ለብዙዎች በረከት ለመሆን ያለንን እድል እና ክብር እናባክነዋለን፡፡

የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። ማርቆስ 15፡29-30

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ስጋ #ምኞት #ማሰብ #ህይወት #ሞት #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ

one way1.jpgኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡15

የሰው መንገድ በምርጫ የተሞላ ነው፡፡ ዛሬ የምንኖረው ኑሮ ትላንት የመረጥነውን ምርጫ ውጤት ነው፡፡ ወደፊት የምንኖረው ኑሮ ዛሬ የመረጥነውን ምርጫ ውጤትን ነው፡፡

ሰው በህይወቱ ዘመን ሁሉ በምድር ላይ ብዙ ምርጫ መምረጥ ቢጠበቅበትም እንደዚህ ያለ የወደፊት ህይወቱን ሁሉ የሚወስን ምርጫ ግን የለም፡፡

አንዳንድ ምርጫ በገንዘባችን ላይ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሌላው ምርጫ በዝናችን ላይ ታላቅ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ሌላው ደግሞ በጥበባችን ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊን ተጽፅእኖን ያመጣል፡፡ ሌላውም በሃይላችን ላይ ተፅእኖ በማሳደር በምድር ላይ ሃያል እንድንሆን ወይም እንዳንሆን ያደርገናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ምርጫዎች ተፅእኖ የሚያደርጉት የምድር ህይወታችንን ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን በምድርም ከምድር ህይወት በስቲያም ህይወታችን ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር ወሳኝ ምርጫ አለ፡፡ ሰው በምድር ላይ ሲኖር በሌላ ምርጫዎች እንኳን ቢሳሳት በዚህ ምርጫ ግን መሳሳት የለበትም፡፡ ሰው በምድር ላይ ሲኖር በሌላ ምርጫዎች የሚሳተው መሳሳት በዚህ መርጫ እንደሚሳሳተው መሳሳት አይከፋም፡፡ ሰው በሌላ ምርጫ ቢሳሳት ውጤቱ የምድር እጦት ብቻ ነው፡፡ ሰው በምድር ምርጫዎች ቢሳሳት የምርጫው ውጤት በምድር ላይ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡

ሰው ግን በዚህ መርጫ ቢሳሳት ውጤቱ የምድርን ቢያጠቃልልም የምርጫው ውጤት በምድር ላይ ብቻ አያበቃም፡፡ ሰው በዚህ ምርጫ ቢሳሳት ውጤቱ በምድርና ከምድር ህይወት በኋላም ይቀጥላል፡፡ ሰው በዚህ መርጫ ቢሳሳት ውጤቱ የማይቀለበስ የዘላለም ነው፡፡ ሰው በዚህ መርጫ ቢሳት ውጤቱ ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለያየትን ያመጣል፡፡

ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡15

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #የታመነ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #ኢየሱስ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም

Untitled-1.jpgእናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ ኤፌሶን 4፡20

ይህ ትክክለኛ የህይወት ዘይቤ ነው ብለው የሚያስተምሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ህይወት እንዲህ ነው ብሎ ጋዜጣ ያስተምራል ፣ ፊልም ያስተምራል የተለያዩ መፅሃፍት ያስተምራሉ ሬዲዮ ያስተምራል ቴሌቪዥን ያስተምራል፡፡

እነዚህ ያስተማሩት ነገር ሁሉም ስህተት ነው ባይባልም ነገር ግን እያንዳንዱ ትምህርት እውነት በሆነው በእግዚአብሄር ቃል አስተምሮት መፈተሽ አለበት፡፡

ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የተለያየ ትምህርት ሰምተውና ተከትለው የተለያየ የህይወት ዘይቤ የሚያሳዩትን ሰዎች እናንተ ግን ይላቸዋል፡፡

ሌላው ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሌላው ሊከተለው ይችላል፡፡ ሌላው ሌላ ነገር ተምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡

ክርስትና ለአንዳንዶች ከሰዎች ሃይማኖቶች አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስትና ከሰው ሃይማኖቶች አንዱ ሳይሆን ከእግዚአብሄር ጋር ያለ የአባትና የልጅ ግንኙነት እና ፍጥረት መሆን ነው፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17

አንዳንዶች ክርስትያን ነን ብለው ነገር ግን ምንም የህይወት ለውጥ በህይወታቸው አይታይም፡፡ በህይወታቸው ንስሃ አልገቡም ከአሮጌው ኑሯቸው መንገዳቸውን አልለወጡም፡፡ አስተሳሰባቸውና ህይወታቸው በምድር ላይ የፈለገውን ነገር ከሚያደርግ አለማዊ ሰው በምንም አይለይም፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2

አንዳንዶች ክርስትናን እግዚአብሄርንና ሰውን ማገልገያ መንገድ ሳይሆን ጥቅም ማግኛ አቋራጭ መንገድ አድርገውታል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም

እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ። ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡4-6

አንዳንድ ሰዎች ክርስትናን ራስን መካድ ሳይሆን የልጅነት ህልማቸውን የሚያስፈፅሙበት መድረክ አድርገውታል፡፡

እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። ሉቃስ 22፡26

አንዳንዶች ክርስትናን የህይወት ለውጥ ሳይሆን ወግና ስርአት የተሞላ ህይወት የሌለው ባዶ ሃይማኖት አድርገውታል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡

እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። ኤፌሶን 4፡17

አንዳንዶች ክርስትና ከሲኦል መጠበቂያ መድህን ድርጅት እንጂ ከሃጢያት በላይ በአሸናፊነት የምንኖረብት የድል ነሺነት ህይወት አይደለም፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ሃይማኖት #መልክ #አምሳል #ልጅ #አባት #ክብር #ማእረግ #መብት #ስልጣን #ስፍራ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ለራሳቸው እንዳይኖሩ

nails.jpgከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ ሮሜ 14:7

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15

ኢየሱስ የሞተልን ንስሃ ገብተን የራሳችንን ህይወት ካቆምንበት እንድንቀጥል አይደለም፡፡ ኢየሱስ የሞተው እኛ ለራሳችን እንድንሞት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለእርሲ እንድንኖርለት ነው፡፡

በክርስትና ስኬታማ የምንሆነው ለራሳችን ስንኖር ሳይሆን ለራሳችን ስንሞት ነው፡፡ በክርስትና የምንከናወነው ለሞተልን ለእርሱ ስንኖር ነው፡፡

ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሉቃስ 9፡24

ነፍሱን ሊያስደስት የሚወድ ፣ ለነፍሱ ስሜት ቅድሚያ የሚሰጥና ነፍሱን በዋነኝነት የሚያከብር ሰው ለሞተለት ለክርስቶስ መኖር አይችልም፡፡

ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። ሐዋርያት 20፡24

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #ነፍሱን #የሚያጠፋ #ሞተ #እንዲኖሩ #እንዳይኖሩ #የሚኖር #የሚሞት #መከተል #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የስጋ መስቀል አይጠቅምም

cross111.jpgሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል። እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል። በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም። ሮሜ 2፡25-29

መፅሃፍ ቅዱስ ስለ ስጋ እና ስለልብ መገረዝ ይናገራል፡፡ በብሉይ ኪዳን ስጋቸውን ስለሚገረዙ ሰዎች ነገር ግን ልባቸው ስላልተገረዘ የእግዚአብሄርን ቃል ስለማይጠብቁ ሰዎች ይናገራል፡፡ ሰው ልቡ ካልተገረዘና በእግዚአብሄር መንገድ ካልሄደ የስጋው መገረዝ ለሰው ምንም አይጠቅመውም፡፡ ነገር ግን ስጋው ያልተገረዘ ልቡ የተገረዘ ሰው እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡ እግዚአብሄር የውጭውን ስርአት ሳይሆን የልብን ነገር ነው የሚመለከተው፡፡

አሁን ማንሳት የፈለግኩት ስለግርዘት ሳይሆን ሰለመስቀል ነው፡፡ የመስቀልን በአል በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ ብናከብር ነገር ግን የመስቀል ህይወት ከሌለን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም የመስቀልን በአል የማያከብር ነገር ግን መስቀልን በህይወቱ የሚለማመድ ሰው ይሻላል፡፡

የመስቀልን በአል በየአመቱ ብናከብር የመስቀል ቃል በህይወታችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡ የመስቀል ቅርፅ በአንገታችን ብናስር የመስቀል ህይወት ግን በልባችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡

 1. መስቀል ኢየሱስ የሞተበት ነው፡፡

መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያችን የውርደትርን ሞት እንደሞተ ይናገራል፡፡ መስቀል ስለኢየሱስ መስዋእትነት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ይናገራል፡፡

ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ማቴዎስ 26፡28

 1. የመስቀሉ አሰራር ዘላለማችን የሚወስን ነው፡፡

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ ለአንዳንዶች ሞኝነት ነው ለሌሎች የእግዚአብሄር የማዳኛ ሃይል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የመስቀሉን አሰራር በፍፁም አይቀበሉትም ሌሎቹ ደግሞ ሁለንተናቸው መስቀል ነው፡፡ ለኢየሱስ የመስቀል ስራ ያለን እምነት ዘላለማችንን ይወስነዋል፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ሊያድን በመሆኑ የመስቀሉን ትምህርት የተቀበሉ ሰዎች ከሃጢያት ባርነት ነፃ ይወጣሉ፡፡

የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18

ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21

 1. መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡

መስቀል ሃጢያታችንን በደሙ ሊያጥብ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ያለደም ስርየት የለም እንደሚል የሃጢያታችንን ይቅርታ የምናገኘው ሃይማኖታው ስርአት ስለፈፀምን ሳይሆን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰልንን ደም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበል ነው፡፡

ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ዕብራውያን 9፡14

 1. መስቀል ከእግዚአብሄር ጋር ሰላምን እንዳገኘን ይናገራል፡፡

ኢየሱስ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በመስቀሉ እንደሻረው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰውና የእግዚአብሄርን ጠላትነት ሻረ፡፡ ማንም ሰው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራለትን ስራ ቢቀበል እግዚአብሄር ወደቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡

እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። ኤፌሶን 2፡14-16

 1. መስቀል እኛም አብረነው እንደተሰቀል ይናገራል፡፡

መስቀል ስላለፈው ሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን በሃጢያት ላይ ሃይል ስላገኘንበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የእኛን የሃጢያተኛ ስጋ ወክሎ ነው የሞተው፡፡ በኢየሱስ ስጋ የእኛ የሃጢያት ስጋ ተገድሎዋል፡፡ ኢየሱስ ይቅር ያለው ያለፈውን ሃጢያታችንን ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን ከተቀበልን በኋላ ሃጢያት እንዳንሰራ የሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀሉ ላይ ገድሎታል፡፡

ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። ሮሜ 8፡3-4

ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6

 1. መስቀል ለሞተልን እንድንኖር ይናገራል፡፡

መስቀል ስለኢየሱስ ሞት ብቻ ሳይሆን ሰለእኛም ሞት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ ስለእኛ ስለመሞቱ ብቻ ሳይሆን እኛ ለአለም  ስለመሞታችንን ይናገራል፡፡

ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14

 1. መስቀል በየእለቱ ለስጋችን ፈቃድ ስለምንሞትበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡

መስቀል የስጋችንን ፈቃድ በየእለቱ እንቢ የምንልበት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ በእያንዳንዱ ቀን የሃጢያተኛ ስጋችንን ፈቃድ እንቢ ለማለት ሃይልን የምናገኝበት የእግዚአብሄር አሰራር ነው፡፡

ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ሮሜ 8፡36

 1. የክርስትና ስብከት ልቡ ያለው መስቀል ላይ ነው፡፡

ሞት የሌለው መስቀል ጌጥ እንጂ ምንም አይደለም፡፡ መስቀል የሌለው ስብከትም ሆነ ትምህርት ክርስትና አይደለም፡፡ የመስቀል ህይወት የሌለው በአል ድግስ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ኢየሱስ ለእናንተ ሞቶዋል ለሃጢያትና ለአለም ሞታችኋል ለክርስቶስ ኑሩ የማይል ስብከት መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡

እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡1-2

ባገኘነው አጋጣሚ መስቀልን ማክበር አለብን ነገር ግን በህየወት የማይከበር መስቀል ለምንም አይጠቅምም፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #መስቀል #ስቅለት #ሃጢያት #ሞት #ስቅለት #ጠቦት #መጋረጃ #ደም #ትንሳኤ #ስርየት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተፈፀመ #ቤተመቅደስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ኃጢአት አይገዛችሁምና

sin1.jpgሃጢያት አስከፊ መንፈሳዊ በሽታ ነው፡፡ ሰዎች ለብዙ በሽታዎች መድሃኒት ሰርተዋል ለሌሎቹም በሽታዎች መድሃኒት ለመስራት እጅግ ይጥራሉ፡፡ ከበሽታዎች ሁሉ የከፋው በሽታ ደግሞ ሃጢያት ነው፡፡ ከእስራቶች ሁሉ አስከፊው እስራት የሃጢያት እስራት ነው፡፡ የሃጢያት መድሃኒት ያለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሰዎችን ከእግዚአብሄር የለየውንና ከአላማቸው ያሰናከላቸውን የሃጢያትን መድሃኒይት ለሰው ላመምጣት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ለማዳን ነው፡፡

ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21

ከሃጢያት ካልዳንክ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ዋናውን አላማ ስተኸዋል ማለት ነው፡፡ ሃጢያት አሁንም የሚገዛህ ከሆነ ስለመዳን ያልተረዳኸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡

ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡11-14

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለሁለት ምክኒያቶች ነው፡፡

ኢየሱስ ወደምድር የመጣበት ምክኒያት ከዚህ በፊት የሰራነውን ሃጢያት እዳ ለመክፈልና በደሙ ሃጢያታችንን ለማጠብ የሃጢያት ይቅርታን እንድናገኝ ስለሃጢያታችን በመስቀል መስዋእት ሊሆን ነው፡፡

በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ኤፌሶን 1፡7

ኢየሱስ ሃጢያታችን ይቅር ብሎን ብቻ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ከሃጢያት የበላይ የምንሆንበትን አሰራር ባያዘጋጅ ኖሮ ከሃጢያት የዳንን ሳንሆን ሃጢያት የሚገዛን ባዶ ሃይማኖተኞች ብቻ እንሆን ነበር፡፡

ኢየሱስ ግን ስለበፊቱ ሃጢያታችን እዳ መክፈል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ ተመልሰን በሃጢያት እንዳንኖር ሃጢያት የሚያሰራንን ስጋዊ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመስቀል ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው ለሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ሃጢያት እንዳይገዛን ሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመግደል ነው፡፡

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለራሱ አይደለም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው እኛን ወክሎና ተክቶ ነው፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ የተሰቀለው የእኛን ሃጢያተኛ ስጋ ይዞና ተክቶ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተሰቅሎዋል፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ ሲሞት ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተገድሎዋል፡፡ አሁን ስጋዊ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡

ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6

ሃጢያተኛ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡ ያልተረዳ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ የተታለለ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ አሁን ሃጢያት አይገዛንም፡፡

ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14

ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ የሚለው፡፡

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20

ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የሚያስመካው የእርሱ ጉልበት ሳይሆን ሃጢያተኛ ስጋው በመስቀል ላይ እንዲሰቀልና ከሃጢያት እንዲድን ያደረገው የእግዚአብሄር አሰራር እንደሆነ የሚናገረው፡፡

ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ስጋ #ስጋዊባህሪ #መስቀል #ኃጢያት #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በኢየሱስ ሞት የተፈፀሙ ሶስት ነገሮችና ትርጉማቸው

cross jesus2.jpgኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተበት ጊዜ ሶስት ታላላቅ ትርጉም ያላችው ሁኔታዎች ተፈፅመዋል፡፡

 1. የቤተመቅ ደስ መጋረጃ ተቀደደ

ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ ማቴዎስ 27፡50-51

እግዚአብሄር ቅዱስ ነው፡፡ በሃጢያት ምክኒያት ሰው ወደ እግዚአብሄር መግባት አይችልም ነበር፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እዳ ሙሉ ለሙሉ ስለከፈለ እግዚአብሄርና ሰው መለያየት ቀረ፡፡ ሰው በኢየሱስ በኩል ወደ እግዚአብሄር መግባት ተሰጠው፡፡

እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ ዕብራውያን 10፡19-20

 1. ቅዱሳን ከሞት ተነሱ

መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። ማቴዎስ 27፡52-53

ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እዳ በመስቀል ላይ ስለሞተ በኢየሱስ ያመንም ሁላችን አሁን በትንሳኤ ህያው እንደሆንን ያሳያል፡፡

ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌሶን 2፡5

 1. የኢየሱስንም የእግዚአብሄር ልጅነት የማያምኑ መሰከሩ

ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ ሉቃስ 23፡44

የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው፦ ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ። ማቴዎስ 27፡54

የምድር መናወጥና በቀን ጨለማ ሆነ፡፡ ተፈጥሮ እንኳን ስለኢየሱስ ሞት መልስን ሰጠች፡፡ የኢየሱስ መሞት ዋናው አላማ ሰዎች በስሙ አምነው ከሃጢያታቸው እንዲድኑ ነው፡፡

እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። ሉቃስ 24፡46-48

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #መስቀል #ስቅለት #ጠቦት #መጋረጃ #ደም #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተፈፀመ #ቤተመቅደስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: