Category Archives: Jesus

የህይወት ሚስጥር

conscious.jpgህይወት ሚስጥር ነው፡፡ ህይወትን የሰራውና የሰጠን እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ማስተዋሉ አይመረመርም፡፡

ህይወት በአንድ ቃል እንዲህ ነው ተብሎ አይተረጎምም፡፡

ከየት መጣሁ ወደየት እሄዳለሁ ለምን በዚህ ምድር ላይ አለሁ የሚሉት ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ማግኘት የህይወት ጥራታችንን ይወስነዋል፡፡ በዚህ ምድር የመኖር አላማዬ ምንድነው የሚለውን ማወቅ ይህንን የህይወት ስጦታ በደስታ ተቀብለን ለታለመለት አላማ እንድናውለው ያደርገናል፡፡

የህይወትን ሚስጥር ማንም ፈላስፋ በትክክል ሊያስረዳን አይችልም፡፡ የህይወት ሚስጥር የምናገኘው የህይወትን ስጦታ ከሰጠን ከእግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

የህይወትን ሚስጥር የምንረዳው ህይወትን ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ስለ ህይወት ብዙ ብለዋል፡፡ ነገር ግን የህይወትን ሚስጥር በትክክል የምንረዳው ከመፅሃፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ ስለህይወት እንዲህ ይላል፡፡

ሰው ህይወትን ለመረዳት ከፈለገ ኢየሱስን መረዳት አለበት፡፡ ካለ ኢየሱስ ህይወትን ለመረዳት መሞከር ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ የህይወት ትርጉም ኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ ህይወት ነው፡፡

ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። የዮሐንስ ወንጌል 14፡6

ኢየሱስ የህይወት እንጀራ ነው፡፡ ሰው በህይወት አለመራብ ከፈለገ ኢየሱስን መገናኘት አለበት፡፡ ሰው በህይወት መርካት ከፈለገ ከኢየሱስ ጋረ መጣበቅ አለበት፡፡ ሰው ህይወትን መኖር ከፈለገ ኢየሱስን ማግኘት አለበት፡፡ ሰው ህይወትን መለማመድ ከፈለገ በኢየሱስ መኖርን መለማመድ አለበት፡፡  ሰው በህይወት መኖር ከፈለገ በኢየሱስ መኖር አለበት፡፡

ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። የዮሐንስ ወንጌል 6፡57

እውነተኛን ህይወት የምናጣጥመው በኢየሱስ ነው፡፡ እውነተኛን ህይወት ለማጣጣም ወደ ኢየሱስ መምጣት ግዴታ ነው፡፡

እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። የዮሐንስ ወንጌል 5፡39-40

እውነተኛ የህይወት ርካታ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስን በሚገባ በመከተል ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። የዮሐንስ ወንጌል 4፡13-14

ኢየሱስን ስንከተል የህይወትንም መንገድ እንከተላለን፡፡ ኢየሱስን ስናየው ህይወትን እናያለን፡፡

በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36

በኢየሱስ ስንኖር በህይወት እንኖራለን፡፡ ከኢየሱስ ውጭ ስንኖር ከህይወት ውጭ እንኖራለን፡፡

በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡4-5

በኢየሱስ ስንኖር ለህይወት ሃይል እናገኛለን፡፡ በኢየሱስ ካልኖርን ለህይወት ሃይል አናገኝም፡፡ በኢየሱስ ካልኖርን በሃይል አንኖርም፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡5

የህይወት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #መደሰት #ስኬት #ህይወት #ስጦታ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #ማስተዳደር #እረፍት

Advertisements

የክርስቶስም ሙላቱ ልክ እስክንደርስ

church leader.jpgሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡12-13

የክርስትና ጉዞ የእድገት ጉዞ ነው፡፡ የክርስትና ጉዞ መነሻ ያለው መድረሻም ያለው ጉዞ ነው፡፡

የክርስትና ጉዞ ሲጀመር የሚታወቅ ግቡም የሚታወቅ ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የማይታወቅ የግምት ረቂቅ ጉዞ አይደለም፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የሚገመት ባዶ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ክርስትና መነሻውም መድረሻውም የማይታወቅ የወግና የስርአት ብዛት አይደለም፡፡

ክርስትና የሚጀመረው በንስሃ ከአሮጌ ኑሮ ፍጹም ወደኋላ በመመለስ ነው፡፡ ክርስትና የሚጀመረው ዳግም ከመወለድ ነው፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው ደግሞ ያድጋል፡፡

የክርስትና እድገት ወግና ስርአት መፈፀም አይደለም፡፡ የክርስትና እድገት የውጫዊ ስርአትን መጠበቅ አይደለም፡፡

ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡18-19

የክርስትና እድገት ጣራው የክርስቶስ ሙላት ልክ ነው፡፡ የክርስትና መጨረሻው ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ የክርስትና መጨረሻው የክርስቶስ ሙላት ልክ ነው፡፡ የክርስትና ግቡ ክርስቶስን ሙሉ ለሙሉ መከተልና መምሰል ነው፡፡

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡12-13

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #ክርስቶስእስኪሳል #መምሰል #ክርስቶስንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም

the cross.jpgበዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

በሰው ህይወት የባለቤትነት ጥያቄ ሲመለስ ብዙ ጥያቄዎች ይመለሳሉ፡፡ የባለቤትነት ጥያቄ ሲመለስ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች  ይመለሳሉ፡፡

አንድ ነገር የማን ነው የሚለው ጥያቄ ሲመለስ ማን መብት አለው የሚለውም ጠያቄ አብሮ ይመለሳል፡፡ አንድ ነገር ባለቤቱ ማን አንደሆነ ጥርት ያለ ነገር ከሌለ በነገሩ ላይ ማን ምን መብት አለው የሚለው ጥያቄ ሊመለስ አይችልም፡፡

እግዚአብሄር እኛን የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኛን የፈጠረን ለራሱ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን ለእኛ ለራሳችን አይደለም፡፡ ይህን እውነት ካልተረዳን ሌላ ምንም እውነት ልንረዳ አንችልም፡፡ በዚህ ካልተግባባን በሌላ በምንም ልንግባባ አንችልም፡፡ እኛ ፈጣሪዎች አይደለንም፡፡ እኛ የእግዚአብሄር የፈጠረን ፍጡሮች ነን፡፡ የህይወታችን ባለቤት እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙር 95፡7

እግዚአብሄር ለክብሩ ፈጥሮናል፡፡ እኛ የእርሱ ነን፡፡ እኛ የራሳችን አይደለንም፡፡

በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ኢሳያስ 43፡6-7

እግዚአብሄር በእኛ ላይ ሙሉ ባለመብት ነው፡፡ እኛ በራሳችን ላይ መብት የለንም፡፡

እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፦ አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን፦ አታስተውልም ይለዋልን? ኢሳያስ 29፡16

ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ፦ እጅ የለውም ይላልን? ኢሳያስ 45፡9

ሰው እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን ነገር በማድረግ በማመፁ ለሃጢያትና ለሰይጣን ተሽጦ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ልጁን ኢየሱስን በመስቀል ላይ መስዋእት እንዲሆንልን በማድረግ እኛን በደሙ መልሶ ገዛን፡፡

በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ኤፌሶን 1፡7

አሁን ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ያመንን ሁላችን  በክርስቶስ ኢየሱስ ደም በከበረ ዋጋ ተገዝተናል፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19

በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

ከአሁን በኋላ ለራሳችን በመሞት ህይወት ለሰጠን ለእርሱ እንኖራለን፡፡

ስለዚህ የራሳችን አይደለንም፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለራሳችን እንድንሞት ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለሞተልን ለእርሱ እንድንኖር ነው እንጂ ወደፊት ለራሳችን እንዳንኖር ነው፡፡

ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡14-15

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ባለቤት #ዋጋ #መዋጀት #ብር #ወርቅ #ደም #ክብር #ራእይ #አላማ #ግብ #ውሳኔ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የኢየሱስና የእኛ ልጅነት እንድነት እና ልዩነት

sonship_toga_virilus (2).jpgሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ፅሁፌን ከሚከታተሉ ቅዱሳን መካከል በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ስላለ ልዩነት ብታስረዳ የሚል ጥያቄ ተቀብያለሁ፡፡ እኔም ይህ ለትምህርት ለሁላችን ይጠቅማለ ብዬ ስላሰብኩ ዛሬ ስለዚህ ሃሳብ በአጭሩ አንዳንድ ነገሮችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ ትምህርቱ በጣም ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ ናቸው የምናለውን ብቻ ስለዚህ በጣምአስረዳለሁ፡፡

የኢየሱስንና የእኛን የልጅነት አንድነትና ልዩነት ለመረዳት መጀመሪያ አንድነታችንን ብንመለከት ጥሩ መንደርደሪያ ይሰጠናል፡፡

የኢየሱስና የእኛ አንድነት

 1. ኢየሱስ በስጋ ነው የተወለደው እኛም በስጋ ነው የተወለድነው፡፡

ኢየሱስ የእኛን ስጋ ነው የለበሰው፡፡ የኢየሱስ ስጋ ከእኛ ስጋ በምንም አይለይም፡፡

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ . . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራዊያን 2፡14-15

 1. ኢየሱስ እኛ በምንፈተንበት ፈተና ሁሉ ተፈትኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ስጋ ሃጢያትን የሚያሙዋልጭ ስጋ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አልስማማም፡፡ ኢየሱስ በስጋው ሃጢያት መስራት ባይችል ኖሮ አይፈተንም ነበር፡፡ ፈተና ያለው መውደቅ ስላለ ነው፡፡ አግዚአብሄር ይመስን ኢየሱስ ግን በሃጢያት ተፈተነ እንጂ በሃጢያት አልወደቀም፡፡

ኢየሱስ በሃጢያት የማይወድቅ ስጋ ቢኖረው ኖሮ ለእኛ የቅድስና ምሳሌ ሊሆንልን አይችልም ነበር፡፡

ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። ዕብራዊያን 4፡15

 1. ኢየሱስ በተፈጥሮአዊ መንገድ በጥበብ እና በሞገስ ያደግ ነበር እኛም እናድጋለን

እኛ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ብለን ተምረን በእግዚአብሄር ነገር እንደምናድግ ሁሉ ኢየሱስን ወደምድር ሲመጣ ራሱን ባዶ በማድረጉ የተነሳ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ሁለት ብሎ መማርና ማደግ ነበረበት፡፡

ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ሉቃስ 2፡52

 1. ኢየሱስ የሚያበረታው መንፈስ ቅዱስን መቀበል ነበረበት

በስጋው ወራት ካለመንፈስ ቅዱስ አሸናፊ የእግዚአብሄ ልጅ ሆኖ ማለፍ ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን መሞላት አስፈልጎታል፡፡

ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ሉቃስ 4፡1

 1. በእግዚአብሄር ከኢየሱስ ጋር እኩል ተወደናል

እግዚአብሄር ኢየሱስን ከሚወደው ያነሰ እኛን አይወደንም፡፡

እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23

 1. ከኢየሱስ ጋር ወንድማማቾች ነን

ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው እኛም የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ኢየሱስ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም፡፡

የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13

 1. ኢየሱስን እንድንመስል ነው የተወሰንነው

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ሮሜ 8፡29

ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ምሳሌ ሊያሳየን ናሙና ሊሆንልን ነው፡፡ አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር ሊያሳየን ነው፡፡

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14

 1. ኢየሱስ በምድር ላይ እንደተላከ እኛም ተልከናል፡፡

ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

 

በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነገሮች መመልከት ይጠቅመናል፡፡

የኢየሱስና የእኛ ልዩነት

 1. ኢየሱስ ሃጢያት ሰርቶ አያውቅም እኛ ግን በንስሃ ከሃጢያታችን ተመልሰን ነው፡፡

እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21

 1. ኢየሱስ የሞተ መንፈስ ኖሮት አያውቅም እኛ ግን በአዳም በሃጢያት ከእግዚአብሄር የተለየው መንፈሳችን ዳግመኛ ተወልዶ ነው፡፡

ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3

 1. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የእግዚአብሄር ብቸኛ ልጁ ነበር፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃነስ 3፡16

 1. እኛ ከዳንን በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል

ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ እና እኛም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበለው የእግዚአብሄር ልጆች በመሆናችን የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ የነበረው ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል፡፡ አሁን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንጂ አንድያ ልጅ አይደለም፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃነስ 1፡12

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

 1. ኢየሱስ አዳኛችንና ቀዳሻችን ነው

ሁላችንም በሃጢያት እስራት ውስጥ ወድቀን በነበርን ጊዜ ስለሃጢያታችን እዳ መስዋእት የሆነልን ኢየሱስ ነው፡፡

የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13

 1. ኢየሱስ ጌታችን ነው እኛ ተከታዮቹ ነን

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሮሜ 10፡9

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ናሙና #አንድያ #በኩር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ

secrat.jpgለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ቆላስይስ 1፡27

እግዚአብሄር ልጆቹ ሁሉ አንዲያሸንፉ ስለፈለገ በነገር ሁሉ ያሸነፈው ኢየሱስ በሚያምኑት ሁሉ ውስጥ እንዲኖርና እነርሱ እንዲያሸንፉ አደረገ፡፡

ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4

. . . ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ . . . ኤፌሶን 3፡16-17

ክርስቶስ የክብር ተስፋ አለው፡፡ የክብር ተስፋ የለው ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡

አንድ እቃ መግዛት ከፈለጋችሁ ቀብድ ታስይዛላችሁ፡፡ ቅበድ አስያዛችሁ ማለት እቃው ለእናንተ ይቀመጥላችኋል እንጂ የሌላ ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ሌላ ገዢ ከመጣ ቀብድ ተከፍሎበታል አይሸጥም ይባላል፡፡

እንዲሁም እግዚአብሔር በክርስቶስ የደም ዋጋን በመክፈል የእርሱ አድርጎናል፡፡ የእርሱ መሆናችንን ማረጋገጫ የሚሆንብን የመንፈሱን መያዣ ሰጥቶናል፡፡ እኛ የእርሱ ነን፡፡ ተስፋችን ሙሉ ነው፡፡

ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።2ኛ ቆሮንቶስ 5:5

በምድር ላይም አሸናፊ ሆነን የምንኖረው የክብር ተስፋ በእኛ ውስጥ ስላለ ነው፡፡ የምድር አሸናፊነታችንም ተስፋ በሰማይና ምድር ሁሉ ስልጣን የተሰጠው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡5

ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ቆላስይስ 1፡27

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በልባችን #የእግዚአብሄርቤተመቅደስ #ክርስቶስ #ክርስቶስበእኛ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ክርስቶስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በመንፈሱ #የእግዚአብሄርቤተመቅደስ #እምነት

ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም

nothing new under the sun.jpgየሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። መክብብ 1፡9

በምድር ላይ ቢሆንልኝ ብለን እጅግ ስንመኘው የነበረ ስናገኘው ለዚህ ነው እንደዚህ የሆንኩት ብለናል፡፡ በምድር ላይ እንደተራራ ገዝፎብን የነበረ ላይ እንደተራራት ትንሽነቱ አስገርሞናል፡፡ በምድር ላይ ስንናፍቀው የነበረ ስናገኘው ሰልችቶናል፡፡ በምድር ላይ እንደ አድማስ ርቆብን የነበረ ነገር ስንቀርበው ምንም አዲስነት አላገኘንበትም፡፡ እደርስበት ይሆን ብለን እጅግ የፈለግነው ውይ ይሄ ነው እንዴ ብለናል፡፡

በምድር ላይ ብናገኘው ህይወታችን ይለወጣል ብለን አስበን የነበረው ነገር ህይወታችንንን ሊለውጥ ሳይችልና ሲቀር ቅር ሲያሰኘን ምስክር ሆነናል፡፡

በምድር ላይ ይህ ያላቸው ሰዎች የታደሉ ናቸው ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ያገኙትን ስናገኝ ቀድሞ እንዳስብነው እንዳልታደሉ ደርሰንበታል፡፡ አሁንም ሰዎች እኛ ፈልገን ስናገኘው የተሰናከልንበትን ነገር እጅግ ሲፈልጉ ስናይ ይህ የተሳተ ግምታቸው ነግሩን ባገኙት ጊዜ ቅር እንደሚያሰኛቸው ስለምናውቅ እናዝናላቸዋለን፡፡

በምድር ላይ አንዲህ ብሆን እኮ ብለን የተመኘነውን ስንሆን ወዲያው ረስተነው አሁን ደግሞ ፍላጎታችን እጅግ የተለየ ሆኗል፡፡

ከሰማይት በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር ያለ ከመሰለን ስላልደረስንበት ብቻ ነው፡፡ የደረሱበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ እንደተረዱት ስንደርስነበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ይገባናል፡፡ ውይ እነርሱን ባደረገኝ የምንላቸው ሰዎች ከዚህ መቼ በወጣሁ ብለው ሲመኙ ደርሰናል፡፡

ብቻኛው አዲሱ ነገር የእግዚአብሄርን ስራ በምድር ላይ ሰርቶ እግዚአብሄርን በህይወታችንና በአገልግሎታችን ማክበር ነው፡፡

እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ ዮሃንስ 17፡4

ብቸኛው አዲሱ ነገር ሰውን መውደድ ፣ ሰውን ማገልገል ፣ ሰውን መጥቀምና ሰውን ማንሳት ነው፡፡

በምድር ላይ አዲሱ ነገር በዘላለማዊ እይታ የምድር ህይወትን እንደ እንግድነት መኖር ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር በምድር ላይ እንደ እግዚአብሄር መልክተኛ ፈቃዱን ፈፅሞ ማለፍ ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ አዲሱ ነገር በሰማይ መዝገብን መሰብሰብ ነው፡፡

ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20

በምድር አዲሱ ነገር በዘላለማዊ ሽልማትን እንደሚቀበል ራስን መግዛት ነው፡፡ በምድር አዲሱ ነገር በምድር ገንዘብ የዘላለም ወዳጆችን ማፍራት ነው፡፡

እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9

ብቸኛው አዲስ ነገር በምድር ለሚቀር ዘላለማዊ ላልሆነ ለጊዜያዊ መብል አለመስራትና ዘላለማዊ ለሆነ ለማይጠፋ መብል መስራት ነው፡፡

ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንስ 6፡27

ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሃንስ 2፡17

አዲሱ ነገር ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ከጌታ ጋር መኖር ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን ኢየሱስን መከተል ብቻ ነው፡፡ ዘመን የማይሽረው አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ፣ ጌታን መከተል ፣ ጌታን ማገልገል ብቻ ነው፡፡

ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ዮሃንስ 3፡31

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ዘላለማዊ #አዲስ #ልብ #ሰማይ #ዘላለም #ጌታ #ከፀሐይበታች #ያልፋሉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል

jesus.jpgሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ . . . የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9፡6

የአለቅነት ብቸኛው ጥቅም ሰዎች ሲገለገሉና ሲጠቀሙ ማየት ነው፡፡ አለቅነት በራሱ ጥቅም አይደለም፡፡ የአለቅነት ጥቅም ሰዎች ካሉበት እግዚአብሄር ወደ አየላቸው ደረጃ ሲደርሱ ማየት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎች ከታሰሩበት ነገር ተፈትተው በነፃነት እግዚአብሄርን ሲያገለግሉ ማየት ነው፡፡

አለቅነትን ለራሳቸው ጥቅም የሚጠቀሙበት ሰዎች በአለም ላይ ስላሉ አለቅነት ከጥቅም ጋር ተያይዞዋል፡፡ በአገራችንም ያለውም አባባል ሲሺም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው አባባል የመጣው አለቅነትን ከተጠቃሙነት ጋር አያይዞ ነው፡፡ ነግር ግን አባባሉ መሆን የነበረበት “ሲሾም በትጋትና በታማኝነት ህዝብን ያላገለገለ ሲሻር ይቆጨዋል” መሆን ነበረበት፡፡ አለቅነት ሰውን ከመጥቀም ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡ አለቅነት ግን እግዚአብሄርን አገልግሎ ከእግዚአብሄር ሽልማትን ከመቀበል ውጭ ጥቅማ ጥቅም የለውም፡፡

የአለቅነትን ሃላፊነት የተረዱ ሰዎች አለቅነትን እንደ ጥቅም አይጓጉለትም፡፡ የአለቅነት ሃላፊነትን የተረዱ ሰዎች ሸክሙ እንጂ ጥቅሙ ትዝ አይላቸውም፡፡ የአለቅነትን ሸክም የተረዱ ሰዎች አላቅነትን እንደጥቅም አይፈልጉትም፡፡

እርግጥ ነው በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን እንደመጠቀሚያ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች ከሰው ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለመጠቀም የአለቅነትን ስልጣን በጭካኔ ይጠቀሙበታል፡፡ በአለም ብዙ አለቅነት ያለው ብዙ ይጠቀማል ትንሽ አለቅነት ያለው ትንሽ ይጠቀማል፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች አለቅነትን ሰውን ለመበዝበዝ ይጠቀሙበታል፡፡

ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። ማቴዎስ 20፡25-26

አለቅነትን ለራስ ጥቅም መጠቀሚያ ማድረግ የእግዚአብሄር ሃሳብ አይደለም፡፡ አለቅነት የመጠቀሚያ መንገድ አይደለም፡፡

በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3

አለቅነት ሃላፊነት ነው፡፡ አለቅነት ሸክም ነው፡፡ አለቅነት የትጋት ስራ ነው፡፡ አለቅነት ታማኝነት ነው፡፡ አለቅነት መሰጠት ነው፡፡ አለቅነት ፊት ቀዳሚነት ነው፡፡ አለቅነት ማንም ባያደርገው እኔ አደርገዋለሁ ማለት ሃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ አለቅነት ምሪትን በየጊዜው በመስጠት የመጥቀም የማገልገል መንገድ ነው፡፡

በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ማቴዎስ 20፡26-28

አለቅነት ሰላምን መስጠት ነው፡፡ አለቅነት ሰዎችን ወደ ሰላም ምንም ወዳልጎደለበትና ምንም ወዳልተበላሸበት ቦታ መርቶ ማድረስ ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ሰላም #ድንቅመካር #ሃያልአምላክ #የሰላምአለቃ #የዘላለምአባት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ማገልገል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አለቅነት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

#ኢየሱስ

#ኢየሱስ.jpgየገና በአል ትርጉም የተረሳ ይመስላል፡፡ የገና በአል ሲታሰብ መብላት ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብን መጠጣት ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰንብ መልበስ ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ የገና ዛፍ ከታሰበ የገና በአል ሲታሰብ ከረሜላ እና ቸኮሌት ከታሰበ ፣ የገና በአለ ሲታሰብ ጣፋጭ ብስኩትና ኬክ ከታሰበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ እረፍትና መዝናናት ከታሰበ ፣ የገና በአልዕ ሲታሰብ ዘፈንና ዳንራ ከታሰበበ ፣ የገና በአል ሲታሰብ መጠጣትና መስከር ከታሰበ ምንም ሃይማኖተኛ ብንሆን የገናን ትርጉም አናውቀውም ማለት ነው፡፡

ገና የሚበላበት የሚጠጣበት የሚዘፈንበት የሚጨፈርበት አይደለም፡፡ ገና እግዚአብሄር ለሰዎች የሰጠው ስጦታ ኢየሱስ የሚዘከርበት እግዚአብሄር የሚመሰገንበትና በስጦታው ምክኒያት ያገኘነው የክርስትና ነፃነት በአል የሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡ ገና የእግዚአብሄርን ስጦታ የማክበርበት ጊዜ ነው፡፡ ገና የእግዚአብሄርን ስጦታ የምናጣጥምበት ጊዜ ነው፡፡

የገና ምክኒያት ኢየሱስ ነው፡፡

ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21

የገና ምክኒያት እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ስጦታ መስጠቱ ነው፡፡

በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16

የገና ምክኒያት ስጦታውን የተቀበሉ ከሃጢያት መዳናቸው ነው፡፡

እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ቲቶ 3፡5

የገና በአል በእግዚአብሄር ስጦታ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃችን ነው፡፡

እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡19

የገና በአል ኢየሱስን የተቀበልን የእግዚአብሄር ልጅ መሆናችን ነው፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ሃጢያት #መዳን #ነፃነት ## #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #ኢየሱስ #ጌታ

ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ

apple-464182_1920.jpgእርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡20-21

በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ . . . ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌሶን 2:1-2

የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው። ሮሜ 6፡23

እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21

በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ ዮሃንስ 1፡9

እነርሱም፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። ሃዋሪያት 16፡31

እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ቲቶ 3፡5

ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። ሐዋሪያት 2፡38

ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሃነስ 8፡31-32

ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21

ሃጢያታችን ይቅር ካልተባለ ፣ በክርስቶስ ደም ይቅር ካልተባልን ፣ ከእግዚአብሄር ጋር ካልታረቅን ፣ የእግዚአብሄር ልጆች ካልሆንን ፣ በኢየሱስ ከሃጢያት ሃይል ካልዳንን ፣ የእግዚአብሄር መንግስት የመንግስተሰማያት ወራሾች ካልሆንን ኢየሱስ ወደምድር የመጣበትን ምክኒያት አጥተነዋል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ሃጢያት #መዳን #ነፃነት ## #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

የሃቀኛው ንጉስ ታሪክ

Jesus-RealName-GettyImages-77886330-57a36c913df78cf4590bc046.jpgኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ምክኒያቶች አሉ፡፡ ኢየሱስ ራሱን ሳያዋርድ በእግዚአብሄር መልክ እየኖረ እኛን ያላዳነበት ምክኒያት አለው፡፡ ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት 5 ምክንያቶችን ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡

ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት 5 ምክንያቶች፡-

የእግዚአብሄር ፅድቅ ስለሚጠይቀው ነው፡፡

በድሮ ዘመን በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሀቀኛ ንጉስ ይኖር ነበረ ይባላል ፡፡ አንድ ጊዜ ይህንን ጥፋት ያጠፋ ሰው በአርባ ግርፋት ይቀጣል ብሎ ህግ ያወጣል፡፡ ያ ንጉስ ሲኖር ሲኖር ቆይቶ አንድ ቀን ይህን ያደረገ አርባ ይገረፋል ብሎ የተናገረበትን ጥፋት ያጠፋ ሰው ይዘውለት ይመጣሉ፡፡ ያ ጥፋተኛ እናቱ ነበረች፡፡ ንጉሱ እናቱ ጋር ሲደረስ ህጉን ለመሻር አልቻለም፡፡

ስለዚህ እንዲህ አለ፡፡ ስለ እናቴ ስል የሃገሩ ህግ ብሽር እውነተኛ አልሆንም፡፡ ነገር ግን ስለእናቴ ስል  አርባውን ግርፋት እኔ ራሴ እገረፍላታለሁ በማለት ህጉንም ሳይሽረው ህጉንም ለመፈፀም በእናቱ ፋንታ አርባውን ግርፋት ተገረፈላት ይባላል፡፡

ሃጢያትን የሰራች ነፍስ እርሱዋ ትሞታለች ያለው እግዚአብሄር ቃሉን አይለውጥም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄር በመልክና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ለዘላለም ከእርሱ ሲለያይ ማየት አልወደደም፡፡ ስለዚህ ህጉንም ሳይለውጥ ህጉን የሚፈፅምበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡ ስለዚህ ሃጢያት ያላቀውን ልጄን እልካለሁ፡፡ ስለሃጢያታቸው ሙሉውን የሞት ዋጋ ይከፍላል በማለት አብ ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው፡፡

ኢየሱስ ወደምድር የተላከው ሃጢያትን የሰራች ነፍስ እርስዋ ትሞታለች የሚለው የፅድቅ ቃል ሙሉ ለሙሉ እንዲፈፀም ነው፡፡

ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ሕዝቅኤል 18፡20

የሰው ልጅ ሊፈፅም ያልቻለውን እግዚአብሄር በሃጢያተኛ ልጅ ምሳሌ አድርጎ ኢየሱስን በመላክ የህጉን ፍላጎት ሁሉ ፈፅሞታል፡፡

ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። ሮሜ 8፡3-4

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ምንም ቢወደንም ስለሚወደን እኛ ጋር ሲደርስ ህጉን ስለማይሽር ፃዲቅ ስለሆነ ነው፡፡

ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት – ለእኛ የትህትናና የልጅነት ክብር ምሳሌ ለመሆን ነው

እግዚአብሄርን ያየው አንድስ እንኳን የለም፡፡ እግዚአብሄርን ወደምድር ወርዶ በሰው ቋንቋ የተረከው ኢየሱስ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር በተግባር ያየነው በኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስን አይተን ነው የልጅነት ስልጣናችንን የምንረዳው፡፡ ኢየሱስን አይተን ነው ፀሎታችን በእግዚአብሄር ዘንድ እንዴት እንደሚሰማ የምናውቀው፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን እንዴት እንደወደደው አይተን ነው እኛን እንዴት እንደወደደን የምናውቀው፡፡

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23

እግዚአብሄር በተለያየ መንገድ ራሱን በከፊል ቢገልጽፅም ኢየሱስ ግን የእግዚአብሄር ሙሉ ነፀብራቅ ነው፡፡

መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። ዮሃንስ 1፡18

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ዕብራውያን 1፡1-3

ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት – ሰይጣንን እንደ ሰው ለመርታት ነው

እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄረ ሰውን የፈጠረው እንዲገዛ ነው፡፡ የዚህ አለም ገዢ ሰው ነበር፡፡ ሰው ግን እግዚአብሄርን መታዘዝ ትቶ የሰይጣንን ቃል ሲሰማ የልጅነት የገዢነት ስልጣኑን አጣው፡፡ ሰው በራሱ እጅ ነው ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠው፡፡ ሰይጣን የዚህ አለም ገዢ እንዲሆን ያደረገው ሰው ነው፡፡

ስለዚህ በሰው አለመታተዘዝ የታጣውን ስልጣን መመለስ የሚቻለው በሰው መታዘዝ ነው፡፡ በሰው ሃጢያት የተነጠቀውን የሰውን ስልጣን መመለስ የሚቻለው ሃጢያት በሌለበት ሰው ነው፡፡ በሰው የተነጠቀውን ስልጣን በአምላክ መመለስ አግባብ አይደለም፡፡

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራውያን 2፡14-15

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።  ቆላስይስ 2፡15

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደፍፁም ሰው ባይመላለሰ ኖሮ ኢየሱስን እንድንመስል አይጠበቅብንንም ነበር፡፡ ኢየሱስ እንደ እኛው በነገር ሁሉ ተፈትኖ እንደ ሰውነት ባይኖር ኖሮ ክርስቶስን መምሰላችን ተግባራዊ አይሆንም ነበር፡፡

ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30

እግዚአብሄር ለሰው ያለውን ክብር ለማሳየት ነው

አንዳንድ ጊዜ አንድን እቃ ለመግዛት እንፈልግና የእቃውን ጥራቱን ለማወቅ እውቀቱ ከሌለን ዋጋውን እናያለን፡፡ ለእቃው የሚጠየቀውን ዋጋ አይተን የእቃውን ጥራት እንገምታለን፡፡ ብዙ ገንዘብ የሚጠየቅለ እቃ ዋጋው ከፍ ያለ ውድ እቃ ነው፡፡ ትንሽ ገንዘብ የሚጠየቅለት እቃ ደግሞ ዋጋው ዝቅ ያለ ርካሽ እቃ ነው፡፡ እኛን ለማዳን የተከፈለውን ዋጋ ስናይ የእኛን ዋጋ እናይበታለን፡፡ የክብራችንን ከፍተኝነት የምናውቅው ከእኛ የተከፈለውን ዋጋ በማየት ነው፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19

እንዲያውም በምድር ላይ በአምላክነት መመላሱ ሳይሆን እንደ እኛ በስጋ መመላለሱን አለማመን ነው ከእምነት የሚያወጣው፡፡

የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 1ኛ ዮሐንስ 4፡2-3

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ስጋናደም #የልጅነትክብር #ክብር #የልጅነትስልጣን #ሰውነት #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: