Category Archives: BLESSED

የእውነተኛ ውበት ሁለቱ መለኪያዎች

inner beauty.jpgለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4

ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤ ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

የውጭ ውበት መልካም ነው ዋጋም አለው፡፡ ነገር ግን ከውጭው ውበት ጋር ሲነፃፀር የውስጡ ውበት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡

ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ብዙ ዋጋ አያስከፍልም፡፡ ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ባነሰ ጊዜና ጥረት ይገኛል፡፡

የውጪው ውበት ለሰው የእግዚአብሄር ስጦታ ሲሆን ማንም ሊመካበት የማይችል ውበት ነው፡፡ የውስጡ ውበት ግን የሰው ለእግዚአብሄር ስጦታና ሰውን የሚያስመሰግነው ውበት ነው፡፡ የውጭው ውበት ራስን በማስለመድ የሚመጣ መልካም ባህሪ ነው፡፡

እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ – 1ኛ ጢሞቲዮስ 4፡7

የውጭው ውበት አንዴ ተሰርተነው የምናስደንቅበት ሲሆን የውስጡ ውበት ግን የህይወትን ዘመን ሁሉ ትጋትን የሚጠይቅ ዘለቄታዊ ውበት ነው፡፡

ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ምሳሌ 31፡30

የውጭው ውበት እግዚአብሄርን አያስደንቀውም የውስጡ ውበት ግን እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው ስለሆነ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የውጭው ውበት እንደ ዛፍ ቅጠል ሲሆን የውስጡ ፍሬ ግን እንደ ዛፍ ፍሬ ነው፡፡

የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22

የውስጡ ውበት የሚለካው ተለዋዋጭ በሆነው በገፅታ ሳይሆን በባህሪ ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅላት ሳይሆን በአመለካከት ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በርዝመት ሳይሆን በትግስት ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅጥነት ሳይሆን በትህትና ነው፡፡

የውስጥ ውበት የሚለካባቸውን እግዚአብሄር ከእያንዳንዳችን የሚፈልጋቸውን ሁለት ወሳኝ ባህሪያትን እንመልከት፡-

የዋህነት

የዋህነት ማለት ክፉን በክፉ ለመመለስ ሙሉ ሃይል ይዞ ነገር ግን ሃይልን ለክፋት ላለመጠቀም መወሰንና ራስን ማግዛት ነው፡፡

የዋህ ማለት ሞኝ ማለት ሳይሆን ክፋትን በክፋት ላለመመለስ ራሱን የሚገዛ ቁጥብ ሰው ማለት ነው፡፡ የዋህ ማለት ሃይል እንዳለው እያወቀ ሃይሉን ለክፋት ሳይሆን ለመልካምነት ብቻ ለመጠቀም የወሰነ ራሱን የሚገዛ ማለት ነው፡፡

የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5

ዝግተኛነት

ዝግተኛ ማለት እግዚአብሄርን የማይቅድም ፣ እግዚአብሄርን የሚያስቀድም ፣ እግዚአብሄርን የሚከተል ፣ የእግዚአብሄርን እርምጃ የሚታገስና በእግዚአብሄር የሚመራ ሰው ማለት ነው፡፡ ዝግተኛ ወይም ጭምት ማለት በራሱ አነሳሽነት ድርሻዬ ነው ብሎ የፈለገውን የማይወስድ እግዚአብሄር ድርሻውን እስኪያሳየው የሚጠብቅ እግዚአብሄር ካላሳየው በራሱ ማስተዋል የማይደገፍ በራሱ የማይመራ ማለት ነው፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ ምሳሌ 3፡5

ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ

slide-connected.jpgበወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23

ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።(አዲሱ መደበኛ ትርጉም) 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23

በአለም ላይ ሰዎች ከትልቅ ድርጅት ስለገዙት አክሲዮን ይናገራሉ፡፡ ሰዎች በአለም ላይ ስለገዙትና ስላላቸው ቦንድ በኩራት ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ለምድር ይጠቅማል፡፡

ሰው ግን የታወቁ የምድር ማህበሮች ማህበርተኛ ሆኖ ነገር ግን በወንጌል ማህበርተኛ ካልሆነ ምስኪን ሰው ነው፡፡

የምድር ጉዟቸውን መልስ ብለው ሲያዩ ፎቅ አልሰራሁም ታዋቂ አልሆንኩም ውድ መኪና አልነዳሁም ነገር ግን በህይወቴ ዘመን ሁሉ ቤተክርስትያንን ደግፌያለሁ የሚሉ የተባረኩ ሰዎች አሉ፡፡

የምድር ጉዟቸውን መለስ ብለው ሲያዩ ተምሬ ዶክተር አልሆንኩም ነገር ግን ወንጌልን ለመስበክ ህይወቴን ሙሉ ሰጥቼያለሁ በማለት በህይወታቸው የሚረኩ ሰዎች አሉ፡፡

እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9

አላገባሁም አልወለድኩም ነገር ግን በህይወቴ ሁሉ የእግዚአብሄርን ቤተክርስትያን የወንጌል ስራ ስደግፍ ኖሬያለሁ የሚሉ በሚገባ የተኖረ ህይወት የሚኖራቸው ሰዎች አሉ፡፡

በምድር ላይ የምንም ማህበር አባል ያልሆኑ የወንጌል ግን ማህበርተኛ ለመሆን ህይወታቸውን የሚያፈሱ ጉልበታቸውን ገንዘባቸውን እውቀታቸውን ጊዜያቸውን ለወንጌል ስራ የሚሰጡ የተባረኩ ሰዎች አሉ፡፡

አሁንም በ2018 ዓም ያዳነንን ወንጌል ማህበርተኛ ለመሆን የማይጠፋ የዘላለም ሽልማት ስለሚያስገኘው ስለወንጌል ሁሉንም ለማድረግ እንወስን ፡፡

በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ወንጌል #ማኅበረተኛ #ስብከት #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #የአመፃገንዘብ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የፍላጎትና የቅንጦት መለያ መንገድ

tumblr_static_lamborghini-gallardo-luxury-car.jpg

ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው ሰው የተፈጠረው ለተወሰነ አላማና ግብ ነው፡፡ ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው በምድር ላይ ማድረግ የሚችለው የተወሰነውን የእግዚአብሄርን ልዩ አላማ ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሄርን ስንከተል እርሱ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላል፡፡ እግዚአብሄር የሚያቀርብልን የሚያስፈልገንን ነገር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አያቀርብልንም፡፡ ሰውም የሚያገኘው አቅርቦት በተጠራበት በተለየ አላማ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው የሚያቀርበው ለፈጠረው አላማ ብቻ ነው፡፡  የፈጠረው ሰው የሚያስፈልገው ነገር እንዳይጎድልበት እግዚአብሄር በትጋት ይሰራል፡፡ ለመሰረታዊ ፍላጎታችን ሁሉ እግዚአብሄር ሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ለቅንጦት ፍላጎታችን ሃላፊነት አይወስድም፡፡

የሰው ስኬት የሚወሰነው በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት በመቻሉ ላይ ነው፡፡ የሰው ተግባራዊ ጥበብ የሚለካው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳቱ ነው፡፡ በቅንጦትና በመሰረታዊ ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አንዳንዴ ቀላል ባይሆንም ስለሁለቱ ልዩነት ከእግዚአብሄር ቃል መማር እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃልን ከተመለከትንና ከተረዳን ህይወታችንን በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮር እግዚአብሄር የሚሰጠንን አቅርቦት ለታለመለት አላማ በሚገባ መጠቀም እንችላለን፡፡

ሁለት ተመሳሳይ ሰዎችን የሚለየው ይህ መርህ ነው፡፡ አንዱ ያገኘውን ነገር ሁሉ ራሱን በመግዛት በሚያስፈልገው በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ያጠፋዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በሚፈልገው ነገር ላይ ሁሉ ማጥፋት ሲጀምር የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ይጎድለዋል፡፡

ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። ምሳሌ 12፡9

የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል። ምሳሌ 12፡9 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ብዙን ጊዜ ችግራችን የእግዚአብሄር አቅርቦት ማግኘት እጥረት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ችግራችን መሰረታዊ ፍላጎትንና ቅንጦትን መለየት  አለመቻላችንና ለመሰረታዊ ፍላጎት የተሰጠንን አቅርቦት በቅንጦት ላይ ስለምናውለው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከራሳችንና ከሰዎች ጋር ሰላም የምናጣው ከመሰረታዊ ፍላጎት አልፈን ለቅንጦት ስንሮጥ ነው፡፡

በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1፣3

በክርስትና ስኬታማ ለመሆን የመሰረታዊ ፍላጎት መርህ ሊገባን ይገባል፡፡ በህይወት ለመሳካት መሰረታዊ ፍላጎትን ከቅንጦት መለየት አስፈላጊ ስለሆነ ሁለቱን እንዴት እንደምንለይ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡

መሰረታዊ ፍላጎትን መለያው መንገዶች

  1. መሰረታዊ ፍላጎት ግዴታ የሆነ ነገር ነው፡፡

መሰረታዊ ፍላጎት በጣም ግዴታ ከመሆኑ የተነሳ ፍላጎታችን ካልተሟላ የህይወት አላማችንን መፈፀም አንችልም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት እግዚአብሄር በምድር ላይ ያስቀመጠንን ልዩ አላማ ለመፈፀም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡8

አንዳንዴ ግን አጥተነው እስካላየን ድረስ ብዙ ነገሮች የሚያስፈክልጉን ይመስለናል፡፡ አጥተነው ግን ምንም ሳንሆን በተግባር እስካላየን ድረስ የማንረዳው ብዙ የሚያስፈልጉ የሚመስሉን ነገር ግን የማያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡

መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13

ለምሳሌ የምግብ አላማ ብርታት መስጠት ፣ ሰውነታችንን መገንባትና ከበሽታ መከላለከል ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርግልን ምግብ መብላት መሰረታዊ ፍላጎት ሲሆን ስለምግቡ ጣእም ፣ ስለምግቡ ትኩስነትና ቅዝቃዜ ከተነጋገርን ግን ስለመሰረታዊ ፍላጎት ሳይሆን ስለምቾት ወይም ቅንጦት እየተነጋገርን ነው፡፡ ቅንጦት ቢገኝ ጥሪ ነው ነገር ግን ግዴታ አይደለም፡፡

ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። ሐጌ 1፡6

  1. መሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡

በሁለቱ መካከል መምረጥ ግዴታ ከሆነብን የምንመርጠው ነገር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት የምናስቀድመው ነገር ነው፡፡ ቅንጦት ቢቆይ ችግር የለውም እንዲውም ባይገኝ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የምንለው ነገር ቅንጦት እንጂ መሰረታዊ ፍላጎት አይደለም፡፡

ለዚህ ምሳሌ የሚሆንን የእስራኤል ህዝብ ነው፡፡ የእስራኤል ህዝብ ከግብፅ ሲወጡ በህይወታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነፃነታቸው እንጂ በመንገድ ላይ የሚበሉት የምቾት ወይም የቅንጦት ምግብ አልነበረም፡፡ በምድር በዳ ሲጓዙ እግዚአብሄር ሁሉንም ፍላጎት የሚያሟላ ጉልበት የሚሰጥ ፣ ሰውነትን የሚገነባና ከበሽታ የሚከላከል ንጥረ ነገርን ሁሉ ያካተተመናን መናን ሰጣቸው፡፡ የእስራኤ ህዝብ ግን እንደለመዱት አይነት ሆድን ያዝ የሚያደርግ ከበድ ያለ ምግብ ስላልነበረ ስለመና በእግዚአብሄር ላይ አጉረመረሙ፡፡ የእስራኤል ህዝብ ጥያቁ የመሰረታዊ ፍላጎት ጥያቄ ሳይሆን የምቾትና የቅንጦት ጥያቄ ነበር፡፡

ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። ዘኍልቍ 21፡5

በሁሉም የህይወታችን አቅጣጫ በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት ተረድረተን ለመሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ ከሰጠን በህይወታችን ከእኛ አልፈን ብዙዎችን ማገልገል እንችላለን፡፡

ያም ሆነ ይህ የክርስትና የመጨረሻ ደረጃ የመጨረሻው የስኬት ጣራ ስለ መሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡

ፀሎት፡ እግዚአብሄር አምላክ ሆይ ይህንን ቃል እንድሰማ ስለረዳኝ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በተማርኩት መሰረት ለመሰረታዊ ፋልጎት ቅድሚያ መሰጠት እችል ዘንድ ልዩነቱን ስለምታስተምረኝ አመሰግናለሁ፡፡ በእያንዳንዱም የህይወት ክፍሌ በሁለቱ መካከል መለየት አችል ዘንድ ጥበብን ስለምትሰጠኝና ስለምትረዳኝ አከብርሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም አሜን፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የመርገም ሀሁ

Are-You-Suffering-From-the-Curse-of-Knowledge.jpgእግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ፈጥሮ ባረከው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመባረክ ወደ ክንውን ወደ መሳካትና ወደፍሬያማነት ለቀቀው፡፡  ነገሮች ሁሉ ለሰው በጎነትና ክንውን እንዲሰሩ እግዚአብሄር ሰውን ባረከው፡፡

እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡27-28

ሰው በበረከት በኖረበት ዘመን ሁሉ የኖረው በሙላት በክንውን በፍሬያማነት ነው ፡፡ በሰው ላይ የሚበረታና የሚያይልበት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ተፈጥሮ ሁሉ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ተፈጥሮ ሁሉ አንደሃይሉ መጠን ይሰጠው ነበር፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በታዘዘ ጊዜ ሁሉም ነገር ለእርሱ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ታዝዞ በኖረበት ጊዜ ሁሉ የሚሰራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር፡፡ ሰው በመታዘዝ በኖረበት ዘመን ሁሉ በታላቅ ስልጣንና ሃይል ኖረ፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ስልጣን ስር እስከነበረ ድረስ ለሰው ስልጣን የማይገዛ የማይሰማውና የማይታዘዘው አንድም ሃይል አልነበረም፡፡ እግዚአበሄርን ታዞ በኖረበት ዘመን ሁሉ ሰው በሙላት ኖረ፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ታዞ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ድካም ፣ አለመከናወን ፣ በሽታና ማጣት በሰው መዝገበ ቃላት ውስጥ የማይታወቁ ነገሮች ነበሩ፡፡

ሰው አታድርግ የተባለው ባደረገ ጊዜ ግን ከእግዚአብሄርን በረከት አጣው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ ሲያምፅ ነገሮች ሁሉ አመፁበት፡፡ ሰው እግዚአብሄርን መታዘዝ  ሲያቆም ሁሉም ነገር ለሰው መታዘዝ አቆመ፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ በማመፅ የእግዚአብሄርን በረከት እና ስልጣን አጣው፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ በማመፁ ሁሉም ነገሮች በእርሱ ላይ አመፁ፡፡

ሰው በሃጢያት ሲወድቅና እግዚአብሄር የፈጠረውን አላማ ሲስት ሁሉም ነገር ተዘበራረቀበት፡፡ ሰው በሃጢያት ሲወድቅ በሽታ ማጣት ሞት የሚባሉ ነገሮች የህይወቱ ክፍል ሆኑ፡፡

አሁንም ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን ሲቀበል እግዚአብሄር ይቀበለዋል፡፡ ኢየሱስን የተቀበለ ሰው ከጨለማ ስልጣን ድኖዋል፡፡ ኢየሱስን የሚከተል ሰው ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት ፈልሶዋል፡፡

እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ  1:13-14

ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታችን የተቀበልን ሁሉ በእግዚአብሄር ምህረት ስር ነን፡፡ ኢየሱስን የምንከተል ሁሉ በሰይጣን ምህረት ስር አንኖረም፡፡ ሰይጣን በእኛ ላይ ስልጣን የለውም፡፡

በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36

በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2

የኢየሱስን የመስቀል ስራ ለእኔ ነው ብለን የተቀበልን ሁላችን አሁን የቁጣ ልጆች አይደለንም፡፡

በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌሶን 2፡3

እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ሮሜ 8፡1

በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። ኤፌሶን 1፡3

የበረከት ልጆች እንጂ የመርገም ልጆች አይደለንም፡፡ የተጠራነው በረከትን ልንወርስ እንጂ የተጠራነው ለመርገም አይደለም፡፡

ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9

አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19

እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡8-9

ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕቆብ፡25

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መርገም #እርግማን #ክርስቶስ #ህይወት #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #እረፍት

በክርስትያን ህይወት ላይ የሚሰራ የመርገም ሃይል

curse.jpgመርገም አለመሳካት አለመከናወን ማለት ሲሆን መርገም በቀላሉ የበረከት ተቃራኒ በተፈጥሮአዊው አለም ላይ ተፅእኖ የሚያደርግ ልእለ ተፈጥሮአዊ ሃይል ነው፡፡

አንዳንዴ አንድን ነገር ከመተርጎም ይልቅ ተቃራኒውን ነገር መተርጎም የተሻለ መረዳት ይሰጣል፡፡ የመርገም ተቃራኒ በረከት ሲሆን በረከት ማለት ደግሞ ደስተኝነት ፣ እምቅ ጉልበት ፣ ሞገስ ፣ የተመሰገነ ፣ የታጠቀ ፣ የተለቀቀ ማለት ነው፡፡

ሰው ሲፈጠር ተባርኮ ነው የተፈጠረው፡፡ ሰው እንዲወጣ እንዲገባ እንዲበዛ ፣ እንዲያፈራ እንዲወርስ ነበር በእግዚአብሄር የተባረከው የታጠቀውና የተለቀቀው፡፡

እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡28

መርገም የተጀመረው ሰው እግዚአብሄር ያዘዘውን ባለመታዘዝ የሰይጣንን ድምፅ ሰምቶ እግዚአብሄር ላይ ካመፀ በኋላ ነው፡፡

አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ ዘፍጥረት 3፡17-19

ሰው በሃጢያት ከመውደቁና በመርገም ሃይል በታች ከመውደቁ በፊት ነገሮች በቀላሉ ይሰሩለት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ይታዘዘው ፣ ይገዛለትና ይተጋለትና ይሰራለት ነበር፡፡ ሰው በአመፃው ምክኒያት ሲረገም ሁሉም ነገር ለገመበት፡፡ ሁሉም ነገር እንደአቅሙ መጠን አልሰጥም አለው፡፡

ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ ዘፍጥረት 4፡12

እግዚአብሄር አብርሃምን ከጠራው በኋላ በያቆብ ወይም እስራኤል የራሱን ህዝብ ከለየ በኋላ የእስራኤል ህዝብ የሚረገምበትንና የሚባረክበትን መንገድ አሳያቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን መርገም የእስራኤልን የብሉይ ኪዳን ህግ ከመጠበቅና ካለመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

እስራኤላዊያን የታዘዙትን መተዳደሪያ ደንባቸውን ትእዛዙን ባይሰሙና ባያደርጉት የሚከተለው መርገም እንዳለ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል። ዘዳግም 28፡15

የእግዚአብሄርን የብሉይ ኪዳን ህግ ያልፈፀሙ የእስራኤ ህዝብ አግዚአብሄር እንደተናገረው በብዙ መርገም ውስጥ ያል ነበር፡፡

በአዲስ ኪዳን ደግሞ በአይሁድ ህግ ሲኖሩ ለነበሩ ኢየሱስን ለተቀበሉ አይሁዳዊያን የእስራኤል ህዝብ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሰቀል መርገም ስለሆነላቸው ከህግ እርግማን እንዳዳናቸው ያስተምራል፡፡

በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ ገላትያ 3፡13

በአዲስ ኪዳን በግልፅ የተቀመጠው ብቸኛው መርገም ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ሰው የተረገመው መርገም ነው፡፡

ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። 1ኛ ቆሮንቶስ 16፡22

ምክኒያቱን እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መድሃኒት ኢየሱስንም ያለተቀበለ ሰው አንድያ ልጁን በመስጠት እግዚአብሄር ያዘጋጀው የመዳኛ መንገስድ ስላልተቀበለ በእግዚአብሄር ቁጣ ስር ይኖራል፡፡

በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36

በልጁ በኢየሱስ የሚያምን ሰው አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ ኢየሱስን እንደአዳኝ የተቀበለ ሰው እግዚአብሄር ተቀብሎታል፡፡ ኢየሱስን በሚከተል ሰው እግዚአብሄር ደስ ተሰኝቶበታል፡፡

ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17

እርግጥ ነው ክርስትያን ከሃጢያት እና ከሃጢያት ውጤቶች ነፃ ይወጣ ዘንድ የእግዚአብሄን ቃል መፈለግ መወቀበልና ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ተቀብሎ ባደረገው መጠን በክርስቶስ ያለውን እጅግ አስደናቂ አርነት ይለማማዳል፡፡

ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሃንስ 8፡31-32

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መርገም #እርግማን #ክርስቶስ #ህይወት #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #እረፍት

እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው

BLESSED2.jpgምስጉን ነው የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተባረከ ፣ የተመሰገነ ፣ የታደለ ፣ የተሞገሰ ፣ የተወደደ የተከናወነ ፣ የተሳካ ፣ የተለየ ፣ የከበረ ፣ የሚቀናበት ፣ የተጠቀመና እድለኛ የሚሉት በከፊል ሊገልፁት ይችላሉ፡፡

የእግዚአብሄር ህዝቦች እጅግ የተባረክብ ስለሆንን ማንም ተቃውሞን አይዘልቅም፡፡

እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ሮሜ 8፡31

የእግዚአብሄር ህዝብ እጅግ ከመመስገኑ የተነሳ እግዚአብሄር ሊያወስው የጠራው ነው

እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።  መዝሙር 33፡12

የእግዚአብሄር ህዝብ እጅግ ከመመስገኑ የተነሳ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ይኖራል

አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? ዘዳግም 4፡7

የእግዚአብሄር ህዝብ እጅግ ከመመስገኑ የተነሳ እግዚአብሄር ህዝቡን ለመቤዠት ከፊቱ ይሄዳል

አንተ እግዚአብሔር ከግብጽ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ በታላቅና በሚያስፈራ ነገር ለአንተ ስም ታደርግ ዘንድ፥ ለአንተም ሕዝብ ትቤዥ ዘንድ እንደሄድህለት እንዳንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን? ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነኸዋል። 2ኛ ዜና 17፡21-22

አምላኩ እግዚአብሄር የሆነ ህዝብ የተባረከ ህዝብ ነው

እንደዚህ የሚሆን ሕዝብ የተመሰገነ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው። መዝሙር 144፡15

አምላኩ እግዚአብሄር ከመሆን በላይ የሆነ ደረጃ የለም

ለአንተም ሕዝብ ትቤዥ ዘንድ እንደሄድህለት እንዳንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን? 2ኛ ዜና 17፡21

እግዚአብሄር አምላኩ የሆነ ህዝብ ካልተደሰተ ፣ ከተጨነቀ ፣ ካልተረጋጋና ካልፈነጠዘ ማን ሊደሰት ይችላል?

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #አምላክ #የተባረከ #የተመሰገነ #የታደለ #የተሞገሰ #የተወደደ #የተከናወነ #የተሳካ #የተለየ #የከበረ #የሚቀናበት #የተጠቀመ #እድለኛ #ክብር #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

%d bloggers like this: