Category Archives: Unity

ለመጣላት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም

pride.jpg

መጣላትና መለያየት ብርቅ አይደለም፡፡ ሰው ለመጣላትና ለመለያየት ምክንያት አላገኘሁም ካለ ይዋሻል፡፡ ለመጣላትና ለመለያየት ምክንያት ሞልቷል፡፡ ሰው ለመለያየት ምክንያት አገኘሁ ካለ አያስደንቅም፡፡ ሰው ከእከሌ የምጠላው ነገር አለ ቢል ወይጉድ እንዴት የማይመቸው ነገር ሊያገኝ ቻለ ብሎ የሚደነቅ ሰው የለም፡፡ ከሌላው ሰው የምትጠላውና የማትወደው ከአንድ በላይ ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ለመጣላትና ለመለያየት አስተዳደጋችን ፣ ባህላችን ፣ አስተሳሰባችን ፣ አመለካከታችን ስጦታችን መለያየቱ ብቻ ይበቃል፡፡

ለመጣላት ሌላ ሰውም አያስፈልግም፡፡ ከራሳችሁ ህይወት የማትወዱት ነገር አለ፡፡ ይህ በህይወቴ ባይሆን ኖሮ የምትሉት ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ ይህን ነገር ብለውጠው ኖሮ የምትሉት ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ለመጣላት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ለመጣላት ጥረት ማድረግ  አያስፈልግም፡፡ ጥል አጠገባችሁ ነው፡፡

ህይወት ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ለመጣላት የሚያስፈልገው ለስጋችሁ ትንሽ አርነት መስጠት ብቻ ነው፡፡ ለመጣላት የሚያስፈልገው ከመጠን በላይ ዘና ማለት ብቻ ነው፡፡ ለመጣላት አንደበትን አለመግዛት በቂ ነው፡፡ ትንሽ ስንፍ በማድረግ ሳታውቁት ተጣልታችሁ ታገኛላችሁ፡፡ ካልተጠነቀቃችሁ በማይሆን ነገር ከገዛ ራሳችሁ ጋር እንኳን ተጣልታችሁ ትገኛላችሁ፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡13

ሚስት ከባልዋ የማትወደውን ነገር ቢኖራት አያስደንቅም፡፡ እንዴት ያስደንቃል? እንዲያውም የሚያስደንቀው ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ሁሉን ነገር እወድለታለሁ አንድም ነገር እንዲለውጥ አልፈልግም ካለች ነው፡፡

አብሮ ለመስራት ግን ባህሪ ይጠይቃል፡፡ አብሮ መኖር ግን መሸከም ትህትና የዋህነት ይጠይቃል፡፡ አብሮ ለመስራት ግን መዋደድ ሃጢያትን መሸፈን ከእኛ የተለየውን ሰው መረዳት ይጠይቃል፡፡

ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4፡8

አብሮ መስራት ስጋን መጎሸም ይጠይቃል፡፡

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡27

በአንድነት አብሮ መስራት ንቃትና በመጠኑ መኖርን ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡

በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡13-14

ለዲያቢሎስ ስፍራን ላለመስጠት ትምክትን ዋጥ አድርጎ በአንድነት መኖርና በአንድነት መስራትን ይጠይቃል፡፡ ለአንድ አላማ ለመስራት ትጋትን ይጠይቃል፡፡

በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #መለያየት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

ቢስማሙ + በስሜ በሚሰበሰቡበት = በመካከላቸው እሆናለሁ

IMG_3804 1.jpgደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19-20

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው መጮኻችን አይደለም፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው መለመናችንና ማልቀሳችን አይደለም፡፡

ኢየሱስ በህዝቡ መካከልና መገኘት አብሮ መስራት ይፈልጋል፡፡ እኛ በመካላችን እንዲገኝና እንዲሰራ ከምንፈልገው በላይ ኢየሱስ በመካካላችን ተገኝቶ አብሮ በሃይል መስራት ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን የሚገኘው እርሱ እንዲገኝ የሚያደርገውን ነገሮችን ስናደርግ ነው፡፡

ኢየሱስ በመካላችን እንዲገኝ የሚያድርገውን ሁለት ነገሮች እንመልካት፡፡

  1. በአንድ ልብ መሆን

 

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19

በአንድ ሃሳብ መሆን ኢየሱስ በማካከላችን እንዲገኝ ያደርገዋል፡፡ አንዱ አንድ ሌላው ሌላ አላማ ካለው ኢየሱስ የተደበላለቀን ነገር ሊሰራ አይገኝም፡፡

በሃዋሪያት ላይ የእግዚአብሄር መንፈስ ከመውረዱ በፊት በአንድ ሃሳብ ይፀልዩ ነበር፡፡

በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። የሐዋርያት ሥራ 2፡1-2

ሃዋሪያው ስለዚህ ነው ደስታዬን ፈፅሙልኝ በአንድ ሃሳብ ተስማሙ እያለ የሚናገረው፡፡

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡1-2

  1. የመሰብሰብ አላማ

 

ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡20

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ መሰብሰባችን አላማ ያስፈልገዋል፡፡ እንደው ለመሰብሰብ የሆነ መሰብሰብ ኢየሱስ እንዲገኝ አያደርገውም፡፡ ኢየሱስ እንዲገኝ የሚያደርገው መሰብሰብ በስሙ የሚደረግ መሰብሰብ ብቻ ነው፡፡

በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ደግሞ ስብሰባው ሲጀመር በኢየሱስ ስም ፕሮግራማንን እንጀምራለን ማለት አይደለም፡፡ በስሙ መሰብሰብ በኢየሱስ ስም ብሎ ከመናገር ያልፋል፡፡

በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ኢየሱስን ወክሎ መሰብሰብ ማለት ነው፡፡ የኢየሱስ አላማ የእግዚአብሄርንም መንግስት ማስፋፋት እንደሆነ ሁሉ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅምና መስፋት እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት ቤተክርስትያን በምድር ላይ ያለችበትን አላማ ለማስፈፀም እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡ በኢየሱስ ስም መሰብሰብ ማለት እኛ የኢየሱስ ተከታዮች ደቀመዛሙርት በምድር ላይ ያለንን የእግዚአብሄርን መንግስት እና ፅድቁን የመፈለግ አላማ ለማስፈፀም እንሰበሰባለን ማለት ነው፡፡

ኢየሱስ በመካከል እንዲገኝ የሚያደርገውን የልብ አንድነትና የእግዚአብሄር መንግስት አላማ ከተሟላ ኢየሱስ እራሱ ይገኛል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #መገኘት #ህልውና #ቃል #ህልዎት #አንድነት #በስሜ #በኢየሱስስም #ፅድቅ #የጌታመንፈስ #አብሮነት #ክብር #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ምስክርነት #አማርኛ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ነፃነት #ሞገስ #እርፍት #እርካታ #አርነት #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #ፌስቡክ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

አንድነትን ለመጠበቅ የሚጠቅሙ ምክሮች

UNITY OF DIRECTION.jpg

በአንድነት ውስጥ ብቻ የተቀመጠ ታላቅ እምቅ ጉልበት አለ፡፡ አንድነትን መፈለግ ጤነኝነት ነው፡፡ አንድነት ግን በምኞት ብቻ አይመጣም፡፡ አንድ ለመሆን በመፈለጋችን ብቻ አንድነት አይመጣም፡፡

አንድነት በእድል አይመጣም፡፡ አንድነት ከሌለን ስላልሰራንበት ነው እንጂ እድለኛ ስላልሆንን አይደለም፡፡ አንድ ከሆንን አንድ የሆነው የአንድነትን መንገድ ተረድተን በትጋት ስለሰራንበት እንጂ እድለኛ ስለሆንን አይደለም፡፡

አንድነት ቅፅበታዊ አይደለም፡፡ አንድነት ረጅም ቀጣይነት ያለው ትጋትን የሚጠይቅ ግብ እንጂ በቅፅበት የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡

በአንድነት ውስጥ የታመቀ እጅግ ታላቅ ጉልበት አለ፡፡ ያንን ታላቅ ጉልበት መጠቀም የምንችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ ያለውን ጥቅም ለመጠቀም ለአንድነት ትጋትን መማሳየት ይኖርብናል፡፡

አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር? ዘዳግም 32፡30

አንድነት ለሰነፎች እና ለልፍስፍሶች አይደለም፡፡ ማንም መንገደኛ አንድነትን ሊረብሽ ይችላል፡፡ አንድነትን ለመጠበቅ ግን ትጋትና ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በስንፍና አንድነትን ሊያፈርስ ይችላል በአንድነት ውስጥ የተቀመጠውን ጠቅም ለመጠቀም ግን ጥበብና ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው በስንፍና አንድነትን ሊያፈርስ ይችላል ነገር ግን አንድነት በትጋት ይጠበቃል፡፡

አንድነት በልባችን እኛን ለማይመስል ሰው ስፍራን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ ማንም መንገደኛ የሚመስለውንና የሚመቸውን ይሰበስባል፡፡ ማንም መንገደኛ አዎ አዎ የሚለውን ሁሌ ሃሳቡን የሚቀበለውን ይወዳል፡፡ ማንም መንገደኛ ከእርሱ የተለየወን ሰው ይጥላል፡፡ ነግር ግን ለአንድነትና ስለላቀ ውጤት የማይመስሉንን ሰዎች የሚቀበል የልብ ስፋት ይጠይቃል፡፡

ማንም ሰው የእርሱ ሃሳብ ትክክለኛ ይመስለዋል፡፡ አንድነት ከእኛ የተለየ የሚያስቡትን ሰዎች ሃሳብ ማስተናገድ ይጠይቃል፡፡ ሞኝ ትክክለኛ ስለመሰለው ስለራሱ ሃሳብ የሌሎችን ሰዎች ሁሎ ሃሳብ ሊጥል እና አንድነትን ሊረብሽ ይችላል፡፡

አንድነት ተመሳሳይነት አይደለም፡፡ አንድነት የተለያዩ ሰዎች ለአንድ አላማ መስራት ነው፡፡ ሰውን ሁሉ ተመሳሳይ ለማድረግ የሚፈትነውን ማለፍ ካላለፍን ለእንድነት መስራት አንችልም፡፡ የተለያዩ ሰዎችን ማስተናገድ ፈተና ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ቢሆን ይቀላል፡፡ ሰው ለሁሉም ሰው አንድ ህግ አውጥቶ ሁሉም አንድ እያሰቡ ፣ ሁሉም እንድ እየተናገሩና ሁሉም አንድ እንዲኖሩ ይመኛል፡፡ ሰው ሁሉንም ተመሳሳይ ለማድረግ ተስደፋ ካልቆረጠ አንድነት የማይታሰብ ነው፡፡

አንድነት የተለያዩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲሆኑና ነገር ግን ለአንድ አላማ እንዲሰሩ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ ተመሳሳይ ለማድረግ መሞከር ሰዎችን ሁሉ መግደልና በሰዎችን ውስጥ ያለውን የተለያየ እምቅ ጉልበትን ማባከን ነው፡፡

እንዲያውም አንድነት ማለት እያንዳንዱ የራሱን ስራ መስራት ማለት እንጂ አንድ ጣራ ስር መሰብሰብ ፣ አንድ አይነት መልክ መያዝ አንድ አይነት አስተሳሰብ ማሰብና አንድ አይነት ነገር መናገር አይደለም፡፡ አንድነት ማለት በአንድ አለማ ስር በመሆን እያንዳንዱ የተሰጠውን ስራ የራሱን ልዩ ስራ መስራት ማለት ነው፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አላማ #ግብ #ፅናት #ትግስት #ትጋት

አንድም አሳብ ይሁንላችሁ

Unity-1000x550.jpgበክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2:1-2

እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡1-3

የእግዚአብሄር መንግስት ስራ ሁሉም ያለውን ፀጋ የሚያዋጣበት የህብረት ስራ እንጂ የአንድ ሰው ስራ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ስራ የህብረት ስራ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት መፍትሄ ሁሉ በአንድ ሰው ውስጥ ብቻ አልተቀመጠም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ብዙ ብልቶች እንዳሉት አካል ይመሰላል፡፡

አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 12፡12

በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። ሮሜ 12፡4-5

የእግዚአብሄር ስራ የህብረት ስራ በመሆኑ አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ በሰዎች መካከል አንድነት ከፈረሰ ህብረት ይፈርሳል፡፡ አንድነት ከፈረሰ መንግስት አይቆምም፡፡

እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ማቴዎስ 12፡26

በመፅሃፍ ቅዱስ አንድነት እንዲኖረን አንድነታችንን ተግተን እንድንጠብቅ አበክሮ የሚያስጠነቅቀን ለዚህ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር የሚሆንበትን ምክኒያት ከመግለፅ ይልቅ አንድ ነገር የማይሆንበትን ምክኒያት መግለፅ ይቀላል፡፡ አንድነት አሁንም አንድነት የሚጠበቅበትን ሁኔታ ከማስረዳት ይልቅ አንድነት የማይጠበቅበትን ሁኔታ ማስረዳት ስለ አንድነት ያለንን መረዳት ይጨምራል፡፡

አንድነት የማይጠበቅበትን ምክኒያትና አንድነትን መጠበቅ የማይፈልጉ አምስት አይነት ሰዎችን እንመልከት፡፡

  1. ሰዎች ከጋራ አጀንዳ ይልቅ የራሳችው የግል አጀንዳ ሲኖራቸው አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡

ሰዎች ህብረትን የሚፈልጉት የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሆን ህብረትን አይፈልጉም፡፡

ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይሆን ምኞቱን ከተከተለ አንድነትን ሳይሆን መለየትን ይፈልጋል፡፡

መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1

  1. ሰዎች ጨካኞችና የማይራሩ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡

ሰዎች ለእግዚአብሄር መንግስት ስምረት ግድ ሳይኖራቸው ሲቀር ለአንድነት ግድ አይኖራቸውም፡፡ ሰዎች ከእግዚአብሄር ምነገሰት ሸክም ይልቅ የሚያከብሩት ሌላ አለማ ካላቸው ለአንድነት ዋጋ ለመክፈል ዝቅ ማት ያቅታቸዋል፡፡ አንድነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንድነት እኛን የማይመስሉንን ሰዎች መቀበል ይጠይቃል፡፡ አንድነት የተለያየን ሰዎች ለአንድ አላማ መቀራረብን ይጠይቃል፡፡ ለመንግስቱ እውነተኛ ሸክም ያለው ሰው ለአንድነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ይከፍላል፡፡ ለመንግስቱ ሸክም ያለው ሰው ከእርሱ ስሜት ይልቅ የአንድነት የጋራ ጥቅም ይበልጥበታል፡፡

እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። ቆላስይስ 3፡13-14

  1. ሰዎች ሰነፍና ሀሞተ ቢስ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡

አንድነትን መጠበቅ ለሰነፍ ሰው አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አንድነትን መጠበቅ መነጋገር መወያየት በቀጣይነት በትጋት ችግሮችን መፍታት ይጠይቃል፡፡ አንድነትነ መጠበቅ የደካማ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትም መጠበቅ የፈሪዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የደካ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የእምነት ሰዎች ነው፡፡ አንድነትን መጠበቅ የልበ ሰፊ ሰዎች ነው፡፡  አንድነትን መጠበበቅ የደፋር ሰዎች ነው፡፡

በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3

 

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡12-13

  1. ትእቢተኛና ትምክተኛ ሰዎች አንድነትን መጠበቅ አይችሉም፡፡

ሰዎች ከሌላው እበልጣለሁ ሲሉና ሁሉንም የሚያውቁ ሲመስላቸው አንድነትን መጠበቅ ያቅታቸዋል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን አዋርደው ወደ አንድነት ሃሳብ ከመምጣት ይልቅ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሁን ካሉ አንድነት ሊጠበቅ ይችልም፡፡ ሰዎች ለመሸነፍ ሲፈቅዱ አንድነት ይመጣል፡፡ ሰዎች የእኔ ሃሳብም ባይሆን የሚበልጠው ይሁን ካሉ አንድነት ይመጣል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሁሌ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክለ ካሉ ከማንም ጋር መስማማትና መስራት ያቅታቸዋል፡፡

በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡8

እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ 12፡16

  1. ሰዎች ስስታም ሲሆኑ አንድነትን አይፈልጉም፡፡

ሰዎች ስስታም ሲሆኑ ህይወታቸውን ለሌላ ሰው ለማካፈል ሲሰስቱ አንድነትን ይቃወማሉ፡፡ በማካፈልና በመስጠት ብቻ ላይ ነው አንድነት የሚመሰረተው፡፡ ሰዎች ግን መስጠት ሲሰስቱ ለማካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑና መቀበል ብቻ እንደሚገባቸው ሲያስቡ አንድነት አይታሰብም፡፡

ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡10

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

ኢየሱስ በመካከላችን እንዲገኝ የሚያደርገው

Publication15.jpg

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። ማቴዎስ 16፡18-20

የእግዚአብሄርን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን የተቀበሉ ሁሉ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ተወካዮች ናቸው፡፡ ኢየሱስን የተቀበሉ ሁሉ ኢየሱስ በምድር ላይ መስራት የጀመረውን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ሊፈፅሙ በምድር ላይ የተሾሙ የእግዚአብሄር ተወካዮች ናቸው፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

እግዚአብሄር በሰማይ እንዳለ ሁሉ ቅዱሳን በምድር ላይ ላይ ናቸው፡፡ በክርስቶስ ያመኑ የእግዚአብሄር ልጆች በሰማይ ያለው የእግዚአብሄር አምባሳደሮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር የሚያስፈፅሙ የኢየሱስ ተወካዮች ናቸው፡፡

አማኞች ሲሰበሰቡ ለአንድ አላማ መስበሰብ አለባቸው፡፡ አላማ የሌለው መሰባሰብ ከግብ አያደርስም፡፡ ለመሰብሰብ ብቻ የሆነ መሰብሰብ ውጤት አያመጣም፡፡ መሰብሰባችን አንድ የጋራ አላማን ይጠይቃል፡፡

እያንዳንዳችን በየራሳችን የግል አላማ ሳይሆን በአንድ አላማ መሰብሰብ ይኖርብናል፡፡ የመሰብሰባችን አላማ የኢየሱስ ስም መሆን አለበት፡፡ ስንሰበሰብ በኢየሱስ ስም ልንሰበሰብ ይገባል፡፡ የሚያሰባስበን የኢየሱስ ስራ ፣ የኢየሱስ ተልእኮና የኢየሱስ ስም መሆን አለበት፡፡ የምንስበሰበው ኢየሱስ በምድር ላይ መስራት የጀመረውን ለመጨረስ ኢየሱስን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ለመፈፀም ሊሆን ይገባዋል፡፡

ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤ ሐዋርያት 1፡1-2

የምንሰበሰበው ኢየሱስ በምድር ላይ ሰርተን እንድፈፅመው የላከንን ስራ ለመስራት መሆን አለበት፡፡ የምንሰበሰበው ኢየሱስን ወክለን መሆን አለበት፡፡ የምንሰበሰበው አብ ኢየሱስ እንደላከው ኢየሱስ የላከንን ተልእኮ ለመፈፀም መሆን አለበት፡፡

ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

ኢየሱስን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ለመስራት ባለ አንድ አላማ ከተሰበሰበን ኢየሱስ በመካከላችን ይገኛል፡፡ ለእግዚአብሄር መንግስት አላማና ኢየሱስን ወክለን ስንሰበሰብ ኢየሱስ በመካከላችን አንዲገኝ መለመንና መጨቅጨቅም እሰከማያስፈልገን ድረስ እንደቃሉ በቃሉ በመካከላችን ይገኛል፡፡ ኢየሱስ በመካከላችን የሚገኘው በእርሱ ቦታ ሆነንና እርሱን ወክለን የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ለማስከበርና መንግስቱን ለማስፋት የምንለምነውን ሁሉ አብ እንዲያደርገው ነው፡፡ በኢየሱስ ስም ስንሰበሰብ በመካከላችን የሚገኘው ስለ እያንዳንዳችን የግል ጥቅም ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ እግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ነው፡፡

ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። ማቴዎስ 16፡18-20

በኢየሱስ ስም ከተሰበሰብን መገኘቱ ይሰማንም አይሰማንም ኢየሱስ በመካከላችን የምንለምነው ይደርግልናል፡፡

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መሰብሰብ #ጉባኤ #በኢየሱስስም #ተልእኮ #አላማ #የእግዚአብሄርመንግስት ##መንፈስ #መካከል  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #ውክልና #እንደራሴ #አምባሳደር #ፀሎት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በሰላም ማሰሪያ

unityበትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4:2-3
የመንፈስን አንድነት የምንጠብቀው በሰላም ነው፡፡ ካለሰላም የመንፈስ አንድነት ሊጠበቅ አይችልም፡፡ የአንድነት ማሰሪያው ሰላም ነው፡፡ ለአንድነት የሚያስፈልገው ሰላም ነው፡፡
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም ከሆነ አንድነት ይቀለዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄ ጋር ባለው ሰላም ከረካ ከሰው ጋር ሰላም ይሆናል፡፡ ሰው ወደ ሰው የሚሄደው ሰላምን ፈልጎ ሳይሆን ሰላምን ሊሰጥ መሆን አለበት፡፡ ለሰው ሰላምን በመስጠት ላይ ካተኮረ የሚያሰናክለው ነገር አይኖርም አንድነትንም መጠበቅ ይችላል፡፡
ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ማቴዎስ 10፡12-13
ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። ሉቃስ 10፡5-6
ትህትና ሌላው ለአንድነት ወሳኝ የሆነ ነገር ትህትና ነው፡፡ ዝቅ አለማለት ሰላምን የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ አንድነትን የሚፈጥረው ሌላው ከእኛ እንደሚሻል መቁጠር ብቻ ነው፡፡ ሌላውን አለመቀበል የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሁን ማለት የአንድነት ጠር ነው፡፡ ሌላውን አለመቀበልና በመናቅ አንድነትን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ሰው መለየት ከፈለገ ምኞቱን ብቻ መከተል ይበቃዋል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፥1
ትእግስት ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን፡፡ ከእኛ የተለየውን ሰው ካልታገስነው አንድነትን ልንጠብቅ አንችልም፡፡ ልዩነታችንን ካልተቀበለን ሁሉንም ሰው ጨፍልቀን ተመሳሳይ ለማድርግ ከሞከርን ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ከማይመስሉን ሰዎች ጋር አብረን መኖር ፣ መስራትና ማገልገል ካልቻልን ሰላም ሊጠበቅ አይችልም፡፡
ይቅርታ ይቅር መባባል ሰላምን ብሎም አንድነትን ይጠብቃል፡፡ ሰው ይቅር ማለት ካልቻለ አንድነቱም መጠበቅ ያቅተዋል፡፡ ይቅር ማለት አንደነትን የመጠበቂያው መንገድ ነው፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ቆላስይስ 3፡13
የዋህነት ሌላው አንድነትን ለመጠበቅ አስፈላጊው ነገር የዋህነት ነው፡፡ የዋህነት ያለንን ሃይል ለክፋት አለመጠቀም ነው፡፡ የዋህ ሰው ለፍቅር ለሰላምና ለአንድነት የሚሸነፍ ሰው ነው፡፡ ተንኮል በሌለበት ፣ ሁለት ሃሳብ በሌለውና የሚናገረውና የሚያስበው አንድ በሆነ ሰው ሰላም ይጠበቃል፡፡
ፍቅር ፍቅር ደግሞ ወሳኙ የአንድነት ንጥረ ነገር ነው፡፡ ሌላውን ካልተረዳነውና ከሌላው ጋር ራሳችንን ካላስተባበርን አንድነትን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ካለፍቅር አንድነት የለም፡፡ ሌላውን መውደድ ሌላውን መቀበል ሌላውን ማክበር አንድነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ቆላስይስ 3፡14-15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#አንድነት #የዋህነት #ፍቅር #ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #የመንፈስአንድነት #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ብልቶች

publication11በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ሮሜ 12:5-8
የሰው አካል ክፍሎች በአንድነትና በህብረት ተግተው ለአካሉ መልካምነት እንደሚሰሩ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖችም ብዙ አይነት የአገልግሎት ጥሪዎችና ስጦታዎችም ቢኖሩን ሁላችን ለአንድ ግብ እንደምንሰራ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
በአንድ አካል ላይ ያለን የተለያዩ ብልቶች ብንሆንም ሁላችንም ለአንድ አካል የምንሰራ የአካል ክፍሎች ነን፡፡
ለአንድ አላማ ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ስራ መስራት የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት ሰዎች መሆን የለብንም፡፡ ለአንድ መንግስት ለመስራት ሁላችንም አንድ አይነት አገልግሎት ሊኖረን አይገባም፡፡ የእምነት ደረጃችን እኩል መሆን የለበትም ለአንድ መንግስት ለመስራት፡፡ ሁላችንም አንድ አይነት ስራ ከሰራን ውበትም ውጤትምን አይኖረውም፡፡
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡17
ሁላችንም ስራችን የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም ለአንድ ግብ መስራት እንችላለን፡፡
የሁላችንም ስራ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም እጅግ አስፈላጊዎች ነን፡፡ የማያስፈልግ የአካል ብልት የለም፡፡ እንዲያውም ደካማና የማያስፈልጉ የሚመስሉት እነርሱ ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡22
ማንም ከማንም ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ነው እንጂ እንዲፎካከር አልተፈቀደም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲመካ በፍፁም አልተፈቀደም፡፡
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3
የአንድ አካል ብልቶች ሆናልና አንድ አካል ሲከብር ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይከብራሉ አንድ አካል ሲሰቃይ ብልቶች ሁሉ በአንድነት ይሰቃያሉ፡፡
አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡26
እንዲያውም ደካማ ለሚመስለው የአካል ብልት ይበልጥ ክብር ይጨመርለታል፡፡ ፀጋም የሚበዛለት ለደካማው ብልት ነው፡፡
ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡23
እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡27
ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። ኤፌሶን 4፡15-16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
#ኢየሱስ #ጌታ #አካል #ብልት #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ
%d bloggers like this: