ለጭንቀት ጥያቄ አምስቱ የተሳሳቱ መልሶች

Worry-2 (1).jpgሰይጣን ሰውን የሚያጠቃው በጭንቀት ነው፡፡ ሰይጣን ሃሳብን በመላክ ሰውን ያስጨንቃል፡፡ ሰይጣን ወደ ሰው አእምሮ ሃሳብን በመላክ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡

ሰይጣን እንደዚሁ አይነት ንግግር ጀምሮ ነው ሄዋንን የጣላት፡፡ ሰይጣን ሃሳብን ያስገባል፡፡ ሰይጣን ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡

እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ዘፍጥረት 3፡1

ሰይጣን ኢየሱስንም ሊጥለው የነበረው በተመሳይ መንገድ ነበር፡፡ ሰይጣን ጥያቄን ይጠይቃል፡፡ ለጥያቄው መልስ ከሌለን ሰይጣን ያስጨነቀናል፡፡ ለጥያቄው የተሳሳተ መልስ ከሰጠን እንጨነቃለን እንደክማለን ሰላማዊ ህይወታችን መኖር ያቅተናል፡፡

ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። ማቴዎስ 4፡3

አሁንም ሰይጣን የሚዋጋን በዚሁ መልክ ነው፡፡ ሃሳብን ይልካል ፡፡ ሰይጣን ቅን ያልሆኑ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡ መልስ ካላገኘን ያስጨንቀለናል፡፡ ትክክለፃውን መልስ ካልሰጠን ያዋርደነባል፡፡

በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3

ሰይጣን ምንም ይበል ምንም ሰይጣን የተለያየ ርእስ ያምጣ የሰይጣን የጭንቀት ጥያቄ ሲጨመቅ እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡

  1. አንተ አታውቅም

ሰይጣን አንተ አታውቅም የሚል እንደምታ ሊሰጠን ሲሞክር እኔ አውቃልሁ ብለን ከተንፈራገጥን ይጥለናል፡፡ አውቃለሁ ብለን ስላልተገለጠልን ወደፊት ማስረዳት ከሞከርን እንስታለን፡፡ ወይም ያልተገለጠልንን ወደፊት እኛ ራሳችን ፈልገን ለመድረስና ለመረዳትና ለማስረዳት ከሞከርን እንሳሳታለን፡፡ ሰይጣን አታውቅም ሲለን ራሳችንን ትሁት ማድረግ አለብን፡፡ የማናውቀውን አናውቅም ማለት ትህትና ነው፡፡ አዎ ስለ ወደፊቴ ሁሉንም ዝርዝር አላውቅም ማወቅም አያስፈልገኝም መልስ ነው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ የሚመራኝ አባት አለኝ ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ሁሉን የሚያውቀው ይጠነቀቅልኛል ይመራኛል፡፡

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

  1. አንተ አትችልም

ሌላው ሰይጣን የሚልከው የጭንቀት ጥያቄ ሲጨመቅ የምናገኘው ሌላው መልክት አንተ አትችልም የሚል ነው፡፡ እችላለሁ ብለን ከተከራከርነው የማንችልበትን ብዙ ተፈጥሮአዊ ምክኒያቶች ደርድሮ ያዳክመናል፡፡ አትችልም ለሚለው መልሱ አዎ በራሴ አልችልም የሚል ነው፡፡ አዎ በራሴ ጉልበት የለኝም ነገር ግን አንተን በመስቀል ላይ ድል የነሳህ ኢየሱስ ጉልበቴ ነው ማለት ይጠበቅብናል፡፡

ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡13

  1. ለእግዚአብሄር እየኖርክ አይደለም

ሌላው ከተቀበልነው ጭንቀት ውስጥ የሚያስገነባን ሰይጣን የሚልከው ሃሳብ ለጌታ እየኖርክ አይደለም የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ እግዚአብሄር በክርስቶስ ወዶኛል፡፡ ምንም ሳልሆነ ፣ ምንም ሳላደርግለትና ምንም ሳይኖረኝ ጠላት ሳለሁ ወዶኛል፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ደስ ተሰኝቶብኛል፡፡ እግዚአብሄር የማይፈልገው ነገር ካለ ደግሞ ይነግረኛል፡፡ አንተ የምን ቤት ነህ፡፡ አጥፍቼ ከሆነ ከእርሱ ጋር እጨርሳለሁ ፡፡ ይህ የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በቤተሰብ ጉዳይ ጣልቃ አትግባ ማለት ይጠበቅብናል፡፡

  1. ይህ እና ያ የለህም

ሌላው ሰይጣንን የሚልከውን ሃሳብ እህ ብለን ከሰማነው ሊያሳምነን የሚሞከረው የሚያስፈልግህ የለህም የሚል ነው፡፡ ይህ እና ይህ ላይኖረኝ ይችላል፡፡ የሚያስፈክልገኝ ግን አለኝ፡፡ ይህ እና ይህ አሁን ላይኖረኝ ይችላል በሚያስፈልገኝ ሰአት ግን ይኖረኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የሌላኝ ግን የማያስፈልገኝነው፡፡ እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም፡፡ የሌለኝ ነገር ካለ አያስፈልገኝም ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 23፡1

  1. ይህ ጉድለት አለብህ

አዎ ይህ ጉድለት አለብኝ፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሄ ፀጋ የተዘጋጀው፡፡ የማልችለውን ሊያስችል ጉድለቴን ሊሞላ ድካሜን ሊያበረታ ክፍተቴን ሊሸፍን የሚያስችል የእግዚአብሄር ፀጋ ተሰጥቶኛል፡፡

ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡4-6

እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡9

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ማረፍ #ፀጋ #ቅንነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on January 29, 2018, in Trust, worry. Bookmark the permalink. Comments Off on ለጭንቀት ጥያቄ አምስቱ የተሳሳቱ መልሶች.

Comments are closed.

%d bloggers like this: