“መልካም” ወይስ የእግዚአብሄር ሃሳብ

good or god.jpgከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። ዘፍጥረት 3፡5-6

የክርስትና ህይወት የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ በክርስትና ያሉት ምርጫዎች ደግሞ መልካሙን እና ክፉውን የመምረጥ ምርጫዎች አይደሉም፡፡ ብዙ መልካም የሆኑ የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን ያልሆኑ ነገሮች በህይወታችን ይመጣሉ፡፡

ሰይጣን አታላይ ነው፡፡ ሰይጣን ወደሄዋን የመጣው እኔ ሰይጣን ነኝ ብሎ አይደለም፡፡ ሰይጣን ወደ ሄዋን የመጣው መልካም በሚመስል ነገር ነው፡፡ ሰይጣን ለሄዋን ያሳያት መልካም አሳቢ በመምሰል ነው፡፡

ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ዘፍጥረት 3፡6

እግዚአብሄር መልካም ካላለው ምንም መልካም ነገር የለም፡፡ አብላጫው ድምፅ መልካም ቢለውም እግዚአብሄር መልካም ካላለው መልካም አይደለም፡፡ ያማረ ቢሆንም እግዚአብሄር መልካም ካላለው ህይወት የለበትም፡፡ ለአይን ቢያስጎመጅም እግዚአብሄር የእግዚአብሄር ፈቃድ ከሌለበት አሳሳች ነው፡፡ ለጥበብም መልካም እንደሆነ ብናይም እግዚአብሄር መልካም ካላለው መልካም አይደለም፡፡

እግዚአብሄር በነቢዩ በራሳቸው ማስተዋል ብቻ በጭፍንነት ስለሚመሩ ሰዎች ያስጠነቅቃል እንዲህ ሲል፡-

ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! በዓይናቸው ጥበበኞች በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው! ኢሳይያስ 5፡20-21

አለም በክፉ ተይዟል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከህዝብ አብላጫ ድምፅ አናገኘውም፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚገኘው መልካም በሚመስል ነገር ውስጥ ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግለን ለማለፍ ሰዎች መልካም የሚሉትንና እኛ መልካም የመሰለንን መከተል ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከእግዚአብሄር ቃልና ከመንፈሱ ማግኘትና መከተል ይኖርብናል፡፡

የእግዚአብሄርን ቃል እንደ መናገር የከበረ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በህይወታችን ውስን ስለሆንን መንፈስ ቅዱስ በእስያ እና በሚስያም እንዳንናገር ይልቁንም በመቄዶንያ እንድንናገር የሚፈልግበት ጊዜ አለ፡፡ እዚህ ቃሉን መናገር መልካም ነው ግን የእግዚአብሄር ሃሳብ አይደለም፡፡

በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ ሐዋርያት 16፡6-7

ኢየሰስ ለአይሁድ ተላልፎ እንደሚሰጥ ለደቀመዛሙርቱ ሲነግራቸው ጴጥሮስ መልካም ሃሳብ አምጥቶ አየሱስን ከመሞት ሊከለክለው  ሞከረ፡፡ የኢየሱስ መሞት በሰው እይታ መልካም አይደለም ግን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፡፡ ሰይጣን የሰውን መልካም ሃሳብ ተጠቅሞ ኢየሱስን ከመሞት ሊያስቆመው ነበር፡፡

ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። ማቴዎስ 16፡22-23

ስለዚህ ነው በራስህ ማስተዋል ጠቢብ አትሁን የሚለው፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ ምሳሌ 3፡5-7

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #መልካም #መታመን #መደገፍ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት  #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on May 16, 2017, in mind, word. Bookmark the permalink. Comments Off on “መልካም” ወይስ የእግዚአብሄር ሃሳብ.

Comments are closed.

%d bloggers like this: