ኢየሱስን ተመልክተን

focus.jpgእንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2

ሰው ሊሰራ የሚችለው ነገር ከእግዚአብሄር እንደተሰጠው ስጦታ መጠን ብቻ ነው፡፡ ከጥሪያችን አልፎ ለብክነት የሚተርፍ ነገር አልተሰጠንም፡፡ ስለዚህ ነው በክርስትና ህይወት ትኩረት ወሳኝ ነገር የሆነው፡፡ ሰው ውስን ስለሆነ ትኩረት ሊያደርግ በትክክል ሊሰራ የሚችለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ሰው ከአንድ ነገር በላይ ላይ ትኩረት ለማድረግ ከሞከረ በአንዱም ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ ስለሚያቅተው በምንም ነገር ላይ ውጤታማ ሳይሆ ይቀራል፡፡

ትኩረታችንን የሚፈልጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ነገሮች ወደእኔ ተመልከት እኔን ካላገኘኸኝ ወዮልህ በማለት ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ፡፡ ትኩረታችንን ከምንም ነገር ላይ አንስተን እነርሱ ላይ እንድናደርግ የሚገፋፉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ማቴዎስ 14፡29-30

ጴጥሮስ ኢየሱስ በውሃ ላይ ሲራመድ አይቶ ልምጣ ብሎ ጠየቀ፡፡ ኢየሱስም ና ባለው ጊዜ ጴጥሮስ ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውሃ ላይ ሄደ፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ አይኑን ከኢየሱስ ላይ አንስቶ ውሃው ወጀቡ ላይ ባደረገ ጊዜ መስመጥ ጀመረ፡፡

ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ አበክሮ ኢየሱስ ላይ ማተኮር እንዳለብን የሚናገረው፡፡ ከኢየሱስ ውጭ ያሉ ነገሮች ሁሉ አስተማማኝ አይደሉም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የሚታየው ሁሉ ሃላፊ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሁሉም ነገር እያለፈ ያለ ነው፡፡ ለዘላለም የሚኖረው ኢየሱስ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ሁሉም ነገር አላፊ ነው፡፡

የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18

ኢየሱስን ስናይ እንበረታለን፡፡ አካባቢያችንን ካየን የሚያደክሙ ብዙ ነገሮች በዙሪያችን አሉ፡፡ አለም በሃጢያት የተበላሸ እንደመሆኑ መጠን ከአለም ፍፁምነት መጠበቅ አንችልም፡፡  ከእግዚአብሄር ውጭ ራሳችንን ስናይ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ኢየሱስን ስናይ ተስፋችን ይታደሳል ሃይልም ይሆንልናል፡፡ ኢየሰሱስን ስናይ ተስፋ በሌለው ነገር ላይ ተስፋችን ይለመልማል፡፡

የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡30-31

አካባቢያችን ላይ ካተኮርን ብዙ የሚያስፈራራ ነገር አለ፡፡ ኢየሱስን ስናይ ግን ኢየሱስ አለምን ስላሸነፈ እንፅናናለን፡፡ በኑሮ ላይ ካተኮርን በቁማችን ሊውጠን ዝግጁ ነው፡፡ ኢየሱስን ካየን ግን በቃኝ ብለን እግዚአብሄርን አገልግለን እናልፋለን፡፡

በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8:14

በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ። ዮሃንስ 16፡33

አካባቢያችንን ስናይ እናዝናለን፡፡ ሁኔታዎችን ስናይ ምቾት አይሰማንም፡፡ ኢየሱስን ስናይ የስጋችንን ድካም ረስተን በእርሱ እንበረታለን፡፡ ኢየሱስን ስናይ በአካባቢያችን ጨለማ ላይ ብርሃን ይበራበታል፡፡ ተስፋችን ይታደሳል፡፡

ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ቆላስይስ 1፡27

ኢየሱስን ስናይ ከወደቅንበት እንነሳለን፡፡ ኢየሱስን ስናይ የአለምን መከራና ነውር እንንቃለን፡፡ ኢየሱስን ላይ ስናተኩር የጊዜውን መከራ ሳይሆን የዘላለምን ክብር ላይ እናተኩራለን፡፡ ኢየሱስን ስናይ በህይወት ውጤታማ እንደምንሆን እናምናለን፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5

በምድር ላይ ትርጉም ያለው ነገር ካደረግን የምናደርገው በራሳችን ሳይሆን በኢየሱስ ነው፡፡

እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሃንስ 15፡5

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ ዕብራውያን 12፡2

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ተመልክተን #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on May 3, 2017, in Jesus, word. Bookmark the permalink. Comments Off on ኢየሱስን ተመልክተን.

Comments are closed.

%d bloggers like this: