እግዚአብሄርን የሚያስደስቱ ሰባት አይነት ሰዎች

fear vs faith.jpgእግዚአብሄር በተፈጥሮአዊ አይን አይታይም፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ በተፈጥሮ ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት እንችልም፡፡  ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ማንኛውም ግንኙነት መደረግ የሚቻለው በእምነት ነው፡፡ ካለ እምነት ከእግዚአብሄር ጋር ልንገናኝ የእግዚአብሄርን ነገር ማድረግ እንችልም፡፡ ካለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ (ዕብራዊያን 11፡6)

በእምነት በመኖር እግዚአብሄርን ማስደሰታችንን ማወቅ ይገባናል፡፡ በእምነት መኖራችንን የሚመሰክሩ ነገሮች፡፡

  1. የልቡን ሰላም የሚከተል

የልብ ሰላም ያለው ሰው በእምምነት እየኖረ መሆኑ ማረጋገጫው ነው፡፡ በእምነት የሚኖር ሰው አካባቢው ሊታወክ ይችላል፡፡ የአእምሮም ሰላም በእምነት እንደምንኖር ላይመሰክር ይችላል፡፡ ምክኒያቱም አእምሮ ብዙ አይነት ሃሳቦች የሚስተናገዱበት ስለሆነ በአእምሮዋችንን ጥርጥር ሊመጣ ይችላል፡፡ በአእምሮዋችን፻ጥርጥር መጣ ማለት እምነት የለንም ማለት አይደለም፡፡ በአካባቢያችን ያለውን ሁኔታን ወይም በአእምሮዋችን ያለውን የተለያየ ሃሳብ ሳይሆን የልባችንን ፀጥታና ዝምታ ከተከተልን በእግዚአብሄር እንደተደገፍን እናውቃለን፡፡

በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15

  1. በእግዚአብሄር የሚደሰት

እግዚአብሄር ደስ የሚልህ ከሆነ በእምነት እየኖርክ ነው፡፡ ይህን ካላገኘህ በደስታ አተኖርም፡፡ ደስታ ያለው በእኔ ውስጥ ነው፡፡ እኔን ካላገኘህ አለቀልህ ማለት ነው የሚሉ ብዙ ነገሮች ባሉበት አለም ውስጥ በእግዚአብሄርና በቃሉ ብቻ ደስ ካለህ በእምነት እየኖርክ መሆኑን ማረጋገጫው ነው፡፡

ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ጌታ ቅርብ ነው። ፊልጵስዩስ 4፡4

  1. የማይናወጥና የማይቸኩል

እግዚአብሄር አለምን እንደሚያስተዳድራትና እግዚአብሄር ለአንተ የሚያስባትን ሃሳብ የሚያውቅና በትጋትንም እየሰራበት መሆኑን ካወቅክ አትቸኩልም፡፡ እግዚአብሄርን የሚቀድመው ሰው እንደሌለ አንተን የሚቀድምህ ሰው እንደማይኖር ካለፍርሃት በመረጋጋት ከኖርክ ታምነሃል፡፡

የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15

ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። ዮሐንስ 14፡1

  1. የእንግድነት ስሜት የሚሰማው

በእንግድነት በምድር ላይ እንደምትኖር የሚሰማህ ከሆነ በእመነት እየኖርክ ነው፡፡ የሚታየው ሁሉ ሃላፊ እንደሆነ ካወቅክ በእመነት እየኖርክ ነው፡፡ ምድርን ጊዜያዊ የእንግድነትና የስደት ቤትህ እድርገህ ካየሃት በእምነት እየኖርክ ነው፡፡ እንደእንግዳ ሰው ነፍስን ከሚያረክስ ነገር ራስህን ከጠበቅክ በእምነት እየኖርክ ነው፡፡

እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡6-8

  1. የአለምን ውድድር ውስጥ የማይገባ

በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁንም የመፈለግ አላማ ስለሌላቸው ትልቁ አላማቸው በልብስና በመኪና ብራንድ መወዳደርና ማሸነፍ ነው፡፡ በምድር ላይ ካለው የአለም ፉክክር በፈቃዳችን ራሳችንን ካገለልን ፅድቁንና መንግስቱን በመፈለግ እንኖራለን በዚያም በእምነታችን እግዚአብሄርን ደስ እናሰኛለን፡፡ ሰው እግዚአብሄንና መንግስቱን ሲያይ የዚህን አለም ውድድር ይንቃል፡፡ ሃዋሪያው አለም ለእኔ ሙት ነች አትስበኝም ይላል፡፡

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20

  1. የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅ የሚፈልግ

ስለኑሮው የማይጨነቅ ይልቁንም የእግዚአብሄን ፅድቅና መንግስት ለመፈለግ የሚያስብ ሰው በእምነት የሚኖር ሰው ነው፡፡ የእኔን የህይወት ፍላጎት እግዚአብሄር ነው የሚያሟላው የእኔ ሃላፊነት የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ነው ብሎ የሚያምን ሰው በእምነት የሚኖር ሰው ነው፡፡

እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33

  1. ባለው ነገር እግዚአብሄርን የሚያመሰግን

ባለው ነገርና በደረሰበት ደረጃ ረክቶ የሚያመሰግን ሰው እግዚአብሄርን በእምነት ያስደስተዋል፡፡ ስላለው ነገር የሚያመሰግንና ለዚህ መልካም ጌታ ምን ላድርግለት ምኔን ልስጠው ብሎ በእግዚአብሄር ስራ ላይ የተጠመደ ሰው የእምነት ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም (መዝሙር 23፡1) የሚለው ቃል ከእምነት ሰው የሚወጣ ነው፡፡

በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on April 10, 2017, in Faith. Bookmark the permalink. Comments Off on እግዚአብሄርን የሚያስደስቱ ሰባት አይነት ሰዎች.

Comments are closed.

%d bloggers like this: