የወዳጅነት ጥበብ

girl-948251_960_720በሰው ህይወት ውስጥ በጣም ከፍተኛ ስፍራ ካላቸው ነገሮች አንዱ ወዳጅነት ነው፡፡

ወዳጅነት የሌላውን ስሜት መረዳት ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት የሌላን ድንበር ማክበር ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ ሌላውን ማገልገልን ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ የአንዱን ሸክምን መሸከምን ይጠይቃል፡፡

ሰው የራሱ የግሌ የሚለው ክልል አለው፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚያስቀረው ሚስጥር ሊኖረው ይችላል፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚፈቅደው ግላዊነት ይኖረዋል፡፡ ያንን የግል ክልል ማክበር ወዳጅነትን ያጠናክራል፡፡

ወዳጅነት አንዱ ለሌላው መድረስን ያካትታል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ እንደሚወድ ያስተምረናል፡፡

ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል ምሳሌ 17፡17

ወዳጅነት ሃላፊነት ነው ፡፡ ወዳጅነት ማካፈል ነው፡፡ ወዳጅነት ለሌላው መገኘት ነው፡፡ ወዳጅነት መስጠት ነው፡፡ ሰው ለሁሉም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ለሁሉም ሊሰጥ የሚፈልግ ሰው ለማንም ሳይሰጥ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ መርጠን በመልካም በወዳጅነት ላይ ኢንቨስት እንድናደርግ የሚያስተምረን፡፡

ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ። ምሳሌ 18፥24

ወዳጅነት በአንድ ዘመን ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ወዳጅነት ለትውልድ ይተላለፋል፡፡ አንዳንዴ ከዘመድ ይልቅ ወዳጅ ቀድሞ ይደርሳል ይጠቅማልም፡፡

ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። ምሳሌ 27፥10

ወዳጅነት በመተማመን ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡ ስለዚህ ነው ወዳጅነት በአንድ ለሊት የማይገነባው፡፡ አንዱ ለሌላው ያለውን መሰጠት በማየት ነው አንዱ ለሌላው ራሱን የሚሰጠው፡፡ ወዳጁ ያለውን ታማኝነት በማየት ነው በታማኝነት ራሱን ለወዳጅነቱ ቀስ በቀስ የሚሰጠው፡፡ ወዳጅነትን ሊያፈርስ የሚመጣውን ነገር በጥንቃቄ መከታተል ይጠይቃል፡፡

ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል። ምሳሌ 16፥28

ወዳጅ በመልካም መንገድ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ትጉህ ወዳጅ ወዳጁን ትጉህ ያደርገዋል፡፡ አስተዋይ ወዳጅ ወዳጁን ማስተዋል እንዲጨምር ይረዳዋል፡፡ እንደ ወዳጅ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ለማድርግ ሰፊ እድል ያለው የለም፡፡

ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ምሳሌ 13፡20

ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። ምሳሌ 27፡17

ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። ምሳሌ 12፡26

ወዳጅ ያሳርፋል፡፡ ወዳጅ ያስደስታል፡፡

ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል። ምሳሌ 27፡9

በተቃራኒው ደግሞ ከክፉ ባልንጀርነት መሸሽ ህይወትን ይጠብቃል፡፡ በባልንጀርነት አመል እንዳይበላሽ መጠንቀቀ ያስፈልጋል፡፡

ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋር አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። ምሳሌ 22፡24-25

አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡33

ወዳጅነት ምህረት ይቅር ማለት መሸከም ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው የማንወድለት ይህን ቢያስተካክል የምንለው ነገር አለው፡፡ ሁሉም ነገሩ የሚያስደስተን ሰው በምድር ላይ የለም፡፡ ስለዚህ ሌላውን መሸከም የሰውን መልካምነት እንድንጠቀም ያስችለናል፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ግን መለየት ነው የሚፈልገው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ወረተኛ ነው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው በወዳጅነት አይፀናም፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ከወዳጅነት በላይ ሌሎች ጥቅሞችን በማስቀደም ታላቁን ስጦታ ወዳጅነትን ይጥላል፡፡

መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1

ወዳጅነትን የሚያከብር ሰው በምህረት ይመላለሳል፡፡ ለወዳጅነት ዋጋ የሚሰጥ ሰው ወዳጅነትን የሚያጠፋውን ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል ዋጋም ይከፍላል፡፡

ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል። ምሳሌ 17፡9

ወዳጅነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወዳጅ ወዳጁን እጅግ በጣም ከማመኑ የተነሳ ከጠላት መሳም ይልቅ የወዳጅ ማቁሰል እንኳን ተቀባይነት አለው፡፡

የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው። ምሳሌ 27፡5-6

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ወዳጅ #ጓደኛ #መታመን #ጥበብ #ፍቅር #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on December 30, 2016, in Wisdom. Bookmark the permalink. Comments Off on የወዳጅነት ጥበብ.

Comments are closed.

%d bloggers like this: