ፍቅር እና “ፍቅር”

love-1እንደ ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር የለም፡፡ እንደ ፍቅር ደግሞ ትርጉሙ የተዛባ ነገር በአለም ላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ፍቅር የሚሉት ምኞታቸውን ነው፡፡ የፍቅርንና የምኞትን ባህሪያት ከእግዚአብሄር ቃል በመመልከት ልዩነታቸውን እስኪ እንመልከት፡፡
ፍቅር የሚያተኩረው ሌላው ላይ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን በመጥቀም ሌላውን በማንሳት ሌላውን በማገልገልና በሌላው ላይ ዋጋን በመጨመር ላይ ያተኩራል፡፡
ምኞት የሚያተኩረው ራስ ላይ ነው፡፡ ምኞት በማንኛውም ግንኙነት የሚያስበው እርሱ ምን እንደሚያገኝና እንደሚያተርፍ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሄድ ምኞት ግን የራሱ ፍላጎት ብቻ ለማሟላት ይሄዳል፡፡
ፍቅር ሌላውን ሲያስቀድም ምኞት ራሱን ያስቀድማል፡፡ ፍቅር የራሱን ፍላጎት ስለሌላው ፍላጎት ያዘገየዋል፡፡ ምኞት ግን ስለሌላው ፍላጎት የሚያዘገየው ምንም ጥቅም የለም፡፡
ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7
ፍቅር በመረዳት የሚደረግ ሲሆን ምኞት በስሜት የሚመራ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን እንዳይወድ የሚፈትኑትን አሉታዊ ስሜቶች ሰምቶ ፍቅርን ከመከተል አይመለስም፡፡ ምኞት ግን ስሜቱን ብቻ ይከተላል፡፡
ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፊልጵስዩስ 1፡9
ፍቅር እኔ እበልጣለሁ ፣ እኔ ይገባኛል ፣ እኔ የእኔ ለእኔ ነው ሁልጊዜ የሚለው፡፡ ፍቅር ግን አንተ ይገባሃል ፣ አንተ ትሻላለህ ፣ አንተ ትበልጣለህ ብሎ ሌላውን በትህትና ይቆጥራል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
ፍቅር ምክኒያታዊ ያልሆነ ሲሆን ምኞት ምክኒያታዊ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር እንካ በእንካ አይደለም፡፡ ፍቅር የሌላውን ሁኔታ ሳያይ የራሱን ሌላውን የማክበር ሃላፊነት ይወጣል፡፡ ምኞት ቀድሞ እንኳን መልካም ካደረገ ያደረገው የተሻለ ጥቅምን ፈልጎ ብቻ ነው፡፡ ወይም መልካም ላደረጉለት ብቻ ነው መልካም የሚያደርገው፡፡ ምኞት ምንም ጥቅም ያላገኘበት ወይም ወደፊት የማያገኝበት ከሆነ ዞር ብሎ አያየውም፡፡
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴዎስ 5፡46-47
ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ማቴዎስ 5፡38-39
ፍቅር የህይወት ዘመን ሃላፊነት ሲሆን ምኞት የአንድ ሰሞን ጊዜያዊ ነው፡፡ ፍቅር የእውነተኛ ሰው ህይወቱ ነው፡፡ ሰው ፍቅርን የሚከታተለው በውሳኔ ስለሆነ ሰው ከፍቅር መቼም አይለወጥም፡፡ ምኞት ግን ከሌላው በሚገኘው ጥቅም ላይ ስለተመሰረተ ጥቅሙ በቆመ ጊዜ ለመቀጠል አቅም አይኖረውም፡፡
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13
ፍቅር ሌላውን ለማገልገል በሌላው ላይ የማይደገፍ ሲሆን ምኞት የራሱን ስለሚፈልግ በሌላው ላይ ያለመጠን የሚደገፍ ነው፡፡ ፍቅር ለሰው መልካም ለማሰብ መልካም ለመናገርና መልካም ለማድረግ የማንም ፈቃድ አያስፈልገውም፡፡ ምኞት ግን ሌላውን ለማስወጣት በሌላው ላይ ከመጠን ያለፈ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ምኞት ሁልጊዜ ያዝናል ተስፋ ይቆርጣል፡፡
ፍቅር ሌላውን በማርካት ብቻ ይረካል ምኞት ራሱን በማርካት ብቻ ይረካል፡፡ ፍቅር የምሰጠው አለኝ ባለጠጋ ነኝ ስለሚል ለሌላው በመስጠት ይረካል፡፡ ምኞት ግን ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ስላለው እኔ ምንም የለኝም ፣ የምሰጠው የለኝም ፣ ደሃ ነኝ የሚሰጠኝ እፈልጋለሁ ስለሚል የሚረካው በመቀበል ብቻ ነው ፡፡
ፍቅር ሌላውን ለመንከባከብ እንዲያስችለው ሌላውን ለመረዳት ይጥራል፡፡ ፍቅር ትጉህ ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን በተሻለ ለመንከባከብ እንዲያስችለው የሌላውን ፍላጎትና ባህሪ በትጋት ያጠናል፡፡ ምኞት ለሌላው ግድ ስለሌለው ሌላውን ለማጥናት ስንፍና ስለአለበት የራሱን ስሜት ብቻ ያዳምጣል፡፡ ፍቅር በስንፍና እይመጣም ፍቅር ጥረትና ድካም ይጠይቃል፡፡
በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥2-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #ምኞት #አላማ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on December 1, 2016, in Love. Bookmark the permalink. Comments Off on ፍቅር እና “ፍቅር”.

Comments are closed.

%d bloggers like this: