ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው

44265123-beautiful-wallpapers.jpgነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡11 ፣ 1
ምንም ነገር ውብ የመሆን እምቅ ጉልበት ቢኖረውም በእርግጥ ውብ የሚሆነው በራሱ ጊዜ ነው፡፡
የህይወታችን እቅድ ሁሉ ቀድሞውንም በእግዚአብሄር ዘንድ አለ፡፡ እግዚአብሄር የህይወት ንድፋችንን የሚሰራው በየጊዜው የምንፀልየውን የፀሎት ርእስ ሰብስቦ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን የሚሰራበትን ሃሳብ በየጊዜው አንሰጠውም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ለእግዚአብሄር በትልቁ አናልምለትም፡፡ ወይም በጥሩ ሃሳብ እግዚአብሄርን አናስደንቀውም፡፡
የእያንዳንዳችን የህይወት እቅድ በእግዚአብሄር ዘንድ ቀድሞውንም አለ፡፡ ወደዚህ ምድር የተወለድነው በምድር ላይ ልንሰራ ያለው የተለየ ነገር ስላለ ነው፡፡
ስለተወለድንበት የህይወት እቅድና ዲዛይን መሰረት እግዚአብሄር በህይወታችን እየሰራ ነው፡፡ እኛ ማድረግ የምችለው የተሻለ ነገር እግዚአብሄር በህይወታችን በጊዜው የሚሰራውን ተከትለን አብረነው መስራት ነው፡፡ ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሐንስ 5፡17
እግዚአብሄር የሚሰራውን ስራ ሁሉ የሚሰራው በጊዜውና በዘመኑ ነው ፡፡ እግዚአብሄር አይቸኩልም፡፡ እግዚአብሄር በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለመስራት አይሞክርም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን አንድን ነገር የሚሰራበት የራሱ ዘመንና ጊዜ አለው፡፡ በሰማይ እኛ እንዳለን አይነት ዘመንና ጊዜ የለም፡፡ ሰማይ በእኛ አይነት ዘመንና ጊዜ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከሰማይ በታች ያለው ነገር ሁሉ ግን በጊዜና በዘመን ውስጥ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
· ትላንት
ትላንት አልፎዋል ያንተም አይደለም፡፡ ባለፈው ስኬትህም ሆነ ውድቀትህ በፍፁም አትያዝ፡፡ ጆይስ ሜይር ስታስተምር በትላልቱ ላይ በጣም የሚቆይና በጣም የሚያሰላስለው ሰው ከነገ ይበልጥ ትላንት ይሻላል እያለ ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ በትላንትህ ላይ በጣም የምታተኩር ከሆንክ ሳታውቀው ትላንት እንደገና ትኖረዋለህ፡፡ ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። መክብብ 7፡10
ትላንትን ግን መኖር የለብህም፡፡ እግዚአብሄር ላንተ ዛሬ አዲስ ነገር አለው፡፡ ከዛሬ ይልቅ ትላንት በፍፁም አይሻልም፡፡
ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ሰቆቃው ኤርምያስ 3፡22-23
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ ፊልጵስዩስ 3፡13
· ዛሬ
ያለህ እድል ዛሬ ነው፡፡ ለመስራት ለመሮጥ ለመድከም ለመትጋት ያለህ እድል ዛሬ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ መስራት ያለብህን ነገር ለነገ አታስተላልፍ፡፡
አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። መክብብ 9፡10 ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። መዝሙር 27፡1
ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። ዮሃንስ 9፡4
ደስታህንም ለነገ አታስተላልፍ፡፡ ደስተኛ ለመሆን በፍፁም ነገን አትጠብቅ፡፡ ደስተኛ ለመሆን በህይወትህ የሆነ ነገር እስኪሆን አትጠብቅ፡፡ ነገ እንዲሆኑልህ የምትፈልጋቸ ነገሮች በጊዜው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዛሬን ግን ባለህበት ደረጃ አክብረህ ተደስተህበት ካላከለፍክ ተመለሰህ አታገኘውም፡፡ ጊዜ ወደኋላ ተመልሶ አይጠነጠንም፡፡
ህይወት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ዛሬ እንድንደሰትበት የተሰጠን ስጦታም ነው፡፡ በህይወት ተደሰትበት፡፡ ስለነገ ተስፋ ብለህ ዛሬን አታጣጣል፡፡ ዛሬ ባለበት ደረጃና ሁኔታ ልንደሰትበት የሚገባ እግዚአብሄር ክቡር ስጦታ ነው፡፡
ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መክብብ 3፡12-13
· ነገ
ነገ የራሱ ጊዜና ዘመን አለው፡፡ የነገን ስራና ሃላፊነት ደግሞ ዛሬ ለመስራት አትሞክር፡፡ የዛሬን ስራ ሰርተህ ዘና በል፡፡
የነገን ስራ በዛሬ ጉልበት ልንሰራው ስንሞክር ስለማንችለው ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ዛሬ እንደተራራ የሆነብህን በነገ ጉልበት ግን ትገፋዋለህ፡፡ ጊዜ አለህ እስከ ነገ ታገስ፡፡ ዛሬ የማይለቀቅ ሲነጋ ብቻ የሚለቀቅ እምነትና ፀጋ አለ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆነህ ስለነገ አትፍራ፡፡ ዛሬን ብቻ በትክክል መኖርህን እርግጠኛ ሁን፡፡ ለነገ አትጨነቅ፡፡ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ ወንጌል 6፡34
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡11 ፣ 1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ
Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on November 15, 2016, in godliness. Bookmark the permalink. Comments Off on ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው.

Comments are closed.

%d bloggers like this: