ትንቢትና ነቢያት

TB-Joshua.jpgበክርስትና ለቤተክርስቶን ከተሰጡ አገልግሎቶች መካከል ትንቢት አንዱ ነው፡፡ ትንቢት የሚመጣው ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ነው፡፡
ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡3
መፅሃፍ ትንቢትን እንዳንንቅ ያስተምረናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሀሰት ትንቢቶችን ስንሰማ በአጠቃላይ ትንቢትን ለመናቅ እንፈተናለን፡፡
ነገር ግን ትንቢትን መናቅ እግዚአብሄር በትንቢት ውስጥ ካስቀመጠው በረከት ጋር እንድንተላለፍ ያደርጋል፡፡ ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 14፡29
ያ ማለት ደግሞ ትንቢትን ሁሉ እንዳለ እንቀበላለን ማለት አይደለም፡፡ ትንቢት መመርመር አለበት፡፡ ትንቢት እንደ እግዚአብሄር ቃል ካልሆነ ትንቢቱን ለመጣል መፍራት የለብንም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እንጂ ትንቢት የመጨረሻ ስልጣን የለውም፡፡ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡20-21
ትንቢትም የተናገረ ሁሉ ደግሞ ነቢይ አይደለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ስንሰበሰብ በጉባኤ መንፈስ እንደወደደ ትንቢትን በልሳን መናገርን መግለጥን የመሳሰሉትን ስጦታ እንደሚሰጥ ይናገራል፡፡ ይህ የፀጋ ስጦታ ነው፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡8-11
የፀጋ ስጦታ መንፈስ እንደወደደ ጉባኤውን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም የሚሰጠው ስጦታ ነው፡፡ ነቢያት ግን እንደ ሃዋሪያትና አስተማሪዎች ለቤተክርስቲያን የተሰጡ አገልጋዮች ናቸው፡፡
የአዲስ ኪዳን ነቢይነት ከብሉይ ኪዳን ነቢይነት በእጅጉ ይለያል፡፡ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሄር መንፈስ የሚመጣው በጥቂት ሰዎች ላይ ነበር፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የእግዚአብሄር መንፈስ በነገስታት በነቢያትና በካህናት ላይ ይመጣ ነበር፡፡
ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። 1ኛ ሳሙኤል 16፡13
ስለዚህ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች የእግዚአብሄር መንፈስ በውስጣቸው ስለማይኖር የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ሲፈልጉ ወደ እነዚህ ነቢያት ይመጡ ነበር፡፡
በአዲስ ኪዳንም ግን ጌታ ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን ነቢያት ነገስታትና ካህናት ተደርገናል፡፡ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር መንፈስ በኢየሱስ ተከታዮች ውስጥ ሁሉ ይኖራል፡፡
ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። ሮሜ 5፡16
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9
በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራቸው በአማኞች ውስጥ ይኖራል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ በውስጣቸው ያለውን መንፈስ ይጠይቃሉ፡፡
ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። ዮሃንስ 16፡13
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
ክርስቲያን ወደእውነት ሁሉ የሚመራው የእግዚአብሄር መንፈስ በልቡ ተሰጥቶታል፡፡ በአዲስ ኪዳን ትንቢት የእግዚአብሄር መንፈስ ያለበትን ክርስቲያንን እንደአዲስ ሊመራ አይመጣም፡፡ ነገር ግን ትንቢት ቀድሞ እግዚአብሄር የተናገረንን ነገር ለማረጋገጥ እንደ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይመጣል፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡16 በአዲስ ኪዳን የሚመጣን ትንቢት ክርስቲያን በውስጡ ካለው የመንፈስ ምስክርነትን ሳይሰማ መቀበል የለበትም፡፡ ትንቢት ስህተት ሊሆን ስለሚችል መመርመር አለበት፡፡ እራሳቸው በልባቸው ከእግዚአብሄር ሳይሰሙ በትንቢት ተመርተው ህይወታቸው የተበላሸ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡
ስለመጣልህ ትንቢት እግዚአብሔር በልብህ ካልተናገረህ አትቀበል፡፡ ቀድሞ እግዚአብሄር የተናገረህን ካፀናልህ መልካም ነው፡፡ ትንቢት የሚናገር ሰው ሊሳሳት ይችላል፡፡ ሲሳሳት ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ በአንድ ትንቢት ተሳሳተ ማለት ግን ከዚሀ በፊት የሰራቸውን የእግዚአብሄር ስራ ሁሉ ከንቱ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on November 12, 2016, in Prophecy. Bookmark the permalink. Comments Off on ትንቢትና ነቢያት.

Comments are closed.

%d bloggers like this: