እውነተኛ ትህትና

7a9915bb2774378c0c0035704e52fd73ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖርና አሸናፊ ለመሆን ትህትና እጅግ አስፈላጊ ባህሪ ነው፡፡ ካለ ትህትና ከእግዚአብሄ ጋር እጣላለን ፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ወገን አይሆንም ፡፡ እንዲያውም እግዚአብሄር ትዕቢተኛውን ይቃወማል፡፡
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ። ያዕቆብ 4፡6
ትህትና ይህን ያህል አስፈላጊ ከሆነ ትህትና ግን ምንድነው ብለን መጠየቅ ጥበብ ነው፡፡ ትህትናን በደንብ ልንማረውና ልናጠናው ተግተንም ልንለማመደው የሚገባ የተወደደ ባህሪ ነው፡፡ ሰዎች ትህትና ብለው የሚያደርጉዋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እውነተኛ ትህትና ግን ምንድነው፡፡
  • · ትህትና ለሁሉም ሰው ያለ አክብሮት ነው፡፡ ትሁት ሰው ለወገኔ ይጠቅማል በማለት አንዱን ከሌላው ሰው በወገናዊነት አያበላልጥም፡፡ ትሁት ሰው ለሁሉም ከፍ ያለ አክብሮት ያለው ሰው ሲሆን ሁሉንም ለማገልገልና ለመጥቀም የተዘጋጀ ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ፊልጵስዩስ 2፡3
  • · ትሁት ሰው ሌላው ሰው ከእርሱ እንደሚሻል በቅንነትና በእውነት የሚያምን ነው፡፡ ትሁት ሰው ራሱን ብቻ አስፈላጊ አድርጎ የማይመለከት ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው የሰውን ሁሉ አስፈላጊነት የሚረዳ ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው በሌላው ሰው ስጦታ ጥሪና ጠቃሚነት የሚያምን ነው፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር ፊልጵስዩስ 2፡3
  • · ትሁት ሰው የራሱን ብቻ የማይፈልግ ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው ሌላውንም የሚጠቅመውን ነገር ለማድረግ የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው ራስ ወዳድ አይደለም፡፡ ትሁት ሰው ለሌላው ጥቅም በትጋት የሚሰራ ሰው ነው፡፡
እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ ፊልጵስዩስ 2፡4
  • · ትህትና እንደ ክርስቶስ ራስን አዋርዶ መኖር ነው፡፡ የሰው ትህትና የሚጀምረው ከሃሳብ ነው፡፡ ሰው ገና በሃሳብ ደረጃ ራሱን ካላዋረደ በትህትና ሊመላለስ አይችልም፡፡ ትሁት ሰው የትህትና መልክ ብቻ ሳይሆን የትህትና ሃሳብና ውሳኔ ያለው ነው፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። ፊልጵስዩስ 2፡5
  • · ከኢየሱስ የምንማረው ትሁት ሰው ለደረጃ ግድ እንደሌለው ነው፡፡ ትሁት ሰው ስለደረጃ አይጣላም አይጨቃጨቅም፡፡ ትሁት ሰው ትኩረቱ ማገልገል ሰውም መጥቀም በሰው ላይ ዋጋን መጨመር ሰውን ማንሳት ላይ እንጂ ስለስምና ስለስልጣን ወይም ጥቅም አይደለም፡፡ ትሁት ሰው የትም ማገልገል ስለሚችል መቼም ለመውረድ የተዘጋጀ ነው፡፡
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ፊልጵስዩስ 2፡6
  • · ትሁት ሰው እግዚአብሄርም እንዲያዋርደው የማያደርግ ቀድሞ ራሱን የሚያዋርድ ነው፡፡ ትሁትን ሰው የምናውቀው ሁኔታ ስላልተመቸው በመዋረዱ ሳይሆን ከፍ የሚያደርግ ሁኔታ እያለ በራሱ ፈቃድ ራሱን የሚያዋርድ ሰው ነው፡፡
ትሁት ሰው ሰዎችን ለመጥቀም በምድር ላይ እንዳለ የሚያውቅ ሰው ሲሆን ሰዎች ሲጠቀሙበት እንደ እድል እንጂ እንደ ሽንፈት የማይቆጥር ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው ሰዎች እንደተጠቀሙበት የሚሰማውን አፍራሽ ስሜት የማይቀበል ሰዎች እንዲጠቀሙበት የሚፈቅድ የባሪያ ልብ ያለው ለራሱ የማይሰስት ሰው ነው፡፡
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ ፊልጵስዩስ 2፡7
  • · ትሁት ሰው ነገሮችን ካደረገ በኋላ ክፍያውን የማይተምን በትህትናው የማይመካ ስላደረገው ስራ ዋጋውን ራሱ የማይተምን ሃላፊነቱን ብቻ እንደተወጠ የሚሰማው ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው ምንጩ እግዚአብሄር እንደሆነ የሚረዳ እንካ በእንካ አገልግሎት የሌለው ሰው ነው፡፡
እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። ሉቃስ 17፡10
  • · ትሁት ሰው ማንነቱን ጠንቅቆ የተረዳ ፣ ክብሩን የሚያውቅ ፣ የእርሱ ዝቅ ብሎ ማገልገል ምንም እንደማያዋርደው የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ትሁት ሰው በእእግዚአብሄር ካለው ክብር እርሱን ሊያዋርደው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ የተረዳ ነው፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-5
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ፊልጵስዩስ 2፡3-8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
Advertisements

About AbiyWakumaDinsa

Johannesburg, South Africa

Posted on October 15, 2016, in Character, grace. Bookmark the permalink. Comments Off on እውነተኛ ትህትና.

Comments are closed.

%d bloggers like this: